አራተኛው ዙር አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐግብር በጉለሌ እጽዋት ማዕከል እጅግ በሚገርምና እጅን በአፍ በሚያስጭን ልምላሜንና ተስፋን በሚያጋባ መድረክ ተከናውኗል። ባለፉት ሶስት አመታት ከ18 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ከስድስት ቢሊየን በላይ ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለተከላ ከተዘጋጁት 52 በመቶ የሚሆኑት ችግኞች የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ መሆናቸው ይች አገር በሚቀጥሉት ሶስትና አራት አመታት ከፈጣሪ ጋር ልምላሜዋና በረከቷ የሚያስገርምና ተዝቆ የማያልቅ እንደሚሆን ከወዲሁ አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል። በአራት አመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የነበር ቢሆንም ዘንድሮ ዕቅዱን ከማሳካት ታልፎ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ተጨማሪ ችግኞች ይተከላሉ።
በጉለሌ የዕጽዋት ማዕከል የተዘጋጀውን የ4ኛ ዙር” ኢትዮጵያን እናልብሳት ! “ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት መድረክ እጅን በአፍ በሚያስጭን ልምላሜና በአበባ አጊጦና ምድራዊ ገነት መስሎ ትንግርተ ውበት ተጎናጽፎ ስመለከት፤ ሁለት ነገሮች በአእምሮዬ እየተመላለሱ ነበር። የመጀመሪያው ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ከአራት አመታት በፊት ያስጀመሩት “አረንጓዴ አሻራ” ከአመታት በኋላ አገራችንን ቀይሮ ምን ሊያስመስላት እንደሚችል ፍኖተ ካርታውን አበክረው በዛ ለማመን በሚቸግር መድረክ ማመላከታቸው። ሁለተኛው ከዚህ ከአይነ ህሊና የማይጠፋ ሁነት ጀርባ ሁል ጊዜ የሚገርመኝና የሚደንቀኝ አንዳንድ ጊዜም ግራ የሚያጋባኝ የጠቅላይ ሚንስትሩ የመሪነት ተክለ ሰብዕና ነው።
ሰማይ ዝቅ ቢል ምድር ከፍ ቢል አይናቸውን ከትልቁ ስዕል ያለማንሳት ልዩ ሰብዕናቸው። በዚህ ሁሉ ደባ፣ ሴራ፣ ቀውስ፣ መርዶ፣ ዋይታ፣ ለቅሶ፣ ሟርት፣ ጫና፣ ከበባ፣ ጥላቻ፣ ልዩነት፣ በሬ ወለደ፣ ወዘተረፈ አይንን ከትልቁ ስዕል ያለማንሳት፤ በሁኔታዎች ከአገራዊ ህልም ያለመባተት ሰብዕና መላበስ ምንኛ መታደል ነው የሚል መንፈሳዊ ቅናት ይፈጥራል። ውሽንፍሩ ቢበዛ፣ ሰማዩ ቢያጉረመርም ትኩረትን ከራእይ ያለመንቀል የአመራር ተሰጥኦ። ማዕበሉና ወጀቡ ጀልባዋን ቢያናውጠው በዚህ ሁሉ መሀል ካለሙት ለመድረስ በጽናት የመቅዘፍ ሰብዕና።
አጀንዳን ለማስጣል ከተደረገና ከሚደረግ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ጥረትና ርብርብ ጋር ግብግብ እየገጠመና እየተናነቀ አይንን ከተራራዋ ጫፍ ያለመንቀል የመሪነት ሰብዕና በእውነት ምንኛ መታደል ነው። ውሽንፍሩ ቢበዛ፣ ሰማዩ ቢያጉረመርም ትኩረትን ከራእይ ያለመንቀል የአመራር ተሰጥኦ። ማዕበሉና ወጀቡ ጀልባዋን ቢያናውጠው በዚህ ሁሉ መሀል ካለሙት ለመድረስ በጽናት የመቅዘፍ ሰብዕና። አጀንዳን ለማስጣል ከተደረገና ከሚደረግ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ጥረትና ርብርብ ጋር ግብግብ እየገጠመና እየተናነቀ አይንን ከተራራዋ ጫፍ ያለመንቀል የመሪነት ሰብዕና።
