ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚው ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ በማለም መንገድ ጠራጊ በሆኑት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ልዩ ልዩ መመሪያዎች ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ በዘርፉ ልዩ ክህሎት ያላቸው ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ለማብቃት የሚያስችሉ የልህቀት ማእከላትም ወደ ስራ ለማስገባት የሚሰሩ በርካታ መሬት ላይ የወረዱ ስራዎችን ይታያሉ። ይህንን የተግባር ስራ በሚፈለገው ፍጥነትና የጥራት ደረጃ ለመስራት ደግሞ መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመንደፍ ስራ ላይ አውሏል። ከእነዚህ ውስጥ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ›› አንዱ ነው።
በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን ስትራቴጂው በዝርዝር ምን ይዘቶች እንዳሉት በወፍ በረር እንቃኛለን።
ይህ ስትራቴጂ በዋናነት “የቴክኖሎጂ ለውጥ ለማህበራዊ እድገት፣ ምርታማነት ለማሻሻል እና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳለው እሙን ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሰ ነው። በተለይ ዓለማችን የቀጣዩን የቴክኖሎጂ ለውጥ እውን ለማድረግ በዋዜማው ላይ ትገኛለች ይላል። ቴክኖሎጂው በእድገት ደረጃ ላሉ አገራት የተለያየ ዓይነት ምቹ አጋጣሚንም እንደሚፈጥርላቸው ያብራራል።
“ዋናው ጉዳይ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚመረጠው መንገድ በዋናነት ከአገራዊ ርዕይ እና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ብሔራዊ የልማት አጀንዳዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት ሊኖረው ይገባል” የሚለው ሀሳብ በስትራቴጂው ሰፍሯል፤ በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በአገር ውስጥ ከአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ተሃድሶ አጀንዳ እና እየተተገበረ ከሚገኘው ከአስር ዓመቱ የልማት እቅድ (2013 እስከ 2022 ዓ.ም) ጋር፤ ከዓለም አቀፍ አንጻር ደግሞ ከተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች እና ከአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ የዲጂታል ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት አፅእኖት ሰጥቶ ይገልጻል።
እነዚህ መሪ የመንግስት ሰነዶች የማክሮ-ኢኮኖሚ መዛባትን ለማስተካከል፣ የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ችግር ለመፍታት፣ የተመጣጠነ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማምጣት፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች ለመለየት እና በሂደትም ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እና የበለጸገ ህብረተሰብ ለመፍጠር ያለሙ መሆናቸውንም ነው የሚያብራራው።
ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ አዲስ አብዮት ለመፍጠርና እድገቷን በዚያ ላይ ለመገንባት ቆርጣ ወደ ትግበራ ገብታለች። ሁሉም ቁልፍ ዘርፎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲከተሉም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል። በእርግጥ ዓለም በዘርፉ ከደረሰበት የላቀ ደረጃ አንፃር ያለውን የአገሪቱን አፈጻጸም ስንገመግም ወደኋላ ከቀሩት የዓለም አገሮች ጋር የምትመደብ መሆኗ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን እየተመለከትን ነው። ለእዚህም በግብርናው ዘርፍ ላይ በጎ ውጤት ሊያስከትል የሚችለውን የሳተላይት ቴክኖሎጂን፣ የቴሌኮም አገልግሎቶችን፣ የክፍያ ስርአቶችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
መንግስት “ለሳይንስና ቴክኖሎጂ” ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን በርካታ ማረጋገጫዎችን ማግኘት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይንስና ቴክኖሎጂን አስመልክተው እንዳሉት፤ ዓለም ባልተጠበቀ ፍጥነት አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት እያካሄደች ትገኛለች። ሕዝቡ ከዚህ ክስተት ተጠቃሚ እንዲሆን በተለይ ወጣቶች በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ስኬታማ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባታል። በአሁኑ ወቅት እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Arteficial Intelegence)፣ የበይነ መረብ ቁሶች (Internet of things)፣ ናኖ ቴክኖሎጂ፣ እና ውሒብ አስተኔ (Big Data) ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚደገፉ የማምረት፣ የመገናኛ እና የአኗኗር ዘይቤ ሽግግሮችን እየተመለከትን ነው። ታዳጊዎች አዳዲስ ክህሎት እና ዕውቀትን ይፈልጋሉ፤ የወደፊቱን ጊዜ በተሻለ ለመጠቀም እንዲችሉ ማድረግ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጸገ ኅብረተሰብን ለመገንባት የሚያስችላትን አቅም ገና አልፈጠረችም። አቅምን በማጠናከር ስኬታማ ለመሆን ደግሞ ፈጣን ፣ እና ልበ-ሙሉ የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ ላይ ትገኛለች ። በአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ አጀንዳ እና የአሥር ዓመት ብሔራዊ የልማት ዕቅድ (2011-2022) ጸድቀዋል። እነዚህ ሁሉ የአዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ እና እያንዳንዱ ዜጋ ከአገር አቀፍ ብልጽግና ተጠቃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ዕድል ይሰጣሉ።
#ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025$ እና #ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን$
ሰነዱ እንደሚያመለክተው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የአገሪቱን ቁልፍ ዘርፎች ወደ ዲጂታል ሽግግር ለመውሰድ የሚቻልበትን መንገድ የቀየሰ ነው። በጥቅሉ ከዚህ የሚከተለው ዘገባ በ244 ገፅ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ያካተታቸውን ቁልፍና ዋና ዋና ጉዳዮች ያስቃኘናል።
ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሰነድ መረዳት እንደሚቻለው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግስት የሚመራ ተነሳሽነት ነው። ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ አገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረ መሆኑንም ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጀንሲዎች ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሰረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነትን በመለየት የአገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉ አራት ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎችን መለየቱን “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ ሰነድ በግልፅ ያሳያል።
በዋናነትም ግንባር ቀደም ተብለው ከተለዩት ውስጥ ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ቱሪዝም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ይጠቁመናል። ዋና ዋና ጉዳዮችን ለመቃኘት እንዲያመቸን ግንባር ቀደም ተብለው ከተለዩት ውስጥ የተወሰኑትን ከዚህ እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክር።
ግብርና
በስትራቴጂ ሰነዱ እንደተመለከተው፤ በግብርና ውስጥ የበይነ መረብ ቁሶች አርሶ አደሮች ምርታቸውን እንዲቆጣጠሩ ማስቻል፣ ጥብቅ ሰንሰለት (Block chain) ደግሞ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር፣ ደህንነቱ የተጠበቀና የተሻሉ (ርካሽ) የክፍያ አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችላቸው ማድረግ ዋናው የስትራቴጂው ተግባር መሆኑን ይጠቁማል።
ኢትዮጵያን በዚህ ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ሁለት ምቹ እድሎች መለየታቸውንም ያመለክታል። አንደኛው የዲጂታል ግብርና መድረክን መገንባት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቴክኖሎጂ መር የሆኑ የግብርና ኢንተርፕራይዞችን (ቴክ-ግብርና) መደገፍና ማበረታታት መሆናቸውን ያብራራል። እነዚህን ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ማቀናጀት ሲቻል የሚፈለገው ውጤታማነት እውን እንደሚሆንም ይተነብያል።
የማምረቻው ዘርፍ
ሌላኛው ግንባር ቀደም ግብ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ተደራሽነትን ለማስፋት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አዳዲስ የግንኙነት ቴክኖሎጂዎችን መቀበል እና መፍጠር ማስቻል እና ኤክስፖርትን ለማሳደግ በዲጂታል የተደገፉ የሎጂስቲክስ አያያዝ አካሄዶችን ማጎልበት መሆናቸውን ይሄው የስትራቴጂ ሰነድ ያብራራል።
የመረጃ ቴክኖሎጂ
በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ በሶስተኛ ደረጃ ግንባር ቀደም ዘርፍ የሆነው “የመረጃ ቴክኖሎጂ” ነው። ሰነዱ በመረጃ ቴክኖሎጂ አስቻይ የሆነባቸው አገልግሎቶች መገንባትን ይመለከታል። ከዚህ አማራጭ አንጻር በኢትዮጵያ ሁለት መልካም አጋጣሚዎች መለየታቸውን ይጠቁማል። የመጀመሪያው ለባለ ከፍተኛ አቅም እና ተሰጥኦ ማዕከላት መሰረተ ልማት ማቅረብ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መሪ የንግድ ሥራ ሂደት አቅርቦትን ሊስቡ የሚችሉና ተሰጥኦ ማሳደጊያ የመረጃ ቴክኖሎጂ ፓርክን ዳግም በማዋቀር በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ማስገባት ነው።
ቱሪዝም
ቱሪዝምን ተወዳዳሪ ለማድረግ የዲጂታል አሰራር መዝርጋት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ሶስት መልካም አጋጣሚዎች ተለይተዋል። የመጀመሪያው የቱሪዝም ዲጂታላይዜሽን ግብረ ኃይል በማቋቋም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዲጂታላይዝ ማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዲጂታል የገበያ ስርዓትን በማበጀት የቱሪስት ፍሰትን እና የቆይታ እና ተሳትፎ መጠኑን ማሻሻል ነው። ሶስተኛው ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ አቅማቸውን መገንባት ነው።
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምንድነው?
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ነው። በአካል ከሚደረጉ ግንኙነቶች ወጥቶ የዲጂታል አሰራሮችን በመተግበር ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመድረስ ባለ ሂደት ውስጥ ያለ “ጉዞ” ነው። የዲጂታል የሽግግር ጉዞ በመንግስት፣ በንግድ ድርጅቶች እና በማህበረሰቡ መካከል ግንኙነት በአካል ይካሄድ ከነበረበት አናሎግ ህብረተሰብ ወጥቶ ግንኙነትና ልውውጦች በበይነ መረብ በጣም ፈጣን፣ ርካሽ፣ እና ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደሚካሄዱበት የተቀናጀና አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚደረግ ጉዞ ነው።
ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያመለክተው የተሻሻለ የኔትወርክ ግንኙነቶችን እና እርስበርስ ተያያዥነት ያላቸውን የዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም የሚደረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ነው። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከአናሎግ ኢኮኖሚ ይጀምራል። በአናሎግ ኢኮኖሚ ውስጥ በዜጎች በመንግስትና በንግድ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት የዲጂታል ቴክኖሎጂን የማይጠቀም እና በአካል የሚደረግ ነው።
ከአናሎግ ኢኮኖሚ ቀጥሎ የሚገኘው ደግሞ ዝቅተኛ የዲጂታል ተደራሽነት ነው። በዚህ ውስጥ ውስን የዲጂታል መሰረተ ልማት ይኖራል፣ የተወሰኑ የዲጂታል ማሳያዎች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ይቀጥልና አናሎግ ግን የዲጂታል አሰራር እያደገ ይሄዳል። በዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አገልግሎቶች አናሎግ የሆኑበት፣ ግልፅ የሆነ የዲጂታል ራዕይ ካልተቀናጁ አገልግሎቶች ጋር ያሉበት እና የሚተገበርበት ነው።
ይህ አናሎግ እና ያልተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት ደግሞ የተቀናጀ የዲጂታል ስርዓትን ይወልዳል። በዚህ ውስጥ የላቀ፣ የተቀናጀ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና ጠንካራ አስቻይ ስነ ምህዳሮች ይኖራሉ። የዲጂታል ኢኮኖሚም ይገነባል። የዲጂታል ኢኮኖሚ የተሟላ የዲጂታል ኢኮኖሚ የተተገበረበት፣ ከመንግስትና የንግድ ተቋማት ጋር ለመገናኘት የዲጂታል አገልግሎትን የሚጠቀም ነው። የንግድ ተቋማት ፈጠራ የታከለበት አገልግሎት ያቀርባሉ። የመንግስት ስራዎችና አገልግሎቶች ዲጂታል ይሆናሉ። አብዛኞቹ የንግድ መነሻዎች ዲጂታል ይሆናሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014