በቻን ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆኑ ቡድኖች የሚለዩበት ማጣሪያ ከመካሄዱ አስቀድሞ የሚደረገው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በሐምሌ ወር አጋማሽ ይጀመራል። በቅድመ ማጣሪያው ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹም) ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ለሰባተኛ ጊዜ በአልጄሪያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የቻን ዋንጫ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ ወር ይጀመራል። በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚሳተፉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚካፈሉበት የዚህ ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎችም በሐምሌ ወር 2014ዓ.ም አጋማሽ መካሄድ ይጀመራሉ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በበላይነት የሚመራው ይህ ውድድር 18 ቡድኖችን ያሳትፋል።
በዚህ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን የሚችለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም (ዋልያዎቹ) ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ሐምሌ 14 እና 24/2014 ዓ.ም ታንዛኒያ ላይ ለሚደረጉት ጨዋታዎች የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማስተላለፋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል። ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር የሚያደርግ ሲሆን፤ ቅድመ ዝግጅቱን ለማድረግም ከሐምሌ 4/2014ዓ.ም ጀምሮ አባላቱ እንደሚሰባሰቡም ፌዴሬሽኑ አመላክቷል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ምርጫ መሠረትም ግብ ጠባቂዎች፤ ፋሲል ገብረሚካኤል፣ በረከት አማረ እና አላዛር ማርቆስ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ተከላካዮችም ሱሌማን ሀሚድ፣ ሄኖክ አዱኛ፣ ጊት ጋትኩት፣ ያሬድ ባየህ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ ምኞት ደበበ፣ አስራት ቱንጆ እና ረመዳን የሱፍ ናቸው። በአማካዮች በኩል አማኑኤል ዮሐንስ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ከነአን ማርክነህ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ በዛብህ መለዮ እና መስኡድ መሀመድ ተጠርተዋል። አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ዳዋ ሁጤሳ፣ ብሩክ በየነ፣ በረከት ደስታ እና ይገዙ ቦጋለ ለአጥቂነት ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2014