ሸኔና ጭፍራዎቹ በምዕራብ ወለጋ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ያን ለመስማት የሚሰቀጥጥ፤ ለማየት የሚዘገንን ጭፍጨፋ በፈጸሙበት ማግስት፤ ትህነግ በሰሜን ዕዝና በአገር ላይ ክህደት በፈጸመበት፣ በሉዓላዊነትና ሕግን በማስከበር ዘመቻ ወቅት፤ በግብጽ ፉከራ፣ በሱዳን ወረራ፣ በምዕራባውያን ከበባ፣ በሱዳን ትንኮሳና ወረራ፣ በአለማቀፍ ሚዲያውና በመብት ተቆርቋሪዎች ያ ሁሉ ማጠልሸት በተባባሰበት እንኳ ለአፍታ አይንን ከትልቁ ስዕል ያለማንሳት ተክለ ሰብዕና። ከሳምንት እስከ ሳምንት፣ ከወር እስከ ወር እንዲሁም ከአመት እስከ አመት መሪ፣ አገርና ሕዝብ በሀዘን ልቡ ደምቶ፣ ቅስሙ ተሰብሮ እና ቆዝሞ ከሀዘን ድንኳን አዙሪት እንዳይወጣ የተሸረበን ሴራ በጣጥሶ አይኑን ከከፍታው ጫፍ ያላነሳ።
አረንጓዴ አሻራ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ሸገርንና እንጦጦን የማስዋብና የማልማት፣ የጣና የወንጪና የኮይሻ አገር አቀፍ ፕሮጀክቶች ትልም፣ የብር ለውጥ፣ ወደ አገራች የቴሌኮም ኢንዱስትሪ አዲስ ተዋናይ ማስገባት፤ የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የታላላቅ ፕሮጀክቶች ጅማሮ፣ ሒደትና ማጠናቀቅ፣ ወዘተረፈ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ፣ ሕጎችንና አዋጆችን ማሻሻል አዳዲስ አዋጆችን ማውጣት፣ አገራቀፍ ምርጫ ማካሄድ እና የመሳሰሉት በርካታ ተግባራትን ለተመለከተ አገሪቱ ውስጥ አይደለም የማያበራ ቀውስ ኮሽታ ያለ አይመስልም። በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ሰላምና በመደመር ወደ ብልጽግና ስለመሻገር ሳያሳስቡ ቀርተው አያውቁም። ይህን ፈተና እንደምንሻገረው በልበ ሙሉነት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።
ቀውስ ጠማቂዎችና ስፖንሰር አድራጊዎቻቸው የጠቅላይ ሚንስትር አይን ከትልቁ ስዕል አለማንሳት የእግር እሳት ሆኖ የሚለበልባቸው ይመስለኛል። ጥቃቱን አባብሰው የሚቀጥሉትም በዚህ እልህና ቁጭት ሳይሆን ይቀራል። የአዘቦቱ ዜጋ ሆነ ልሒቃኑ ይህን በቅጡ የተገነዘቡት አይመስለኝም።
ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉንም እርገፍ አድርገው ትተው ለምን ከአመት እስከ አመት ፍራሻቸውን አንጥፈው ሀዘን አልተቀመጡም፤ አላስተዛዘኑም፣ አላጽናኑንም የሚል የተሸናፊነትና የተንበርካኪነት ውርክብ ውስጥ የገቡት። ይህ ውልውል በተወሰነ ደረጃ ተገቢነት አለው። ጠቅላይ ሚንስትር በዕለቱ ባገኙት አጋጣሚ ሀዘናቸውን ገልጸዋል። አውግዘዋል። ሆኖም የሐዘን ቀን ያላወጁት፤ ሰንደቃላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ያላደረጉት የንጹሐን ህይወት አልገዳቸው ብሎ ሳይሆን በጠላቶቻችን ፊት ተሸናፊ መስሎ ላለመታየት እና እውቅና ላለመስጠት ይመስለኛል።
የንጹሐን ህይወት መቀጠፍና መፈናቀል አልያም ንብረት መውደምና መዘረፍ ግድ አልሰጣቸው ብሎ ወይም ሀዘኑ ሀዘናቸው አልሆን ብሎ አይደለም። ለጥፋት ኃይሎች ምንም ብታደርጉ ለውጡ ዳር ይደርሳል። የኢትዮጵያ ብልጽግና ለአፍታ እንኳ አይቆምም። ምንም ምድራዊ ኃይል አያስቆመንም የሚል መለዕክትን ለማስተላለፍ፤ እንደ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ለጠላቶቻችን አንበገርም በማለት ሕዝብ ሞራሉ እንዳይጎዳና የተሸናፊነት ስሜት እንዳይጋባባት ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥርሳቸውን ነክሰው ሀዘናቸውን ውጠው አይናቸውን ከፍተው ላይ ማድረግን መርጠዋል ብዬ አምናለሁ።
እንደ አባት የልጅን፣ እንደ ባል የሚስትን፣ እንደ ልጅ የእናት የአባት፣ እንደ ወንድም የወንድምና የእህት፣ እንደ ኢትዮጵያዊ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሞት፣ ጉዳት፣ መነቀል፣ መፈናቀል፣ ወዘተረፈ አልሰማቸው ብሎ አይደለም። በጠላቶቻችን ፊት ተሸናፊ መስሎ ላለመታየት እንጂ። የሆነ ቦታ ጥቃትና ጭፍጨፋ የተፈጸመ ሰሞን ቅስማቸው እንደሚሰበር፤ ፊታቸው እንዴት እንደሚጠቁር በቴሌቪዥን መስኮት እየተመለከትን ነው። ለነገሩ የሐዘን ቀን ይታወጅ፣ ሰንደቃላማ ዝቅ ብሎ ይውለብለብ ቢባል እንደ አገርም ሆነ ሕዝብ አራቱን አመታት ሙሉ ሁሉን እርግፍ አድርገን ትተን ሀዘንተኛ ልንሆን ነበረ ማለት ነው። ይህን በማድረግ የጠላቶቻችንን አጀንዳ አስፈጸምን ማለት ነው።
ከ10 አመታት በፊት አልቃይዳ በአሜሪካ ላይ የመንገደኞችን አውሮፕላን ጠልፎ በኒውዮርክ ከአለም የንግድ ድርጅት መንትያ ሕንጻዎች ጋር በማላተም፤ በፔንታጎንም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያ ዘግናኝ ጥቃት ሲፈጽም የወቅቱ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ዋሽንግተን በሚገኝ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአንዱ ክፍል ተገኝተው ለተማሪዎች መጽሐፍ እያነበቡ እያለ ከደህንነት ሰዎቻቸው አንዱ የሽብር ጥቃት እየተፈጸመ እንደሆነ ሹክ ይላቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ምንም እንዳልተፈጠረ ለልጆቹ የጀመሩላቸውን ንባብ ጨርሰው ተሰናብተው ይወጣሉ። መሪ እንዲህ ስሜቱን ተቆጣጥሮና ዋጥ አድርጎ አገሩን ወደ ዘላቂ መፍትሔ የሚወስድ፤ ደንብሮ ሕዝቡን የማያስደነብር፣ ተሸብሮ ሕዝብን የማያሸብር፣ ተንበርክኮ ሕዝቡን የማያንበረክክ መሆን አለበት የሚባለው ለዚህ ነው። ሌላ አብነት ላክል።
ማዲባ (ኔልሰን ማንዴላ) በረራ ላይ እያሉ ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ነገር ይፈጠራል። ይጓዙበት የነበረ አውሮፕላን አንደኛው ሞተር ይጠፋል። አብራሪዎች፣ አብረዋቸው የነበሩ ባለስልጣናትና አጃቢዎቻቸው ይይዙት ይጨብጡት ይጠፋባቸዋል። ማዲባ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ የጀመሩትን መጽሐፍ ተረጋግተው ያነባሉ። በዚህ ሁሉ ጭንቅና ጥብ የማዲባ ፍጹም መረጋጋትና አለመረበሽ ከማስገረም አልፎ ግራ አጋብቷቸዋል።
አብራሪዎች የካበተ ልምድ ያላቸው ነበሩና ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ አውሮፕላኑን እንደምንም በአንድ ሞተር በሰላም ማሳረፍ ይችላሉ። በዚህም አብራሪዎች፣ ተሳፋሪዎች፣ የበረራ አስተናጋጆች ደስታዎችን በጭብጨባ፣ በሆታና በፉጨት ይገልጻሉ። አሁን ግን ማዲባ የደስታቸው ተካፋይ ሆኑ። ይህን የታዘቡ ጓዶቻቸው ታዲያ እንደዛ ስንጨነቅ ምን እንዳልተፈጠረ የሆንኸው ለምንድን ነው ሲሉ ይጠይቋቸዋል። ከሁላችሁም በላይ የደነግጥሁና የፈራሁት እኔ ነበርሁ። ነገር ግን እናንተን ይበልጥ ማስጨነቅ ስላልፈልጉህ ፍርሀቴን ዋጥ አድርጌ ምንም እንዳልተፈጠረ አስመሰልሁ።
