የ2014 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ እና የውድድር ዓመቱ ምርጦች ሽልማት ስነ ስርአት ከትናንት በስቲያ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል በደማቅ ስነስርዓት ተከናውኗል። በስነስርአቱም ላይ በውድድር አመቱ በየዘርፉ ምርጥ ብቃት ያሳዩ ኮከቦች ተለይተው ተሸልመዋል።
በስነስርአቱ ላይ የውድድር አመቱ ኮከብ ተጫዋቾችን ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ሲሆኑ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች ጋቶች ፓኖም የውድድር አመቱ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ተመርጧል።
ፈረሰኞቹ ከአራት አመት በኋላ ወደ ቻምፒዮንነት ክብራቸው ተመልሰው አስራ አምስተኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ባነሱበት በዘንድሮው የውድድር አመት አስደናቂ ብቃቱን በማሳየት ለክለቡ ስኬት ትልቅ ሚና የነበረው ጋቶች ከክብር እንግዳው እጅ የ210 ሺ ብር እና የማስታወሻ ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በተመሳሳይ ፈረሰኞቹ ገና በውድድር አመቱ መጀመሪያ አካባቢ አዲስ ከቀጠሯቸው ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ የውድድር አመቱን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፈረሰኞቹን እየመራ ለቻምፒዮንነት ክብር ያበቃው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የውድድር አመቱ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን ተመርጧል። በዚህም ከክብር እንግዳው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አሥራት ኃይሌ የ200 ሺ ብር እና የክብር ዋንጫውን ተቀብሏል።
የ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመባል የዋንጫ እና የአንድ መቶ ሀምሳ ሺ ብር ተሸላሚም የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቻርለስ ሉክዋጎ ሆኗል። ዩጋንዳዊው የግብ ጠባቂ በተወካዩ አማካኝነት ሽልማቱን ከቀድሞ ግብ ጠባቂ በለጠ ወዳጆ እጅ ተቀብሏል። የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው የሲዳማ ቡናው ተጫዋች ይገዙ ቦጋለ የዋንጫ እና የ2 መቶ ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል። ይገዙ ቦጋለ በውድድር አመቱ ለክለቡ ምርጥ አቋም በማሳየት አስራ ስድስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ነው ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው።
የውድድር ዓመቱ ምርጥ ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው (ዶ/ር) ሆኖ ሲመረጥ የ105 ሺ ብር እና የዋንጫ ሽልማት ከቀድሞ ዳኛ ኃይለመላክ ተሰማ እጅ ተቀብሏል። በተመሳሳይ የውድድር ዓመቱ ምርጥ ረዳት ዳኛ በመሆን ትግል ግዛው የ105 ሺ ብር እና የዋንጫ ሽልማቱን ከቀድሞ ዳኛ ይግዛው ብዙአየሁ ተቀብሏል።
የውድድር ዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ዓመቱን በሀዋሳ ከተማ ጀምሮ በጅማ አባጅፋር ያገባደደው አላዛር ማርቆስ ከክብር አንግዳው የቀድሞ የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች አንዋር ያሲን እጅ የ105 ሺ ብር እና የዋንጫ ሽልማቱን ተረክቧል።
በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው ከሰባት ሚሊየን ስድስት መቶ ዘጠና ስድስት ሺ ሶስት መቶ ሰባ ሶስት ብር ( 7,696,373 ) እስከ አስር ሚሊየን ዘጠኝ መቶ ዘጠና አራት ሺ ስምንት መቶ አስራ ዘጠኝ ብር ( 10,994,819 ) ተበርክቶላቸዋል ።
በተጨማሪም ውድድሮቹን በማስተናገድ ላይ ለነበሩት ለአምስቱም ስታድየሞች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሚሊዮን ብር ተበርክቶላቸዋል ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ዓመቱን በደማቅ ሁኔታ በማጠናቀቁ እንዲሁም በኮከብነት ለተሸለሙት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ሲል ልባዊ ደስታውን ገልጿል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም