መስጠትና መቀበል በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት መካከል የሚደረግ ግንኙነት ነው። ይህም ያለው ለሌለው በመስጠት። የሌለው ካለው በመቀበል እንዲሁም እርስ በእርስ የመመጋገብ ሂደት ነው።በመሆኑም ሁላችንም በዚህ የህይወት መንገድ ውስጥ እናልፋለን።እንሰጣለን እንቀበላለን።አስበነውም ይሁን ሳናስበው በዚህ ሂደት ውስጥ ማለፋችን የግድ ነው።
በኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች መፅሀፍ ቅዱስ። በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቁርኣን አብዛኞቻችን የህይወት መንገድና መመሪያ አድርገን የምንጠቀምባቸው መጻሐፍት ናቸው። የሁሉም ቤተ እምነቶች መመሪያ በሆነው ታላቁ መፅሀፍ፤ መስጠት የህይወት አንድ አካል መሆን እንዳለበት። በመስጠት ውስጥ ትልቅ መንፈሳዊ በረከት እንደሚገኝ ይመክራል። በመጽሀፍ ቅዱስ ተመዝግቦ የምናገኘው የሀዋርያት ስራ 20፡-35 “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብጹእ ነው“። ይላል ። በዚህ ቃል ላይ የሚሰጥ አለ የሚቀበል አለ። በዚህ ግንኙነት ውስጥ ሰጪው ከተቀባዩ ይልቅ ዋጋው ትልቅ እንደሆነ ያስረዳናል።
ይህም የሚያሳየው ማንም ሰው ሊቀበል ይችላል።ለመቀበል የተለየ ልብ አይጠይቅም።ለመቀበል ምንም አይነት ጉልበት አያስፈልግም።ለመስጠት ግን የተሰጠ ልብ ይጠይቃል።የሚሰጥ ልብ የታደለ ነው።ምናልባት የሚሰጠው ነገር ስለተረፈው ላይሆን ይችላል።ከጉድለቱም ይሆናል የሚሰጠው ዋናው ነገር ለመስጠት የተነሳበት ልብ ነው።ዋጋ ያለው መስጠት ደግሞ ስንሰጥ የማንፈልገውንና የተረፈንን ሳይሆን የሚያስፈልገንን በማካፈል ነው ።ምክንያቱ ደግሞ በሉቃስ መጽሀፍ 21፡-2፡-4 “ አንዲት ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል ጌታ ኢየሱስ አየና እውነት እላችኋለው ይህች ደሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሄር መዝገብ ጥለዋልና ይህች ግን ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ”።ሴቲቱ ድሀ መበለት ብትሆንም ያላትን ሁሉ ነበር የሰጠችው።
ስንሰጥ የስጦታው መጠን ሳይሆን የሚታየው የሰጠንበት ልብ ነው። ደግሞም በምንሰጥበት ወቅት ደስ እያለን።ልባችን ሀሴት እያደረገ መሆን አለበት እንጂ እያዘንን። ቅር እያለን። ጉድለት እየተሰማን መሆን የለበትም።ከእንደዚህ አይነት መስጠት አለመስጠት ይሻላልና። በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የሮሜ መጽሀፍ 12፡-8 ላይ “የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ።የሚሰጥ በልግስና ይስጥ። የሚገዛ በትጋት ይግዛ የሚምር ቢኖር በደስታ ይማር“።ይላል በመሆኑም ስንሰጥ ደስ እያለን በልግስና መሆን ይገባዋል።
