ቀቤናዎች የሚደምቁበት የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት

ጋብቻ የቤተሰብ መሰረት፣ የሀገር ምሰሶ ነው። ትዳር የሀገር አንድነትን ማጠናከሪያም ነው። ጋብቻ ትውልድን በሥነምግባር ማነጺያና ነገ የተሸለ እንዲሆኑ ማድረጊያም ነው። ሥነ-ሥርዓቱ ደግሞ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በመሆኑ ዘመን አይሽሬ እሴቶቻችን የምናዳብርበት ነው። እሴቱ ቤተሰባዊ ትስስራችንን የምናጠናክርበት፣ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን፤ አብሮነታችን የምናጸናበት፣ እንደ ብሔረሰብ ጭምር እርስ በርስ የምንወዳጅበትን መልካም እድሎች የምናገኝበት ነው። የማኅበረሰቡን ባሕል ማስተዋወቂያ አውድም ነው።

የጋብቻ ሥነሥርዓት ዋነኛ ጥቅሙ ከየትኛውም ድግስ የላቀ እና የበለጠ ደማቅ ባሕልን ማስተላለፍ ነው። ከዚህ አኳያም ለየት ያለ የሠርግ ሥነሥርዓት እንደየአካባቢው ሁኔታ ይዘጋጅለታል። በየትኛውም የሀገራችን አካባቢዎች ሲካሄድም አንዱ ከአንዱ የሚወራረሰው ቢኖርም ትንሽም ቢሆን ልዩ የሚያደርጋቸው ሥነሥርዓቶች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያስረዳሉ። በየአካባቢው ሠርግ ወይም የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት መልከ ብዙ ገጽታ ይዞ የምናስተውለውም ነው። በዋናነት ጥንዶቹ በጋብቻ ለመተሳሰር ቃል የሚገቡበት ነው። ራሱን የቻለ የድግስ ሥነ- ሥርዓት ሂደትም አለው። ታድያ ኢትዮጵያ የብዝኃነት መገለጫ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ለዛሬ በ‹‹ሀገርኛ›› የቀቤና ብሔረሰብ ባሕላዊ የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት መረጃ ምንጮቻችንን የተለያዩ ማኅበራዊ ድረገጾች በማድረግ እናስነበባችኋለን።

በቀቤና ብሔረሰብ ዘንድ ባሕላዊ የጋብቻ ሥነ- ሥርዓት አንዱ የብሔረሰቡ የባሕሉና ማንነቱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። በቀቤና ብሔረሰብ ባሕል መሰረት ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሰ ወንድ እና ሴት ወጣቶች ይሄንኑ የሚገልፁበት የራሳቸው የሆነ ባሕላዊ ሥርዓት አላቸው። ወጣቶቹ ለጋብቻ የደረሱ መሆናቸውን ከሚገልፁባቸው ባሕላዊ ሥርዓት ሂደቶች መካከል ወንድ ልጅ ለጎጆ መውጫ የሚሆነው የቤት ቁሳቁስ ወላጆቹን የሚጠይቅበት ሁኔታ ይጠቀሳል። ለጋብቻ የደረሰው ይሄ ወጣት ለአቅመ አዳም መድረሱን ለመግለጽ ሲል ወላጆቹን የግሉ የሆነ ቤት እንዲሰጡት ሁሉ ሊጠይቅ ይችላል። እንደዚሁም ሙሉ የቤት ቁሳቁሶች ሊጠይቅ የሚችልበት ሁኔታም አለ።

አንዲት ለጋብቻ የደረሰች የቀቤና ብሔረሰብ ልጃገረድ ወይም ወጣት በበኩሏ ለጋብቻ የደረሰች መሆኗን የምትገልጽበት የራሱ የሆነ ሥርዓተ ሂደት አላት። ከእነዚህ ሂደቶች መካከልም ለጋብቻ የደረሰች መሆኗን የምትናገርበት ልዩ የሆነ የፀጉር አሠራር ያላት መሆኑ ይጠቀሳል። አንዲት ለጋብቻ የደረሰች የቀቤና ብሔረሰብ ልጃገረድ የምትሠራው ባሕላዊ ፀጉር አሠራርም ”ናኑት‘ ይሰኛል። ”ጨረራ‘ ተብሎም እንደሚጠራ የቀቤና እናቶች እና ለጋብቻ የደረሱ የቀበና ወጣት ልጃገረዶች ይናገራሉ። በመሆኑም የቀቤናዋ ልጅት ለጋብቻ መድረሷን ለሌላኛው የሕብረተሰብ ክፍል ለማሳወቅ የግድ ይሄን ”ጨረራ” ወይም ደግሞ ”ናኑት‘ የተሰኘ የፀጉር አሠራር መሠራት እንዳለባት በባሕሉ ይጠበቅባታል።

በቀቤና ብሔረሰብ ውስጥ የተለያዩ የጋብቻ አይነቶች ሲኖሩ በዋናነትም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በባሕላዊ ጋብቻ ተመዝግበው የሚገኙትና በብሔረሰቡ ውስጥ ተዘወትረው የሚፈፀሙ የጋብቻ አይነቶች ሁለት አይነት ናቸው። አንደኛው የጋብቻ አይነት ”አጩቁ‘ ሲሰኝ ሁለተኛው እና ሌላኛው የጋብቻ አይነት ደግሞ ”ጣጦቄን አዩ‘ ስለመሰኘቱ ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው የመረጃ ሰነድ ያመለክታል።

ሰነዱ እንደሚያስረዳው፣ በብሔረሰቡ እምብዛም ተዘወትረው ባይፈፀሙም ወደ ስድስት የሚጠጉ የጋብቻ ሥነሥርዓት አይነቶችም ይገኛሉ። በተለይ በቀቤና ብሔረሰብ ተዘወትሮ በሚከናወነው በ ‘አጩቅ‘ የጋብቻ ሥነሥርዓት አይነት ውስጥ ተጋቢ ጥንዶቹ በአንድ ጣሪያ ስር በመኖር ለትዳር እንዲበቁና ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርገው የወንዱ ወላጅ አባት መሆኑን በሰነዱ ተጠቅሷል።

በባሕሉ ልጅቱን ለልጁ የሚመርጠውም ቢሆን ይሄው የወንድየው ወላጅ አባት ነው። የልጁ አባት ወይም የወደፊቱ ሙሽራ አባት ወደፊት ለልጄ በአንድ ጣራ ሥራ አብራው በመኖር ሚስቱ ትሆናለች፤ ልጆችም ትወልድና ቤተሰብ ለመመሥረት ታስችላላች ያላትን ወጣት ሴት ይመርጣል። ይህች የወደፊቱ ሙሽራ አባት የሚመርጣት ወጣት ሴት ደግሞ ”ናኑት‘ ወይም ”ጨረራ‘ የተሰኘውን የፀጉር አሠራር አይነት የተሠራች ነች። አባት ምርጫውን የሚያከናውነውም ልጅቱ በተሠራችው የፀጉር ስሬት መሰረት ነው። በመሆኑም በአባት ምርጫ ሂደት ወቅት አንዲት ለጋብቻ የደረሰች የቀቤና ልጃገረድ ለጋብቻ መድረሷን ለማሳወቅ የምትሠራው የፀጉር ስሬት ከፍተኛ ቦታ አለው።

የሙሽራው አባት ለልጁ ሚስት የምትሆነውን ልጃገረድ በዚህ መሰረት ከመረጠ በኋላ ደግሞ ለሁለተኛው ሌላ ተግባር ይዘጋጃል። ይሄም ተግባር ልጆትን ለልጄ ስጡኝ የሚል የሽምግልና ተግባር ነው። በመሆኑም አባት ከልጅቱን ከመረጠ በኋላ ለልጁ ወደ መረጣት ልጃገረድ ቤተሰብ ወይም ወላጆች ቤት አብረውት የሚሄዱ ሽማግሌዎችን ይመርጣል። እናም ከመረጣቸው ሽማግሌዎች ጋር በመሆንም በቀጥታ ለልጄ የወደፊት ሚስት ትሆናለች ብሎ ወደ መረጣት ልጃገረድ ወላጆች ቤት ይሄዳል።

