ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘቻቸው ዕድሎች የሚያሻግሯት እንጂ ወደ ኋላ የሚጎትቷት አልነበሩም። ነገር ግን ጥቃቅን ልዩነቶችን ከመጠን በላይ በመለጠጥ ቅራኔ የመፍጠር ልማድ በመንሰራፋቱ ሲበላሹ ኖረዋል፤ አሁንም ያንኑ ይዛ ዘልቃለች። እንደውም ለመመለስ ጭምር አዳጋች እንደሆኑ አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን ሲናገሩ እናደምጣለን።
ባህላችን የሚነግረንና ከውስጥ ማንነት ባልመነጨ ስሜት የሚወራልን ኢትዮጵያዊያን አንድ ላይ ለመሥራት ጥረት የሚያደርጉ ሕዝቦች ናቸው የሚል ነው። ተግባሩ ግን የተለየ መልክ ይዞ እናየዋለን። የአንድ አገር ልጆች በተለያዩ ጉዳዮች መለያየታቸው ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ ልዩነቶቻቸው ግን አብረው ከመሥራት እንደማያግዷቸውም እሙን ነው። እዚህ ግን ይህ እየሆነ ያለው የተለየ ነው።
ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ያለፈውን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ መዝጋት አለመቻሉ ነው። ለሰላማዊ ውይይት ራስን ክፍት አለማድረግ፣ ክርክርና ድርድሮች እንዲኖሩ አለመፍቀድ፣ መለስተኛ ልዩነቶችን ማግዘፍና አንዳንድ የመንግስት አመራር ሰጪነት የሕዝብን ፍላጎት ያማከለ አለመሆን እንዲሁም ለአገር አብሮ መሥራት የሚለው አስተሳሰብ ጎልቶ አለመውጣት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት ለልዩነቶች ዕውቅና ሰጥቶ ተባብሮ በመሥራት እንጂ፣ በጠመንጃ አፈሙዝ እንዳልሆነ ለማስተዋል የሚከብድ አይደለም። አብሮ መሥራት እየተቻለ ፋይዳ በሌላቸው ምክንያቶች መተናነቅ የኋላቀርነት እንጂ የሥልጣኔ ማሳያም አይደለም። በተለይም በፖለቲከኞች በኩል የሚታየው ይህ እውነታ በበቂ ሁኔታ ተመልካችን የሚፈልግ ነው።
እነዚህ ኃይሎች በቀላሉ መተማመን በሚችሉባቸው ጉዳች መተማመን እያቃታቸው መጥቷል። በዚህም ሕዝባችንን እንደ ሕዝብ ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈሉት ይገኛሉ። ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት ወደማንወጣው ችግር ውስጥ ለመክተት ሌት ተቀን ሲተጉም ይስተዋላል። ይህንን ችግር ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም ከችግሩ ግዝፈትና ውስብስብነት አንጻር ግን የቻለው አይመስልም። ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልተቻለውም።
ከዚህ የተነሳም አንዳንዶች መንግስት ዋነኛ የሆነውን የዜጎችን ሕይወት የመጠበቅ ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም የሚል ቅሬታ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል። በየስፍራው ብሔርን እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ አምባጓሮዎችና ጭፍጨፋዎች በስፋት ቢታይም እየወሰደ ያለው እርምጃ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ወሳኝና አጸፋ የሚባለውን እርምጃም ሲወስድ አይታይም። ይህም በመሆኑ ልበ ሙሉ የሆነ ሽፍታ በየአካባቢው እንዲፈጠር አድርጓል። በምን አለብኝነት የሚሰራ አመራርም እንዲበራከት እድል ፈጥሯል የሚሉም አልጠፉም።
በሀገሪቱ ያሉ ዘመናት ያስቆጠሩ ችግሮችም ሆኑ ፤የፖለቲከኞቻችን የመቆመሪያ ካርዶች በየጊዜው መልካቸው ልዩ ልዩ ነው። ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም ቢሆን መልኩን ቀይሮና እንደመጣበት ሁኔታ አይቶ መራመድን ይጠይቃሉ። ስለዚህም በቂ ጊዜ ከሁሉም በላይ ያስፈልጋቸዋል። በሕዝቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዲኖርም መሥራት ያስፈልጋል። ሕዝቡ በተሻለ ንቃተ ህሊና ችግሮቹን በራሱ ሊዋጋ ከቻለ ሥራው ይቀማል፤ ችግሮችም መፍትሄ ያገኛሉ። እናም ሕዝብ ላይ አቅም መፍጠር ከምንም በላይ ወሳኝ ነው።
የኢትዮጵያ ህልውና ከግለሰብም ሆነ ከፓርቲ ፍላጎት በላይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አስከፊ ከሆነው ድህነት ተገላግሎ በዕድገት ጎዳና ላይ ለመጓዝ ሰላም ያስፈልገዋል። ለዚህ ደግሞ ዘመኑን ከማይመጥን ኋላቀር አስተሳሰብ መውጣት ይኖርበታል።
ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቹ የሚከበሩበት የአስተሳሰብ መሰረት ላይ የተዋቀረ ትውልድ መፍጠርም ወሳኝ ነው። ይህንን ትውልድ ለመፍጠር ደግሞ ፖለቲከኛውን ጨምሮ መላው ሕዝብ ልቡን ክፍት አድርጎ ስለ ተሻሉ ነገዎች ማሰብና በተጨባጭ መስራት ይኖርበታል። በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ከዕልቂትና ከውድመት በስተቀር ምንም ነገር የማይታያቸውም ከታሪክ መማር ይጠበቅባቸዋል።
አገር የምትፈልገው ልጆቿ ተባብረው እንዲያሳድጓት እንጂ እንዲያጠፏት እንዳልሆነም ማወቅ ያስፈልጋል። ሕዝብ እየፈጁና እያፈናቀሉ ፤የአገር አንጡራ ሀብት እያወደሙ በሕዝብ ስም መማልና መገዘት በሕዝብ ማፌዝ እንደሆነ ሊረዱት ይገባል። በነፃነት ስም ፍጅትን መስበክም ሆነ የአሸባሪዎች ተባባሪ መሆን የአገር ጠላት ከመሆን አይተናነስም። ዳር ሆኖ መተቸትም እንዲሁ። ስለሆነም የችግሩ አቅም መሀል ገብቶ ለአገር መሞትን የሚጠይቅ ከሆነ አፍን ይዞ ለመስዋዕት መዘጋጀትን ግድ ይላልና ማድረግ ያስፈልጋል።
ጥቃቅን ልዩነቶችን በአጉሊ መነጽር እየፈለጉ ሕዝብን ወደ ከፋ እልቂት ለመውሰድ የሚደረግ የፖለቲካ ቁመራ ማንንም ተጠቃሚ አያደርግም። ሁሉንም አገር የሚያሳጣ ነው እንጂ። ይህ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ከሶሪያ ከሊቢያና ከየመን ለመማር አልረፈደም። በዚህ መንገድ የሚሳካ የፖለቲካ ዓላማም ሆነ ስልጣን የለም። እናም ዛሬ እንደውም አሁን ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። ጀርባ እየተሰጣጡ የመበላላት የታሪክ ምዕራፍ አሁን መዘጋት አለበት።
አገር መውደድ ማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ጠበቃ በሚያደርጉ እሴቶች ላይ መስማማት ነው። በማህበረሰብ ለታቀፉ ሰዎች ታማኝ ሆኖ ማገልገልም ነው። የአገር መውደድ ስሜት፤ የግድ የሰው ልጆችን ከመውደድ መነሳት ይኖርበታል። በአንተ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌሎች እንዲሆን ካለመፈለግ እሴት ጋር ይሰናሰላልም። እሴቶቹ ሁሉንም ሰዎች ወይም ሕዝቦች የሚመለከቱ ናቸውም።
የአገር ፍቅር በተለያዩ ዘመናት የሚኖሩት ዋነኛ ትኩረቶች የሚለያዩ በመሆናቸው፤ የአገር ፍቅር መገለጫው እንደ ጊዜው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ከሕዝብ ጋር መዋቀርንና ለሕዝብ መቆምን ግን መቼም ቢሆን አያግደውም። ሊለውጠውም አይችልም። ስለዚህም ተለዋዋጭነት እንደ ሕዝብ ከታየ ዘላለማዊነት ነውና የአገራችንን ስሜት በዚህ ለክተን መንቀሳቀስ ይገባናል።
የአገር መውደድ ጉዳይ ማሰብን እና ማስተዋልን ይጠይቃል። አገርን መውደድ በመሠረታዊነት በእሴቶች እና በመርሆዎች ዙሪያ የሚመሰረት አመለካከት ነው። የማይለዋወጥ ነውም የሚባለው ከዚህ አኳያ ነው። ነገር ግን አመራሩ ዘመኑን የዋጀ መሆን ይኖርበታል። መውደድን ለመግለጽ በየዋህነት እና ባለማወቅ ከተመራ አደገኛ ውጤት ይኖረዋል። ለምሣሌ፤ ዴሞክራሲያዊ በሆነች አገር ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ እሴት ይዞ አገር ወዳድ ነኝ ማለት በፍጹም አይቻልም።
አገር ወዳድነት ከግለሰብ ቢመነጭም ከግለሰብና ወይም ከቡድን ጋር መያያዝ የለበትም። ይህ የሚከሰትበትን አጋጣሚ ማየት ይኖርበታል። አጋጣሚዎቹን በማስተዋል መጓዝም ያስፈልጋል። አንድ መሪ፣ ግለሰብ ወይም ቡድን ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚወክል እንዲሁም በሰው ልጆች ሁሉ ተቀባይነት ያለውን እሴት ያነገበ መሪ ወይም ቡድን ሆኖ ሲገኝም ነው አገር ወዳድ ነው ብለን ልንከተለው የምንችለው። ነገር ግን ያ ግለሰብ ወይም ቡድን ከእሴቶቹ ተቃራኒ የሆነ ሥራ ውስጥ ሲገባ መወደዱ ይቀራል። ስለዚህ ለአገር ዘወትር ታማኝ መሆን ይገባል።
ጎራ ለይተው በጦር መሣሪያ እያስፈራሩ መቀጠል እንደማይቻልም መታመን አለበት። ጠመንጃ አምላኪነት ለውድመት ካልሆነ በስተቀር ለልማት አይበጅምና መሪውም ተመሪውም ይህንን እያስተዋለ ይጓዝ። ሰላምና በረከት ለአገራችን ይሁን !!
ክብረ ነገስት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2014