በንጉሱ ዘመን የከፋ ጠቅላይ ግዛት ተብሎ በሚጠራው ጅማ አውራጃ ጢሮ አፈታ ወረዳ ዲምቱ በምትባል ከተማ ነው የተወለዱት። በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ጅማ ከተማ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ የተከታተሉት በሚያዚያ 27 ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፍ በቀድሞ ስያሜው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። ሆኖም አንድ መንፈቀ ዓመት እንደተማሩ የተማሪ አብዮት ተቀሰቀሰ፤ በዚያ ምክንያት እሳቸውም ሆነ በርካታ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜው በማለፉ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።
ይሁንና ጉምሩክ ተቀጥረው ትምህርታቸውን በማታው ክፍለ ጊዜ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ገብተው ቀጠሉ። በዓመቱ ደግሞ የቀን ለመማር ተመዝግበው ሳለ የ1966 ዓ.ምቱ አብዮት ፈነዳ አሁንም ትምህርታቸውን አቋረጡ። ብዙዎች ተማሪዎች ዘመቻ እንዲሄዱ ቢገደዱም እሳቸው ግን የመንግስት ሰራተኛ ስለነበሩ በስራቸው ላይ እንዲቀጥሉ ተደረገ። ወደ አሰብ ተዛውረውም እስከ 1969 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል። አዲስ አበባ ለስራ ጉዳይ በመጡት አጋጣሚ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የውጭ የትምህርት እድል ተወዳድረው አለፉ። ሶቭየት ህብረት ሄደው ለሰባት ዓመት ያህል ትምህርታቸውን ተከታትለው በብሔራዊ ኢኮኖሚ እቅድ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ።
ወደአገራቸው ከተመለሱ በኋላም በዘመቻ መምሪያ ስር በነበረው ብሔራዊ ፕላን እቅድ አስመራ ተመደቡና በሙያቸው ማገልገል ጀመሩ። ማታ ላይ ደግሞ አስመራ ዩኒቨርሲቲ እያስተማሩ የቆዩት እንግዳችን አጠቃላይ መንግስታዊ መዋቅሩ ሲቀየር እሳቸውም የኤርትራ ራስገዝ ፕላን ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሾመውም ነበር። በ1983 ዓ.ም ሻቢያ አስመራን ሲቆጣጠር ለስድስት ወር ያህል ተሃድሶ እንዲገቡ ተደረጉ። የሻቢያ ሰዎች ምንም የሰሩት ወንጀል አለመኖሩን ካጣሩ በኋላ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው።
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም የኢኮኖሚ ልማትና ፕላን ሚኒስቴር በሙያቸው እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል። ካለፉት 16 ዓመታት ወዲህ ደግሞ የራሳቸውን አማካሪ ድርጅት በማቋቋም የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው አስፋው ናቸው። አቶ ጌታቸው ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸውን በርካታ ፅሁፎች በጋዜጦች ላይ በመፃፍ የሚታወቁ ሲሆን አራት መፅሓፎችንም ለህትመት አብቅተዋል። በርካታ ጥናቶችንም በማካሄድ ለአገራቸው ኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን ድጋፍ አድርገዋል። በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በንጉሱ ዘመን የጉምሩክ ፈታሽ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ታስረው እንደነበር ሰምተናል። እስቲ ምክንያቱ ምን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ጌታቸው፡– ጉምሩክ ፈታሽ ሆኜ ተቀጥሬ ስሰራ ዋለልኝ አውሮፕላን ሲጠልፍ እኔ ነበርኩ የፈተሽኩት። ዋለልኝ የአውሮፕላን ጠለፋ በማካሄዱ ምክንያት እኔም ሆንኩኝ ሌሎች ባልደረባዎቼ ታፍሰን ተወስደን ለ20 ቀናት ሶስተኛ በሚባለው ወህኒ ቤት እንድንቆይ ተደርገናል። የታሰርኩበት ዋነኛ ምክንያት በደምብ ለምን አልፈተሽክም የሚል ቢሆንም፤ እሱ ግን መሳያሪያ አልያዘም ነበር። እንደሰማነው ሌላ ሰው ነበር መሳሪያ ያስገባው። የሚገርምሽ በረራው ከማለዳው 12 ሰዓት ገደማ ነበር። አካላዊ ፍተሻውን በሚገባ ነው ያደረኩት። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን ተጠልፏል ተብሎ ተመልሶ መጥቶ አረፈ። ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ አፋፍሰው ሶስተኛ በሚባው ወህኑ ቤት ወሰዱንና ለ20 ቀን አስረው ጉዳዩን ሲያጣሩ ቆይተው ፈቱን። የተፈጠረው ነገር በአጭሩ ይህ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት የምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ምንያህል ውጤታማ ነው ብለው ያምናሉ ?
