ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ (ፈረሰኞቹ) የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ዋንጫን ትናንት ረፋድ ላይ በባህርዳር ስቴድየም በማንሳት ለ15ኛ ጊዜ በሊጉ መንገስ ችለዋል። በአንድ ነጥብ ልዩነት ከተፎካካሪያቸው ፋሲል ከነማ (አጼዎቹ) ጋር እስከ መጨረሻው የሊጉ መርሃ ግብር ጨዋታ ድረስ ልብ የሚሰቅል ፉክክር ያደረጉት ፈሰረኞቹ በመጨረሻም አጓጊውን ጉዞ በድል ደምድመዋል።
በ30ኛው ሳምንት መርሃግብር ቻምፒዮኑን ለመለየት በተደረጉት ወሳኝ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ ላለመውረድ እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገው አዲስ አበባ ከተማን በኢስማኤል ኦሮ አጎሮና አማኑኤል ገብረሚካኤል ሁለት ሁለት ግቦች 4ለ0 በመርታት የአጼዎቹን ውጤት ሳይጠብቁ ዋንጫውን አንስተዋል። በተመሳሳይ ሰአት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም ላለመውረድ የሚታገለውን ድሬዳዋ ከተማን የገጠሙት አጼዎቹ ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ አግኝተው ቻምፒዮን ለመሆን የፈረሰኞቹን ሽንፈት መጠበቅ ነበረባቸው።
ይሁንና ፈረሰኞቹ የራሳቸውን እድል በራሳቸው የወሰኑበትን ውጤት ሲያስመዘግቡ አጼዎቹ በአንጻሩ ሁለት ለዜሮ መምራት ቢችሉም ድሬዳዋ ከተማ ውጤቱን ገልብጦ 3ለ2 በመርታት ከመውረድ የተረፈበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። አዲስ አበባ ከተማም ጅማ አባጅፋርና ሰበታ ከተማን ተከትሎ ሶስተኛው ወራጅ ክለብ ሆኗል። በተመሳሳይ ሰአት ላለመውረድ ከሐዋሳ ከተማ ጋር አጓጊ ፍልሚያ ያደረገው አዳማ ከተማ 3ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን አሸንፎ በመጨረሻ ሰአት ከመውረድ ተርፏል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ተስተካካይ የሌለው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አንጋፋ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ እግር ኳስ ስኬታማ መሆኑ ሁሉንም ያስማማል። ፈረሰኞቹ በርካታ የፕሪሚየርሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ዓመታት ቻምፒዮን በመሆን ይታወቃሉ። በአንድ ውድድር ዓመት የፕሪሚየርሊጉን ዋንጫ ማንሳት ባይሳካላቸው በሌላው የውድድር ዓመት ወደ ቻምፒዮንነት የመመለስ ባህልም አላቸው።
በተለይም ፈረሰኞቹ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ከ1990 ዓ.ም አንስቶ እንደ አዲስ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ተከታታይ የቻምፒዮንነት ድሎችን ማሳካት የቻሉ ሲሆን የፕሪሚየርሊጉን ዋንጫ ከሁለት ዓመት በበለጠ ጊዜ ሳያነሱ የቀሩበት አጋጣሚ የለም። ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት የውድድር ዓመታት ፈረሰኞቹ ከፕሪሚየርሊጉ ቻምፒዮንነት ባልተለመደ መልኩ ርቀው ቆይተዋል። በነዚህ ዓመታት የተለያዩ የውጪ አሰልጣኞችን ቀጥረውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ከመጡት የክልል ክለቦች የፕሪሚየርሊጉን ዋንጫ መንጠቅ አልቻሉም።
የዘንድሮው የውድድር ዓመት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ከመጀመሩ በፊት ፈረሰኞቹን ለመምራት የመጡት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲችም ከቡድኑ ጋር ብዙ ርቀት መጓዝ ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ የውድድር ዓመቱን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ፈረሰኞቹን እየመሩ ትናንት አስራ አምስተኛውን ዋንጫ ከአራት አመት በኋላ ማሳካት ችለዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ ለመጀመርያ ጊዜ ሲካሄድ መካፈል አልቻለም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የብሄራዊ ሊግ ተወዳዳሪ ነበርና። በቀጣይ ዓመት ግን ሊጉን ሲቀላቀል ቻምፒዮን ሆነ። በቀጣዩ ዓመትም ደገመ። በ 1993 መብራት ኃይል ቻምፒዮን በመሆኑ ለሶሰተኛ ጊዜ ዋንጫ ለመውሰድ የነበረው ህልም ሳይሳካ ቀረ። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም በ 1994ና 1995 በተከታታይ የዋንጫ ባለቤት ሆነ። ሀዋሳ ከነማ የ1996 ቻምፒዮን መሆኑ አሁንም ሀትሪክ የመስራት ህልሙ እንዲጨናገፍ አደረገው።
1997ና 1998 ለሶስተኛ ጊዜ የተከታታይ ድል ባለቤት ሆነ። 1999 በክለቦችና በፌደሬሽኑ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ዋነኛ ተዋናይ የነበረው ጊዮርጊስ ራሳቸውን ከውደድሩ ካገለሉ ክለቦች አንዱ በመሆኑ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ቻምፒዮን የመሆን አላማው ለሶስተኛ ጊዜ ተጨናገፈ። በ 2000፤ 2001ና 2002 ዋንጫውን በማንሳቱ ግን በስተመጨረሻው አላማውን እንዲያሳካ አስችሎታል። ክለቡ እስከ 2002 ከተዘጋጁት 13 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች ውስጥ ዘጠኙን በመውሰድም ፍፁም የበላይነቱን አሳይቷል::
በዘንድሮው የውድድር አመት ከመጀመሪያ አንስቶ የደረጃ ሰንጠረዡን ከሌሎች ክለቦች ከአስር በበለጠ የነጥብ ልዩነት መምራት የቻሉት ፈረሰኞቹ አንድ ጊዜ ብቻ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በተለይም የሊጉ የመጨረሻ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎች ከአዳማ ወደ ባህርዳር ከሄዱ በኋላ በአጼዎቹ የደረሰባቸውን ሽንፈት ጨምሮ በተደጋጋሚ ያልተጠበቁ ነጥቦችን የጣሉት ፈረሰኞቹ በጊዜ ቻምፒዮን መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበት እድል ከእጃቸው መውጣቱ የውድድር አመቱን መገባደጃ ከተገማችነት ወደ አጓጊነት ለውጦታል። ይህም የውድድር አመቱን እንደ ጣፈጠ እንዲፈጸም ያደረገ ሲሆን በፈረሰኞቹና በአጼዎቹ መካከል የነበረው የአንድ ነጥብ ልዩነት በምን መልኩ እንደሚደመደም የመጨረሻውን ጨዋታ ብዙዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ ማድረግ ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014