
በሸካቾ ብሔረሰብ ለቅሶ ማሕበራዊ ትስስርን ማጠንከሪያ፣ የሟችን እና የሟች ወገኖችን ማንነት መግለጫ፣ የሀብት መጠን ማሳወቂያ፣ ወዳጅ እና ጠላት መለያ፣ ተደርጎ ይወሰዳል። ማሻ፣ አንድራቻ እና የኪ የተሰኙ ሦስት ወረዳዎችን በውስጡ ባቀፈው እና በዚሁ ብሔረሰብ ዞን 56 የገጠር እና ሰባት የከተማ ቀበሌዎች እንዲሁም ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ይገኙበታል።
በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የ1999 ዓ.ም የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤትን ተንተርሶ በ2002 ይፋ እንዳደረገው መረጃ 219 ሺ 157 ነዋሪዎች በሚገኙበት ሲሆን የብሔረሰብ ባሕላዊ የለቅሶ ሥርዓት ክዋኔ በሁለት የተለያዩ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የወጣው በብሔረሰቡ ባሕላዊ የለቅሶ ሥነሥርዓት ላይ ያተኮረ ጥናት ይስረዳል።
ጥናቱን ያካሄደው ፍፁም ብርሃኑ እንዳሰፈረው ለሟቹ ስንብት ማድረግ የሚጀመረው ገና ነፍሱ ሳትወጣ ታሞ በአልጋ ሳለ ነው። ነፍሱን ከሞት ለመታደግ ከባሕላዊ እስከ ዘመናዊ ሕክምና እና ምግብ የዘለቀ እንክብካቤ ሲደረግለት ቆይቶ ተስፋ የሌለው ከሆነ ስለ ሀብቱ ለተመረጡ ሦስት የሀገር ሽማግሌዎች ኑዛዜና ስንብት ይደረጋል። ከኑዛዜው በኋላ በቤት ውስጥ መቀመጡ ለቋሚ ቤተሰቦቹ መጥፎ እድል ያመጣል ተብሎ ስለሚታመን ከቤቱ በስተጓሮ ጎጆቤት ይሰራለትና ከቤት ወጥቶ እዛ ውስጥ ከሕብረተሰቡ ተገልሎ እንዲቀመጥ ይደረጋል። የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችም አብረውት ይሄዱና ሦስት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ከማንም ንክኪ ሳያደርጉ እስኪሞት አብረውት እንዲቆዩ ይደረጋል። እነኝህ ሰዎች ከማሕበረሰብ የሚቀላቀሉት ታማሚው ከሞተና የቀብር ሥነሥርዓቱ ከተፈፀመ በኋላ እንደፀበል የሚቆጠር ውሃ ተረጭተው ነው።
ፍፁም በጥናቱ እንዳመላከተው በብሔረሰቡ ባሕላዊ የለቅሶ ሥነሥርዓት በሟች እድሜ፤ በሀብት፤ በማሕበራዊ መስተጋብር የተቃኘ ነው። ሟች በሕይወት ዘመኑ ያከማቸው ሀብትና ንብረት ያለው ከሆነ የለቅሶ ሥርዓቱ የዚያኑ ያህል በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ያልፋል። ሟች በእድሜ የገፋ፣ ማሕበራዊ ስልጣን ያለው እና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ የደረጀ ከሆነ የለቅሶ ሥርዓቱ ከሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ይበልጥ የተለያዩ ክዋኔዎችየሚስተዋሉበት እና የደመቀ ይሆናል።