አቶ ጌታቸው፡– እኔ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ አገሪቱ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም የተሻጋገረችበት ወቅት ነበር። ብዙ ጊዜ ደግሞ እንደሚታወቀው አለምን የሚመሩት አለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና አለም ባንክ ናቸው፤ ኢህዴግ ስልጣን እንደያዘ ወደ ነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመግባት የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም በየአገሩ ያስተዋውቁ ነበር። ወደ ኢትዮጵያም መጥተው የመንግስት ሚና በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲቀንስ ስለሚፈልግ ብዙ ሰራተኞችንም ከመንግስት መስሪያ ቤት አፈናቅሏል።
ሰራተኛንና ወጪን በመቀነስ ለግሉ ዘርፍ የማስረከብ አላማ የያዘ በመሆኑ መንግስት በደርግ ዘመን ይዟቸው የነበሩ ትላልቅ ድርጅቶች ሁሉ ወደ ግል ባለሃብቶች እንዲዞር ተደረገ። በተለይ የመዋቅር ማሻሻያውን ተከትሎም የነፃ ኢኮኖሚ ለመተግበር ተሞክሮ ነበር። ነገር ግን ብዙም ውጤት ስላላመጣ የኢህአዴግ መንግስት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልማታዊ መንግስት የሚል አካሄድ ጀመረ። በልማታዊ መንግስት አካሄድ ለውጡ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል።
በዚህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነፃ ገበያ ተባለ እንጂ በተጨባጭ ወደ ነፃ ገበያ አልተገባም ነበር። ሁለቱ አለምአቀፍ ድርጅቶች በፈለጉት መልክ ድርጅቶችን ወደ ግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ቢዞሩም ካፒታልና መሬት ነፃ አልነበሩም። በኢኮኖሚ ዘርፍ ደግሞ መሬትና ካፒታል ዋነኛ የምርት ግብረሃይሎች ተደርገው ነው የሚወሰዱት። እነኚህ ነፃ ካልሆኑ ሌሎች ድርጅቶችና ምርት ነፃ ቢሆንም ነፃ ገበያ አለ ብለሽ ደፍረሽ አትናገሪም። ምክንያቱም ነፃ ገበያ መፈጠር ያለበት በምርት ገበያ ውስጥ ሳይሆን ከምርት ገበያ በፊት አምራቾች የምርት ግብረሃይሎች ወይም ግብዓተ-ምርቶችን ተወዳድረው ነው ማግኘት ያለባቸው። ውድድር መስፈን ያለበትም ገና ምርት ከመመረቱ በፊት ነበረ። በመሆኑም መሬትና ካፒታል ወደ ግል መዞር ነበረባቸው።
ሥልጣን ላይ የነበረው መንግስት ግን ይህንን ሳያዞር ነው ለ27 ዓመታት የቀጠለው። በእርግጥ ካፒታል በተወሰነ ደረጃ የግል ባንኮች በመቋቋማቸው የተወሰነ መሻሻል መጥቷል። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቁን ድርሻ ቢይዝም የግል ባንኮች በማቋቋማቸው በተወሰነ ደረጃ ካፒታል ውድድር ውስጥ ገብቷል ሊባል ይችላል። መሬት ግን እስካሁን በመንግስት እጅ ስለሆነ ውድድር ውስጥ አልገባም። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት በነፃ የኢኮኖሚ ስርዓት ነበርን ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም። ሆኖም ግን አንድ አገር ልትለማ የምትችለው በነፃ ኢኮኖሚ ስርዓት ብቻ ስላልሆነ በልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ስርዓትን የደቡብ ምስራቅ ኤዢያ አገራት በፍጥነት ያደጉበት በመሆኑም እኛም ልናድግ እንችላለን ተብሎ ልማታዊ መንግስት ፍልስፍና እንዲተገበር ተደረገ። በዚህ መሰረት የድህነት ቅነሳ መርሃ ግብርና የአምስት ዓመት እቅዶች ታቅደው እንደነበር የሚታወስ ነው።
