‹‹የባህል ወዙ ጉዝጓዙ›› እንዲሉ ሆነና ሆቴሉ ከአሰራሩ ጀምሮ ባህላዊ የሆነውን ቦታ መርጦ፤ በቄጤማው ጉዝጓዝ አስውቦ ኑ ግቡ ይላል። የእጣኑ ሽታም ቢሆን ስቦ ወደ ውስጥ ያስገባል። በተለይ ወደ ውስጥ ዘለቅ ሲሉ የሚያዩት ነገር ደግሞ የባሰ ውጦ የሚያስቀር ውበት አለው። ምክንያቱም እንደእኔ ተባራሪ ሰው ካልሆነ በስተቀር አንድም ሰው ከባህላዊ ልብስ ውጭ አለበሰም። በወጣቶች በባህላዊ አልባሳት እንዲህ ደምቀው የታዩበት ትዕይንት ይህ ብቻ ይመስላልም።
የደመቀው ቤት ደግሞ ያደጉበትን ሜዳ፣ የቦረቁበትን በዓልና የደስታ ቀናት በማስታወስ ወደ ልጅነቶ ይጎትቶታል። እናም ሳይወዱ በግድ በሰመመን እንዲቆዩ ይሆናሉ። የቦታው ውበትና የመርሃ ግብሩ ዝግጅትም ቢሆን አገር ላይ ሆኖ አገርን መናፈቅን ያስተምራል። የተዘከረው የአገር ጉዳይ ሲሆን፤ በአገር መፍታታትን የሚማሩበትም ነው። በተለይ ወጣቱን መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ስለነበር ሁሉም ተመስጦ የሚከታተለው ሆኖ አልፏል።
ትኩረቱ ‹‹የአገር ባህል ልብሳችን ለወጣቶቻችን›› በሚል ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል። የባህላዊ ልብሳችን ቀንም ነው። ስለሆነም በመድረኩ ላይ ባህላዊ ልብስን የተመለከቱ በርካታ ጉዳዮች በጥናት ተደግፈው ቀርበዋል። ከልጅነት እስከእውቀት ብዙ ነገር የለመድንበት፤ የኖረንበት እንደሆነም ተዳሷል። ዛሬም ዘመናትን እያሻገረ እንድናስታውሰው እንዳደረገንም ተብራርቷል። በተለይም እኛ ከአባቶቻችን ወርሰን ሁሌም ድምቀታችን ሆኖ ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው እንደሆነ በባለሙያዎች ተቃኝቷል። ነገር ግን ከዚህ በፊት አንድ ነገር ማንሳት ግድ ይለናልና ወደዚያ ልግባ። ጉዳዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትን ጥበብና ዘመን ተሸጋሪነት የሚያሳይ ነው። ማን ተናገረው፣ ማን አጠናው የሚለው ጉዳይ ሌላ ቢሆንም።
ኢትዮጵያዊያን ባህላዊ አልባሶቻቸውን መልበስ የጀመሩበት ጊዜ ቀና አልተጠናም። ምን አይነት ምን ያህል የባህል አልባሳት አሉን የሚለውም እንዲሁ ገና ጥናትና ምርምርን የሚጋብዝ ነው። ይህ ደግሞ ከዘረፋ እንዳንድን አድርጎናል። እንደውም ምን ያህል የጥበብ ባለቤት እንደሆንን ከመናገር ውጭ ማስረጃ የለንም። ነገር ግን የውጭ አገራት ዘርፈውን እንኳን ስለእኛ እድሜ ጠገብነት ሲናገሩልን ይስተዋላል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን በአንድ ወቅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዞት የወጣው ‹‹ከ147 ዓመት በፊት የተሰራው ቀሚስ›› የሚል ርዕስ የያዘው ጽሁፍ ነው። ይህ ባህላዊ ልብስ በዲዛይንም ሆነ በውበት ከአሁኑ የጥበብ ሥራ እጅግ የላቀ እንደነበር ይነገርለታል። በየዘመኑ ከዚያ የተሻሉ እንደነበሩም በጽሁፉ ተብራርቷል።
