ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሰማነው የሙስና ቅሌት ጆሮን ‹‹ጭው›› የሚያደርግ ነው። በእርግጥ ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ከአሁኑ የባሰም የሙስና ቅሌት በዚህች ድሃ አገር እንደተፈጸመ እናስታውሳለን። ይህኛውን የተለየ፣ ከባድ እና እጅግ አስደንጋጭ ያደረገው አገር በጦርነትና በግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የእለት ጉርሳቸውን ከሌሎች እጅ በሚጠብቁበት በዚህ ወቅት በሰብአዊ ተግባር ላይ በተሰማራ ተቋም ውስጥ መፈጸሙ ነው።
በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተፈጸመው ከባድ ሌብነት ፣ሌብነት ብቻ ነው ብሎ ለማሰብ የሚከብድ ነው ፣ ሰብአዊ እርዳታ በሚጠብቁ ሚሊየኖች ላይ የተፈጸመ ሰብአዊ ወንጀል ጭምር ነው። ተቋሙ በፈጠረው ወንጀል ምክንያት የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተው ሕጻናት ሳይቀሩ እስከ ህልፈተ ህይወት ዋጋ ከፍለው ሊሆን ስለሚችል ቅሌት በቀላሉ መታየት የለበትም።
ይህን ጸያፍ በደል በአገርና በሕዝብ ላይ የፈጸሙ ግለሰቦች ሌቦች ብቻ አይደሉም። አገርን ከጀርባዋ ከሚወጉ ባንዳዎች ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። እነዚህን አልጠግብ ባይ ሕሊና ቢስ ግለሰቦች የፌዴራል ፖሊስ ሕግ ፊት ለማቅረብ የሄደበት መንገድ የሚደነቅ ጠቋሚ ለህዝብና ለሀገር ያለውን ታማኝነት በአደባባይ ዳግም ያረጋገጠ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው የመንግስት ስርአት ከሌላት መቀነት ፈታ፣ ከእለት ጉርሷ ቀንሳ ነገን የተሻለ ለማድረግ ለግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ያወጣችው ጥሪት ጭምር እንዲህ ነው በማይባል ደረጃ ተዘርፏል። የመንግሥት ሃብትና ንብረት በተደራጁ ኃይሎች ምዝበራ ተፈፅሞበታል። ሜጋ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ሰዓት ካለመጠናቀቃቸው ባሻገር ተጨማሪ ሃብት እንዲወጣባቸው የተደረገበት፣ ግልጽ ባልሆነ አሰራር እና በትውውቅ ፕሮጀክቶች ለሌብነት የተጋለጡበት አሰራር በስፋት ተስተውሏል።
ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋ የሙስና ወንጀል ህዝቡን አስመርሮ በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ገፊ ምክንያትም ሆኗል። ባለፉት አራት ዓመታትም የዘውግ ፖለቲካው ጡዘት፣አገር የገጠማት ጦርነትና የንጹሃን ዜጎች ግድያ የሙስናን ጉዳይ አለዘበው እንጂ አገርን ክፉኛ እያቆሰለ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ይህ ክፉ የአገር ነቀርሳ መንግስታቸው እየተቸገረበት ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመላው ህዝብ አሳውቀዋል።
በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ የኮንዶሚኒየም ቤቶች እጣ አወጣጥ ላይ የተፈጠረው አሳፋሪ ድርጊትም አገርና ሕዝብ ምን ያህል በዚህ ችግር እየተበደሉ እንደሚገኙ ማሳያ ነው። እዚህ ላይ የፌዴራል ፖሊስ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ላይ የተፈጠረውን ዘረፋ እንዳጋለጠው ሁሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮንዶሚኒየም ቤቶች እጣ አወጣጥ ላይ የተፈጠረውን ችግር ራሱ ደርሶበት ለሕዝብ ይፋ ማድረጉና ተጠርጣሪዎችንም በቁጥጥር አውሎ ርምጃ መውሰዱ የሚመሰገን ነው ።ሌብነትን ለመታገል ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳየበት ነው።
በርግጥ ኢትዮጵያ በሌብነት የገጠማት ፈተና መልከ ብዙ ነው። በክልሎችም ይሁን በፌዴራል ተቋማት ችግሩ ዛሬም ድረስ በስፋት ስለመኖሩ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሕዝብም ባገኘው ሁሉ አጋጣሚ ይህን ምሬት ሳይገልጽ አያልፍም። ሕዝቡን እየተፈታተነ ያለ ዋነኛ ነቀርሳ ነው። አገልግሎት ፈልገው ወደ ተለያዩ ተቋማት የሚያቀኑ ዜጎች በኃላፊነት አገልግሎት በደስታ መሸኘት ዛሬም ድረስ ፈተና የሆነባቸው ተቋማት ቁጥር ስፍር የላቸውም። እንኳን ተገልጋይ ቀርቶ ሰራተኞች ራሳቸው በተቋማቸው ብልሹ አሰራር ሲማረሩ መስማት ብርቅ አይደለም።
