ፈረንሳዊው የሒሳብ ሊቅ፣ የፊዚክስ ሊቅ፣ የፈጠራ ባለሙያ፣ ጸሐፊ፣ የሃይማኖት ምሁርና ፈላስፋ ብሌዝ ፓስካል፣‹‹ሰው የተፈጠረው ለማሰብ ነው “ይለናል:: እርግጥ ነው ሰው ማሰብ እንጂ አለማሰብን አይችልም:: አለማሰብ ራሱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ማሰብ ይኖርበታል::
ሰው በህይወት እስካለ ማሰቡን አያቆምም። የሚያስበውን ግን ሊመርጥ ይችላል:: አስተሳሰቡም በተግባርና በምግባሩ ይታያል:: ሲያስብ የተሳሳተ ምግባሩም ሆነ ተግባሩ የተሳሳተ መሆኑም እርግጥ ነው:: ታዋቂው የሥነ ልቦና ባለሙያ ዶክተር ካርል ጁንግ ‹‹Thinking is difficult. That is why most people judge›› ማሰብ አስቸጋሪ ወይም ከባድ ነው:: ብዙ ሰዎች የሚፈርዱት ለዚህ ነው›› ይላል::
እርግጥም ማሰብ የሚከብዳቸው ሰዎች ሰፊውን አለም በጭላንጭል እይታ የሚመለከቱና ቀላሉን የሚመርጡ ናቸው:: የእኔ የሚሉት ሃሳብ የሌላቸው በመሆኑ ከአመክንዮ ጋር ይጋጫሉ:: ምን፣ ለምን፣ እንዴት ? ብለው አይጠይቁም:: እንደጋሪ ፈረስ በማንም ይሾፈራሉ:: ሌሎች ሲፎክሩ ይፎክራሉ:: ጃስ ሲላቸው ይናከሳሉ:: እንያዝ ሲላቸው ያሯሩጣሉ:: በስሜታዊነት ፈረስ በመጋለብ ለጠብ እጃቸውን ለመሰብሰብ እንጂ አንድ ጊዜ እንኳን ለማሰብ ጊዜ የላቸው:: አድርጉ የተባሉ ሁሉ ለማድረግም አያቅማሙም::
በእርግጥ ሁሉም ሰው በራሱ ሃሳብ ትክክል ነው:: ይሑንና አንዳንዶች የእኛ ብቻ ልክ ነው ብለው ስለሚያስብ የሌሎችን ሃሳብ ለመስማትም ሆነ ለማክበር ቦታ የላቸውም:: የሌሎችን ሃሳብም ቢሆን አይመዝኑም:: አይመረምሩም:: ፈትነው አያጣሩም::
በትንሹ ተረድተው በትልቁ ይፈርዳሉ:: ቀድሞ ባወቁት ወይም በተነገራቸው ይደመድማሉ:: ልክነትና ልክነታቸውን ብቻ ያውጃሉ:: ነገር ግን ሃሳብና ምግባራቸው አደባባይ ሲወጣና በሌሎች መመዘን ሲጀምር ትክክለኝነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል::
የልክነት ትርጉሙና ፍቺው በአንድም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲታሰብ ደግሞ ማሰብ ብቻም ሳይሆን በምክንያት መሳብም ተያይዞ ይመጣል:: ምክንያታዊነት ደግሞ በተንኮል ያልታጠፈ፣ በምቀኝነት ያልተቆለመመ፣ በራስወዳድነት ያልተንጋደደ ሃሳብና ምግባር ነው::
ምክንያታዊነት፣ አመዛዛኝነት፣ አስተዋይነት ነገሮችን አንድ በአንድ በጥልቀት በማየትና በመመርመር እውን የሚሆን ነው:: ይሕ እንደመሆኑም ምክንያታዊ አስተሳሰብ መያዝ ከባድ ነው:: ይህ በመሆኑም ብዙዎች ምክንያት አልባነትን ይመርጣሉ::
እነዚህ ሰዎችም በምክንያት ለማሰብ ስላልተዘጋጁ ግብረ መልስ ለመስጠት ደመነፍሳቸውን ይጠቀማሉ:: ስሜታቸውን ያስቀድማሉ:: እነሱ ያሰቡት ብቻ ትክክል ይመስላቸዋል:: ጉዳዩን በሌላ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ሆነው አይመለከቱትም:: እውነታውን ሳይሆን በእነርሱ የታሰበውን ብቻ የመጨረሻ ልክ አድርጎ ይወስዳሉ::
ምክንያታዊ ባልሆነ አስተሳሰብም ያልተጨበጡና በወጉ ያልተጠኑ ትችቶችን እንደጉድ ያወርዳሉ:: ስለተመለከቱትም ሆነ ስላደመጡት እንዲሁም ስላነበቡት ምንነቱን በቅጡ አይረዱም:: ብቻ በሩቁና በጭፍን ይደመድማሉ:: ታርጋ እየለጠፉ ጎራ ያበጃሉ:: ያለምክንያት ይዘልፋሉ:: ይፈርጃሉ:: ጎራ ፈጥረው ጣት ይቀስራሉ:: እኛና እነሱ የሚል ክፍፍል ይሰራሉ:: እርግማን ያወርዳሉ::
እኔ የኢትዮጵያ አሁናዊ አደጋ “Present danger ” ለሁሉም ነገር ምክንያት አልባ ድምዳሜና ግብረ መልስ መስጠት ነው የሚል አቋም ይዛለሁ:: በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ባልጠራ መረጃ ሃሳቡን ሳያጣሩ የሚደመድሙ፣ አንድ ጥግ ቆመው ሌላውን ጥግ የሚያወግዙ በዝቷል::
የሌላውን ሃሳብ ለመረዳት የተዘጉና የተገዘቱት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: ቀድመው የሰሙትን አምነው የተቀበሉና በእሱ ብቻ የሚኖሩ አዲስ ሃሳብ ለመስማት ዝግጁነት የሌላቸው፤ በጠባቡ የሃሳባቸው ዋሻ መሽገውና የሕሊናቸውን በር ዘግተው የተቀመጡ በርካቶች ናቸው::
አሁን ላይ ምክንያታዊነት፣ ሚዛናዊነት፣ አስተዋይነት ገና ያልደረስንበት የሕይወት ጥጋችን ሆናል:: ምክንያታዊ አለመሆን በርካቶች የሚቸኩሉበት ችሎታቸው እየሆነም መጥታል:: ምክንያታዊነት ጠፍቶ ስሜታዊነት ጎልቶ ወጥታል:: በምክንያት አስቦ በምክንያት የሚናገር አንሷል:: ጭፍን ድምዳሜና ችኩል አጠቃሎ ውጦናል:: ድክመትን ብቻ ለመግለፅ፣ የተካነ ትውልድ፤ በአቃቂር ጫፍ የደረሰ ህዝብ በዝቷል::
አሁን አሁን መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱና ካልተናገሩ የሌሉ የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው። ስም ጠርቶ ማውገዝ የለም። እስቲ ጥሩት ሲባሉም የሚጠሩት አሁን የለም። እንዴት እንዲህ ይሆናል ሲሉ እንዴት እንዲህ አይሆንም ለሚለው ቦታ የላቸውም:: ሃሳብ፣ ተግባርን ህልማቸው ቡድናዊ፣ በደንብ ሲጠና ደግሞ ግላዊ ነው።
እንደታዘብኩት ከሆነ ምክንያት አልባዎች የሰቀሉትን አውርደን ለመፈጥፈጥ ይቸኩላሉ:: ሲያወርዱም ይጣደፋሉ:: ደካማ ነገር ማጉላት፣ ድክመቱን ማውጣት፣ ክፍተቱን ፈልጎ ማግኘት ይቀናቸዋል:: ይሑንና ጥቅም ጉዳቱን ፈልቅቆ ለማግኘት አቅምም፣ ዝንባሌም ሆነ ፍላጎቱ ያጥራቸዋል:: የኢትዮጵያ አሁናዊ አደጋ “Present danger” ይሕ ነው::
ፉከራቸው ከዕውቀታቸው ጋር ያልተዋሀደ ነው:: ስለሚያወግዙት ግማሽ መንገድ ተራምደው አይጠይቁም:: ማጣጣል እንጂ ማድነቅ ምርጫቸው አይደለም:: ምክንያት አልባነት ሰለባ ተጠቂዎች እንዲህ ብናደርግ ሲባሉ ቢያንስ ሞክረው ውጤቱን ለመመልከት አዋጭ ከሆነ መቀጠል ካልሆነም ለማቋረጥ ዝግጁና ተባባሪነት አይታይባቸውም:: ይልቁንም ሳይጀምሩ ይጨርሳሉ:: የኢትዮጵያ አሁናዊ አደጋ “Present danger” ይሕ ነው::
ይሁንና እኛ ያልነው ብቻ ልክ ነው ሌሎችን አትስሙ በሚል ትችት ብቻ ማዝነብ፣ ከግዙፉ ነጭ ይልቀቅ ነጥቡን ጥቁር በማጉላት የአገርን የብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ የድንጋይን ሚና መያዝ ተገቢ አይደለም:: እንዲህ ብንደረግስ፣ እንዲህ ሊደረግ ታስቧል እንዲህ ተደረገ በተባሉ ቁጥር ለድምዳሜ መቸኮል የጤነኝነት አይደለም::
መሰል ምክንያት አልባነት አልጫ ነው:: ጣዕም የለውም:: ይሠለቻል:: ኢ- ምክንያታዊ መሆን ነፍስ የለውም:: ምንም አይለውጥም:: አይቀይርም:: አያዘምንም:: አያሰለጥንም:: ለማወቅ ለመመርመር፣ ለመሰልጠን አዳዲስ መንገዶችን ለመፈተሽ ዕድል አይሰጥም:: ጭፍን ድምዳሜ ማንንም አያስተምርም:: አዕምሮ ላይ የሚጨምረው አንዳች ነገር የለውም:: በየትኛውም ጥግ ብንሆን የምንተቸውን ልናውቅ ይገባል::
ምክንያታዊ አለመሆን ሰዎቹ ያሳዩትን መንገድ ብቻ የሙጥኝ ብሎ ከራሱ የሕይወት ጎዳና ጋር ይጠፋፋል:: አንድ ጥግ እንዲቆም የተደረገ አዕምሮ አማራጭ መንገድ የለውም:: በለመደው ጥግ እንደቆመ ጊዜ ያልፍበታል፤ እድሜውም ይባክናል::
አሁን ላይ ኢትዮጵያችን ካሰበችው እንድትደርስ እንደ ጎልያድ መንገድ የሚዘጉና ዘወር ለማድረግ እደ ህዝብ ልናክማቸው የሚገቡና ብዙ ህመሞች አሉብን:: ካሟላነው ይልቅ ያጎደልነው እልፍ ነው:: እንደሐገር ከሰራነው ይልቅ ያልሰራነው ይልቃል::
ይህን ለታሪክ ለመቀየር መተጋገዝ፣ መደናነቅ መተቸቸት ተገቢ ነው:: ይሑንና በዚህ ሂደት ከእያንዳንዱ አስተሳሰብና ተግባራችን ጀርባ ምክንያት መሆንና ምክንያታዊነትን ማስቀደም ግድ ይኖርብናል:: ከሁሉ በላይ የምክንያታዊነት ቁመታችንን ልንሰርዝም ይገባል::
በምክንያት ማሰብ፣ ከድምዳሜ መውጣት የግድ ይለናል:: በምክንያት መውደድና መጥላት፣ መንቀፍና መደገፍ መልመድ ይገባናል:: ጨዋውን ከባለጌ፣ ታማኙን ከከሃዲው፣ አጭበርባሪውን ከሃቀኛው፣ ሙሰኛውን ከደህናው መለየት ይኖርብናል::
ኢትዮጵያችን በአሁን ወቅት ከሚያፈርስ ይልቅ የሚያድስ፣ የመከፋፈል ፋሽን ተቀብሎ የመለያየትን ባንዲራን የማያውለበልብ ትውልድ ትሻለች:: ቀዳዳዋን ከመስፋት ይልቅ የሚያጠብላት ትውልድን ትባጃለች:: የሚያፈርስ ሳይሆን የሚገነባት፣ ጥላቻን፣ መሃይምነትን፣ ቂም በቀልን እንትፍ የሚል በጎ ምግባርንና መልካም ስራን እፍ ብሎ የሚያቀጣጥል ትውልድ ትሻለች:: አሁናዊ አደጋዋን እናስወግድላት:: በጎሰኝነት አስተሳሰብ፣ በመጥበብ ፖለቲካ አናሳዝናት::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2014