ባህላዊ አልባሳቱ የቀድሞዎቹ ባህላዊ አልባሳትም ከዛሬው ባልተናነሰ ሁኔታ ዘመናዊነት ይታይባቸው እንደነበር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። እንዲያውም «የዛሬዎቹ ምን ዘምነዋል ይባላል!» ያስብላል። ምክንያቱም ታሪካዊው ቀሚስ የዘመኑን ጥበብ ሊመሰክርና ቀደምቶቹን ሊያስወድስ ብቅ ያለ ነው ይላል ጽሁፉ። የተሰራው ወይም የተለበሰው 1860ዓ.ም አካባቢ ሲሆን፤ በማን ተሰራ? የሚለውን ግን አይናገርም። ነገር ግን የእኛ ስለመሆኑና በአገራችን ባለሙያዎች ለመሰራቱ ቅንጣት ታክል አጠራጣሪ ነገር አይስተዋልበትም። ምክንያቱም ቀሚሱ ከጥጥ ተፈትሎ የተሰራ እንደሆነ ፍንትው ብሎ ይታያል።
ይቀጥልናም በአገራችን ሸማኔዎች ተሰርቶ፤ በአገራችን እውቅ ጠላፊ ተጠልፎ የንጉሱ የአጼ ቴዎድሮስ ሁለተኛዋ ሚስት ተውበው የሚቀርቡበት የክት ቀሚስ መሆኑ እርግጥ ሆኗል ይላል። ይህ ቀሚስ ታሪካዊ ነውና ታሪኩን በጥቂቱ ለማስታወስ እንሞክር የሚለው ጽሁፉ፤ መጋቢት ወር 1860ዓ.ም ላይ የእንግሊዝ መንግሥት በጄኔራል ሮበርት ናፒየር የተመራው ጦር በጊዜው እጅግ ግዙፍ የተባለ ኃይሉን አሰናድቶ አውሮፓውያን እስረኞችን ለማስፈታት ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው። መጋቢት አምስት ቀን 1860ዓ.ም ይህ ጦር በመቅደላ ምሽግ ላይ በሚገኘው የንጉሱ ጦር ላይ ጥቃት አደረሰ። በውጊያው መሀል ንጉሠ ነገሥቱ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁ እስከ መጨረሻው አሻፈረኝ በማለት በሽጉጣቸው እራሳቸውን ገድለው በጀግንነት አለፉ።
ከጦርነቱ በኋላ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው ከተወሰዱት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቅርሶች መሀል ይህ የአጼ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ባለቤት የልዑል አለማየሁ እናት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ የሐበሻ ቀሚስ አንዱ ሆነ። ለዚህም ነው ወጥቶ ሲታይ ባለታሪክ ጥበበኛ መሆናችን ይፋ የተደረገውም ይላል ጽሁፉ በማብራሪያው። በቀሚሱ ኢትዮጵያ ባለታሪክና የባህል አልባሳት በራሷ የእጅ ጥበብ የምትሰራ መሆኗን አረጋግጧል። የጥንቱ ባህላዊ አልባሳታችን ባህልነቱ ብቻ ሳይሆን ጥበብነቱም ጭምር የላቀ መሆኑንም ዓለምን ጭምር አሳምኗልም ይለናል።
ከዚህ በተሻለ መንገድ መጓዝና ያላወቅነውን በራሳችን አቅም ማውጣት እንዳለብን ግን ሳንጠቁም አናልፍም። ምክንያቱም በየዘመናቱ ታሪክ የሚሆኑ አልባሳት እንደሚኖሩን ይህ ያነሳነው ጉዳይ አመላካች ነው። አጥኒና አስተማሪ ብቻ ነውም ያጣነው። ስለሆነም ይህንን ጉዳይ በስፋት ማየቱ የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት። በእርግጥ የተዘጋጀው መድረክም ይህንኑ ጉዳይ የሚያነሳና የሚያትት ነው። እንደውም የምስራች ጭምር የተነገረበት ሆኖ አግኝተነዋል። ምክንያቱም የባህላዊ አልባሳታችን መለያ አርማ ወይም ሎጎ ሊሰራለት እንደሆነ ሰምተናል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ የፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ናፊሳ አሊማህዲ በወቅቱ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ የሚያስጠራ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት አርማ (ሎጎ) ማዘጋጀት የውዴታ ግዴታ ጉዳይ ነው። እየተዘረፉ መቆየት ከዚህ በኋላ ማክተም አለበት። ይህንን ማስቀረት ደግሞ የሚቻለው የራሳችንን ማስረጃ ይዘን ብራንድ ስናደርገው ብቻ ነው። እናም የሎጎ ሥራው «ባህል ልብሳችን መድመቂያችን» በሚል ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያን ልብስ መለያ የያዘ እንዲሆን ታቅዶ የተከወነ ነው።
የባህል ልብሳችን ብዙ ፋይዳ አለው። የመጀመሪያው ማህበራዊ ሲሆን፤ ማንነታችንን የሚገልጥና የሚያስተሳስረን ነው። ሁለተኛው ደግሞ ኢኮኖሚያችንን ከፍ የምናደርግበት የገቢ ምንጫችን ነው። ሌላው ፖለቲካዊ አቅማችንን የምናጎለብትበት እድል የሚሰጠን ነው። እናም ይህንን ፋዳውን ለማጉላት የእኛ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም መረባረብ አለበት። በተለይም ወጣቱ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ማመን እንደሚገባው ያስረዳሉ።
በባህል ልብሶች ኢንዱስትሪ ላይ ያለውን አሉታዊና አወንታዊ ጎኖች መርምሮ የተሻለውን መንገድ መከተል እንደሚገባና አሰራሮችን መቀየስ እንደሚያስፈልግ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ማህበረሰቡ የራሱን ባህላዊ አልባሳትን ማክበር ላይ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ነጋዴዎችም ቢሆኑ ከመጠን ያለፈ ትርፍን ሳይፈልጉ የአገር ባህል ልብስ ወዳድ ትውልድን መፍጠር ላይ ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ፎሊ ንጉሴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ትውልዱ የባህሉ አክባሪ እንዲሆን ወጣቱን መነሻ በማድረግ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል። በዚህም የባህል አልባሳት ቀን በማለት ማህበሩ እያከበረው ይገኛል። ባህላዊ አልባሳታችን የክት ብቻ ሳይሆኑ የዘወትርም መሆን ይችላሉ። እናም የክትነታቸውን አክብረን የዘወትሩን እያደረግንም ብንደምቅበትና ብንለማመደው ብዙ ነገራችንን መቀየር እንችላለን። ይህን ደግሞ በተለይ ወጣቶች ቢያደርጉት የበለጠ ተሰሚነት ይኖረዋልና የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል።
መወራረሶች መልካም ቢሆንም የራስን ትቶ ለሌሎች መገዛት ግን አይገባም። በተለይ የባህል አልባሳት ላይ ያለው ተጽዕኖ ከባድ በመሆኑ እንደነዚህ አይነት ቀናትን በብሔራዊ ደረጃ በማክበር ወጣቱ ባህሉንና አገሩን ወዳድ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለባህል አልባሳት የሚሰጠው ቦታና ክብር የላቀ እንዲሆን ግንዛቤ መፍጠርም ያሻል። ስለሆነም ማህበሩ ከአንዳንድ በጎ አሳቢ ማህበራት ጋር በመቀናጀት ሥራውን ለዓመታት ሲከውን እንደቆየም ይናገራሉ።
በወቅቱ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ፍሬሕይወት ባዩ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ባህል ይዘነው የምንወለደው ሳይሆን የምንለምደውና የምንኖረው ነው። ለዚህም ነው ዩኔስኮ ባህልን በሁለት ከፍሎ የሚመለከተው። አንዱ መንፈሳዊ ሲሆን፤ ሁለተኛው ቁሳዊ ባህል ነው። ዛሬ የያዝነው የባህል ልብሳችን ጉዳይ ደግሞ በቁሳዊ ባህል ይካተታል። ይህ ሲባል ግን መንፈሳዊ ባህሉን አይዝም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ልብስ እንዲሞቀን ወይም የሰው ዓይን ለመሳብ ብቻ ብለን የምንለብሰው አይደለም። ሲሰራ ጀምሮ አብሮ የሚሰጠው ማንነት አለው።
