
አውስትራሊያ ውስጥ አንዲት ሴት በሥነ ተዋልዶ ክሊኒክ ውስጥ በተፈጠረ የሽል መደባለቅ ምክንያት የሌላ ሰው ልጅ መውለዷ ተሰምቷል። ሽል አዳብሮ በእናት ማህፀን ውስጥ የሚያስቀምጠው ክሊኒክ በፈጸመው ስህተት ምክንያት ነው እናት የሌላ ሰው ልጅ ለወራት አርግዛ የወለደችው። በብሪዝቤን ከተማ የሚገኘው ሞናሽ አይቪኤፍ የተባለው የዘር እንቁላልን በማዳበር በብልቃጥ ውስጥ የሚያዳብረው ክሊኒክ ስህተቱ ሥራውን በሚያከናውኑ ሰዎች ምክንያት ነው ማለቱን የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
“በሞናሽ አይቪኤፍ ስም ለተፈጠረው ነገር እጅግ ከባድ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ማይክል ናፕ ተናግረዋል። አክለው በክሊኒኩ የሚሠሩ ሁሉ ባጋጠመው ስህተት “በእጅጉ ማዘናቸውን” ገልፀዋል። ባለፈው ዓመት ይህ ክሊኒክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሥነ ተዋልዶ ክትትል የሚደረግላቸው ሰዎች ፅንስ በማጥፋቱ ምክንያት 56 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር መቀጣቱ ይታወሳል።
የሞናሽ አይቪኤፍ ቃል አቀባይ እንዳሉት የክሊኒኩ ሠራተኞች ስህተት መሠራቱን ያወቁት ባለፈው የካቲት የግለሰቧ የቀረ ሽል ወደ ሌላ ክሊኒክ እንዲተላለፍ መጠየቋን ተከትሎ ነው።ቃል አቀባዩ “የቀሩትን ፅንሶች በማግኘት ፈንታ ሌላ ተጨማሪ የተከማቸ ፅንስ ተገኝቷል” ማለታቸውን ኤቢሲ ዘግቧል። ሞናሽ እንዳረጋገጠው የሌላ ሴት ሽል በስህተት በመተላለፉ ምክንያት ነው ግለሰቧ የሌላ ሰው ልጅ አርግዛ የወለደችው።
ክሊኒኩ የሠራውን ስህተት ተከትሎ ምርመራ መክፈቱን እና ለሚመለከታቸው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ማሳወቁን ገልጿል። ዋና ሥራ አስኪያጁ ከዚህ ስህተት ባሻገር ሌላ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳላጋጠመ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ሞናሽ አይቪኤፍ 56 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ለመክፈል የተስማማው 700 በክሊኒኩ የሥነ ተዋልዶ ድጋፍ በሚደረግላቸው ሰዎች ሽል ላይ በተፈፀመ ስህተት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
ክሊኒኩ በክምችት ክፍሉ ካስቀመጣቸው ሽሎች መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት ጤናማ እና እርግዝና ሊፈጥሩ የሚችሉ የነበሩ ቢሆኑም ባጋጠመው ስህተት ምክንያት አገልግሎት ላይ የማይውሉ ሊሆኑ በቅተዋል። አይቪኤፍ አሊያም ኢን ቪትሮ ፈርቲላይዜሽን ከሴቶች እንቁላል ተወስዶ ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ በቤተ-ሙከራ ሽል እንዲዳብር የሚያደርግ ሳይንሳዊ መንገድ ነው። እንቁላሉ አድጎ ሽል ሲሆን ወደ ሴቷ ማህፀን እንዲተላለፍ ይደረጋል። ይህ ሒደት ብዙ ገንዘብ የሚያስከፍል ሲሆን፣ ሁሌም ውጤታማ ይሆናል ማለት አይደለም።
በአውሮፓውያኑ 2021 በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ 29 ሺህ 690 ሕፃናት በአይቪኤፍ ተወልደዋል ይላል ከኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም