የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ውድድር መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በዴንማርክ አርሁስ ከተማ ይጀመራል፡፡ የአዘጋጅነቱን እድል ከኡጋንዳ በመቀጠል የተረከበችው ዴንማርክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያደረገችውን ዝግጅት በማጠናቀቅ የውድድሩን እለት በጉጉት እየጠበቀች ትገኛለች። በከፍተኛ ጉጉት እየተጠበቀ ባለው በዚህ ውድድር ከ67 ሀገራት የተውጣጡ 582 ተሳታፊ አትሌቶች እንደሚጠበቁ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የወጣው መረጃ አመላክቷል።
አዘጋጇ ሀገርም የተጠቀሱትን አትሌቶችና ወደ ከተማዋ የሚተሙ የስፖርት ቤተሰቦችን ለማስተናገድ በተለያዩ መልኩ ዝግጅቶች ተጠናቀው መጪውን ቅዳሜ በናፍቆት እየተጠባበቁ መሆኑም ተነግሯል። እ.ኤ.አ. 1973 የተጀመረው ይህ አዝናኝ ውድድር በተለያየ ውጣ ውረድ በመታጀብ ለ43ኛ ጊዜ ለመካሄድ የቀናት እድሜ ቀርተውታል።
በየሁለት ዓመቱ የሚከናወነው የዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ አትሌቲክስ ውድድር የአትሌቶችን አቅም በመፈተን ይታወቃል፡፡ አባጣ ጎርባጣ፣ ውሃማ፣ እንዲሁም ጭቃማ የመሬት አቀማመጥ መለያው እንደመሆኑ፤ በትልቅ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። ከፍተኛ ትኩረት ባገኘው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከወዲሁ ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2017 በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በተከናወነው 42ኛው አገር አቋራጭ ውድድር ኬንያ በ4 ወርቅ፣ በ5 ብርና በ3 ነሐስ በድምሩ በ12 ሜዳልያ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያ በ4 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ1 ነሐስ በዘጠኝ ሜዳልያዎች ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው፤ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን ውጤት መሰረት በማድረግ በዴንማርክ የሁለቱ ምስራቅ አፍሪካ አገራት ፍጥጫ ገዝፎ እንደሚታይ ግምት ተሰጥቶታል። በተለይ ደግሞ፤ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሀገር አቋራጭ ውድድር ከስር መሰረቱ በጀግኖች አትሌቶች ውጤታማነታቸው የታየ መሆኑ በስፋት እየተነሳ ይገኛል።
እ.ኤ.አ. 1973 በተጀመረው የአገር አቋራጭ ውድድር ስማቸውን በደማቁ ካሠፈሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል እ.ኤ.አ. 1982 መሐመድ ከድር፣ በ1985 ወዳጆ ቡልቲ፣ በ1996 አበበ መኮንን፣ በ1992 ፊጣ ባይሳና 1994 ኃይሌ ገብረ ስላሴን፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ በቀነኒሳ በቀለ የተሰሩ ተደጋጋሚ የድል ታሪኮች ዛሬም በዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮናው የድል ግምት እንዲሰጥ ያደረጉ ገድሎች ናቸው።
በቅርብም በእነ ሰለሞን ባረጋ ዓይነት ወጣት አትሌቶች እየታዩ ያሉት ውጤቶች በዴንማርኩ 43ኛው የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድምቀት እንደሚሆኑ ግምት አግኝተዋል። ግምት የተሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድኑ ለዓለሙ የአገር አቋራጭ ውድድር ዝግጅቱን አጠናቅቆ ከትናንት በስቲያ ሽኝት ተደርጎለታል።
ቡድኑ በውድድሩ የሚሳተፉትን አትሌቶች በቅርቡ ከተካሄደው 36ኛው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር ተሳትፈው ባላቸው የተሻለ ውጤት ያላቸው፤ እንዲሁም የእድሜን ተገቢነት ያሟሉ መርጧል። ከየካቲት ወር ጀምሮ ዝግጅቱን የጀመረው ብሔራዊ ቡድኑ ልምድ ባላቸው አሠልጣኞች በመታገዝ ጠዋትና ከሰዓት መርሐ ግብሩ ልምምዱን ማከናወኑ ተገልጿል።
አትሌቶቹ ካምፕ ገብተውም ለውድድሩ የሚረዳቸውን ልምምድም በአዲስ አበባ ስታዲየም፣ በጃንሜዳ እና ከከተማ ውጪ ልዩ ልዩ ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ከስፖርታዊ ስልጠናው ባሻገርም በስነ ልቦና፣ በአመጋገብ፣ በእረፍት አጠቃቀም፣ በህክምና፣ በማሳጅና ፊዚዮቴራፒ እንዲሁም በርስ በርስ መስተጋብር ረገድ በቡድኑ አሰልጣኞች፣ በአመራሮችና በህክምናው ዘርፍ ከፍ ያለ ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ ሰንብተዋል። ብሄራዊ ቡድኑ ካደረገው ቅድመ ዝግጅትና ከነበረው የቀድሞ ታሪክ በመነሳት የቅድሚያ ግምት ያገኙትን 14 ሴትና 14ት ወንድ በድምሩ 28 አትሌቶች የያዘው ብሄራዊ ቡድን ወደ ዴንሟርክ አቅንቷል።
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ በመድረኩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች፤ በአጠቃላይ ሶስት መቶ አስር ሺህ ዶላር ተዘጋጅቷል። በሁለቱም ፆታዎች በአዋቂዎች ምድብ አሸናፊዎች ለሚሆኑ አትሌቶች አንድ መቶ አርባ ሺህ ዶላር የሚቋደሱ ይሆናል።
በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታ አንደኛ ለሚወጡት እያንዳንዳቸው ሰላሳ ሺህ ዶላር፤ ሁለተኛ አስራ አምስት ሺህ፤ ሶስተኛ አስር ሺህ አራተኛ ሰባት ሺህ፤ አምስተኛ አምስት ሺ፣ ስድስተኛ ሶስት ሺ ዶላር ሽልማት የሚሰጣቸው መሆኑም ታውቋል። ለድብልቅ ሪሊም ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በወጣቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችም የእውቅና ሽልማት የሚሰጣቸው ይሆናል። በአገር አቋራጭ ውድድር ላይ እንደ ቡድን የሚመዘገብ ውጤት ፋይዳው የላቀ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ በዘንድሮው ፍልሚያም በበቡድን ለሚያሸንፉ አንደኛ ለሚወጣው ቡድን ከሚሰጠው የአስራ ሁለት ሺህ ዶላር አንስቶ በየደረጃው ሽልማቱን እንደሚረከብ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011
በዳንኤል ዘነበ