በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቁ የውድድር መድረክ ‹‹ፕሪሚየር ሊግ›› በሚል ስያሜ ወጥ በሆነ መንገድ መካሄድ የጀመረው ከ1990 ጀምሮ ነው:: ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ጉዞውም የተለያዩ ቻምፒዮኖችንና መሰረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ለውጦችን አስተናግዷል። የዘንድሮውን ጨምሮም 24 ዋንጫዎችን የተለያዩ ክለቦች ማንሳት ችለዋል:: ከነዚህ 24 ዋንጫዎችም ቅዱስ ጊዮርጊስ የዘንድሮውን ጨምሮ 15ቱን በመሰብሰብ ሃያል ከመሆኑ ባሻገር ፍፁም ሊባል የሚችል የበላይነት አለው። ቀሪዎቹን 9 ዋንጫዎች 5 የተለያዩ ክለቦች ወስደዋል።
የመጀመሪያውን ዋንጫ በማንሳት ስሙን በታሪክ ማህደር ላይ ያሰፈረው ከሊጉ ወርዶ ከዓመታ በኋላ ዘንድሮ መመለሱን ያረጋገጠው የቀድሞው መብራት ኃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነው። መብራት ኃይል ያኔ ከ24 ዓመት በፊት የመጀመሪያውን ዋንጫ ሲያነሳ 32 ነጥቦችን ሰብስቦ ነበር። ይህን ነጥብ የሰበሰበውም ስምንት ግቦችን ብቻ በማስቆጠር ነበር።
ባለፈው ሐሙስ 15ኛ ዋንጫውን መሳም የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ የቀመሰው በ1991 ነው:: 10 ክለቦች ብቻ በተሳተፉበት ውድድር ነበር:: በቀጣይ ዓመትም ፈረሰኞቹ ዋንጫውን የነጠቃቸው አልነበረም። የክለቦች ቁጥርም በዚያ ወቅት ወደ 12 ከፍ ብሎ ነበር። 1993 ዓ.ም መብራት ኃይል ከሁለት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ንግስና የተመለሰበት ነው:: መብራት ኃይል የነዚህን ዓመት ዋንጫ በማንሳት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ከአንድ ጊዜ በላይ ቻምፒዮን የሆነ ብቸኛው የአዲስ አበባ ክለብ ነበር:: ከዚህ ድሉ በኋላ ግን ወደ ዋንጫ አልተመለሰም። በዚያ ወቅት የተሳታፊ ክለቦች ቁጥርም ወደ 14 ከፍ ብሎ ነበር። 1994 የውድድር ዓመት ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ኃያልነት የተመለሱበት ሆኖ ይታወሳል:: ፈረሰኞቹ ለ3 ጊዜ ቻምፒዮን ሲሆኑ፣ በቀጣዩ ዓመትም ለ4ተኛ ጊዜ በሊጉ ነግሰውበታል::
1996 ዓ.ም በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ አዲስ ክስተት ይዞ የመጣ ዓመት ነበር። ሐዋሳ ከነማ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያው የክልል ክለብ ሆነ። ቢያንስ በ2 ዓመት አንድ ጊዜ መንገስ የለመዱት ፈራሰኞቹ ከሁለት ተከታታይ ድሎቻቸው በኋላ ዳግም ወደ ቻምፒዮናነት የተመለሱት በ1997 ነበር። ይህም 5ኛ ድላቸው ሆኖ ሲመዘገብ ቀጣዩን ዓመትም ከቻምፒዮንነት ያቆማቸው አልነበረም:: 1998 ውድድር ዓመት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በ14 ክለቦች መካከል ሲካሄድ የቆየው ፕሪሚየር ሊግ ወደ 15 ከፍ ብሎም ነበር።
ሐዋሳ ከነማ አንድ ጊዜ ብቻ ዋንጫውን አንስቶ አልቀረም፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ተመልሶ በ1999 ዓ.ም ሌላ ጣፋጭ ድል አጣጥሟል። በዚህ ዓመትም የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ብሎ የነበረ ቢሆንም 10 ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉን አቋርጠው በ6 ክለቦች ነበር ዓመቱ የተጠናቀቀው።
የኢትዮጵያ ሚሌኒየም 2000 ዓ.ም ላይ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 25 አሻቅቧል። የእዚህን ዓመት ዋንጫም ፈረሰኞቹ ከአንድ ዓመት ረፍት በኋላ ለ7 ጊዜ አንስተውታል። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም ፈረሰኞቹን ከዙፋናቸው ያወረዳቸው ክለብ አልነበረም። የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ 16 ዝቅ ባለበት 2001 ዓ.ም ፈረሰኞቹ ዋንጫውን ለ9 ጊዜ ስመውታል። ቀጣዩ 2002 ዓ.ም የተሳታፊዎች ቁጥር 18 ነበር። ፈረሰኞቹም 10ኛውን ዋንጫ ከፍ አድርገዋል። ለተከታታይ ሦስት ጊዜ በማንሳትም የመጀመሪያ ታሪካቸው ነው::
2003 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉ ሌላ አዲስ ታሪክ ያየበት ወቅት ነው። የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በእዚህ የውድድር ዓመት ከ16 ክለቦች ጋር ተፎካክሮ ለበርካታ ደጋፊዎቹ ዋንጫ አበርክቷል። በቻምፒዮኖቹ የታሪክ ማህደርም ኢትዮጵያ ቡና መድገም ያልቻለውን ዋንጫ በአሁኑ የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ እየተመራ አዲስ ንጉስ ሆኖ ተመዝግቧል።
ፈረሰኞቹ በ2004 የውድድር ዓመት በቻምፒዮናነት ተመልሰዋል። 14 ክለቦች ቋሚ በሆነ መንገድ መሳተፍ በጀመሩበት የውድድር ዓመት ፈረሰኞቹ ወደ ዙፋናቸው የተመለሱት 59 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነበር። ቀጣዩን ዓመት ግን ፈረሰኞቹ እንደተለመደው ድላቸውን መድገም ሳይችሉ ቀርተዋል። በእዚህም ለፕሪሚየር ሊጉ እንግዳ የሆነውና መሳተፍ ከጀመረ ገና አራት ዓመታትን ያስቆጠረው ደደቢት በኮከብ ግብ አግቢውና ኮከብ ተጫዋች ሆኖ በተመረጠው ጌታነህ ከበደ ፊት አውራሪነት የሊጉ አዲስ ቻምፒዮን ለመሆን በቃ።
ይህም ታሪካቸው ፕሪሚየር ሊጉን ከፈረሰኞቹ ውጪ ያነሱ 4ኛው ክለብ አድርጓቸው ነበር። 2006 ለፈረሰኞቹ እንደተለመደው ከአንድ ዋንጫ በኋላ ወደ ቻምፒዮናነት የተመለሱበት ነው። ቀጣዩ ዓመትም ፈረሰኞቹ ሊጉ ገና ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ለ12 ጊዜ መንገሳቸውን በጊዜ ያረጋገጡበት ሆኗል። የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበም ከ12ቱ ዋንጫዎች 7ቱን አብሮ በማንሳት ከክለቡ ጋር አዲስ ታሪክ አኑሯል።
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊዎቹን ከ14 ወደ 16 ባሳደገባቸው ዓመታት ፈረሰኞቹ ብዙም ሳይቸገሩ ተከታታይ ዋንጫዎችን ማንሳት ችለዋል። በተከታታይ አራት ዓመታት ፈረሰኞቹ ቻምፒዮን በመሆን አዲስ ታሪክ በፃፉበት የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ደረጃና ጥራት ከመውረዱ ባነሰ ጨዋታዎችም ለተመልካች እጅግ አሰልቺና ፉክክሩም ደብዛዛ ነበር።
ከነዚህ የውድድር ዓመታት በኋላ ግን ከ2010 ጀምሮ ፕሪሚየርሊጉ በአዳዲስ ቻምፒዮኖች አብዮት የተቃኘ ሆኗል:: ለሦስት የውድድር ዓመታትም የተለያዩ የክልል ክለቦች ወደ ቻምፒዮንነት ሊመጡ ችለዋል:: የያኔው ጅማ ከነማ የአሁኑ ጅማ አባጅፋር የጀመረውን የቻምፒዮንነት አብዮት መቖለ ከተማና ፋሲል ከነማ ተቀላቅለው ያለፉትን ሦስት ዋንጫዎች ማንሳት ችለዋል:: ፈረሰኞቹም ከነዚህ ዓመታት በኋላ ባለፈው አርብ 15ኛውን ዋንጫ በማንሳት ወደ ቻምፒዮንነት ተመልሰዋል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2014