በሕዝብ ሃብትና ንብረት እንደ ግላቸው ጥሪት አድርገው ከህግም ከህሊናም ውጪ ተቋማትን የሚመሩና ተገልጋይን እንዲሁም ሰራተኛቸውን ጭምር የሚያማርሩ ሹማምንት የሉም ብሎ መንግስትም ቢሆን ደፍሮ መናገር አይችልም። መንግስት የተደላደለ ቤትና መኪና እንዲሁም ዳጎስ ያለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ቸሯቸው አልጠግብ ባይ የተቋማት መሪዎች ዛሬም ሌላ ሃብትና ንብረት ለማጋበስ ሲቅበዘበዙ ማየት የተለመደ ነው።
ይህም ከዘውግ አስተሳሰብ ወጥታ የተረጋጋ ፖለቲካን እውን ለማድረግ ለምትታትር አንድ አገር ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ነው። ሌቦች በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር እያመቻቹ ያሉት መንገድ በፖለቲካ ትኩሳቱ ላይ ቤንዝል እንደማርከፍከፍ ያህል ነው። ይህም አገርና ሕዝብ በምጣኔ ሃብት ረገድ ፈተና ውስጥ እንዲገቡ ከማድረጉ ባሻገር ቀን በቀን እየተመነደገ በመጣው የኑሮ ውድነት ትልቅ ሚና እንዲጫወት አድርጎታል።
ሙስና በኢትዮጵያ አብዝቶ መንሠራፋት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ የሲቪክ ማኅበራት በነፃነት መንቀሳቀስ አለመቻል፣ የፕሬስ ነፃነት መገደብ፣ የሕዝባዊ ተሣትፎ ማነስና የመንግሥት ለሕግጋት ተገዥ አለመሆን እንደሚገኙበት አንዳንድ ምሁራን ይናገራሉ። ይህንንም መንግስት መመልከት አለበት። ጥርስ የሌለው አንበሳ ተደርጎ የሚቆጠረው የጸረ-ሙስና ኮሚሽንን እንደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ምርጫ ቦርድ ገለልተኛና ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣ መንግስትም ተቋሙን የሚያጠናክርና አቅም እንዲኖረው የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት ረገድም ብዙ ርቀት መጓዝ ይኖርበታል።
ሙስና የሚፈጸምባቸው የወንጀል አይነቶች እየተራቀቁ እንደመምጣታቸው ወንጀሉን የመከላከልና የመመርመር ሥራው ተጣምሮ አቅሙ ባላቸው ብቁ ሠራተኞች ቢከናወን በየጊዜው ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን እንደሚችልም ማሰብ ተገቢ ነው። ለዚህም የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
የሙስና ወንጀል በአገር ላይ እያስከተለ ያለውን ኪሳራ ለመከላከል የተደራጀና ንቃተ ህሊናው ከፍ ያለ ማኅብረሰብ ለመፍጠር እንዲሁም ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ፤ የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ፖሊስ እንዲሁም አቃቤ ሕግ በጥምረት ከመቼውም በላይ መስራት አለባቸው።ለዚህ የሚሆን አሰራር ማበጀትም ይኖርባቸዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ሰሞኑን ያጋለጠው የሙስና ቅሌት የጭቃ ውስጥ እሾህ ሆነው መንግስትና ሕዝብን የሚመዘምዙ ተባዮችን ለመንቀል አበረታች ጅምር ቢሆንም የወረት መሆን የለበትም። ችግሩ በየቦታው አለና አበረታች ጅምሩ በህጋዊ ርምጃ ታጅቦ በስፋት ሊቀጥል ይገባል። ይህን ችግር ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተለያዩ ርምጃዎች ሲወሰዱ ነበር። ነገር ግን የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ አጀንዳ ከመሆን የዘለሉ አይሆኑም። አሁንም መንግስት ከፍትህ ተቋማት ጋር በመሆን የጀመራቸውና በሂደት ላይ ያሉ ምርመራዎች እንደሚኖሩ ይታመናል። እነዚህን ጅምሮች አጠናክሮ በመቀጠል ከዳር አድርሶ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ የሰሞኑ ሞራል መቀዝቀዝ የለበትም።
ሙስና ለአንድ ሀገር እድገት እንቅፋት ከሆኑ ችግሮች መካከል የአንበሳውን ድርሻ ከመውሰድ በዘለለ ለአንድ አገረ መንግስት አለመረጋጋት ጉልህ ሚና አለው። መንግስት በዚህ ረገድ እየወሰደ ያለው እርምጃ መልካም ነው። ነገር ግን ያዝ ለቀቅ የሚደረግ ከሆነ እርምጃው በራሱ ለሌላ ፖለቲካዊ ትርጉም የመጋለጥ እድል አለው። ስለዚህ መንግስት በሌብነት ላይ የመዘዘውን ሰይፍ በየቦታው የተዘረጋውን የሌብነት ሰንሰለት እስኪበጥስ ድረስ ወደ ሰገባው ሊመልሰው አይገባም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2014