ደግሞም ሰጥቶ የሚጎድልበት የለም በእጥፍ ይቀበላል እንጂ።ሰጥተን አናጣም።ያለንን ስናካፍል የመስጠት ልባችንን የሚያይ ፈጣሪ ደግሞ አብዝቶ ይሰጠናል።ፈጣሪ በብዙ ነገሮች ሲባርከን በሀብት፤ በእውቀት፤ በጉልበት። በጥበብ ለራሳችን ብቻ እንድንጠቀምበት አይደለም። ሌሎችንም እንድንጠቅምበት እንጂ። ሁላችንም እንደምናምነው ፈጣሪ አንደኛችንን በምቾት እያንደላቀቀ። የምናስቀምጥበት እስክናጣ ድረስ ተትረፍርፈን እየኖርን። ሌላኛው ወንድማችን ደግሞ አንድ ጉርሻ ናፍቆት እንዲኖር የሚፈርድ ኢፍትሃዊ አምላክ አይደለም።ማወቅ ያለብን ሲሰጠን እንድናካፍል ያለንን ለሌላው እንድንሰጥ ነው።ነፍሱን እስከመስጠት የወደደን ፈጣሪ ባለንጀሮቻችንን እንድንወድ ትእዛዝ የሰጠንም ለዚሁ ቅዱስ ዓላማ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
አምላክ ሰው ሆኖ መጥቶ እኛን ለማዳን ነፍሱን በመስጠት ህይወትን ሲሰጠን። በዛውም የመስጠትን ጥግ እያሣየን ነው።መስጠት ምን ድረስ እንደሆነ እያስተማረን ነው። ስንወድ ምትክ የሌለውን ነገር እስከመስጠት እንደሚሆን አሳይቶናል። መስጠት ብዙ አይነት ።ሁሉም ሰው የመስጠት ልብ ይኑረው እንጂ የሚሰጠው ነገር አያጣም።በመቀጠልም ጥቂት የመስጠት (የስጦታ) አይነቶችን እንመልከት።
ፍቅርን መስጠት
ፍቅር ከልብ የጠለቀ የመውደድ ኃይል ነው።ፍቅር የምግባራት ሁሉ አለቃ ነው።የነገሮች ሁሉ ራስ ነው።ፍቅር ታላቅ የመንፈስ ፍሬ ነው።የሚጀምረው ደግሞ ከቤተሰብ ነው።አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ በመጀመሪያ የሚተዋወቀው ከወላጆቹ (ከቤተሰቦቹ) ጋር ነው።በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅር ነው። ከቤተሰቡ በመቀጠል አንድ ሰው እድሜው እየጨመረ።ማህበራዊ ግንኙነቱ እየሰፋ ሲመጣ የሚወዳቸው የሚኖርላቸው ሰዎች (ነገሮች) ቁጥር እየጨመረ ይመጣል።
በዘመናችን ደግሞ ይህ የመንፈስ ፍሬ የሆነው ፍቅር ቀዝቅዟል። ከሰው ልጅ ልብ ላይ የተሰረዘም ይመስላል።ምክንያቱም በተጨባጭ እያየን ያለነው ይህን በመሆኑ ነው።ሰው ተጨካክኗል፤ ራስ ወዳድነት ነግሷል። መከፋፈል።መለያየት አየሩን ተቆጣጥሮታል።አለምን ትተን አሁን አገራችን ላይ እየሆነ ያለውን ብንመለከት የችግሩ ሁሉ ምንጭ የፍቅር መቀዝቀዝ ውጤት መሆኑን አንረዳለን።
እርስ በእርስ መገዳደልን ጨምሮ ብዙ ዘግናኝ እና ሰቅጣጭ እግዚአብሄር በአምሳሉ ለፈጠረው ለሰው ልጅ የማይገባ አሟሟትና አገዳደል እያየን ነው።ታዲያ ከዚህ በላይ ፍቅር መቀዝቀዙን የሚያረጋግጥ ምን ነገር ሊመጣ ይችላል።ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን በደብረዘይት ተራራ ስለአለም ፍጻሜ ሲጠይቁት ምልክቱን ሲነግራቸው በሰው ልጅ ዘንድ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ አሳስቦ ነበር። 1ኛ ጴጥሮስ 4፡-8 ላይም ”ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ ፍቅር የሀጥያትን ብዛትን ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳቹ ተዋደዱ”።ይላል ይህም ከሚመጣብን ክፉ ነገር ማምለጫ መንገዳችን ፍቅር ብቻ እንደሆነ የሚያስረዳ ነው።ይገርማል ፍቅር በፈጣሪ ፊት የበደልነውን በደላችንን የማስተሰረይ የመሸፈን አቅም አለው።ያለዋጋ ያለድካም ልናደርገው የሚገባን ድንቅ ስጦታ ፍቅር ነው።
ለወጥ ማጣፈጫ ጨው እንደሆነ ሁሉ።በብዙ ጥንቃቄ በብዙ ቅመማቅመም የተሰራ ወጥ ጨው ካልተጨመረበት ጣእሙ እንደማይታወቅ። የሰው ልጅ ህይወትም ብዙ ነገሮች ቢኖሩትም። በቁሳዊ ነገር ተሳክቶልኛል ብሎ ቢያስብም በህይወቱ ፍቅር ከጎደለው ግን የነዚህን ነገሮች ሁሉ ጣእም ማወቅ አይችልም።ሁሉ ኖሮን ፍቅር ግን ከሌለን ከንቱ ነን እንዲል ታላቁ መጽሐፍ።
የህይወት ማጣፈጫ ቅመም ፍቅር ነው።እግዚአብሄር ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል ገልጧል።እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ የባህርይ ውድ ልጁ እየሱስ ክርስቶስ ነው።እየሱስ ፍፁም ፍቅሩን ካሳየን በኋላ በዮሀንስ 15፡-12 ላይ “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት“። ሲል እርሱ እንደወደደን እኛም እንዋደድ ዘንድ አዞናል።ሰው እለት እለት በፍቅር የጋለና የተነቃቃ መሆን አለበት። ሰውን መውደድ ማለት ስለዛ ሰው መልካም ማሰብ።መልካም መመኘት እንዲሁም ለዛ ሰው መንገድ መቃናት።ህይወት መሳካት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ማለት ነው።
ይህ ደግሞ ቅንነት የተሞላ ሀሳብ ነው። ውስጣችን በዚህ ሀሳብ ሲሞላ የሚሰማን ሰላም እና እረፍት ነው።ለሰዎች መልካም በማሰብ ውስጥ የሚገኘው እርካታ ከምንም ጋር አይወዳደርም።አሁን በተጨባጭ ያለው ግን የሚያሳዝን ነው።ሰዎች የራሳቸውን ህይወት እንዴት ስኬታማ ማድረግ እንደሚችሉ ሳይሆን የስኬታማ ወዳጃቸውን ስኬት እንዴት እንደሚያጠፉ በማሰብ አእምሯቸው ተይዟል።ይህ የፍቅር ማጣት ምልክት ነው።የጥላቻ ስሜት እንኳን ለሌላው ለራስም ምቾት አይሰጥም። የሰው ልጅ በሕይወቱ ደስተኛ መሆን ከፈለገ ከጥላቻ መራቅ አለበት። ሰላማዊ ኑሮ ለመምራት በእምነት ድር እና በፍቅር ማግ የተገመደ ህይወት ሊኖረን ይገባል።
በታላቁ መጽሐፍ “እንዲህም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሶስቱ ፀንተው ይኖራሉ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው“ ይላል። ፍቅር የምንተርከው ሳይሆን የምንኖረው ህይወት ነው።የነገሮች መቋጫ ማሰሪያ እውነተኛ ፍቅር ነው። ፍቅር ለሰዎች መልካም መሆን የሚጠሉንን እንኳን ቢሆን መውደድ ነው።“ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ” የተባለውም ለዚሁ ነው:: የወደዱንን ብንወድማ ምንም ቸርነት አላደረግንም። የወደደውን የማይወድ ማን አለ? ነገር ግን የሚጠሉንንም በመውደድ የሚረግሙንን በመመረቅ በፍቅር መግዛት።ማሸነፍ ነው ትልቁ ቁምነገር።
ምፅዋት መስጠት
የምፅዋት ስርወ ቃል የመጣው ከግእዝ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ስጦታ።ልግስ።ችሮታ ማለት ነው።አንድ ሰው በሌላኛው ሰው ላይ የሚያየውን ማጣት፣ችግር በማስተዋል በፍፁም ርህራሄና ፈቃ፣የተቸገረበትን ነገር መርዳት፣ ማገዝ፣ መስጠት፤ በጎ ስጦታ ወይም ምፅዋት ይባላል።ፈጣሪ ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ ከተቀባዮች ጋርም የሚቀበል ነው።በመስጠትና በመቀበል በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር።ሀብትን ለሀብታሞች ሲሰጥ ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያግዙበት( እንዲያስተናግዱበት) ነው።ምፅዋት የእለት ምግብና የአመት ልብስ ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት፣ ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ነው።ምንጭ፡- ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ ጎሐ ፅባህ መፅሀፍ።
ጠቢቡ ሰለሞን በመፅሀፈ ምሳሌ 19፡-17 “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሄር ያበድራል በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል“። ይላል ይህ ጥቅስ ምፅዋት ብልሆች በእግዚአብሄር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ መሆኑን ይነግረናል። በዚህች ዓለም ስንኖር ማጣትም ማግኘትም በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ይፈራረቃሉ። ያልተማሩትን በእውቀት።የሙያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሙያ። ደካሞችን በጉልበት ማገዝ ተገቢ እና ቅዱስ ተግባር ነው።
ደግሞም ስንሰጥ ከተረፈን ነገር ሳይሆን ካለን።ከሚያስፈልገን መሆን ይገባዋል።መስጠት ሰው የመሆን ትልቅ ቁልፍ ነውና። አብዛኞቻችን የሀጥያት መሰረት በተባለው በነዋይ ፍቅር። በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ።መስጠት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መመጽወት ነው።ነገር ግን መስጠት ከጉድለታችን ነው።በሌላ አነጋገር በዝቶ የተትረፈረፈ ብዙ ዓይነት ምግብ በልተን የተረፈንን መስጠት ሳይሆን፤ አይነቱን ቀንሰን የሌለው ወንድማችንም እኛ የምንበላውን እንዲበላ ማድረግ ነው።
የተቀደደ እና የማይጠቅመውን ከመስጠት ይልቅ ካልተበላሹ ልብሶቻችን ውስጥ ለተቸገሩት መስጠት ነው ተገቢው ነገር። ምክንያቱም ያም ነዳይ ቀን ጥሎት ተቸግሮ እንጂ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ። እኛ የሚገባን የሚገባው ክቡር የሰው ልጅ ነውና። ስንሰጥ በንፁህ ልብ፤ በልግስና፤ ባለመመፃደቅ ከከንቱ ውዳሴ፤ ከታይታ በፀዳ መልኩ መሆን ይገባዋል። ከዚህም ባለፈ ምላሽ መጠበቅም የለብንም።
ምፅዋት የሚሰጡ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይሰጡት ደግሞ ይጎዳሉ።የመጀመሪያው መስጠት የፈጣሪ ህግ በመሆኑ እሱን ባለመፈፀም ይጠየቃሉ።ሌላው ደግሞ ከመስጠት የሚገኘውን እርካታ ለማወቅ አልታደሉም። በመስጠት ውስጥ የሚገኝ ትልቅ ደስታ አለ። የተሰጠውን ሰው ደስታ ማየት በራሱ የሚሰጠው እርካታ ልዩ ነው።ለሰው መስጠት ማዘን። መራራት። ከፈጣሪ የሚሰጥ ትልቅ መንፈሳዊ በረከት ነው።በሉቃስ መጽሀፍ 6፡- 38 “ስጡ ይሰጣቹሁማል በምትሰፍሩት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላቹሀል” ይላል።የሚሰጥ ይሰጠዋል።
አንድ አባት ስለመስጠት ሲያጫውቱኝ። አንዳንድ ጊዜ ከቤታችን ያለው ነገር ሞልቶ። የሰው ልጅ ፍላጎት አያልቅምና ፈጣሪ እንዲጨምርልን የተሻለ ነገር እንዲሰጠን እንደክማለን እንለምናለን።ግን ደግሞ የልብስ ማስቀመጫችን በቆዩ ልብሶች ተጨናንቋል። ቤታችን ውስጥ የሚያስፈልጉን እቃዎች በሙሉ አሉ ግን የተሻለ ነገር እንፈልጋለን።ሌላ ብናገኝ የምናስቀምጥበት ቦታ እንኳን የለንም።
ፈጣሪ የምንሰራውን ነገር እንዲባርክልንና በተሻለ ነገር እንዲቀይርልን ቤታችን ውስጥ ያሉትን ቆዩ፣ ሰለቹን ያልናቸውን እቃዎች አውጥተን ለሌላቸው፣ እኛ ሰለቸን ያልነው ለሚናፍቃቸው መስጠት ይገባናል።ያን ጊዜ እግዜሩም ሲሰጠን የምናስቀምጥበት እናገኛለን። መጀመሪያ ለመቀበል የሚሆን ቦታ እናስለቅቅ ብለው አስገርመውኛል።እውነት ነው አብዛኞቻችን በዝቶብን የማንጠቀምባቸው ትርፍ እቃዎች አሉን። አዲስ የተሻለ ነገር እንዲጨመርልን ቦታ ማስለቀቅ አለብን።አንዳንዶቻችን ደግሞ ለማን መስጠት እንዳለብን ማወቅ አለብን። ስጦታችን ዋጋ የሚኖርበት ቦታ ላይ ብናውለው መልካም ነው።
በጎ ላልሆነ ዓላማ ለሚያውል፡ ለቁማር፤ አደንዛዥ እፅ ለመጠቀም ወይም ያለአግባብ ከልክ በላይ ለሚጠጣ ሰው ገንዘባችንን ብንሰጥ መስጠታችን ተገቢ አይሆንም። ስለሆነም ስንሰጥ ለማን እንስጥ የሚለው ልዩ ትኩረት ይፈልጋል ማለት ነው። በሌላም በኩል የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ እንደሚለው ብሂል የራሳችንን ቤተሰብ እየበደልንና ለቤታችን ማድረግ የሚገባንን ሳናደርግ የቤተሰባችንን ፍላጎት ችላ ብለን ለሌላው መስጠትም አስፈላጊ አይደለም።
ለምንጠየቀው ጥያቄ ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት
በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተለያዩ አይነት ሰዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ልንጠየቅ እንችላለን። በዚህ ጊዜ ተገቢውን መልስ በተገቢው መልኩ በማክበር። በትህትና መልስ መስጠት አለብን።የተጠየቅነውን ነገር በማወቃችን ልንታበይና ልንኩራራ አይገባም።ሁሉም ሰው በየዘርፉ የተለያየ እውቀት ሊኖረው ይችላል። ሁሉም ሰው ግን ሁሉም ነገር ላይ እኩል እውቀት ሊኖረው አይችልም።በመሆኑም እኛም የማናውቀው።እርዳታ የምንፈልግበት ጉዳይ ሊኖር ይችላልና ሰዎች ያልቻሉትን። ያላወቁትን ነገር ሲጠይቁን በትህትና ማሳየት መንገር ነው የሚገባን።እነዚህን ነገሮች መፈፀም የአንድ መልካም ሰው መገለጫ በተለይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነገር ነው።
በተሰጠን ጸጋ በተሰጠን እውቀት ባገኘነው ነገር ሁሉ ያለስስት ማካፈል ያለመታበይ መስጠት ያስፈልጋል ይህንን ማድረግ ዋጋው ታላቅ ነው።በመጨረሻም በፈቃደኝነትና በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነስተን እንስጥ።እንዲህ ባለ ዝንባሌ ተነሳስቶ መስጠት ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን ሰጪውንም ይጠቅማልና።
ከላይ ልዩ ልዩ ጥቅሶችንና የአባቶችን ምክር አክዬ ለማስረዳት እንደሞከርኩት መስጠት በምድርም ሆነ በሰማይ ዋጋ ያለው ትልቅ ተግባር መሆኑን ተመልክተናል። ሰሚና አንባቢ ብቻ ሳይሆን አድራጊም ሁኑ እንዲል ቅዱስ መጽሓፍ ሁላችንም እንደየአቅማችን በንጹህ ልብ ቤተሰብ ጎረቤትና ዜጋን በመስጠት መጎብኘት ይጠበቅብናል። በተለይ በተለይ ደግሞ ሁሉ ነገር ጨለማ በሚመስለብት በዚህ ክረምት እየተተገበረ ባለው የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባትና ማጋራት ላይ መሳተፍ ሊያመልጠን የሚገባ ዕድል መሆን የለበትም እላለሁ። ሰላም ።
በአክበረት ታደለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014