በመቀጠልም ሁለት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች ታቅደው በዚያ እቅድ መሰረት ስኬቶችም ተገኝተዋል፤ ድክመቶችም ታይተዋል። እንደ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲታይ መንግስት አሁንም ድረስ ትልቁን የኢኮኖሚ ድርሻ ይዞ መቆየቱ ተገቢ አይደለም። በተለይ የልማት ባንክን አቋቁመው ሌሎች ባንኮች ለልማት ባንክ ፈሰስ እንዲያደርጉ ወይም ደግሞ 27 በመቶ የብድራቸውን ለልማት ባንክ እንዲሰጡ ተደርጎ ለተመረጡ የኢንዱስትሪና የግብር ክፍለ-ኢኮኖሚዎች እንዲያበድሩ በመደረጉ በልማታዊ መንግስት ፍልስፍና የተገኙ ውጤቶች አሉ።
ኢኮኖሚው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አድጓል፤ ይሄ የማይካድ ነው። አዲስ አበባን ከ30 ዓመት በፊት የሚያውቃት ሰው ዛሬ ሲያያት የተለየ መልክ ነው ያላት። በከተሞች ደረጃ ለውጥ መጥቷል። ብዙ ከተሞችም በተመሳሳይ መልኩ አድገዋል። በገጠር ግን ያንን ያህል ለውጥ አይታዩም፤ በከተሞችም ቢሆን መንግስታዊ ስራዎች የሚበዙበት ሲሆን ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ደግሞ ያደገው የግንባታ እና አገልግሎት ዘርፉ ነው።
ብዙ ሃገሮች ወደ አገልግሎት ዘርፉ ከመሸጋገራቸው በፊት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ነበር የተሸጋገሩት። እኛ ግን በቀጥታ ከግብርና ወደ አገልግሎት ነው የተሸጋገር ነው። ምንአልባት ይህ ሊሆን የቻለው ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ቁጥር እየጨመረና የኢንዱስትሪ ስራ ሊያገኝ
ባለመቻሉ በቀጥታ ወደ አገልግሎት ዘርፉ ነው የገባው። ከግብርና ወደ አገልግሎት መግባት ደግሞ ትንሽ ሂደቱን ያልጠበቀ ያደርገዋል። ኢንዱስትሪው በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ከማበብ ይልቅ እየኮሰመነ ነው የመጣው። ኢትዮጵያ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ኢንዱስትሪዎች የገነባች አገር ሆና ሳለ እስከዛሬ የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ቁጥር ከ300ሺ አይበልጥም የሚል መረጃ አለ። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው። አሁን ላይ 46 በመቶ የሚሆነው የኢኮኖሚ ክፍል የያዘው አገልግሎቱ ነው። አገልግሎቱ ደግሞ ያው እንደሚታወቀው ምርት አያመርትም፤ በዘርፉ የተሰማራው ሰው አገልግሎት ሰጥቶ ገቢ ያገኛል፤ ግን ገቢውን የሚውለው ምርት ለመግዛት ነው። በአገሪቱ ውስጥ እጥረት ያለው የቁሳዊ ሸቀጥ ምርት ነው።
በዚህ ምክንያት የሃብት ድልድሉ ከቁሳዊ ምርት ይልቅ ወደ አገልግሎት ዘርፍ ስላዘነበለ የዋጋ መዋዠቅና የዋጋ ንረት በአገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቷል። አሁን የምናየው የዋጋ መዋዠቅም ሆነ የዋጋ ንረት ዛሬ የመጣ ሳይሆን ሲንከባለል የነበረ፤ የተዛባ የሃብት ድልድል ያመጣው ጣጣ ነው። በእርግጥ አሁን ላይ በበለፀጉት አገራት የአገልግሎት ዘርፉ ከ60 እስከ 70 በመቶ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ይይዛል። እነሱ ይህን እድገታቸውን ጠብቀው ነው እዚህ ደረጃ የደረሱት። እኛ ደግሞ ሂደቱን ጠብቀን እዚህ ስላልደረስን የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ተከስቷል። ሁሉም ሰው ሸማች ነው፤ የአምራቹ ቁጥር ግን እጅግ አነስተኛ ነው። አሁን ላይ አምራችና ሸማች ሆድና ጀርባ ሆነዋል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ እድገት እንጂ ልማት አልመጣም ሲሉ ይደመጣሉ። ለመሆኑ ይህ ምን ማለት ነው?
