ከሜድትራኒያን ባሕር ደቡባዊ ጥግ እስከ ሠሃራ በረሃ የሚደርስ ሠፊ ግዛትን የምታዋስን፣ ድሆች የከበቧት አንድ አገር ነበረች። እርስዋም የሕዝቧን መሠረታዊ ፍላጎት ሁሉ አሟልታ በማኖር ከአፍሪቃ አቻ ያልነበራት ሀብታም አገር – ሊቢያ ነች።
በሊቢያ የቤት ባለቤትነት እንደሰብአዊ መብት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህም መሪያቸው የነበረው ሙዓመር ጋዳፊ የሊቢያ እያንዳንዱ ዜጋ ቤት ሳይኖረው እርሳቸው ከወላጆቻቸው ቤት እንደማይወጡ በይፋ በመማላቸው አባታቸው እስኪሞቱ ድረስ የኖሩት በጎጆ ውስጥ ነበር፡፡
የአገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት በነፃ ነበር፣ በሊቢያ ሕግ ባንኮች ለዜጎቻቸው የሚያበድሩት ያለምንም ወለድ ነው፡፡ ሙሽሮች ለጎጆ መውጫቸውና ለመቋቋሚያቸው 50ሺ የአሜሪካን ዶላር ይሰጣቸዋል፤ሁሉም ዜጎች ትምህርትና ሕክምና ነፃ ያገኛሉ፡፡
ጋዳፊ የተማረ ሃይል በአገሪቱ እንዲበዛ ይፈልጉ ስለነበር ፊደል የቆጠሩ ዜጎችን ቁጥር ከ25 በመቶ ወደ 83 በመቶ አሳድገዋል፡፡ በዚህም 25 በመቶ ሊቢያውያን የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ነበራቸው፡፡ ወደግብርና የሚገቡ ሊቢያውያን የግብርና መሳሪያና ለግብርና የሚሆን ቦታ በነፃ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ለዜጎቿ ሊቢያ ውስጥ የማይቻል ሕክምና ወጪው በሙሉ በመንግስት ተሸፍኖ በሌላ አገር እንዲታከሙ ሲደረግ፤ እያንዳንዱ ዜጋ በወር 2ሺ300 የአሜሪካን ዶላር የዜግነት ክፍያ ካለሥራ ይከፈለው ነበር፡፡
አንድ የተመረቀ ሊቢያዊ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ በተመረቀበት ሙያ ሊያገኝ የሚችለውን የደሞዝ መጠን ከመንግስት በየወሩ ይከፈለዋል፡፡ ሊቢያውያን መኪና መግዛት ሲፈልጉ መንግስት 50 በመቶ ወጪውን ይሸፍንላቸዋል፤ የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋም 14 ሳንቲም ነበር፡፡ አገሪቱ የማንም አገር ብድር የለባትም፡፡ ከነዳጅ ንግድ ትርፍ ገቢ በጥቂቱ በዜጎች የባንክ አካውንት ውስጥ ተቀማጭ ይደረግላቸዋል፡፡ልጅ የወለደች ሊቢያዊት ልጅ በመውለዷ ብቻ አምስት ሺ የአሜሪካ ዶላር ስጦታ ይሰጣታል፡፡40 ዳቦ በሊቢያ 15 ሳንቲም ይሸጥ ነበር፡፡
ሊቢያ እስከ ዛሬ ሰባት ዓመት ድረስ አንድ ጠንካራ መሪ፣ አንድ መንግሥትና አንድ ብሔራዊ ጦር ነበሯት። ዛሬ የአሸባሪዎች፣የጎጠኞች፣ የሽፍቶች፣ የስደተኛ አስተላላፊዎች፣ የዘራፊዎች መናኸሪያ ሆናለች። ከሰባት ዓመት በፊት አንድ መሪ የነበራት ይህቺ ሀብታም የነበረች አገር ዛሬ አስራ-ሰባት ሺ ታጣቂ ቡድኖች ይርመሰመሱባታል።
ሊቢያ ላይ የዘመተባት የዓለም ምርጥ ጦር ከአየርና ከባሕር ባወረደባት ቦምብና ሚሳይል ሀብት ንብረትዋን አውድሞ፤ ዜጎችዋን ፈጅቶ፤ መሪዋን ከነሥርዓታቸው እጥፍቶ ለመከራ ዳረጋት። ዛሬ ሁለት መንግሥት፤ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ሁለት ምክር ቤት፤ በርካታ የጦር ቡድኖች ይፈነጩባታል።
ሊቢያ ሀብት – ዕዳ፤ ብልፅግና – ጥፋት፤ ሥልታዊነት – መከራ የሆነባት አገር ሆና ሰላም እናሰፍናለን፣ ዴሞክራሲ እናመጣለን ፣ ነፃነት ለሕዝቦቿ እናጎናፅፋለን በሚሉ የዓለም ሃያላን አገራት ሴራና አነሳሽነት እንዲሁም በሕዝቦቿ አስተዋይነት እጦት አገሪቱ ለውድመት፤ ሕዝቦቿ ለስደት፣ ለረሀብ፣ ለስቃይና ለሞት ተዳረጉ፡፡
እ.አ.አ. 2011 ሊቢያውያን አንቀባርሮ ያኖራቸውን መንግሥታቸውን ከጥይት በመለስ ታግለው ለችግሮቻቸው መፍትሄ መፈለግ ሲገባቸው የዓረብ አገራትን ያንቀጠቀጠውን የዓረብ አብዮት ተገን አድርገው በመሪያቸው ላይ ዘመቱ፡፡ በውጭ አገራት የሚደገፉ አማፅያን በአገር ውስጥ፤ ከውጭ ደግሞ በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከአየር በቦምብ ፤ ከምድር በሚሳይል ምድሪቱ ተናጠች፡፡
ለአገራቸው ዜጎች ዋስ ጠበቃ የነበሩት ጋዳፊ ጦራቸው ተበተነ፣ ቤተሰቦቻቸው የጥይት እራት ሆኑ፣ ልጆቻቸው ተበታተኑ፣ እርሳቸውም ተማረኩ፣ በራሳቸው ዜጋ «ተው አንተ አትተኩስ!» እያሉ እየተማፀኑ ተገደሉ፡፡ የእርሳቸው መሞት ለሰባት ወራት ሊቢያን ሲቀጠቅጥ ለነበረ ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር አዛዦች ታላቅ ፌሽታ ሆነ፡፡ የሊቢያ ሕዝብ ከቃል ኪዳኑ አገሮች አዲስ ተስፋ ተንቆረቆረለት።
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማ «ይህ ለሊቢያ ሕዝብ የረጅም ጊዜ የሥቃይ ምዕራፍ ፍፃሜ ነው፤ ከእንግዲህ የአገሪቱ ሕዝቦች በአዲሲቱ ዴሞክራሲያዊት ሊቢያ የራሳቸውን መፃኢ ዕድል መወሰን ይችላሉ፤ የጋዳፊ ሥርዓት ለአራት አስርት ዓመታት በብረት ጡንቻ ገዝቷል፤ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች ተገፍፈዋል፣ንፁሐን ሰላማዊ ሰዎች ታሥረዋል፣ተገርፈዋል፣ተገድለዋል፣የአገሪቱ ሀብት ተመዝብሯል፣ሽብር እንደ ፖለቲካ መሳሪያ አገልግሏል፣ ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ ከነበሩት አምባገነኞች አንዱ ከእንግዲህ ተወግደዋል። ይህ በሊቢያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ አለው። የሊቢያ ሕዝብ ከጋዳፊ ሥርዓት ጋር ጨርሶ የሚቃረን ሁሉን አቀፍ፤ ሁሉን አቻችላ የምታኖር ዴሞክራሲያዊት ሊቢያን የመገንባት ሃላፊነት አለበት» ሲሉ ተናገሩ፡፡
ከቃላት ባለፈ በገቢር ምንም ያልነበረው የሠላም፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ተስፋ ከበነነ ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ። ዴሞክራሲዊ ሥርዓት እንገነባለን ብለው በፓሪስ፤ በለንደን፣ በዋሽንግተንና በሌሎች አገራት ድጋፍ ለማግኘት ሲባትሉ የነበሩት ሁሉ አገርና ሕዝባቸውን አመሰቃቅለው ከፖለቲካው መድረክ ከጠፉ ዓመታት ተቆጠሩ።
ሊቢያን የደበደበው የሰሜን አትላቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር አላማ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊን እስከ መግደል ከነበረ በርግጥ ተሳክቶለታል። ኦባማ እንዳሉት ሰላም፤ ዴሞክራሲ፤ ፍትህ ማስፈን ከነበረ ግን ውድቀት ተከትሏል።
ምክንያቱም እንደ አንድ አገር አንድ መንግሥት የነበራት ሊቢያ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ ከነሥርዓታቸው ከተወገዱ ጀምሮ ከአምስት ያላነሱ መሪዎች ተፈራርቀውባታል። ዛሬ በሊቢያ ረሀብ፣ሞት ፣ድህነት፣ ስደት፣ ስቃይና መከራ እንዲሁም አለመረጋጋት ሰፍነው ዜጎቿ ያሳለፉት የተመቻቸና የቅንጦት ጊዜ ዳግም የማይመለስ ትዝታ ሆኖ አልፎባቸዋል፡፡
«የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም» እንዲሉ እኛ ኢትዮጵያውያን አስተዋይ ከሆንን ሀብታም ሆና ዜጎቿን በአግባቡ ያኖረች፤ ግን ደግሞ የዜጎቿ አለማስተዋልና የውጭ አገራት ተንኮል ለድህነት ከዳረጋት አገር ሊቢያ መማር ካለብን ጊዜው አልረፈደብንም፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየነፈሰ ያለው የለውጥ ነፋስ ሰላማዊነቱ የተረጋገጠ እንዲሆንና በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም አስተዋይነት ያለው ርምጃ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የታየው ዙሪያ ገብ የለውጥ እንቅስቃሴና መንግሥት ላይ ያሳደረው ጫና ለአገር ሰላም ሲባል ያስከተለው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ውሎ አድሮ ግን እንቅፋቶች አልተለዩትም፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሀዊነት ወዘተ… ጥያቄዎች መልስ ማጣት ያሳደሩት ቅሬታ በለውጡ ከሞላ ጎደል ምላሽ ማግኘታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ በመሆኑም በርካታ ወገኖቻችን ከእስር ተለቅቀዋል፣ ተቋማት አሰራራቸውን እየለወጡ ይገኛሉ፤ መገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን በነፃነት ያሰራጫሉ፤ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከብስል እስከ ጥሬ፣ ከአስፀያፊ እስከ መልካም ዜና ያከፋፍላሉ፤ በሙስና የተጠረጠሩ ተጠያቂ እየሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በከፊልም ቢሆን የምንፈልገውን አግኝተናል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም እንኳ ቋጠሮው እያፈተለከ ማስቸገሩ ይታያል፡፡
ስለአንድ አገራችን እናስብ ሲባል አስተሳሰባችን ዘቅጦ አንድ ቀበሌ ክልል ካልሆነ ብለን እርስ በርስ እንገዳደላለን፡፡ ማንነቴ እከሌ ይባልልኝ በሚል ሰበብ አብሮ የኖረ፣ በጋብቻ የተሳሰረ፣ በችግር ወቅት በአንድነት የቆመ ሕዝብ ከአካባቢዬ ውጣልኝ ተብሎ ለችግር ይዳረጋል፡፡ ከብዙ ጉዳት በኋላ እርቅ ሲወርድ «እኛ አብረን የኖርን፣ የተጋባን፣ የተዋለድን ወዘተ…» እያልን ቃላት እንደረድራለን፡፡ ያኔ ለጥፋት ከመነሳታችን በፊት አብረን መኖራችንን፣ በጋብቻ መተሳሰራችንን፣ በክፉና በደጉ መደጋገፋችንን ማሰብ እንደምን ተሳነን?
በቀደመው ጊዜ በአንዲት አገር ኢትዮጵያና በአንድነት ያምን የነበረ ዜጋ የብሄር ማንነትህ ተከብሮልሃል ሲባልና በህገ መንግስት ሲረጋገጥለት በልዩነት ውስጥ ውበት እንዳለ ተገንዝቦ ከወገኖቹ ጋር ተስማምቶ መኖር እንደምን ያቅተዋል?
ዜጎች ተነፍገናል ያሉት ዴሞክራሲና ነፃነት ካለገደብ ተሰጥቶ፣ በእስር ይማቅቁ የነበሩ ነፃ ወጥተው፣ ለስደት የተዳረጉት በነፃነት ወደአገራቸው ተመልሰው፣ ነፍጥ አንስተው በረሀ የገቡ የሰላም ጥሪ ተደርጎላቸው አገራቸው ገብተው ሳለ በየክልሉ የሚታየው አለመረጋጋት በዕውነት ሰላምን እፈልጋለሁ ሲል ከነበረ ዜጋ የማይጠበቅ ድርጊት ሲሆን፤ አለመረጋጋትን መፈለግ ግን ከብጥብጥ እጠቀማለሁ ብሎ ከማለም የሚመነጭ ከንቱ እሳቤ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የተያያዝነው የለውጥ ሂደት ጅምር በመሆኑ ብዙ ተግዳሮቶች ሊገጥሙን እንደሚችሉ የሚገመት ቢሆንም፤ ሰላምን የሚፈልግ ማንኛውም ወገን ግን በትንንሽ ጉዳዮች ወደ ብጥብጥ ለመግባት ከመፈለግ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ትንንሽ ጉዳዮች አለመረጋጋታችንን ለሚፈልጉና ወደለየለት ብጥብጥ እንድናመራ ለሚያልሙ ክፉ አሳቢዎች መንገድ ስለሚከፍት ችግሮቻችንን በተረጋጋ ሁኔታ በውይይት መፍታት ይኖርብናል፡፡
ከብጥብጥ እንጠቀማለን ብላችሁ የምታልሙ ክፉ አሳቢዎች፤ ከእርስ በርስ ጦርነት ምንም ማትረፍ እንደማይቻል ከሊቢያና ከሶሪያ ትምህርት አግኙ፡፡ ብጥብጥ ሲነሳ እንዘርፋለን ብላችሁ የምታልሙ ካላችሁም አገር ከተበጠበጠ ለዘረፋ መሰማራት ቀርቶ በእጅ የያዙትን እንኳ በወጉ መቅመስ የማይቻልበት ሁኔታ እንደሚከሰት አስቡ፡፡ ከብጥብጥ እንጠቀማለን ብላችሁ ሕዝብን ለማባላት የቋመጣችሁ ካላችሁም ሌላው ተበጥብጦ እኛ በሰላም እንኖራለን ማለት ከንቱ መሆኑን ተረዱ፡፡
በምቾት ይኖሩ የነበሩ ሊቢያውያን የተሻለ እናገኛለን ብለው የያዙትን አጥተው በጦርነትና በችጋር ተጠበሱ፡፡ ሶሪያውያን በእርስ በርስ ጦርነትና በበሽታ እያለቁ አገራችን በስደት መጥተው ሕይወታቸውን የሚያቆዩበት ምግብ መግዣ ምፅዋት እንድንሰጥ እየለመኑን ይገኛሉ፡፡ ይህንን የእነርሱን ችግር ማየታችን ከእኛ ከሚያገኙት እርዳታ ይልቅ የሚሠጡን ትምህርት የሚበልጥ ነው፡፡ የውጭ ጠላት ሳይፈትነን እርስ በእርሳችን ለመጠፋፋትና አገራችንን ለክፉዎች አሳልፈን ልንሰጥ ሌሊትና ቀን የምንተጋ ኢትዮጵያውያን የያዝነው መጥፎ አማራጭ መድረሻው የት እንደሆነ የጥፋት ማዕበል ከመታቸው አገሮች ልንማር ይገባል፡፡