በኢትዮጵያ ህትመት ታሪክ በአንጋፋነቱ ይታወቃል፡፡ በርካታ ጸሐፍትንም አፍርቷል አዲስ ዘመን ጋዜጣ። አንዳንዶች የአገር ሃበት ፣አለፍ ሲልም ታሪክ ማጣቀሻ(ኢንሳይክሎፒዲያ) ሲሉ ባለውለታነቱን ይገልጻሉ።
እንዲህ የተባለለት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ተነባቢነትና ተፈላጊነት አብሮት መዝለቅ አለመቻሉንም የሚያነሱ ጥቂት አይደሉም። አዲስ ዘመን ጋዜጣን ወደቀድሞ ተነባቢነቱ ዝናው ለመመለስ ጥረት በአሳታሚው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጥረት እየተደረገ ነው።
ከረጅም አመት በፊት በጋዜጣው ላይ ይጽፉ የነበሩት አቶ ጌታቸው በለጠ ‹‹አዲስ ዘመን የአገር ታሪክ፣ አለፍ ሲልም የብዙ ክዋኔዎች ማጣቀሻ››ሲሉ ገልጸውታል፡፡በርካቶችንም በጋዜጣው ላይ የሰላ በዕራቸውን በማሳረፍ አገርን ወገንን እንደጠቀሙም ያስታውሳሉ። እርሳቸውም አዲስ ዘመን ጋዜጣን «የህይወት ጉዞዬ መነሻ አስተማሪዬ »በማለት ውለታውን አልዘነጉም። በጋዜጣው ላይ ብዙ ጽፈው ብዙ አንብበው እዚህ ለመድረሳቸው እርሾ ስለሆናቸው።
« ብዙ ሊነበቡ የሚችሉ ጽሁፎች የነበሩት ጋዜጣ በተለያዩ የአንባቢ ድርቅ መቶት ማየት ያማል»በማለት በቁጭት የተናገሩት አቶ በለጠ የቀድሞ ዝናውን ለመመለስ አረፈደም ብለዋል፡፡የባለሙያዎች አቅም ማጎልበት፣ በዚህም የጋዜጣው መልህቅ (አንከር) የሆኑ ጋዜጠኞችን ማውጣት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ባለሙያውን የማብቃት ስራ እስኪሰራ ተነባቢነትን ለማሳደግ ቀደም ሲል በጋዜጣው ላይ የሰሩትንም ሆነ ያልሰሩትን በትርፍ ጊዜ (በፍሊራንስ )ቀጥሮ ማሰራት እንደሚገባ ይናገራሉ። በሌላ በኩልም የጋዜጣውን መሸጫ ሱቆች ማብዛት ሌላው የተነባቢነት መንገድ መሆኑንም አክለዋል።
አቶ በለው አበበ ሌላው የአዲስ ዘመን የተነባቢነት መቀነስ የሚቆጫቸው ጸሀፊ ሲሆኑ፣ በሰጡት አስተያየት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የእድሜውን ያህል ተነባቢነቱ አልጨመረም። ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥሩ የሚባሉ መሻሻሎችንም እያሳየ ይገኛል፤ በቀጣይም የዜና ጋዜጣነቱን እንደገና መልሶ የህዝብ ብሶት ማሰማት መቻል አለበት፤ ይህንን ማድረግ ከቻለ ደግሞ ወደ ነበረ ዝናና ክብሩ የማይመለስበት ምክንያት የለም በማለት ሀሳብ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ሌላው ፈተናው የፎቶ ግራፍና የዲዛይን ችግር ነው ያሉት አቶ በለው ይህንንም ለማስተካከል ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ፣ ባለሙያዎችን ማብቃት አልፎ ተርፎም ደረጃውን የጠበቀ ወረቀት በራሱ እስከ ማስመጣት መድረስ እንዳለበትም አብራርተዋል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም በየአገሩና በውጭ አገር ስርጭቱን ማብዛት ዘመኑ የሚጠይቀው አስፈላጊ እርምጃ ስለመሆኑም አቶ በለው አስገንዝበዋል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስያሜ ታሪካዊ በመሆኑ መቀየርን ማሰብ አዋጭ አይደለም ያሉት ደግሞ አቶ አጥናፍሰገድ ይልማ ናቸው። እንደእርሳቸው ስያሜ ከምንም በላይ እራስን መሆኛ ታሪክን ማስታወሻ ነው ። ይህንን ማሰብ ታሪክንም ጋዜጣውንም ማጥፋት ነውም ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለተነባቢነቱ ችግር የህብረተሰቡን ጥያቄ ያለመያዙና ኩነት ተኮር መሆኑ ነው፤ ከዚህ ወጣ ብሎ መስራት ቢችል ጋዜጣው ወደ ሰው ሳይሄድ ሰዎች እራሳቸው ፈልገውና ተሻምተው የሚያነቡት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ጥሩ ነገርን መኮረጅ መልካም ነው የሚሉት አቶ አጥናፍሰገድ ሌሎች መሰል የህትመት ውጤቶች እንዴት ነው የሚሰሩት? ለተነባቢነታቸውስ የሚያደርጉት ጥረት ምንድን ነው? የሚለውን በመፈተሽ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ በውይይት መድረኩ ላይ ‹‹በድርጅቱ የሚታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በርካታ ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን ያሳለፈ አንጋፋ የህትመት ውጤት ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችንም በማፍራት ይታወቃል›› ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ አዲስ ዘመን በ1960 ዎቹ የነበረው የተነባቢነትና የስርጭት መጠን ከፍተኛ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የተነባቢነቱም ሆነ የተጽዕኖ ፈጣሪነት አቅሙ ቀንሷል። ይህ መድረክም ጋዜጣውን ወደነበረበት ለመመለስ ትልቅ ግብዓት የሚገኝበት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
አዲሱ አመራርና ማኔጅመንትም አንጋፋ ጸሀፍትንና ስለ ጋዜጣው መለወጥ ቀናይ የሆኑ አካላትን ለማሳተፍ በሩ ክፈት ነው ያሉ አቶ ጌትነት ማንኛውም የለውጥ ሀሳብ አለኝ የሚል አካልም ሀሳቡን ቢሰጥ በደስታ ለመቀበል ዝግጁነት መኖሩን አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅትን እንደገና ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅም ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ ላይ የአገሪቷ አንጋፋ ደራሲያን፣ የጋዜጣው ቀደምት ጋዜጠኞች፣ የማህበራት ተወካዮችና አመራሮች እንዲሁም የድርጅቱ ሰራተኞችና አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ ቀጣይነት እንደሚኖረው ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።
እፀገነት አክሊሉ