ፍቼ ጫምባላላ-የሰላም በዓል

“ የሲዳማ አያንቱዎች (የባሕል አባቶች) በተፈጥሮ የቆጠራ ጥበብ ተመርተው የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ቀን ፍቼ ጫምባላላ በዓል መቼ መሆን እንዳለበት ይወስናሉ። በዚሁ መሠረት የፍቼ ጫምባላላ በዓል በታላቅ ሥነ ሥርዓት በየዓመቱ ይከበራል። አከባበሩ ለየት ያለ በባሕላዊ አልባሳት የተዋበና የደመቀ ነው። በበዓሉ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት በባሕሉ ሕግና ሥርዓት መሠረት ይከበራል። ፍቼ ጫምባላላ የአደባባይ በዓል ሆኖ ብሔረሰቡ ባሕላቸውን ለዓለም የሚያሳዩበት ዝግጅት ጭምር በመሆኑ ልዩ ድምቀት አለው። በዚሁ በዓል አከባበር ላይም ከመላ ሀገሪቱ እንግዶች በዓሉን ለማክበር ይገኛሉ። በዓሉ እጅግ በተዋቡ የባሕል አልባሳት የተንቆጠቆጡ አባቶች ጋሻና ጦር ይዘው፣ ሴቶችም በአልባሳት እና በጌጣጌጥ አምረው፤ ወጣቶችም በተመሳሳይ የበዓሉን ማድመቂያ ተውበው የሚያከብሩት ነው። ይሄም ትልቅ የቱሪስት መስህብ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ፍቼ ጫምባላላ በዓል በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የማይዳሰሱ ቅርስ ሆኖም ተመዝግቧል። ዘንድሮ 10ኛ ዓመት በዓሉን ያከብራል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው ባሕላዊ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት አላቸው፤ ከእነዚህ አንዱና ተጠቃሹ ፍቼ ጫምባላላ ነው። የዘመን መለወጫ ቀን አቆጣጠሩ ደግሞ ምንም መዛነፍ የሌለበት በየዓመቱ ወቅቱን ጠብቆ የሚከበር ሲሆን አንድ የተቆረጠ ቋሚ ቀን ግን የለውም። የብሔሩ ተወላጆችም በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ በመገኘት በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓት ያከብሩታል፤ የፍቼ ጫምባላላ ባሕላዊ ሥርዓት ባሕላዊ ምግብንም የሚያካትት ነው። የፍቼ ጫምባላላ ከዋዜማው አንስቶ በዓሉ መከበር ይጀምራል። ጎረቤት ተሰብስቦም ከእንሰት የሚዘጋጀውን «ቦርሻሜ» ተብሎ የሚጠራውን ምግብ በወተት ይመገባሉ። ከሚበሉ ባሕላዊ ምግቦችና ከሚከናወኑ ጭፈራዎች በተጨማሪ የተለያዩ ባሕላዊ ሁነቶችም ይካሄዳሉ። ቄጠላ፣ ኛፋሮና የመሳሰሉ ሙዚቃዎችም በበዓሉ ማድመቂያ ናቸው። በዓሉ የሚከበረውም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ነው። ይሄውም የበዓሉ ዋዜማ ቀን ፍቼ ሲባል የአዲስ ዓመት መጀመሪያው ቀን ደግሞ ጫምባላላ መሆኑን የሲዳማ ክልል የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊና የባሕል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ዳንጊሶ ይናገራሉ።

የበዓሉ ምንነት

በርካታ የማንነታችን መገለጫ ከሆኑ አኩሪ ባሕሎቻችን ውስጥ አንዱ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል (ፍቼ ጫምባላላ) ነው። ይህ በዓል በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል።

የፍቼ ጫምባላላ በዓል በርካታ ባሕላዊ ክንዋኔዎችን በውስጡ የያዘ ነው። ለአብነትም በዓሉ የሲዳማ ብሔር የአዲስ ዘመን መቀበያ ከመሆኑም ባሻገር በዓሉ ዘመዳሞች የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶች ተፈተው እርቅ የሚወርድበት፣ ሀገር በቀል የሆኑ ዕውቀቶች ማለትም ባሕላዊ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት በብሔሩ ባሕላዊ ሊቃውንቶች የሚከወንበት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የሥነ ምህዳር እውቀቶች ለወጣቱ ትውልድ የሚተላለፉበት እንዲሁም ባሕላዊ የምግብ አዘገጃጀት ጥበብ የሚታይበት በዓል ነው። ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ የተለያዩ ባሕላዊ ጭፈራዎች የሚደምቅበት ልዩ ቀን መሆኑን ነው የሚጠቅሱት።

ቀኑ እንዴት ይቆረጣል

የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ቀን የሚወሰነው የሲዳማ ብሔር አያንቱዎች የበዓሉን ዕለት ለመቁረጥ ያለ ዘመናዊ የመቁጠሪያ ቀመር እና ርዳታ የጠፈር አካላትን ክስተት እየመረመሩ፤ በጨረቃና ከዋክብት ኡደታዊ እንቅስቃሴ ላይ በመመሥረት እንዲሁም ጊዜውን በማስላት ጭምር ነው። ከቀደምት አበው ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ባሕላዊ የዘመን መቁጠሪያ ቀመር መሠረት የፍቼ ጫምባላላ በዓል በየዓመቱ ያበስራሉ። ይሄ የሲዳማ ብሔር በራሱ ሀገርኛ አቆጣጠር አስልቶ የዘመን መለወጫ ቀን የሚቆጥርበት ብሔረሰቡ የተግባቦትና የሚተገብረው ነው። በዓሉ ከዘመን መቁጠሪያነቱ ባለፈም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን፣ ቂምና ቁርሾ እንዳይኖር ፤ ቀማኛ የሰውን ሀብት የሚመኝ እንዳይኖር ለማድረግም ያገለግላል። የፍቼ ጫምባላላ ዋነኛ ትርጉም ሰላም ነው። አንድነትና ፍቅር የበዓሉ መለያ ናቸው።

የተጣሉ ሰዎች በፍቼ ጫምባላላ በዓል ላይ ይታረቃሉ። ሀዘን ላይ የነበሩ ሰዎችም የሀዘን ልብሳቸውን ይቀይራሉ። ወንዶች አዞ ለመምሰል ቆዳቸውን ይበሳሉ። ዘንድሮ ያገባች ሴት ሙሽርነቷን ጨርሳ ከሌሎች ሴቶች ጋር የምትቀላቀልበት በዓል ነው። እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬው ርቆ የነበረ ሰው በፍቼ ጫምባላላ ወደቀዬው ይመለሳል።

ለዚህ በዓል ተብሎ እርድ አይፈጸምም። ከብቶችን መምታትም ክልክል ነው። ላሞች ሣር የበዛበት መስክ ላይ ይሰማራሉ።

በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ በፍቼ ጫምባላላ በዓል ወቅት ማረስ ነውር ነው። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የፍቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮም ጭምር ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

በዓሉ የሚከበረውም የተጣላ ታርቆ፣ የተቀያየመም በይቅርታ የሚሻገርበት ልዩ ባሕላዊ እሴቶችን ያቀፈ ነው። ይህ በዓል ከሀገር ውስጥና ከመላው ዓለም የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎችን ጨምሮ ዘንድሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይታደምበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በዓሉ የሚከበረው ለሁለት ቀን ሲሆን በዋዜማው መጋቢት 18 የ«ፊጣራ» ዕለት ሲሆን በታላላቅ (ዕድሜ ቅደም ተከተል) በ”ሁሉቃ” የመሻገር ሥርዓት እየተፈፀመ “ቡርሳሜ” ይበላል። ጾም የሚፈታበት እለት ነው። በማግስቱ ጫምባላላ በሶሬሳ ጉዱማሌ ይከበራል።

በዚህም ጊዜ ገንዘብ ያበደረ እንዲመለስለት የማይጠይቅበት፣ ከብት የማይታረድበት፣ ዛፍ የማይቆረጥበት፣ ያጠፉ ይቅር የሚባልበት ዕለት ነው።

በዩኔስኮ ለመመዝገብ ያበቁት

ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ቀን ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የዛሬ 10 ዓመት ነው። ለምዝገባው የበቃውም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የብሔሩ አባላት ያቀረቡትን ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከ2005 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የፍቼ ጫምባላላ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የጥናት ሰነዶች አዘጋጅቶ በማቅረብ ነው። ሰነዱ በወቅቱ ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ከሲዳማ ዞን ባሕል፣ ቱሪዝምና መንግሥት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ጋር በቅንጅት ተዘጋጅቷል። የተዘጋጀውም ሰነድ መጋቢት 2006 ዓ.ም ለዩኔስኮ እንዲላክ ተደርጓል። ይህ የኖሚኔሽን ፋይል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው ከሰኔ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በዩኔስኮ ድረ ገፅ ላይ እንዲጫን ተደርጓል። በዩኔስኮ ድረ ገፅ ላይ ተጭኖ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው የተደረጉት ሰነዶችም፤

  1. የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በቅርስነት መመዝገቡን የሚያረጋግጥ (National Inventory document)
  2. ስለ ፍቼ ጫምባላላ ሰፋ ያለ መረጃ የያዘ የኖሚኔሽን ሰነድ፤ (ICH-02 Nomination Form)
  3. ፍቼ ጫምባላላን ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ የ10 ደቂቃ ቪዲዮ፤
  4. ፍቼ ጫምባላላን የሚያመለክቱ ፎቶግራፎች፤
  5. የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ተጽእኖ ወይም ግፊት በራሳቸው ተነሳሽነት ፍቼ ጫምባላላ በዩኔስኮ እንዲመዘገብላቸው መስማማታቸውን የገለጹበት የጽሑፍ ሰነድና ይህንንም ከስማቸው አኳያ በፊርማቸው ያረጋገጡበት መረጃዎች ናቸው።

ይሄም ሰነድ ፍቼ ጫምባላላ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ዩኔስኮ የሚጠይቀውን ሂደት ጠብቆና የተለያዩ የግምገማ መስፈርቶችን አልፎ በዩኔስኮ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እ.ኤ.አ ከNovember 30– December 04/2015 ድረስ በናሚቢያ በተካሄደው 10ኛው የዩኔስኮ የኢንታንጀብል ባሕላዊ ቅርሶች ጥበቃ የኢንተርገቨርንመንታል ኮሚቴ መደበኛ ጉባዔ ላይ ቀርቧል። ለምዝገባ ውሳኔ በጉባዔው ላይ 35 የኢንታንጀብል ባሕላዊ ቅርሶች የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም አንዱ ፍቼ ጫምባላላ ነበር። በጉባዔው 23 የኢንታጀብል ቅርሶች እንዲመዘገቡ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል። ከነዚህም አንዱ ፍቼ ጫምባላላ ሆኖ መመዝገብ ችሏል። ይህም ለሀገራችን ትልቅ ጥቅም ያለው ሲሆን በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የማይዳሰስ ቅርስ ቁጥርን አሳድጓል። ከዚህም ጎን ለጎን የቱሪስት ፍሰቱ ከዓመት ዓመት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ዓይናቸውን ማረፊያ አድርገው ወደ ሥፍራው ይሄዳሉ። በሀገር ውስጥ ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያሳድግ የባሕል ትውውቅን የሚያሰፋ አንዱ መንገድ ነው። የውጭ ቱሪስቶችን በመሳብ ለውጪ ምንዛሬ ገቢ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ችሏል።

የሲዳማ ሕዝብ የጨረቃና ከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት አዲስ ዓመት ማክበር ከተጀመረ ከ1800 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ።

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You