አቶ ጌታቸው፡– እንደተባለው በአንድ አገር ውስጥ ልማትና እድገት መመጣጠን አለባቸው። ነገር ግን ልማት አልመጣም እድገት ብቻ ነው የሚለው ነገር አከራካሪ ነው። በነገራችን ላይ ልማት የኢኮኖሚ እድገትንም ያካትታል። ግን ልማት ሰፋ ይላል። የኢኮኖሚ እድገት የሚለካው በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ነው። ልማት ደግሞ ከዚያ ሰፋ ብሎ እንዳልሽው የትምህርት ተሳትፎ፣ የጤንነት ሁኔታ፣ ማህበራዊ አገልግሎት፣ ዜጎች የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን ምርጫው ሲሰፋ ሰው ለማ ይባላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከንጉሱ ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች ከአራት አይበልጡም ነበር። አሁን ላይ ግን ከ40 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ተስፋፍተዋል፤ ይህ ማለት ግን የጥራቱን ጉዳይ ሳናስብ ማለት ነው። መሰረተ ልማቶችም ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት ተደርገዋል። ይህ ሆኖ ሳለ ልማት አልመጣም አንልም። የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ተነድፎ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው ልማት ለማምጣት ነው። ስለዚህ የዜጎችን ገቢ በማየት ብቻ ሳይሆን ምርት ሲሰፋ ነው ልማት መጣ የሚባለው።
እዚህ አገር ልማት የሚመጣው በአብዛኛው በመንግስት ነው። የገበሬው ደጃፉ ድረስ መንገድንም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት በሙሉ የተጣለው መንግስት ላይ ነው። ስለዚህ እኔ በኢትዮጵያ ልማትና እድገት አልተመጣጠኑም ከማለት ይልቅ ይበልጥ ጥሩ የሚሆነው የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተሳትፎና የመንግስት ተሳትፎ አልተመጣጠነም ቢባል ይሻለኛል። መንግስት ለልማት ብሎ ብዙ ሃብት በራሱ እጅ አድርጎ መሰረተ ልማትን በመዘርጋት፤ ማህበራዊ አገልግሎቶች በመስጠት ብዙ እንቅስቃሴ አድርጓል፤ የማይካድ ነው። ነገር ግን እድገት ደግሞ የሚመጣው በመንግስት ተሳትፎ ሳይሆን በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተሳትፎ ነው።
አንደኛ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ ስለሚሆን ስለሚያመርታቸው ምርቶች ሸማቹን የሚያረኩ ነው የሚሆኑት። ትልቁ የኢትዮጵያ ችግር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ያለማደግ ነው እንጂ ልማትና እድገት ባለመመጣጠናቸው ወይም ደግሞ ልማት ወደኋላ በመቅረቱ አይደለም።
አንዳንዶች የሰው ጭንቅላት ላይ አልተሰራም ብለው ይከራከራሉ። በእኔ እምነት ግን ባለፉት 20ና 30 ዓመታት በእኛ ምክንያትም ይሁን በአለም አቀፍ ሁኔታ የወጣቱ ጭንቅላት መጥቋል። በተለይ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና መስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል ብዬ ነው የማምነው። ይሄ ሁሉ የሚያመለክተው የሰው ጭንቅላት ላይ መሰራቱን ነው። በእርግጥ አስቀድሜ እንዳልኩሽ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ያለመመጣጠን ሁኔታ አለ። ሁለተኛ ደግሞ በገጠሩና በከተማ መካከልም ያለመጣጠን አለ። ሃብት በሙሉ የተከማቸው በከተማ ነው። የተሰራው ግንባታ በሙሉ በከተማ ነው።