አባትና ሽማግሌዎቹ ልጅቱ ወላጆች ቤት እንደደረሱ ወዲያው መቀመጥ አይችሉም። ገና ቤት ውስጥ እንደዘለቀ ለልጅቱ አባት ”ልጅህን ለልጄ ስጠኝ‘ የሚለውን ጥያቄያቸውን በሀገሬው ቋንቋ ያቀርባሉ። አቀራረቡ አክብሮት የታከለበት እና ትህትናም የተላበሰ መሆን ይኖርበታል። አባት ላቀረበው ለዚህ ”ልጅህን ለልጄ ስጠኝ‘ ጥያቄ በቀጥታ ባይሆንም ለሽማግሌዎች አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ የሚሰጥበት ሁኔታም አለ።

በቀቤና ብሔረሰብ ዘንድ አጭር ወይም ረጅም ቀጠሮ የሚሰጥበት ሂደት አለ። ይሄ የልጅቱ አባት ከሽማግሎቹ ጋር ተማክሮ ምላሽ የሚሰጥበት የቀጠሮ ሂደት በአብዛኛው የተለመደ ነው። ይሁንና የቀጠሮው መርዘም ወይም ማጠር በራሱ የልጅቱ አባት ሊሰጥ የሚችለውን ምላሽ አመላካች ስለመሆኑ አባቶች መናገራቸውን ዋቢ ያደረገው የቢሮው መረጃ ያስረዳል። የልጅቱ አባት ”ልጅህን ለልጄ‘ ተብሎ በወንዱ ልጅ አባት አማካኝነት በሽማግሌዎች በተጠየቀበት ወቅት ረጅም ቀጠሮ ከሰጠ ጥያቄውን ላይቀበለው ይችላል ተብሎ ይገመታልም።

በተለይ የሰጠው ቀጠሮ እስከ ሦስት ወር የዘለቀ ከሆነ ጋብቻውን ሙሉ በሙሉ አልተቀበለውም ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። ሆኖም የልጅቱ አባት ቀጠሮውን ያስረዘመበት የራሱ ምክንያት ሊኖረው ስለሚችል በብሔረሰቡ ባሕል ዘንድ ቀጠሮ ማርዘም በራሱ አባት ጋብቻውን አልተቀበለውም የሚል ድምዳሜ ላይ አያደርስም። በመሆኑም በቀቤና ቤሔረሰብ ባሕል መሰረት የልጁ አባት ለልጅቱ አባት ”ልጅህን ለልጄ ስጠኝ‘ ጥያቄውን አቅርቦ አጭርም ሆነ ረጅም ቀጠሮ ከተሰጠው በኋላ የግድ ተረጋግቶ የቀጠሮው ወቅት እስኪደርስ መጠበቅ አለበት። በዚህ መልኩ ሲጠብቀው የቆየው አጭርም ሆነ ረጅም የልጅቱን አባት ምላሽ ያገናዘበ ቀጠሮ ሲደርስም ሌላ የዝግጅት ሂደት ይከተላል። ይሄ ሂደት ደግሞ ልጁ እና ልጅቱ በ ” ኒካ‘ ወይም በቀለበት እርስ በርስ የሚተሳሰሩበት ሂደት ነው።

በብሔረሰቡ ባሕል ዘንድ አንዲት የብሔረሰቡ ተወላጅ ልጃገረድ በዚህ መንገድ ኒካ ወይም ቀለበት ከታሰረላት በኋላ ቀለበት ካሰረላት ልጅ ውጭ በፍፁም ሌላ ወንድ እንዲጠጋት አይፈለግም። ይህች በዚህ መንገድ ቀለበት ያሰራች የቀቤና ተወላጅ ልጃገረድ በብርቱ ትከበራለች። ወንዶች ይህችን ልጃገረድ በሙሉ ዓይናቸውም እንዲያይዋት በባሕሉ በፍፁም አይፈቀድም። እነሱም ባሕሉን አጥብቀው የሚያከብሩ እና የሚጠብቁ በመሆናቸው በሙሉ ዓይናቸው ሊያይዋት አይደፍሩም።

በመግቢያችን እንደጠቀስነው ሁለተኛው እና በብሔረሰቡ ዘንድ ተዘወትሮ የሚፈፀመው የጋብቻ ሥነሥርዓት አይነት ”ጣጦቄን አዩ‘ የተሰኘው ነው። ይሄ ”ጣጦቄን አዩ‘ የተሰኘ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የድንገቴ ጋብቻ ተብሎም ይጠቀሳል። አንዳንዴ ‹‹ተጠምጥሞ ገባ›› በሚልም ስያሜ ስለመጠቀሱ ከቢሮው የወጣው የተጻፈ ሰነድ ይገልፃል። ታድያ በዚህ ”ጣጦቄን አዩ” ወይም ደግሞ ”ተጠምጥሞ ገባ” በተሰኘ የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ሂደት ልጅቱን የሚያገባው ወጣት የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው። እንዴት ቢባል አግቢው ወጣት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሳይታሰብ በድንገት ከወደዳት ልጅ ወላጆች ቤት ይገባል።

ልጁ መግባት ብቻ አይደለም ከገባ በኋላም ቢሆን አይወጣም። በመሆኑም ይሄ ወጣት በድንገት ከገባበት የወደዳት ልጅ ወላጆች ቤት አልወጣም በማለቱ ምክንያት ጋብቻውን ከልጅቱ ጋር ይፈፀማል። ጋብቻው ”ተጠምጥሞ ገባ” የሚል ስያሜ የተሰጠውም ለዚህ ነው። ይሄ ጋብቻ ለልጅቱ ወላጆች ዱብ ዕዳ በመሆኑ ድንገተኛ ይባል እንጂ ለተጋቢዎቹ ግን ድንገተኛ እንዳልሆነ ይነገራል። እንደሚባለው ሁለቱ ተጋቢዎች ወይም እጮኛሞች ቀደም ብለው በምስጢር የተስማሙበት በመሆኑ ለተጋቢዎቹ በተለይም ለልጅቱ አዲስ አይደለም። እናም በዚህ አይነት ከልጅት ጋር የተደረገ ስምምነት ልጅት ወላጆች ቤት ከነጓደኞቹ ይገባል። የሴቷ ቤተሰቦችም ወጣቱን ከየት እንደመጣ፤ ምን እንደሚፈልግ፤ ቤታቸውንም ለቆ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ይጠየቃል። ነገር ግን ምንም ቢባል ቤታቸውን የሙጥኝ ይላል እንጂ በጄ ብሎ አይወጣም። ከልጅቱ ወላጆች የይሁንታ ምላሽ እስከሚያገኝም ድረስ ይቀመጣል።

በምስጢር የተስማማችው ልጅቱ (የወደፊቷ ሙሽሪትና ሚስቱ) ተጠምጥሞ መግባቱን ስታውቅ ፈጥና በቅርብ ጓደኞቿ ትታጀባለች። ወደዚሁም የልጁ ወላጆች ልጃቸው ተጠምጥሞ ከገባበት ከልጅቱ ወላጆች ቤት ሽማግሌ ይልኩና የጋብቻው ሥነሥርዓት ይከናወናል።

በቀቤና ብሔረሰብ ከእነዚህ ተዘወትረው ከሚፈፀሙ ሁለት ባሕላዊ የጋብቻ አይነቶች በተጨማሪ ሌሎች ሕግ ያላቸው አራት ባሕላዊ የጋብቻ አይነቶችም አሉ። እነርሱም ‹‹ረገዑ›› የሚሰኘው የውርስ ጋብቻ፣ ‹‹ዶረቱት›› የተሰኘው የምትክ ጋብቻ፣ ‹‹ወጌቱታ›› የተሰኘው የፈት ጋብቻ እና ‹‹ሙሪታ ባዩን›› የተሰኘው የሴቷ ወላጆች ለልጃቸው የመረጡላትን ወንድ ጠርተው የሚድሩበት ባሕላዊ የጋብቻ አይነት ናቸው። እነዚህን የጋብቻ አይነቶች ዘርዘር አድርጎ ለማውራት ጊዜ ይፈጃልና እናንተው በተጨማሪነት እንድታነቧቸው በመጋበዝ ለዛሬ ተሰናበትን። መልካም ሳምንት!

የቀቤና ብሔረሰብ ባሕላዊ ሠርግ ሥነሥርዓት

በሠላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You