መንግስት በየተቋማቱ የሚስተዋለውን የፋይናንስ አሰራር ችግር ለመፍታት በየጊዜው አዳዲስ አሠራሮችን በመዘረጋት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይም ከ2004ዓ.ም ጀምሮ በተመረጡ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት በመዘርጋት የፋይናንስ አሰራር ችግር ሆነው ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና አሰራሮች ምላሽ እየተሰጠባቸው ይገኛል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደሚሉት፤ የመንግስት ባለባጀት መስሪያ ቤቶች ፋይናስንም ሆነ ያላቸውን ሀብት የሚመሩት በወረቀት ላይ በተመሰረተ የተንዛዛ አሰራር ነው፡፡ ይህም በተቋማቱም ሆነ በተቆጣጣሪው የመንግስት አካል የተቀናጀና ቀልጣፋ አሰራር እንዳይኖር አድርጎታል፡፡ መንግስትም ያለውን ሀብትና ንብረት በውል እንዳያውቀው ሆኗል፡፡ በተለይም ንብረቶች የሚመዘገቡበት መንገድ ቋሚና ዘላቂ ስለመሆናቸውና ባለመለየታቸው ለብክነት ተጋላጭ የሆኑባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ ናቸው፡፡
«ለረጅም ዓመታት ስንከተለው የቆየነውና አሁንም በአብዛኞቹ መስሪያ ቤቶች እየተሰራበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ንብረቶችን ከግምጃ ቤት ወጪ በምናደርግበት ጊዜ ምን ያክል ሀብት አለ? ምን መገዛት አለበት? የሚለውን መረጃ የሚያሳይ የተቀናጀ አሰራር ባለመኖሩ በየዓመቱ አላግባብ ግዢ ይፈፀማል፡፡ ክፍያዎችም ለማንና ለምን እንደተፈፀሙ በውል የሚታወቅበት አሰራር አልነበረም» ይላሉ፡፡
በዋነትም መረጃዎች የሚያዙበት አሰራር በደረሰኝና በመዝገብ የተመሰረተ በመሆኑ የተቋማቱን አሰራር እንዳይቀላጠፍ ከማድረጉም ባሻገር ለብክነት የሚዳርግና ተጠያቂነት ለማምጣት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አቶ ገመቹ ያስረዳሉ፡፡
የተቀናጀ የፋይናስ ሥርዓት በተወሰኑ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች መተግበር ከተጀመረ ወዲህ በተቋማቱ በጀት ወጪና ገቢውን፣ ንብረቱንና የሰው ኃይሉን በተቀናጀ መልኩ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መቆጣጠር እንደተቻለ የሚገልፁት አቶ ገመቹ፤የአሰራር ሥርዓቱ የፋይናስ ባለሙያው ሁሉንም ስራዎች መስራት እንዲችል የሚረዳ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ይደረጉ የነበሩ ምልልሶችን በማስቀረት ገንዘብና ጉልበትን የሚቀንስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የተቀናጀ የፋይናንስ ሥርዓትን ከሰው ሀብት አሰራር ጋር በማቆራኘት ማንኛውም ሰራተኛ በሰራባቸው ሰዓታት ልክ ብቻ ደመወዙ እንዲከፈለው በማድረግ የሰው ሃይሉን በአግባቡ ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ፣ይህም ያለስራ ይባክን የነበረውን ጊዜ ከመታደጉም ባሻገር ወጪንም እንደሚቆጥብ አቶ ገመቹ ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ገመቹ ገለፃ፤ የተቀናጀ የፋይናስ ሥርዓት መዘርጋት ተቋማት እያንዳንዱ ተሰብሳቢ ወይም ተከፋይ የምንለው ባለቤት እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ይህም ምን ያክል ተከፈለ? ምን ይቀራል? ምን ያህል ተወራረደ? የሚለውን ዝርዝር የሂሳብ አሰራር ለማወቅ ያስችላል፡፡ በወቅቱ ሂሳብ ለመዝጋትም ያግዛል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በየቀኑ ሂሳብ እያስታረቁ መሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ከዚህ ቀደም በበጀት መዝጊያ ወቅት ያጋጥሙ የነበሩ የስራ መጨናነቆችን ያቃልላል፡፡ በየመንግስት መስሪያ ቤቶች ያለውን ብልሹ አሰራር ከማስቀረት አኳያም ትልቅ ሚና አለው፡፡
በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ይህ ሥርዓት መተግበሩን የሚጠቁሙት አቶ ገመቹ፤ በኢትዮጵያ ከተጀመረ አራት ዓመታን እንዳስቆጠረና በእነዚህ ዓመታትም ሥርዓቱን በተጨባጭ ተግባራዊ ያደረጉት ተቋማት ከ50 እንደማይበልጡ ያመለክታሉ፡፡ ይህን የፋይናንስ ሥርዓት የማዘመን ሂደት አዝጋሚ መሆን በተቋማት የሚካሄደው የፋይናስ ስራ ችግር መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ሁሉ ውጤታማነት ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ እያሳረፈ መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡
ሥርዓቱን ለመተግበር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝርጋታ የሚያስፈልግ በመሆኑ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ፣የሰለጠነና በቂ የሰው ሃይል መመደብ የሚጠይቅ መሆኑን ነው የሚናገሩት አቶ ገመቹ፤ በሌላ በኩልም ሥርዓቱን በተገበሩት ውስን ተቋማትም ቢሆን የኔትወርክና የሃይል መቆራረጥ በመኖሩ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ አለመቻሉን ያስገነዝባሉ፡፡
በጂኦሌጂካል ሰርቬይ የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ዘውዱ ንጉሴ በበኩላቸው፤
በተቋሙ የፋይናንስ የአሰራር ድክመት ምክንያት ባለፉት ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ የተከማቹና ያልተወራረዱ፤ ሊከፈሉና ማስረጃ ሊቀርብባቸው የማይችሉ ሂሳቦች ወደ 1ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚደርስ ብር በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር አማካኝነት ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲሰረዝ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያስችል ዘንድም በቅርቡ የተቀናጀ የፋይናንስ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንደተጀመረ ይጠቁማሉ፡፡
«የሥርዓቱ መተግበር ከዚህ ቀደም የነበረውን ውዝፍ የፋይናንስ ስራ ለማስቀረት እያስቻለን ነው» የሚሉት ተወካዩ፤ የተጀመረው አሰራር ከበጀት አጠቃቀም ጀምሮ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መቆጣጠር ስለሚችል የፋይናስ አሰራር ሥርዓቱ ላይ ቀልጣፋና ውጤታማ ስራ ለማከናወን እንደሚረዳ ይገልፃሉ፡፡ ከንብረት አያያዝና አጠቃቀም አንፃርም ቢሆን ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት ከመስክ ሥራ ጋር ተያይዞ በየቦታው ተበታትነው የሚገኙ ንብረቶች በመኖራቸው ይህ አሰራር ምላሽ እንደሚሰጥና የተጠያቂነት ሥርዓት እንዳለው ነው የሚያመለክቱት፡፡
እንደተወካዩ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ጥናቱ ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑንና የፋይናስ አሰራር ሥርዓትን ጠብቆ መረጃዎችን ማጠናከርና ከማን ላይ ምን አለ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የፋይናስ ዳይሬክቶሬት እየሰራ ይገኛል፡፡ ቀጣይ የተቋሙ ሰራተኞች አዲስ የተጀመረውን የፋይናንስ አሰራር ሥርዓትን ተከትለው ማንኛውንም የፍይናንስ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዲያስችላቸው ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ስራውን በተደራጀ አግባብ ለመስራት ግን በቂና የሰለጠነ የሰው ኃይል የማግኘቱ ጉዳይ ለተግባራዊነቱ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነበት ተወካዩ አልሸሸጉም፡፡ በተለይም ብቃት ያለውን የሰው ኃይል በስፋት ያለማግኘትና ቢገኝም አወዳድሮ ለመቅጠር ችግር መኖሩን ያመለክታሉ፡፡ ከኔትዎርክና ከኃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ በዋና ኦዲተሩ የተነሳው ችግርም በእነሱ ተቋም ላይም ስለመከሰቱ ተናግረዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሳ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ የዚህ ሥርዓት መዘርጋት መንግስትን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በተለይም ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመምራትና ለመቆጣጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው፤ ይህንን ታሳቢ በማድረግም በሙከራ ደረጃ ሥርዓቱን የመዘርጋት ስራ የተጀመረው በተወሰኑ ተቋማት ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በዘርፉ ያለው አቅም እየጎለበተ በመጣ ቁጥር በሁሉም ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የማስፋፋት ሥራ እንደሚከናወን የጠቆሙት አቶ ሃጂ፤ ከሰው ኃይል እጥረት ጋር ተያይዞ የቀረበው አስተያየት ተገቢ እንደሆነ፣ ነገር ግን ይህ ችግር በሁሉም መሥሪያ ቤቶች ላይ ያለ መሆኑን፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በስፋት ማምረት ከተቻለ ክፍተቱን ለመሙላት እንደሚቻል፤የኔትወርክና የኃይል መቆራረጥ ችግርም በተመሳሳይ በሁሉም የልማት ስራዎች ላይ እንደሚስተዋልና ችግሩንም የሚፈታው በሂደት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህሌት አብዱል