ባንኮች አርሶአደሩን አስጨንቀው እንዲቆጥብ ካደረጉት በኋላ በተቆጠበው ብር ህንፃ የሚሰሩት ከተማ ውስጥ ነው። ለገጠሩ ህዝብ የሚሆን ምርት ማምረት የሚያስችል ኢንዱስትሪ አልተገነባም። በሚያሳዝን ደረጃ የኢትዮጵያ ገጠሮች ውስጥ ዳቦ ፋብሪካ እንኳን የለም። አንድ የግብርና ውጤቶችን የሚያቀነባብር ኢንዱስትሪ አልተገነባም። በደርግ ጊዜ እንዳውም የትኖራ የሚባል የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ጎጃም መንገድ ላይ ነበር።
ይህ ማቀነባበሪያ ከብቶችን እያረባ፤ ወተት ያቀርባል፤ ቂቤና ሌሎች የግብርና ምርቶችን እያመረተ ለተጠቃሚ ያደርስ ነበር። እንዲህ አይነት ፋብሪካዎች በገጠር መስፋት ሲገባቸው ባለፉት 30 ዓመታት የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ያተኮረው ከተማ ላይ ብቻ ነበር። የሚገነቡት ህንፃዎች በአብዛኛው የከተማዋን ነዋሪ የሚጠቅሙ መኖሪያ ቤቶች ላይ ሳይሆን ለድርጅትና ለንግድ ማዕከላት ላይ በመሆኑ የመኖሪያ ቤት እጥረቱን እንኳን መቅረፍ አልተቻለም።
ግንባታ ለኢኮኖሚ እድገት መሰረት ነው፤ ነገር ግን ግንባታ ብቻውን ቢያድግና ሌሎቹ ካላደጉ ጥቅም የለው። በገጠሩ ላይ መሰራት የሚገባውን ያህል ባለመሰራቱ ለምግብ ፍጆታ የሚውል ምርት እንኳን ማግኘት አልቻልንም። ግብርና ኢንዱስትሪው ተመጋቢ ሆነው እንዲሰሩ አልተደረገም። በአንድ የኢንዱስትሪ እድገት ውስጥ አንዱ ለአንዱ ጥሬ እቃ አቅራቢ ሆኖ የአቅርቦት ሰንሰለት መመስረት ነበረበት። እኛ አገር የአቅርቦት ሰንሰለት ደካማ ነው። ይህም በመሆኑ ምርት በሚፈለገው መጠን አልተመረተም፤ ለአዲሱ ትውልድም የስራ እድል መፍጠር አልተቻለም።
ከዚያ ይልቅ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ወጣቱ ለራሱ ስራ እንዲፈጥር ብቻ ሲወተወት ነው የነበረው። እርግጥ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙ ወጣት የራሱን ስራ እንዲፈጥር መበረታቱ መልካም እንደሆነ ባምንም ብቻውን ደግሞ ትልቅ ስትራቴጂ ተደርጎ መወሰድ አልነበረበትም። ፋብሪካ በሰፋ ቁጥር የስራ አጡን ቁጥር እንቀንሳለን፤ ይሁንና ብዙ ትንንሽ ድርጅቶች እዚህም እዚያም መመስረታቸው ሰንሰለት ያለው እድገት ልናመጣ አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- አርሶ አደሩ ላይ ያለመሰራቱ አሁን ላይ ለተፈጠረው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ያለውን አሉታዊ ሚና እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ጌታቸው፡- በበለፀጉት አገራት ከአጠቃላይ ህዝቡ ገቢ ውስጥ 70 በመቶ የደመወዝ ገቢ ነው፤ 30 በመቶ ነው የትርፍ ገቢ። ኢትዮጵያ ውስጥ እዳልኩሽ ላለፉት 30 ዓመታት ግንባታ ላይ ብቻ በማተኮራችን ግንባታ ደግሞ በባህሪው ካለቀ በኋላ ሰራተኛውን ያሰናብታል። ግንባታው እስካለ ድረስ ብቻ ነው ሰራተኛው ገቢ የሚገኘው። ባለሃብቱ የገነባውን ህንፃ አከራይቶ እድሜ ልኩን ሃብት ያፈራበታል። ሰራተኛው ግን ግንባታው ካለቀ በኋላ ደህና ሰንብት ይባላል።
ደመወዙ ይቋረጣል፤ ሥራአጥ ይሆናል፤ ስራ ፍለጋም ይንከራተታል። ምክንያቱም ህይወቱን በሙሉ ሊያስቀጥል የሚችል የስራ እድል አልተፈጠረለትም። ይህም የሃብት ድልድሉ ወደ ባለሃብቱ ብቻ ያደላ መሆኑን ያሳያል። ጥቂት ሰዎች ውስጥ ብቻ ነው ሃብት የገባው። በጣም የሚያሳዝነው የሚቆጥበው ደሃው ገበሬ ሆኖ ሳለ ባንኮች ብድር የሚሰጡት ለባለሃብቱ ነው። ያንን ደሃው የቆጠበውን ገንዘብ ጥቂት ባሃብቶች ተበድረው ህንፃ ይሰሩበታል፤ ሃብት ያካብቱበታል።
በአጠቃላይ ባለፉት 30 ዓመታት የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው ቆጣቢውን የጎዳና ተበዳሪውን የጠቀመ ነበር። ምክንያቱም የዋጋ ንረት 10 በመቶ ሆኖ በሰባት በመቶ ወለድ ባንክ ብትቆጥቢ በአመቱ አንቺ ከሳሪ ነሽ። ያስቀመጥሽው 100 ብር በዓመቱ 97 ብር ሆኖ ነው የምታገኚው። ስለዚህ በዚህ አይነት ሁኔታ የወለድ ምጣኔው ከዋጋ ንረቱ ምጣኔ ዝቅተኛ በመሆኑ ቆጣቢዎች እየተጎዱ ተበዳሪ ተጠቃሚ ነው የሚሆነው። በዋጋ ንረቱ ምክንያት የብር የመግዛት አቅም ተዳክሟል።
ተበዳሪው በመበደሩ ምክንያት ብቻ ያተርፋል፤ ምክንያቱም የሚመልሰው ብር የመግዛት አቅሙ የወደቀ ነው። በዚህ ምክንያት ላለፉት 30 ዓመታት ደሃ ቆጣቢ የባሰ እየተጎዳ፤ ሃብታም ተበዳሪ የበለጠ እየተጠቀመ ነው የመጣው። ስለዚህም ነው የአገሪቱ ሃብት በጥቂት ሃብታሞች እጅ ላይ የተሰበሰበው። ይህ ችግር ሲንከባለል ቆይቶ አሁን ላይ የድሃው ቁጥር እየበዛ፤ የሃብታሙ ቁጥር እያነሰ ጥቂቶች ብቻ የሚቆጣጠሩት ሆኗል።
በምርት ሂደቱ በኩል ደግሞ ሲታይ በተለይ ውድድር ባለመኖሩ፤ መሬት በመንግስት እጅ የተያዘ በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪው እንዳያድግ ሆኗል። ከዚያ ይልቅም መሬት አየር በአየር የሚቸበችበት ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርዓት ነው የተፈጠረው። ምክንያቱም ምርት ከማምረት ይልቅ ዛሬ የገዛሽው መሬት ሁለትና ሶስት እጥፍ አድርገሽ ትሸጭዋለሽ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አበክረው ከሚናገሩት ነገር አንዱ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚለውን ቃል ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት በራሱ ኢኮኖሚያዊ ትርጉም አለው። ሳይለፋበት የተገኘ ገቢ ማለት ነው። መሬት ሳይለፋበት ገቢ የሚገኝበት ከሆነ ተለፍቶበት እንዲገኝ ማድረግ ነው የሚጠቅመው። ስለዚህ ከወሬ ባሻገር በተግባር ኢኮኖሚው የተመጣጠነ እንዲሆን፤ ለህዝቡ እንዲጠቅም አልተደረገም።
አዲስ ዘመን፡- ለዋጋ ንረቱ መባባስ የውጭ ተፅዕኖ ምንያህል ነው ብለው ያምናሉ? በአገር ውስጥስ ያልተሰራው የቤት ስራ ምንድነው ይላሉ?
አቶ ጌታቸው፡- አሁን ያለንበትን ሁኔታ እንደኢኮኖሚስት ሳያው ብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ እንዳለን ነው የምረዳው። ከጭንቅላታችን ጀምሮ አሁን ሽግግር ላይ ነው ያለነው። ብዙዎቻንን ከደርግ ዘመን ጀምሮ ያየነው ከመንግስት ጠባቂነት ነው። ሥራ መንግስት ይሰጠኛል፤ ሁሉንም ነገር መንግስት ያቀርብልኛል ብለን ነው የኖርነው። ማግኘትና ማጣታችን መንግስትን ከማጥቃት ጋር አያይዘነዋል። በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ዋናዎቹ ተዋናዮች ