ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን ውድድሮች ገናና ስም ቢኖራቸውም እንዳላቸው ትልቅ አቅም በዓለም ቻምፒዮና መድረኮች ወርቅ ማጥለቅ የቻሉት በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር። የመጀመሪያውን ወርቅ ታሪካዊው አትሌት ገዛኸኝ አበራ እኤአ በ2001 ኤድመንተን ላይ አስመዘገበ። ሁለተኛው የርቀቱ ወርቅ ደግሞ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በ2019 የዶሃ የዓለም ቻምፒዮና በሌሊሳ ዲሳሳ ነበር የተመዘገበው። ዘንድሮ ደግሞ ሌላ ተአምር በወጣቱ አትሌት ታምራት ቶላ ኦሪገን ላይ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ቻምፒዮና ተሰራ።
ያለፈው ቻምፒዮና አሸናፊው አትሌት ሌሊሳ የአየር ሁኔታው ከብዶት ወደ ኋላ በቀረበትና ብርቱ ፉክክር ባስተናገደው ውድድር ኢትዮጵያውያን ወርቅ የማጥለቃቸው እድል ስጋት ውስጥ የገባ ቢመስልም ከበርካታ የማራቶን ከዋክብት እግሮች መካከል ተአምር የሚሰራ ቁመተ ለግላጋ ኢትዮጵያዊ ሳይታሰብ አፈትልኮ ወርቁን አጠለቀ።
ታምራት የርቀቱ የዓለም ከዋክብት አፈትልከው ለመውጣት ሲያመነቱ ቆራጥ ውሳኔ ወስኖ የወጣበትና መሪነቱን እስከ ወርቅ ያዘለቀበት መንገድ የእውነትም ተአምር ነው። ኢትዮጵያውያን በዚህ ውድድር በታምራት ብቻ ፈንጥዘው አላበቁም። ባለፈው ቻምፒዮና በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ሞስነት ገረመው ከተፎካካሪዎቹ የገጠመውን ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ትንቅንቅ በራሱ መንገድ መርቶ ዳግም የብሩ ባለቤት ሆነ።
እነዚህ ሁለት ጀግኖች በዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከተፎካካሪዋና ከርቀቱ ቁንጮ ኬንያ ጋር ያላትን የሜዳሊያ ልዩነት ማጥበብ ችለዋል። ኬንያ በርቀቱ አምስት ወርቆችን ስታጠልቅ ኢትዮጵያ እስካለፈው ቻምፒዮና ድረስ አንድ ብቻ ነበር ወደ ካዝናዋ ያስገባችው። የዘንድሮውና ያለፈው ቻምፒዮና ድሎች ግን የወርቁን ልዩነት ወደ ሁለት እንዲጠብ አድርገዋል። የብር ሜዳሊን በተመለከተ ደግሞ ኢትዮጵያ ስድስት ሜዳሊያ ስታስመዘግብ ሞስነት ገረመው የሁለቱ ባለቤት በመሆን ስሙን በወርቅ ቀለም መጻፍ ችሏል።
ከዚህ ቀደም በዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን በዓለም ቻምፒዮናው መድረክ ኢትዮጵያ እና ማራቶን ትውውቃቸው እ.ኤ.አ በ1983 ሄልሲንኪ ላይ በተደረገው የመጀመሪያው የዓለም ሻምፒዮና ላይ የጀመረ ነበር ። በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክሎ በብቸኝነት የተወዳደረው አትሌት ከበደ ባልቻ በ2:10:27 ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናም ሆነ በማራቶን የመጀመሪያውን ሜዳልያ ማስገኘት ችሎ ነበር ።
በመድረኩ የመጀመሪያ ወርቅ ያገኘነው ደግሞ በ8ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነበር ። በ2001 ካናዳ ኤድመንተን ላይ በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና አትሌት ገዛኸኝ አበራ በ2:12:42 በቀዳሚነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት መሆን ችሏል ።
ከገዛኸኝ አበራ ድል በኋላ ግን ኢትዮጵያ በመድረኩ ሌላ የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት 18 ዓመታትን መጠበቅ የግድ ብሏት ነበር ። ከሶስት ዓመታት በፊት በኳታር ዶሀ በተደረገው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለሊሳ ዴሲሳ ሙስነት ገረመውን አስከትሎ በ2:10:40 በመግባት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ማስመዝገብ ችሏል ። በዚህም ኢትዮጵያ በኦሪገኑ የዓለም ቻምፒዮና ላይ አራት አትሌቶችን ለማሳተፍ ችላለች ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014