አለም ብዙ በሽታዎች አሏት። በጉያዋ ውስጥ በርካታ ሰውኛ ጉድፎችን ታቅፋ የምትኖር ናት። በጣም የሚገርመው ደግሞ እኚህ ሁሉ በሽታዎች በሰዎች መፈጠራቸው ነው። ባለፉት በርካታ አመታት ውስጥ አለምን እንደ ሰው ልጅ ያስጨነቃት የለም። ከትናንት እስከዛሬ የአለም መከራ የሰው ልጅ ሆኖ ዘልቋል..አሁንም የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ሆነን እየኖርን ነው። ዘረኝነት፣ ወገኝተኝነት፣ አክራሪነት፣ እኔነት፣ ሃይማኖተኝነት፣ ብሄርተኝነት አለምን እያስለቀሱ ያሉ ሰው ሰራሽ በሽታዎች ናቸው።
አሁናዊውን የሀገራችንን ገጽታ ዞር ብለን ብናየው በዚህ ደዌ የተጠቃች ሆና እናገኛታለን። የእኚህ ሁሉ ደዌዎች ጠንሳሾች ደግሞ እኛ ነን። በራሳችን ላይ ሞትና ጉስቁልናን እያወጅን ያለነው እኛ ነን። ይሄ የዘረኝነት አስተሳሰብ ከውስጣችን እስካልወጣ ድረስ ሁሌም ታማሚ፣ ሁሌም እዬዬ ባዮች ነው የምንሆነው።
ባለፉት የአሸባራ ሕወሓት የስልጣን ዘመን የተዘሩ የዘረኝነት ዘሮች ዛሬ ላይ አብበውና አፍርተው እኩይ ፍሬአቸውን እየሰጡን ነው። እኚህ የዘረኝነት ፍሬዎች እስካልደረቁና እስካልጠወለጉ ድረስ ትውልዱ ሁሌም ታማሚ ነው፣ ሀገራችን ሁሌም ስቃይ ውስጥ ነች ። የምንፈልገው የእድገትም ሆነ የከፍታ ጥግ ለመድረስ በዘሩ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቱ የሚያስብ ትውልድ ያስፈልገናል።
አለም እንደ ዘረኝነት በሽታ የላትም። ዛሬ ላይ እየገደለንና እያጎደለን ያለው ይሄ አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያዊነት መልክና ወዙን አጥቶ በብሄር የምንባላው ከሰውነት በገዘፈ ምናምንቴ እውቀት ነው። ድሀ ሀገር ይዘን፣ ድሃ ማህበረሰብ ታቅፈን ምንም በማይጠቅመን ነገር ላይ ጊዜአችንን ማባከናችን እንደ አንድ ዜጋ ያስቆጫል። ከፊትለፊታችን ካሉ ልንደርስባቸው ከምንታትራቸው የስኬትና የለውጥ ጫፍ ለመድረስ ዘረኝነትን ገለን ኢትዮጵያዊነትን ማሳደግ አለብን።
ብሄርተኝነትን ቀብረን እኛነትን ማበልጸግ አለብን። የሰው ልጅ እንደ ጥላቻ ህመም የለውም። የሞታችን ሁሉ መንስኤ የራሳችንን የሆነን ብሄርና ሃይማኖት፣ ቋንቋና ቀለም ሌላም ሌላም ነገር ከሌሎች አስበልጠን ማየታችን ነው። ለጉስቁልናችን ሁሉ ምክንያት በአንድ ያሰባሰበንን ኢትዮጵያዊነት ሽረን ሀገር ለሚያጠፋና ትውልድ ለሚመርዝ የእኔነት አስተሳሰብ እጅ መስጠታችን ነው።
ቀና ማለት አለብን..ከኖርነውና እየኖርነው ካለው ነውረኛ የህይወት ልምድ ወጥተን ወዳላየነው ሌላ አቅጣጫ መመልከት መቻል አለብን። ለሀያ ሰባት አመታት አንድ ቦታ እያየን፣ አንድ ቦታ እየረገጥን፣ ስለ አንድ ነገር እያሰብን ከክብራችን ጎድለን ከርመናል።