ባህላዊ ልብስ የተሰራለትን ማህበረሰብ እምነት፣ ፍልስፍና፣ ጥበብን የመሳሰሉ ነገሮችን በውስጡ ይይዛል። ከዚያም ሻገር ሲል ሀገረሰባዊ የእጅ ሥራ፤ ሀገረሰብዓዊ ሥዕል፤ ሀገረሰብዓዊ ምህንድስናን አጉልቶ ያሳያል። ከቃላዊ ተግባቦት ባሻገር በተግባርም የምንግባባበት ነውም የሚሉት ዶክተር ፍሬሕይወት፤ ሀገረሰባዊ ልብስ ብቻውን ሳይሆን ጌጦችንና አብረው የሚያዙ ነገሮችን ጭምር የሚያካትት ነው። እናም ቁሳዊነቱን ስናብራራው ቀለም፤ ቅርጽ፣ የሚሰራበት ሂደት፣ እውቀትን ይጨምራል። የማህበረሰብ እሴትን በሙሉ ይሸከማልም። ይህንን ካልያዘ ባህል ሊባል እንደማይችልም ያስረዳሉ።
ቁስ ውርስ በመሆኑ አላቂ፣ የሚሰበር ነገር ግን የሚተካ ነው። ቋሚ ግን ደግሞ ዘላቂም ነው። ከዚህ አንጻር ባህላዊ አልባሳትም አላቂ ግን ተተኪ፤ ቋሚ ግን ደግሞ ዘላቂ ናቸው የሚባለውም ለዚህ ነው። ይህ ባህሪያቸው ደግሞ ዘመናትን ያሻግረናል። በእርግጥ በዘመናት ሂደት ባህል ተለዋዋጭ ነውና አንዳንድ ነገሮች ሊተካኩ ይችላሉ። ሆኖም አይጠፋም። የሚተካው ያንን ታሪክ እያስቀመጠ የሚሄድ ስለሚሆንም ይገነባባል እንጂ አይጠፋፋምም ይላሉ።
ሌላው ያነሱት ነገር ቁስ በባህል ውስጥ ይገለጻል፤ ባህሉም እንዲሁ ቁሱን ያብራራዋል የሚለው ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ የልብስ ወሰኑን ስናይ አገልግሎቱ ላይ ብቻ የማናርፈው ለዚህ ነው። በማን፣ ለምን በዚህ ቀን፣ መቼ ይለበሳል የሚሉትን ለማየት የሚያስገድደውም አንዱ ከአንዱ ጋር ተመጋጋቢና ውክልና ያለው ስለሆነ ነው። በተጨማሪም አገረሰባዊ ልብሶች ከማንነት ጋር መያያዛቸው አንዱ በአንዱ እንደሚገለጽ ያሳየናል። ማንነት ደግሞ ግለሰባዊ፣ ማህበረሰባዊና አገራዊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም በእነዚህ ውስጥ ሁለቱን ሳንነጥል እንድናይ እንደምንሆንም ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ፍሬሕይወት ገለጻ፤ ቁሳዊ ባህል ማለትም እንደ ሀገረሰባዊ አልባሳት አይነት ለመኮረጅ በጣም ቅርብ ናቸው። የእኔ ነው ለማለትም ያስቸግራሉ። በዚህም በሌሎች የመወሰዳቸው ምጣኔ እጅግ የሰፋ ነው። ለምሳሌ፡- ቻይና በእኛ አሰራር ምርቷን አምጥታ በርካሽ ስትቸበችብ ማንም ያልጠየቃት መከራከሪያ ስለሌለን ነው። በዚህ ደግሞ ባህላዊ አልባሳቶቻችን ቦታውን ለሌላ ለቀዋል። ልብስ ጠፋ ማለት ደግሞ ማንነት ጠፋ ነውና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። መፍትሄው ደግሞ የራስን ማስከበር የሚያስችል ሥራ መስራት ሲሆን፤ አንዱ በመረጃ የተረጋገጠ ማስረጃ መያዝ ነው።
ሀገረሰባዊ አልባሳት የምንላቸው ራሳችን አምርተን የምንጠቀመው ሲሆኑ፤ በዋናነት የጥጥ ልብሶች ናቸው። በእነቻይና አይነት አሰራር የሚመጣብን ካለና አካሂዳችን በዚሁ ከቀጠለ ምን አልባትም ዛሬ የምናየው ማንነታችን የእኛ ላይሆን ይችላል። በዘመን ሂደት ውስጥ እንዲህ ነበረ የሚለውንም ጭምር ልናጣ እንችላለን። ስለሆነም ከህሊናችንም ሆነ ከተግባራችን ጋር ባህላችንን ማስተሳሰር የዛሬ ባለአደራዎች ግዴታችን እንደሆነም ያስገነዝባሉ።
