ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር በስፖርቱ እድገትና ውጤት ሁለንተናዊ ሚና እንዳለው ይታመናል። የስፖርት ፖሊሲውም ይሄንኑ መሰረት በማድረግ በትኩረት አቅጣጫው ካደረጋቸው አበይት ጉዳዮች ውስጥ ህብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚማርበትና በሚሠራበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ ተሳታፊ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲሚመቻች ያትታል።
በትምህርት ቤቶች ከሚደረገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተጓዳኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስፖርታዊ ክንውን በማዘጋጀት ፍሬያማነቱን በትምህርት ቤቶች ውድድር ይመዝናል። ውድድሩ ተማሪዎች የላቀ የስፖርት ችሎታቸውን በስፖርታዊ ጨዋነት ታንፀው የሚያቀርቡበት፣ የሚታዩበትና የተሻሉት ፍላጎታቸው ከታከለበት ባሉት የሀገራችን የስፖርት አካዳሚዎች፣ ክለቦች በየስፖርት ዲስፕሊኑ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚታዩበትን እድል የሚፈጥር፣ ለኦሎምፒክ ራሳቸውን የሚያጩበት ትልቅ መድረክ እንደሆነ ይታመናል። ለነገይቱ ኢትዮጵያ ስፖርት ውጤት ትልቅ ተስፋ እንዳለው የሚታመነው አገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች ውድድር ለ3ኛ ጊዜ በትግራይ ክልል አዘጋጅነት በመቀሌ ከተማ ተዘጋጅቷል።
«በትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር የተማሪዎችን ማህበራዊ ሰላምና ግንኙነት ማጠናከር፤ የአብሮነት ባህልን ማዳበር» በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር ለሀገሪቱ ስፖርት ውጤታማ የሆኑ ታዳጊዎች የሚታዩበት መድረክ ይሆናል የሚል ተስፋ የሰነቀ ነው። በሌላ ወገን፤ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ውድድር ተማሪዎች የላቀ የስፖርት ችሎታቸውን በስፖርታዊ ጨዋነት ታንፀው የሚያቀርቡበት ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ይጠበቃል። በመሆኑም በዘንድሮ ውድድር ከምንም በላይ ስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እንዳይፈጠር ተሳታፊ ክልልሎቸም ሆኑ አዘጋጁ ክልል ከፍተኛ ዝግጅት
ማድረጉ ተነግሯል። ተሳታፊዎች አጋጣሚውን እንደመልካም እድል በማየት የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ትልቅ አውድ እንደሚሆን ከስፖርታዊ ክንውኑ በተጓዳኝ የሚጠበቅ ውጤት ይሆናል።
በዚህ መንፈስ ከመጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ በመቀሌ ስታዲየም የተጀመረው ውድድር በከፍተኛ ፉክክርም እንደቀጠለ ይገኛል። እስከ ትናንት በነበረው ቆይታ የምድብና ዙር እንዲሁም የፍጻሜ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በሴቶች ቼስ ስፖርት የዙር ውድድር ድሬዳዋ ከአማራ ጨዋታቸውን ያከናወኑ ሲሆን የአማራ ክልል ድሬዳዋን 3ለ1 ረትቷል። በእለቱ የተከናወነው ሌላው የቮሊቦል ጨዋታ ነበር።
በቮሊቦል የምድብ ውድድር በወንዶች ኦሮሚያ ከደቡብ ተገናኝተው ደቡብ 3ለ1 በሆነ ውጤት ኦሮሚያን ረትቷል። ትግራይ ሀረሪን 3ለ0 ሲያሸንፍ፤ አዲስ አበባ አማራን 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ጋምቤላ ከአፋር ክልል ጋር ባደረገው ጨዋታ ጋምቤላ በጨዋታ ብልጫ ጭምር 3 ለ0 በመርታት የምድብ ጨዋታቸውን በድል ጀምረዋል። በውድድሩ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሴቶቸ እግር ኳስ አማራና ተግራይን ያገናኘ ሲሆን፤ አዘጋጁ ክልል የ3ለ1 ሽንፈት ደርሶበታል።
በወንዶች የቅርጫት ኳስ ውድድር አዲስ አበባ ከደቡብ ያደረጉት ጨዋታ በእጅጉ ትኩረት የሳበ ነበር። ብርቱ ፍክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ አዲስ አበባ ደቡብን 39 ለ 52 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በተመሳሳይ፤ አማራ ከሀረሪ 28 ለ 39፣ ጋምቤላ ከትግራይ 41 ለ 53፣ ኦሮሚያ ከድሬዳዋ 44 ለ 28 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆነዋል። በአትሌቲክስ፤ የወንዶች ርዝመት ዝላይ ኦሮሚያ 1 እና 3ኛ ደረጃን ሲይዝ ፣ትግራይ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማሸነፍ ችለዋል። በ100 ሜትር ወንድ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ከ1 እስከ 3 ያለውን ደረጃ ሲይዙ በሴቶች አማራ 1ኛ እና 3ኛ ደረጃ በመያዝ ሲያሸንፍ፤ ኦሮሚያ 2ኛ ደረጃ አግኝቷል። በሴቶች ኦሮሚያ 1ኛ እና 2ኛ ሲይዙ፤ ትግራይ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል።
በ800 ሜትር ወንዶች ኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ከ1 እስከ 3 ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ በሴቶች ኦሮሚያ አሸናፊ ሲሆን የትግራይ ተወዳዳሪዎች 2ኛ እና 3ኛ ሆነዋል። በዲስከስ ውርወራ ሴቶች፤ ኦሮሚያ1ኛ ሲወጣ አማራ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቀቅ፤ በ110 ሜትር መሰናክል ወንዶች አማራ አሸናፊ ሲሆን፤ ኦሮሚያ 2ኛ 3ኛ ደረጃ ይዟል።
በዝግጅቱ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ውድድሮች ሲኖሩ፤ አትሌቲክስ የፍፃሜ ውድድር በ5000 ሜትር ወንዶች ኦሮሚያ ወርቅ፣ ትግራይ የብርና ነሀስ ፣ ስሉስ ዝላይ ኦሮሚያ የወርቅ፣ ትግራይ የብር፣ አማራ የነሀስ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችለዋል። በአሎሎ ውርወራ ሴቶች ኦሮሚያ የወርቅ፣ የብርና የነሀስ ተሸላሚ ሲሆኑ በ3000 ሜትር አማራ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን፤ ትግራይ የብርና የነሀስ ተሸላሚ ሆኗል። በሴቶች ርዝመት ዝላይ ውድድር አማራ ወርቅ፣ ኦሮሚያ ብርና ነሀስ አሸናፊ ሆነዋል። በሴቶች ብስክሌት የግል ክርኖ ውድድር ትግራይ የወርቅ እና የብር፣ አማራ የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆኑ፤ በወንዶች አዲስ አበባ የወርቅ ፣ ትግራይ የብር እና የነሃስ ተሸላሚ ሆነዋል።
በመቀለ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው 3ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድር እስከ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ይቀጥላል። በውድድሩ ሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፤ አማራ 565፤ ኦሮሚያ 507፤ አዲስ አበባ 650፤ ድሬዳዋ 239፤ ደቡብ 405፤ ሀረሪ 107፤ አፋር 79 ፤ ጋምቤላ 128 እና አዘጋጁ ትግራይ ክልል 473 የስፖርት ልዑካንን እያሳተፉ ይገኛሉ። የሶማሌና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በበጀት ችግር ምክንያት በዚህ ውድድር አልተሳተፉም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011
በ ዳንኤል ዘነበ –