ሟች ከመቀበሩ በፊት ከአንድ እስከ ሦስት ወር ይቆያል። ይሄም የሚደረገው በዋናነት በየአካባቢው ያሉ የብሔረሰቡ ተወላጆች በቀብሩ ዕለት እንዲገኙ ጊዜ ለመስጠት መሆኑን ፍጹም በጥናቱ ላይ አመላክቷል። ባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ ለለቀስተኞች ለማዘጋጀት እና በሟች ማሳ ውስጥ መፈፀም ያለባቸውን የእርሻ ሥራዎች ለማከናወን ስለመሆኑም ያስረዳል። የብሔረሰቡ አባል የትኛውንም አማራጭ ተጠቅሞ በቀብሩ ዕለት የመገኘት ማሕበራዊ ግዴታ አለበት። ይሄን አምኖ የተቀበለ በመሆኑ በቀብሩ ዕለት የሚገኘው ለቀስተኛ ቁጥር በእጅጉ ከፍተኛ ነው። ቁጥሩ የሚጎላው ሟች አንድ አይነት ባሕላዊ የስልጣን ባለቤት ወይም ታዋቂ ግለሰብ ሲሆን ነው።
ነገር ግን የሟች የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ ከሆነ የደመቀ ለቅሶ እና ሰፋ ያለ ሥርዓት አይኖርም። በሌላ አንፃርም ሟች በሕይወት ዘመኑ ከማሕበረሰቡ ጋር የነበረው መስተጋብር ዝቅተኛ ከሆነ በዚያው መጠን የለቅሶ ሥርዓቱ ይደበዝዛል። የለቅሶ ሥነሥርዓቱ ከእምነት ጋርም ይሰናሰላል።
ለምሳሌ ፦በብሔረሰቡ ዘንድ አንድ ጥርስ ያላበቀለ ሕፃን ሲሞት መሬት ውስጥ የሚቀበር ከሆነ እናትየው ማሕፀኗ ይደርቃል፤ዳግም ልጅ አትወልድም፤ተብሎ ይታመናል። በመሆኑም ከእናታቸው እቅፍ ሳይ ወርዱ ወይም ጥርስ ሳያበቅሉ በሞት የሚነጠቁ ሕፃናት የሚቀበሩት በሌላው የዕድሜ ክልል ከሚገኝ የሕብረተሰቡ አባል በተለዬ መልኩ፤ በአካባቢ በሚገኝ አንድ ትልቅ ዛፍ ውስጥ ነው።
የብሔረሰቡ ተወላጅና የማሻ ኗሪው ሽውራሻ ጫሊቶ እንደሚያስረዱት “ጌዳሜ ጣኦ” ይሰኛል። ታድያ ቀደም ባለው የሸክቾዎች ባሕል መሰረት በሁለት የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ የቀብር ቦታ እንዲዘጋጅ ይደረግ ነበር። አንደኛው በሟች መኖሪያ አካባቢ ባለ የግል ማሳ የሚሰናዳ ሲሆን በማሳው ውስጥ የሚቀበረው ሟቹ በኑዛዜው ወቅት “በማሳዬ ውስጥ ቅበሩኝ” ያለ እንዲሁም ቤተሰቦች በአቅራቢያችን ተቀብሮ መቃብሩን በየጊዜው እየጎበኘን መንከባከብ እንፈልጋለን የሚል ሀሳብ ያቀረቡ እንደሆነ ነው።
ሁለተኛው የቀብር ቦታ ከአካባቢው ወጣ ብሎ በሚገኝ ኮረብታማ ሥፍራ ላይ የአካባቢው ሰዎች በጋራ ያሰናዱት የቀብር ሥፍራ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በእንዲህ ያለ ሥፍራ የሚቀበሩት ነገስታት፣ የጎሳ መሪዎች፣ ቃልቻዎች እና በማሕበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ስም ያላቸው ሰዎች ናቸው። በመሆኑም በቀብሩ ዕለት ሴቶች ለቀብር በተከለለው አጥቢያ ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም። ይህ የሚሆነውም ቦታው ንፁኃን ያረፉበት የተቀደሰ ሥፍራ ተደርጎ ስለሚቆጠር ምናልባት የወር አበባ ላይ የሆኑ ሴቶች ተቀላቅለው ገብተው ያረክሱታል ተብሎ ስለሚታመን ጭምር ነው።
የሾበቻ አካባቢው ነዋሪና የብሔረሰቡ ተወላጅ የሀገር ሽማግሌ በጭሮ አንገሎ እንደሚናገሩት ፤የቀብሩ ዕለት ሦስት ቀን ሲቀረው ወደ ቀብር ሥፍራ መሄጃ መንገዱን ሰፋ አድርጎ የመመንጠር ሥራ ይከናወናል። ቀጥሎም ልምዱ ያላቸው ሰዎች ተለይተው ቀብሩ እዚህ ጋር ቢሆን የተሻለ ይሆናል የሚሉትን ቦታ በመምረጥ በአራት ማዕዘን ቅርፅ አራት ክንድ ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ሰፋ አድርገው ይቆፍራሉ። ከዚያም የሬሳ ሳጥኑ የሚያርፍበትን ዙሪያ ገባ በሙሉ ድንጋይ ቀደም ሲል በሸክላ አፈር ፤በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሲሚንቶ እያጣበቁ በጥንቃቄ ይደረድራሉ። ስመ ጥር የጎሳ መሪዎች ሲሞቱ አስክሬን የሚታጀብበት ሰረገላ፣ ዝግጅትም በዚሁ ጊዜ አብሮ የሚከናወን ነው። እንደሳቸው ገለፃ የሚዘጋጀው በቀርቀሃ ሆኖ የቤት ቅርፅ እንዲይዝ ይደረጋል። አንዱን ቀርቀሀ ከሌላኛው በሀረግ እና በቃጫ በአግባቡ ከታሰረ በኋላ ደማቅ ከለር ባላቸው ጨርቆች እንዲሸፈን ይደረጋል። አስክሬኑ በሰረገላው ውስጥ ሆኖ የሚጓዝ ከመሆኑ አንፃር በሰረገላው ዝግጅት ወቅት አስክሬኑን በፍርርቅ ተሸክመው የሚጓዙ ከ20 የማያንሱ ሰዎችን በአግባቡ ታሳቢ ይደረጋል። ይሄን ሰረገላ በአራቱም ማዕዘን ከውጭ ሆነው በመተጋገዝ እንዲይዙ ጠንከር ፤ጠንከር ያሉ ወንዶች ይመረጡና በነዚሁ ትከሻ ላይ አርፎ እያዘገሙ እንዲጓዝ ይደረጋል። አስክሬኑን የተሸከሙት ሰዎች አረማመዳቸውን ከውጭ ባሉት ሰረገላ ተሸካሚዎች የእንቅስቃሴ ልክ በማስተካከል እየተጓዙ ቀብር ሥፍራው ይደርሳሉ።
በሸካቾዎች ባሕል ዋነኛው ለቅሶ የሚከወነው የቀብሩ ዕለት ሲሆን በዚህን ጊዜ ሁሉም እጅጉን መሪር በሆነ ለቅሶ ሟችን የመሰናበት ማሕበራዊ ግዴታ አለበት። በዚህ ቀን ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት እና ጓደኞች ወፍ ሳይንጫጫ ከያሉበት በሟች ቤት ተሰባስበው ወንዶች ጦር፣ ሴቶች ደግሞ የቆጮ መቁረጫ ቢላቸውን በመያዝ ወደ ቀብሩ ሥፍራ ይጓዛሉ። እዚያ እንደደረሱም ሁሉም ከ30 ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ በጣም አልቅሰው ሴቶች በያዙት ቢላዋ በአቅራቢያቸው ካለ ቆጮ ቅጠል እየቆራረጡ፣ ወንዶቹ ደግሞ በጦራቸው መሬት እየወጉ በጋራ `ደፒዮ – ዳፒዮ ኤሰቤ’ ወይም ከዚህ በኋላ ሞት እኛን መግደሉን ያቁም፣ ሞት በዚሁ ይብቃ በማለት ለቅሶዋቸውን ያሳርጋሉ።
በተለይ ግብዓተ መሬት ሲፈጸም መሪር ለቅሶ ያለቅሳሉ። በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ሞት በተከሰተባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ለቅሶ የሚሰናዳበት ሥርዓት አንድ ዓይነት አይደለም። በሸካቾ ብሔረሰብ እነዚህ ልዩነቶች ከሚከሰቱባቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ ፆታ ነው። በብሔረሰቡ ወንድ ሲሞት እና ሴት ስትሞት የሚኖረው የለቅሶ ሥርዓት ከሥርዓተ ግንዘት እስከ ግብዓተ መሬት ፍፃሜው ድረስ የሚለያዩባቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ። ሀብታም – ደሃ፣ ጀግና – ፈሪ፣ ጌታ ፤ሎሌ፣. ሌሎች መንትያ ተቃርኖዎችን ለተለያዩ ሰዎች ሲሰጥ መመልከት የተለመደ ተግባር ነው። ይሄ በሕብረተሰቡ የተሰጠው ደረጃ ሰውየው ከዚህ ዓለም በሞት ሲሰናበትም በሚደረግለት ሥርዓት ወቅት በብርቱ ሲንፀባረቅ ይስተዋላል።
ብሔረሰቡ ከሌሎች ማሕበራዊ አጋጣሚዎቹ ይልቅ ብርቱ ማሕበራዊ መስተጋብር ላለው ለለቅሶ ሥርዓቱ የሚሰጠው ቦታ ከፍ ያለ ነው። ይህ አጋጣሚ ሕብረተሰቡ ማሕበራዊ ትስስሩን የሚያጠነክርበት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን የሚገልጥበት፣ አስተሳሰቡን የሚያጎላበት፣ ልዩ ልዩ ባሕላዊ እሴቶቹን እና እምነቱን የሚያፀናበት እንዲሁም በጉልህ የሚያንጸባርቅበት ከትውልድ ትውልድ የሚያሸጋግርበት ነው።
የሸካቾ ብሔረሰብ በቀብሩ ዕለት የሚፈፀመውን መሪር ሀዘን የሚያሳርገው “ጎሞ” በተባለ ባሕላዊ ዘፈን እና ጭፈራ ነው። ይህ ጭፈራ የሟችን እና የቤተሰቦቹን መልካም ገፅታዎች የሚያወሱ፣ ሞት ለሁሉም የቀረበ ግዴታ መሆኑን ና ዳግም የሟችን ቤተሰቦች እንዳይጎበኝ የሚመኙ ግጥሞች የሚደረደሩበት ነው። ጭፈራው በከበሮ፣ በክራር እና በጥሩንባ ታጅቦ የሚከወን ሲሆን ዓላማውም የሟች ቤተሰቦች ሀዘን እንዳይጎዳቸው ማድረግ እና “ሞት ሀዘን ሲበዛ ተደጋግሞ የሚመጣ በመሆኑ ሀዘኑ በቅቶን መደሰት ጀምረናል” የሚል መልዕክት ለማሕበረሰቡ ተወላጅ በተለይም ለሟቹ ቤተሰቦች ለማስተላለፍ ስለመሆኑም በጭሮ አንገሎ ያነሳሉ። የጎሞ ሥርዓት የሚከናወነው ከቀብር መልስ ነው። ለቀስተኛው ሁሉ አንድ በአንድ ክብ ሰርቶ ይሄን ሥነሥርዓት መታደም ይጀምራል። በክዋኔው ሂደት ታዳሚው ሞት የተወጋ ያህል ከለቅሶ መልስ የፈገገ ፊት እያሳየ በጭብጨባ ያደምቀዋል። ለከዋኝነት የሚመረጡት በአካባቢው በጀግንነታቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች ስለሚሆኑ ታዳሚው እግረ መንገዱን ለከዋኞቹ የጦር አሰባበቅ እና አፎካከር ሂደትም ድጋፉን ያሳያል። በዚህ ወቅት በባሕላዊ ጌጦች ያሸበረቁ ፈረሶችን የያዙ ሰዎች ወደ ትርዒቱ በመቀላቀል ፈረሶቹን ወዲያና ወዲህ እያንጎማለሉ ለሟች ጀግንነት ተጨማሪ ምስክርነታቸውን በድርጊት ይገልፃሉ። በመቀጠልም ክራር የያዙት ባሕላዊ ዘፋኞች ቅኝታቸውን ማሰማት ይጀምራሉ። በዚህን ጊዜ ታዳሚው ወዲያውኑ መቧደን ስለሚጀምር ባሕላዊ ዘፋኞቹ በየቡድኑ አንዳንድ እየተዘሩ ክዋኔውን ማድመቅ ይጀምራሉ።
