በአሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ምዕራፍ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ከ29 ተጫዋቾች ውስጥ አራት ተጫዋቾችን ቀነሰ። ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በላከልን መረጃ እንዳመላከተው፤ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ 29 ተጫዋቾችን በመያዝ በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን በጥሩ ሁኔታ እየሰራ የሚገኘው የሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን፤ የዝግጅቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ልምምድ ትናንት ማምሻውን ከወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በአዲስ አበባ ስቴዲየም በመስራት አጠናቅቋል።
ፌዴሬሽኑ በመረጃው፤ በመጀመሪያ ምርጫ ጥሪ ከተደረገላቸው 29 ተጫዋቾች መካከል አራት ተጫዋቾች ቅነሳ መደረጉን ጠቅሶ፤ ምህረት ተሰማ ግብ ጠባቂ ፣ ትዕግስት ኃይሌ ተከላካይ፣ ትዕግስት ያደታ አማካይ እና ዮርዳኖስ ምዑዝ ከአጥቂ የተቀነሱት ተጫዋቾች ናቸው። በአሁኑ ወቅት 25 ተጫዋቾች የቀሩ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ሳምንት የኡጋንዳ አቻውን እስኪገጥም ድረስ ተጫዋቾቹ ከቡድኑ ጋር አብረው እንደሚቆዩ ተረጋግጧል።
በዚህ መሰረት በግብ ጠባቂነት ታሪኳ በርገና ከጥረት ኮርፖሬት፣ አባይነሽ ኤርቄሉ ከሀዋሳ ከተማ በቡድኑ ተካትተዋል። በተከላካይ ክፍል ከአዳማ ከነማ አራት ተጫዋቾች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን መስከረም ካንኮ፣ እፀገነት ብዙነህ፣ ናርዶስ ዘውዴ፣ ነፃነት ፀጋዬ ናቸው። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገነሜ ወርቁ፣ ታሪኳ ደቢሶ፣ ብዙዓየሁ ታደሠ ሲሆኑ ከመከላከያ መሠሉ አበራ፣ ከጥረት ኮርፖሬት አሳቤ ሙሶ ናቸው።
በአማካይ ስፍራ ብርቱካን ገብረ ክርስቶስና ሕይወት ዳንጊሶ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ከመከላከያ እግር ኳስ ክለብ አረጋሽ ከልሳ እና እመቤት አዲሱ፤ ብርሃን ኃይለ ሥላሴ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰናይት ቦጋለ ከአዳማ ከተማ፣ ዓለምነሽ ገረመው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በምርጫው የተካተቱ ተጫዋቾች ሆነዋል።
በአጥቂ ስፍራ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረሃማ ዘርጋው፤ የአዳማ ከተማ ተጫዋች የሆኑት ሎዛ አበራ፣ ሴናፍ ዋኩማ ፣ ሰርክአዲስ ጉታ የተካተቱ ሲሆን፤ ምርቃት ፈለቀ ከሀዋሳ ከተማ፣ ሔለን እሸቱ ከመከላከያ እንዲሁም፤ ምስር ኢብራሂም ከጥረት ኮርፖሬት እግር ኳስ ክለብ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ብሄራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን የፊታችን መጋቢት 25 ከኡጋንዳ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል።
በኦሎምፒክ በሴቶች እግር ኳስ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሪዮ 2016 ማጣሪያ ላይ አልተሳተፈም። በቀደመው (ለንደን 2012) ደግሞ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ 3ለ0 ድምር ውጤት ተሸንፎ በመጀመሪያው ዙር ተሰናብቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011