ያቆሸስና ኢትዮጵያዊነት የሚያስቆጨን መቼ ይሆን? ድህነትና ኋላቀርነታችን የሚሰማን መቼ ይሆን? ሰው ከምንም ነገር በላይ ሀገሩን ሲያስበልጥ ሀገሩን በሚጎዳ ነገር ላይ ጊዜውን አያባክንም። ሰው ከምንም ነገር በላይ ወገኑን ሲያስቀድም ወገኑን በሚጎዳ ሀሳብ ላይ አይጠመድም። ችግሩ ከጉዳያችን የምትበልጥ ሀገር አለመኖሯ ነው..ችግሩ ከጉዳያችን የቀደመ ህዝብ ማጣታችን ነው።
በብሄርና በዘረኝነት ስም ይሄ ሁሉ ነውረኛ ድርጊት ሀገራችንና ህዝባችን ላይ ሲካሄድ ከሀሳባችን የምትበልጥ ኢትዮጵያና ከሀሳባችን የሚልቅ ኢትዮጵያዊነት አልነበረንም ማለት ነው። አሁን ላይ ያን ማንነት ነው መገንባት ያለብን..የቱን ካላችሁኝ ከጉዳያችን የምትበልጠውን ኢትዮጵያ፣ ከሀሳባችን የሚልቀውን ኢትዮጵያዊነት መፈለግ ይኖርብናል። ዛሬ ላይ አለምን እያስለቀሳት ያለው ይሄ የዘረኝነት በሽታ ነውና።
ስንገድል ኢትዮጵያን እየገደልን እንደሆነ ልናስብ ይገባል። ስንገድል ከባህልና ከእሴታቸው ገምሰው ማንነትን የሰጡንን ወገኖቻችንን እየገደልን እንደሆነ እናስብ። ስንገድል ብዙሀነት ያቆማትን ብዙዋን ኢትዮጵያ እያሳነስናት እንደሆነ ሊገባን ይገባል። ሰንገድል ታሪካችንን፣ ማንነታችንን፣ ባህል ወጋችንን እያጣን እንደሆነ እንዲገባን ያስፈልጋል። ስንገድል፣ በብሄር ስም ስንጠላላ፣ በማንነት ስንገፋፋ ያደመቀንን የኢትዮጵያዊነት ካባ ከላያችን ላይ እያወለቅንና ርቃናችንን እየሆንን እንደሆነ ማመን መጀመር አለብን።
በአለም ታሪክ ዳግም እንዳይመለሱ የሚፈለጉ በርካታ ብሄር ወለድ መከራዎች አሉ። በሰው ልጅ ታሪክ በታወሱ ቁጥር የሚያሙ የዘረኝነት እዳዎች አሉ። ዛሬ ላይ እነዛን አለም የተጸየፋቸውን የመከራ ዘመናት ለመውለድ እያማጥን ነው። ከሌላው መማር አቅቶን በእኛ ላይ ሲሆን ለማየት ያልበላንን እያከክን ነው። እንዲህ አይነት ድርጊቶች ታሪክ ከማበላሸትና በወንድማማቾች መካከል አሳዳጅና ተሳዳጅነትን ከመፍጠር ባለፈ ትርጉም የላቸውም። ለድሀ ነፍሳችን፣ ምን ለሌላት ለድሀ ሀገራችን የሚበጃትን የፍቅርና የአብሮነት ከተማ መፍጠር ነው።
የኢትዮጵያ መሰረት የአንድነት መሰረት ነው። ታሪክ ቢገለጥ ፣ ገድል ቢጠና ኢትዮጵያዊነት ከፍቅርና ከአብሮነት ውጪ ምንም እንዳይደለ ትደርሱበታላችሁ። ይሄን ሁሉ የሶስት ሺ ዘመን በአብሮነት የተራመድነው በኢትዮጵያዊነት ስም እንጂ በብሄር ስም አይደለም፣ በአንድነት እንጂ በመለያየት አይደለም። ታዲያ ከየት ተምረን፣ ከየት አውቀን፣ ከየት ዘምነን ነው በጋራ ያቆመንን የጋራ መሰረታችንን ለመናድ የምንለፋው?።
ዘመን ሲዘምን አብሮ የሰው ልጅም መዘመን አለበት እንጂ ወደ ኋላ ማሰብ የለበትም። ጊዜው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምንገነባበት እንጂ የተገነባ ስርዐትና ወግን፣ አንድነትና አብሮነትን የምናፈርስበት አይደለም። አለም ዘረኝነትን ጥሎ እውቀትና ስልጣኔን የሙጥኝ ባለበት ጊዜ ላይ እኛ ያውም ሀገራችንን፣ ያውም ወንድሞቻችንን በብሄር ሰበብ መግቢያ ማሳጣታችን እውነት ለሰሚው ግራ ነው።
ማንም ገሎን እኮ አያውቅም። ማንም አጥቅቶን፣ ማንም አፈናቅሎን አያውቅም። ማንም አጎሳቁሎን፣ ማንም አሰቃይቶን አያውቅም። የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ነን። ከትናንት እስከዛሬ የምንባላው እርስ በርስ ነው። ጠላቶቻችን ውጪ ቆመው በሚሰፍሩልን ቀለብና፣ በሚሰጡን ዶላር እዚህ ሀገራችንንና ህዝባችንን እናሰቃያለን። ይሄ ለማናችንም የማይጠቅም ሴይጣናዊ ስራ ነው።
በዚህም በዛም በብሄር ስም የሞቱ ወገኖቻችን ደም ይፋረደናል። ምንም የማያውቁ፣ ፖለቲካ ምን እንደሆነ ቢጠየቁ መልስ የሌላቸው፣ ከመውደድና ከማፍቀር ሌላ እውቀት የሌላቸው በርካታ ንጹሀን በብሄር ስም ተገድለዋል። ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀን ውጪ ሌላ ነገር የማያውቁ፣ ማናችሁ ላላቸው እኛ ኢትዮጵያዊ ነን ከማለት ሌላ መልስ የሌላቸው ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሞተዋል። የእነኚህ ንጹሀን ነፍስ ደም በእኛ ላይ መከራ ከማውረድ ሌላ ትርጉም የለውም። የአቤል ደም ለቃየል ስቃይ ነበር።
ዛሬ ላይ የምንገድላቸው፣ የምናሰቃያቸው ወገኖቻችን ነገ ላይ የማንመልሰው ጥያቄዎቻችን ናቸው። ነገን እንዳናይ ምክንያት ከመሆን ውጪ ምንም አይሆኑም። ገዳዮቻችን ለምን እንደሚገሉ ቢጠየቁ መልስ የላቸውም፣ ሟቾችም ለምን እንደሚሞቱ ቢጠየቁ አያውቁም። በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ ፖለቲካና ብሄርተኝነት ውስጥ ነን። ምክንያት የሌለው ሞት ለገዳይም ሆነ ለሟች ትርፍ የለውም። ሲጀመር ማንም እንዲገድልና እንዲሞት አልተፈጠረም። የተፈጠርነው ለመሞት ሳይሆን ለመኖር ነው።
የገዛ ራሳችንን እንገድላለን፣ የገዛ ወንድማችንን እናሰቃያለን..ከዚህ እውነት ጀርባ ያልተጠየቁ፣ ተጠይቀውም ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄና መልሶች አሉ። መልስ የሚፈልጉ በርካታ ለምኖች አሉ። አሁን እነዛን ለመሞታችንና ለመግደላችን ምክንያት የሆኑንን ያልተጠየቁ ጥያቄዎቻችንን መመለስ ነው ያለብን። ከሞታችን ጀርባ፣ ከመከራዎቻችን ኋላ ያሉትን የለምን ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለብን።
በኢትዮጵያ ምድር ሞት የሚያበቃበት ፖለቲካም ሆነ አስተሳሰብ እንዲፈጠር በጋራ መምከር አለብን። ለችግሮቻችን መፍትሄ የምናመጣበት የምክክር መድረክ ግድ ይለናል። የሟችና የገዳይ ታሪኮች እንዲያበቁ በብሄራዊ ምክክር ሂደት ላይ ሀሳብ በማዋጣት አሸናፊነታችንን ማወጅ አለብን። ያለምክንያት መሞት ምን ያክል እንደሚያም ሊሰማን ይገባል። ሰው ሲሞት ሀገር ነው የሚሞተው..እስካሁንም በእያንዳንዱ ሞታችን ጀርባ ያላየነው የሀገር ሞት አለ። ሰው ሲሞት ታሪክ ነው የሚሞተው፣ ስርዐት ነው የሚበላሸው።
አማራ ሲሞት ኦሮሞ እየሞተ ነው፣ ኦሮሞ ሲሞት አማራና ሌላው ብሄር እየሞተ እንደሆነ ልናስብ ይገባል። ህይወታችን ብቻ አይደለም ሞታችንም የተቆራኘ ነው። የአንድነታችን ሚስጢር የአንዱ ሞት የሌላው ሞት፣ የአንዱ ደስታ የሌላው ደስታ እንደሆነ ነው የሚነገረን።
በኢትዮጵያ ምድር የብቻ ሞት የለም..ገዳዮች እዚህ ሲገሉ እዛ እየሞቱ እንደሆነ ቢረዱ እንዴት መልካም ነው። መሞት እንዲበቃን፣ መገፋፋት እንዲርቀን፣ ፖለቲካዊም ሆኑ ማህበራዊ ችግሮቻችን እልባት እንዲያገኙ የተግባቦት ሀሳቦች፣ የምክክር መድረኮች ያስፈልጉናል፡ ሰው እንደተፈጥሮ ቢኖር ሞትና ህመም አይኖርበትም ነበር። ተፈጥሮ የሰጠችንን መልካም ሰውነት በእኔነትና በራስ ወዳድነት ቀየረን እየተሰቃየን እንገኛለን። የበሽታዎቻችን ሁሉ መንስኤ እኛ ራሳችን ነን። የራሳችን ጠላት ራሳችን ነን ።
ከፊታችን በጎ ውጤት እንደሚያመጣ እምነት የተጣለበት ብሄራዊ የእርቅና የምክክር ሂደቶች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። በዚህ የጋራ ምክክር ላይ ችግሮቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥለን ውጤት የምናመጣበት እንዲሆን የሁላችንም የጋራ ጥረት ይጠበቃል። የሚበጀን መግደል ሳይሆን መነጋገር ነው። ለጥያቄዎቻችን መልስ እስካላገኘን ድረስ ሁሌም ሟች ሁሌም ገዳዮች ከመሆን አናመልጥም።
ለበሽታዎቻችን መድሀኒት እስካላገኘን ድረስ ሁሌም ስቃይ ውስጥ ነን። ሀገራችን እንደሀገር እንድትቀጥል የወንድማማችነት ሀሳቦች ያስፈልጉናል። ህልሞቻችን በመገዳደል ውስጥ አይሰምሩም። የወንድማማችነት ሀሳቦች በመግደል ሳይሆን በመመካከር ውስጥ የሚፈጠሩ ናቸው። በመጠላላት ውስጥ ሳይሆን በመከባበር ውስጥ የሚሰምሩ ናቸው። ህልሞቻችንን በጋራ ለማስመር የአንድነት መንፈስ፣ የወንድማማችነት ራዕይ ያስፈልጉናል። ለብቻ ተራምደን፣ ለብቻ የምንደርስበት የስኬት ጎዳና የለም።
ኢትዮጵያ ተብለን በአንድ ስም እስከተጠራን ድረስ መንገዶቻችን ሁሉ፣ ስኬቶቻችን ሁሉ፣ ችግሮቻችን ሁሉ የጋራ ናቸው። በጋራ ሀገር ላይ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ እሴት፣ የጋራ ስርዐት መገንባት ነው ዘመናዊነት። የጋራ ባህል፣ የአብሮነት ወግ ልማድ መገንባት ነው ስልጣኔ።
ለበሽታዎቻችን መድሀኒት እንፈልግ። ለበሽታዎቻችን መድሀኒት ሳንፈልግ የምናሽረው ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ደዌ አይኖርም። ለበሽታዎቻችን መፍትሄ ሳንፈልግ የምናድነው የብሄር ሞት አይኖርም። ለበሽታዎቻችን መድሀኒት የምንፈልገው በመግደል አይደለም፣ በማፈናቀል አይደለም። ጦርና ጎራዴ በመታጠቅ አይደለም። ንጹሀንን በማሰቃየት፣ የብሄር ጸብ በማስነሳት አይደለም። በመነጋገር ነው፣ በመወያየት ነው።
ለበሽታዎቻችን መድሀኒት የምናገኘው በሽታዎቻችንን ለይተን በማወቅ፣ ምንጩን በመረዳትና ለዛ በሽታ መፍትሄ በመፈለግ ነው። በሽታዎቻችን የታወቁ ናቸው እነሱም የዘረኝነት በሽታ፣ የኔነት ስሜት፣ የራስ ወዳድነት ልክፍት፣ የብሄር ዛር፣ የስልጣን ጥም ናቸው። በሽታዎቻችን የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የሀሰት ትርክቶች ናቸው። እነዚህን የዘመናት በሽታዎቻችንን ምንጭና መነሻ በመረዳት የሚደርቁበትን መፍትሄ መፈለግ ነው የሚያዋጣው። በሞተ እያዘንን መኖር ሳይሆን፣ ስንት ሰው ሞተ፣ ምን ያክል ሰው ተገደለ እያልን መቁጠር ሳይሆን ዳግመኛ ሰዎች የማይሞቱባትን ኢትዮጵያ መፍጠር ነው ያለብን።
ይሄ እንዲሆን ብሄራዊ መግባባት፣ ብሄራዊ እርቅ ያስፈልጉናል። ይሄ እንዲሆን ዋጋ ያላቸውን፣ ሊያቀራርቡን የሚችሉ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ማጎልበት አለብን። ይሄ እንዲሆን ወጣቱ በስርዐትና በግብረገብነት እንዲያድግ ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ስለ ኢትዮጵያዊነት ሁላችንም ያገባናልና መሳሪያችንን ጥለን፣ ገዳይነታችንን ትተን ፍቅርን እጅ መንሳት አለብን።
በገደልን ቁጥር እየሞትን ነው። በየትኛውም መስፈርት ቢታይ መግደል መፍትሄ አይሆንም። መግደል ሌሎችን ለጸብና ላልተፈለገ እንቅስቃሴ ከመዳረግ ባለፈ ለገዳዩም ሆነ ለሟች የሚሰጠው አንዳች ጥቅም የለም። የቆምነው ተደጋግፈንና ተያይዘን ነው። የቆምነው አንዳችን ለአንዳችን አስፈላጊዎች ሆነን ነው። የቆምነው ኢትዮጵያዊነት በኳለው፣ ሀበሻነት ባጸናው በጋራ እውነታችን ላይ ነው። በዚህ መስተጋብር ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም አላስፈላጊ ነገር ይዞን ነው የሚጠፋው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014