ሴቶችም ለብቻቸው ተቧድነው በከበሮ እና በጭብጨባ በመታገዝ ደመቅ አድርገው እየጨፈሩ የሚጠበቅባቸውን ማሕበራዊ ግዴታ ይወጣሉ። ሟች ሴት ከሆነች ከፍ ሲል ከተጠቀሱት የክዋኔ አይነቶች ጦር እና ጋሻ ይዘው የሚፎክሩት፣ ፈረስ አስጊጠው ላይ እና ታች የሚሉት ይቀርና በሴቶች ብቻ የሚከወን “ሸሬ የጦ” ወይም ግማሽ አካሉ መሬት ውስጥ የተቀበረን ጋን በሰፌድ እየመቱ የመስበር ሥርዓት በተሰኘ ክዋኔ ይተካል። ይህን ተግባር የሟች የቅርብ ዘመድ የሆኑ እና “ከእጇ በልቻለሁ፣ ጠጥቻለሁ !” የሚሉ ሴቶች ክብ ሰርተው ቀደም ተብሎ የጎሞ ሥርዓቱ በሚከናወንበት ቦታ ላይ የተዘጋጀን ጋን ባሐላዊ የማፅናኛ ዘፈን ግጥሙን እየደረደሩ ተራ በተራ በያዙት ሰፌድ ጫፉን እየመቱ የጋኑን አፍ ይሰብራሉ። በዚህ ጊዜ በዙሪያቸው የተሰበሰቡ ሴቶች ከፍ ባለ ድምፅ እና በከበሮ ታጅበው የማፅናኛ ዘፈኑን በድምቀት ይወጡታል።
ይህ “ሸሬ የጦ” የተሰኘው ተግባር ለምን እንደሚከወን የአበሎ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ ዘውዲቱ ሲያብራሩ አንድ ሴት ትዳር መስርታ የራሷን ኑሮ መምራት ከጀመረች በኋላ ስትሞት ከእጇ የበሉ እና የጠጡ ሴቶች ሀዘናቸውን የሚገልፁት እሷ በሕይወት ሳለች ትጠቀምበት የነበረውን አንድ ጠጅ፤ ጠላ መጥመቂያ የሆነውን ጋን እየተቀባበሉ አፉን ሲሰብሩ ነው። ይህ የሚሆነውም ‘ሟች ለተቸገረ የምታበላ፣ የምታጠጣ ደግ እና ሞያተኛ ነበረች፣ ዛሬ ግን አፈር በላት’ የሚለውን ለማመልከት ነው። ከሌሎቹ ዕቃዎቿ ይልቅ ጋን የሚመረጠውም በአካባቢው ጠጅ በአግባቡ የመጣል ብቃት ከሙያዎች ሁሉ የሚሞገስ በመሆኑ ነው። ከዚህ በኋላ ሀዘንተኛው ሁሉ እጁን እና ፊቱን ታጥቦ በሟች ቤት የተዘጋጀውን ምግብ በመቅመስ ሀዘኑን ይፈፅማል፤ የነበረበትን ዳስ እና ለአስክሬን የተሰራውን ቤት በማፍረስ ሁሉም እራሱን ለሥራ ያዘጋጃል። ይህ ሥርዓት በእኛ ማሕበረሰብ ዘንድ እንደ ቀብሩ ቀን ሁሉ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ በተለያየ ምክንያት በቀብሩ ዕለት ያልተገኘ ሰው በዚህ ዕለት ደርሶ ሀዘኑን በመግለፁ በቀብሩ ዕለት ባለመድረሱ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው ቅሬታ እንዲወገድለት ያደርጋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም