ሀገር በታሪክ በአንዱ ወቅት ችግር ውስጥ ትገባለች። ችግሩ ከቆመችበት የታሪክ ምእራፍ ሊያራምዳት፤ ወደ ኋላ ሊመልሳት ወይም በቆመችበት ሊያስቀራት ይችላል። ትልቁና ዋንኛው ጉዳይ ግን በችግር የማለፉዋ እውነታ ነው ። ይህንን እውነታ ያላለፈ ሀገርና ህዝብ የለም። ጥያቄ የሚሆነው ግን ይህንን ወቅት እንዴት እንለፍ የሚለው ነው ።
የቅርቡን የአለም ታሪክ እንኳን በወፍ በረር ለመቃኘት ብንሞክር የአለም ህዝቦች በታሪካቸው ያስተናገዷቸውን የአለም አንደኛና ሁለተኛ ጦርነቶችን ጨምሮ ብዙ ጦርነቶች ፤ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስተናግደዋል። ችግሮቹን ለመከላከል ሆነ ከተከሰቱም በኋላ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ለመቀነስ አለም ብዙ ዋጋ ከፍሏል።
ለምሳሌ ሁለቱን የአለም ጦርነቶች ጥፋትና ውድመት ለመከላከል ሀገራት አለም አቀፍ ህብረት ፈጥረው ተንቀሳቅሰዋል ። የሀገራቱ ህልውና ተባብሮ በመንቀሳቀስ ላይ መሰረት ያደረገ ስለነበር ጉዳዩን በአግባቡ ተረድተው ፈጥነው በመንቀሳቀስ የተደቀነባቸውን የህልውና አደጋ መሻገር ችለዋል፤ በዚህም አስከ ዛሬ ህልውናቸውን አስጠብቀው ለመቆየት በቅተዋል ።
ዛሬም ቢሆን ሀገራዊ ጥቅምና የጋራ ህልውናን መሰረት ያደረጉ አካባቢያዊና አለም አቀፍ ህብረቶች አሏቸው ። ባለንበት ዘመንም አለም በአስቸጋሪ ወቅት ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህል አዳብሯል ።ይህም በችግር ወቅት በተናጠል የሚከፈለውን ዋጋ የሚቀንሰው ከመሆኑም በላይ አቅም አስተባብሮ በችግር ላይ ለመሰልጠንና ዋነኛ አቅም መፍጠሪያም ነው።
ይህ ዘመን እያስቆጠረ ያለ አለም አቀፋዊ እውነታ በኛ ሀገር መሰረት ሊይዝ ቀርቶ አስፈላጊነቱ ላይ እንኳን የጋራ መግባባት የተደረሰበት አይመስልም ። በተለይም ፊደል ቀመስ በሆነው ጥራዝ ነጠቅ የህብረተሰባችን ክፍል /ምሁር/ ውስጥ ያለው እውነታ ለወሬ የሚመች አይደለም ።ይህ የህብረተሰብ ክፍል አብሮ መስራትን እንደ ድክመትና ትንሽነት አልፎም እንደ ተሸናፊነት በሚያይ የአስተሳሰብ በሽታ የተለከፈ ነው። ሞክሮም የተሳካለት የጎላ ታሪክ የለውም ።
በችግር ወቅት አቅምን አስተባብሮ በጋራ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ለችግሮች ብቸኛ መፍትሄ ሆኖ መቅረብ ፤ አማራጭ መፍትሄዎችን ማጥላላት ፤ ከዛም አልፎ አስተሳሰብን መሰረት ያደረጉ ጠላትነቶችን መፈልፈልና ታቅፎ ማሳደግ ተምረናል ለሚሉት ዋነኛ የባህሪ መገለጫዎች ናቸው ። በዚህም ከግማሽ ምእተ አመት በላይ ተጉዟል ።
በአግባቡ ባላዳመጠውና ትኩረት ሰጥቶ ባላየው ነገር ዙሪያ ፈጥኖ አቃቂር ማውጣት ፤የአቅሙን ያህል ከመስራት ይልቅ ከአቅሙ በላይ ማውራትን ፤ ባልጠሩ አስተሳሰቦች ሌሎችን መፈረጅና በጠላትነት ማየት የተለመዱ ናቸው ።
በዚህ ባህሪው የ 1960 አ.ም የለውጥ ንቅናቄ ይዞት ከመጣው ተስፋ ይልቅ ፤ ያልታሰበ ቅዥት ፤ይዞት ከመጣው አዲስ የታሪክ ምእራፍ ፤የአሮጌ ቅዳጅ ገጾች ስብስብ ፤ከአዲስ የዝማሬ ዜማ ይልቅ ፤የገለማ አሮጌ የአዝማሪ ዜማ ሆኖ እንዲቀር አድርገውታል ።
ለዚህ በእንጭጩ ካለመደማመጥና ሀገርን በህብረት ለማሻገር ፈቃደኝነት ከማጣት በተፈጠረ እልኸኝነት ለጨነገፈው ለውጥ ህዝባችን የከፈለው ዋጋ የቱን ያህል መራራ እንደሆነ እኛ ቀርተን አለም የሚያውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው ።
ገና ከፊውዳል የአስተሳሰብ መሰረት ያልተላቀቀው የወቅቱ ምሁር የለውጡን አደባባይ የአቅም መፈታተኛና የመጠላለፊያ መድረክ በማድረግ ፤ለውጡ በየትኛውም መልኩ ባልተዘጋጀ አካል እጅ ገብቶ እንዲመክን ምክንያት ሆኗል።
የእውቀት ማህበራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ትርጉም ሊኖረው የሚችለውም ከማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ጋር ተሳስሮ ሲተገበር ፤ ውጤታማነቱም የሚሰላው በዚሁ እውነታ እንደሆነ ይታመናል ።
ትውልዱ /የወቅቱ ምሁር / እውቀት እንደ ልብስ ፋሽን ሄደህ ከእውቀት ገበያ የምትገዛውና አደባባይ ወጥተህ የምትንጎማለልበት ሸቀጥ ሳይሆን ማህበረሰብን እንደ ማህበረሰብ ከአንድ የታሪክ ምእራፍ ወደ ሌላ የታሪክ ምእራፍ የማሸጋገሪያ አቅም መሆኑን ለማስተዋል ጊዜ አጥቶ አደባባዮችን በዲስኩር ሞልቶ፤ በትውልዱ ውስጥ የዲስኩር ዘር ዘርቶ አልፏል ።
ከመደማመጥ ይልቅ ያለኔ በሚል እልኸኝነት ፤ተባብሮ ለአንድ አላማ ከመቆም ይልቅ በልዩነት ሰልፍ በጠላትነት ማነሳሳትን ፤ስለሀገር ህዝብን አንድ ቋንቋ ከማናገር ይልቅ ፈቅዶና ወዶ በባቢሎን ድብልቅልቆሽ ግራ መጋባትን በመምረጥ ፤እስከ ዛሬም ትውልዱ የዘሩት ዘር ፍሬ አጫጅ ለመሆን በተገደደበት ሀገራዊ እውነታ ውስጥ ለመኖር ተገደናል።
ከሁሉም የሚያሳዝነው የትናንቱ ሳይሆን የዛሬውም ትውልድ ሀገር እንደ ሀገር በችግር ወቅት በሆነችበት በዚህ ወቅት በጥራዝ ነጠቅ እውቀት ጦዞ ስለሀገሩ በአንድነት የሚቆምበትን አቅም እያጣ መምጣቱ ነው ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለ ሀገር አንድ ሆኖ መቆምን እንደ አንድ የፖለቲካ ህጸጽ አድርጎ የማየቱ እውነታ ነው።
ለዚህ ደግሞ እንትና የተባለ ፓርቲ እንትና ከተባለ ፓርቲ ጋር አብሮ መስራቱ ተገቢ አይደለም ፤ይህ ክህደት ነው ፤ይህ ለሕዝብ የገባነውን ቃል የሚያፈርስ ነው… ወዘተ በሚሉ ዲስኩሮች በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታው ተስፋ የተጣለባቸው ፓርቲዎች ሳይቀር ችግር ውስጥ ገብተው መታየታቸው ነው።
እንደኛ ላሉ በብዙ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ፤ገና ፊውዳላዊ ከሆነ የአስተሳሰብ መሰረት ላልተላቀቁ ሕዝቦችና ከነዚህ ህዝቦች ለሚፈልቁ ፖለቲከኞች ለሀገራዊ ተልእኮ ውጤታማነት ለሀገርና ለህዝብ አብሮ መስራት ከፍ ያለ ጥቅም እንደሚኖረው መገመት የሚከብድ አይደለም
አብሮ የመስራቱ ጉዳይ ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን በጋራ ከማስፋት ጀምሮ ፤መደማመጥን ፣መማማርንና መከባበርን ከመፍጠሩም በተጨማሪ ፤መላው ሕዝብ በሀገራዊ ፖለቲካ ላይ የተሻለ መተማመን እንዲኖረው ፤ከዚህም በመነሳት ተሳትፎውን በማሳደግ ሀገረ መንግስቱ አስተማማኝ በሆነ ሕዝባዊ መሰረት ላይ እንዲዋቀር እድል የሚሰጥ ነው ።
የሀገራችን ምሁራን ከትናንት ዋጋ ካስከፈለን ስህተታቸው ተምረው በመደማመጥ ከዚያም በላይ የወቅቱ ፋሽን ከሆነው ከግዚያዊ ጥቅምና የማይዘልቅ ተወዳጅነት ከዛም በላይ ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች ራሳቸውን በመጠበቅ ከታሪክ ተወቃሽነት ራሳቸውን ሊያተርፉ ፤ የሀገር ግንባታው አንድ አካል በመሆን በቅንነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
የሚናገሩትም የሚሰሩትም ነገር ሁሉ የሀገርን ጥቅም ለማስከበርና የኖረውን የአብሮነት እሴት የሚያስቀጥል መሆን አለበት። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀደም ባለው ዘመን ሆነ አሁንም ከምሁራኑ ያተረፈው ነገር ቢኖር አንድም ለውጥ በመጣ ቁጥር እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ የሚል ዲስኩር ፤ ሁለትም ሀገርና ህዝብ ችግር ውስጥ ከተዘፈቁ በኋላ በሚዲያና በመጽሀፍ ድሮም እኛ ብለን ነበር የሚል ተረት ተረት ብቻ ነው።
የዚህኛውም ዘመን ምሁራን ከፊሎቹ የቀደመው የስህተት ጉዞ አካል የነበሩ ፤ አዳዲሶቹም ቢሆኑ ዘመኑ ያፈራውን ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቅሞ ስሜትን ከማራገብ የዘለለ ተግባር ሲከውኑ አይታዩም።ይህ ደግሞ እንደ ሀገር በእንቅት ላይ ጆሮ ደግፍ ከሆነብን ውሎ አድሯል ።
በርግጥ የሀሳብ ልዩነት አይኑር አይባልም እንኳን በተማረ ፊደል በቆጠረ ስለ ሀገር በሚመክር ስብስብ ውስጥ ይቅርና በአንድ የመንደር እድር ውስጥም የአመለካከት ልዩነት ይፈጠራል። ልዩነቱ የትኛውም እድርተኛ በትንሽ ጥሪት ያቋቋመውን እድር ለሱ ፍላጎትና ጥቅም አሳልፎ ሲሰጥ አለመታየቱ ፤ ምሁሩ ግን በሀገርና በህዝብ ህልውና ላይ ያለ ይሉኝታ በአደባባይ ለመደራደር ፈቃደኝነት ማሳየቱ ነው።
ይህ ደግሞ አስተምሮ ለወግ ለማረግ አደረስኩ የሚለውን ህዝባችን ተስፈ የሚያስቆርጥ ፤በዘመናት በኛና በተስፋችን ላይ ለሚያደቡት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሀገራችንን እንዲያፈርሱና ሀገር አልባ እንዲያደርጉን የተመቻቸ እድል መፍጠር ነው ።
ለጊዜው ሁሉም ይቅርና ሀገር በችግር ወስጥ ስላለች ልዩነቶቻችንንና ልዩነት የማስዋብ እና የማስፋት ትርክቶቻችንን አቁመን በአንድነት እንንቀሳቀስ ።ይህ የዛሬ ተሞክሯችን ነገ ያደገ ፍሬ የሚያፈራበትን እድል ስለሚፈጥር እንፍጠን !።
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014