የአሜሪካ ታዋቂ የፕሬዚዳንቶች ታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ/presidential Historian/ዶሪስ ኬርነስን “Leadership in Turbulent Times the Lessons of Presidents”በተሰኘ ግሩም ድንቅ መጽሐፏ በዚህ አጋጣሚ ያላነበባችሁት አፈላልጋችሁ እንድታነቡት እጋብዛለሁ ፤ አብርሀም ሊንከን ፣ ቴዎዶር ሩዝቬልት ፣ ፍራንክሊን ሩዝቬልትና ሊንደን ጆንሰን በግል ህይወታቸውም ሆነ በፕሬዚዳንትነታቸው የገጠሟቸውን ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ፈተናዎች እንዴት በጽናትና በጥበብ አልፈው ለውጤት እንደበቁ ታስረዳለች። ለዚህ ነው ዶሪስ ከአንድ መሪ ስለሚጠበቁ ባህሪያት ስታወሳ ሁል ጊዜ “ለፈተናዎች አለመበገር” የሚለውን ቀድማ የምታወሳ። “ኢትዮጵያን እናልብሳት!”ብዬ ጀምሬ ስጠፋ “ ኸረ ወደ ገደለው !?”አትሉኝም፤
አገራችን በታሪኳ ከፈጸመቻቸው እየፈጸመቻቸው ካሉ ግዙፋን ፕሮጀክቶች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ አንድ ላይ ቢደመሩ የ” አረንጓዴ አሻራ “ን ያህል ክብደት አልሰጣቸውም፡፡ የህዳሴውም ሆነ የሌሎች ታላላቅ ግድቦች ህልውና እንዲሁ 80 በመቶ አገሬው ኑሮ የተመሰረተበት ግብርና እጣ ፈንታ የሚወሰነው ዛሬ በትጋት በምንከውነው የአካባቢ ወይም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ነውና፡፡ በቀደሙት ሶስት አመታት ከ18 ቢሊዮን በላይ አገር በቀል ችግኞችን ለዛውም ከሞላ ጎደል ስነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረጉ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች መትከል ተችሏል፡፡ ከተተከሉ ችግኞች መካከል እንደ አቡካዶ፣ ማንጎ፣ አፕል፣ ፓፓየ፣ ሙዝ እንዲሁም ቡና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በአራቱም ዙር ከ90 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በችግኝ ተከላው ተሳትፏል።
ችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የአለም ሙቀት መጨመርንና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንም ሆነ ድህነትን፣ የምግብ ዋስትና ጉድለትን፣ የምርታማነት ተግዳሮትን፣ ድርቅን፣ ርሀብን፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት፣ የውሀ እጥረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተትት፣ ስራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን፣ የጸጥታና የደህንነት ችግርን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡ ለዚህ ነው ችግኝ ተከላን የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ማስተር ኪይ ነው የምለው፡፡
በየአመቱ በአገራችን ከ92ሽህ ሔክታር መሬት በላይ ደን ይመነጠራል። ይጨፈጨፋል። በዚህ የተነሳ የደን ሽፋናችን ከ50 አመታት በፊት ከ35 በመቶ ከነበረበት ደረጃ ወደ ሶስት በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር። ለዝናብ እጥረት፣ ለድርቅና ለከባቢ አየር ለውጥ ተዳረግን። በየአመቱ ምርታችን ከ10 በመቶ በላይ መቀነስ ጀመረ። በየአመቱ ከ35 እስከ 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይቀንሳል። ሆኖም ባለፉት ሶስት አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት በተከናወኑ የችግኝ ተከላና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የደን ሸፋኑን ወደ 17 በመቶ ማገገሙ ይበል የሚያሰኝ ነው።
እንደ መውጫ
የበጋ ስንዴ፣ የኩታ ገጠም ግብርናን፣ በተወሰነ ደረጃ ስነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂና የሜካናይዜሽን እገዛ፣ የከርሰና የገጸ ውሃን አሟጦ የመጠቀም፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመስራት፣ በተለይ ከአለፈው አመት ጀምሮ የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ግብ መጣሉ የአተያይ ለውጥ በማምጣቱ ተስፋ ያስቆረጠን ግን ደግሞ ብቸኛ ሊባል በሚችለው ግብርና ከምግብ ዋስትና ባሻገር ተስፋችንን እንድናድስ አድርጎናል፡፡ ለዚህ ነው ተስፋ ሰጭ ጅምር እውቅና መስጠት የሚያስፈልገው፡፡
ችግሮቻችንን ሁሉ ፈታተን፣ በታትነንና አገላብጠን ብንመረምራቸው አብዛኛዎቹ ከአንድ ቅርጫት የሚገኙ ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ካለመንከባከብ፣ ካለመጠበቅና ካለማልማት ቅርጫት፡፡ የአለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የተፈጥሮ ሀብታችን እየተጎሳቆለ በመምጣቱ ማለትም መሬታችን የተራቆተ፣ ዝናባችን የአጠረና የተቆራረጠ በመሆኑ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃችን በመመናመኑ ግብርናው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡
በዚህ የተነሳ በግብርና ላይ የተመሰረተው የዜጋው ህይወት፤ የአገሪቱ ልማት ችግር ላይ ወድቋል፡፡ ይህ የሀብት ውስንነትን ፈጥሯል፡፡ በዚህ የተነሳ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከአመት አመት እየተባባሱ መጡ፡፡ እነዚህን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችን እንዲያገግም ሌት ተቀን መሰራት አለበት፡፡ መሬት ማገገም፣ ውሃ መያዝ አለባት፡፡ ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ችግኝ በመትከልና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስፋት በማከናወን ነው፡፡
“ አረንጓዴ አሻራ “ የበሽታውን ምልክት ከማከም ይልቅ መነሻውን በማያዳግም ሁኔታ የመፈወስ አቅም እንዳለው በማመን ነው፤” አረንጓዴ አሻራ ! “ የእንቆቅልሾቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ (ማስተር ኪይ) የምለው፡፡
ከኢትዮጵያ አምላክ ጋር መጭው ዘመን ጥሩ ይሆናል !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2014