ሌላው ጥናት አቅራቢ አቶ ኢያሱ በሬንቶ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሰው ፊት ጎልቶ ለመታየትና ለመደነቅ እንደ ባህላዊ ልብስ ምንም አይኖርም። ውክልናቸው ጭምር የብዙዎችን ቀልብ የሚሰብ ነው። ነገር ግን እንደ አገር ሲታይ በብዙ መልኩ እንዲጎሉ ሲደረግ አይታይም። የመገፋፋት ልክም ሆነው ይቀርባሉ። የብሔረሰቡ ብዛት ድምቀት እንደሆነ ቢታመንበት ግን እንደ ኢትዮጵያ የተዋበ አገር ለማየት ይቸግር ነበር። በባህላዊ አልባሳታችን መሞላላትና መዋዋብ እንችልም ነበር። ምክንያቱም በእኛ ህሊና ውስጥ ደስታና እርካታን መፍጠር ካልቻሉ አምሮባቸዋል ልንላቸው አንችልም። ስለሆነም አንዱ በአንዱ መድመቅን ልምዱም ምግባሩም ማድረግ ይኖርበታል።
‹‹ህሊና የምልከታዎቻችን ፤ የእይታዎቻችን ስብስብ እንጂ ይህ ነው የሚባል ቁስ ነገር አይደለም›› የሚሉት አቶ ኢያሱ፤ ነገሮች ገና የሚዋቡና ብዙ ነገርን የሚፈልጉ ናቸው። እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ አንድም ውበት የለም። ምክንያቱም ከቀነሰ የሚያየው አይኖርም። እናም እኛ ኢትዮጵያዊያን ለመድመቃችን ምስጢር የሆነውን ብዙ የመሆናችንን ነገር ማክበር አለብን። የእይታዎቻችን ድምር ውጤትም መልካሙ ላይ እንዲያደርሰን ማድረግ ይኖርብናል። የአገር ባህል ልብሳችን አገር እንጂ ክልልና ድንበር የለውምና ይህንን ገንዘብ እናድርገው መልእክታቸው ነው።
የጥፍጥሬ ኢቨንትና ኦርጋናይዘር መስራችና የበዓሉ አዘጋጅ አቶ ቁብላቸው አበበ እንደሚሉት፤ ባህል ማሕበረሰባዊ ስሪት ነው። የአንድን ትውልድ ማንነት እና ምንነት ወጥ አድርጎ የሚቀርጽና አዲስ የሚያደርግ ነው። የግለሰቦች ድርጊት እና ስሜት የፈጠራቸው እና ያነጻቸው ማሕበረሰባዊ ነጸብራቆች የሚታዩበትም ነው። ባህላዊ አልባሳታችንን ስናነሳ ደግሞ ትህትና፣ ፍቅር፣ ይቅርባይነት፣ ሰብዓዊነት፤ ደስታን የምንላበስበት መድመቂያችን ነው። በአጠቃላይ በጎ ምላሾችን የምንሰጥበት ፍካታችን ነው። እናም ይህንን እንቁ ባህላችንን ከማሕበረሰቡ የተማርናቸውን ባህሪያት እኛ ኖረንበት ለነገዎቹ ማድረስ ይገባናል። ግዴታችን እንደሆነ አስበንም ልንሰራበት ያስፈልጋል።
ባህላዊ አልባሳቶቻችን ሐገርኛ ውክልናችን እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ቁብላቸው፤ ዛሬ ላይ እያየን ያለነው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። የሌላ ናፋቂ እንጂ የራሳችን አድናቂ አልሆንም። ይህ ተግባር ደግሞ የምንኮራበትን ታሪክ አያስቀማንም ለማለት ያስቸግራል። ስለሆነም ቆም ብለን የምናስብበት ጊዜ ላይ ነንና ለባህላችን እንኑር፤ እንስራም ይላሉ። እኛም የክትና የዘወትር ሆነው እያደመቁን የቀጠሉትን ባህላዊ ልብሶቻችንን ከዘመኑ ጋር እያዘመኑ ተወዳጅና ተፈላጊ አድርገው ያስቀጠሉንን ሸማኔዎችና ዲዛይነሮች እያመሰገንን ማስቀጠሉ የሰርክ ተግባራችን ይሁን በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን።
ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2014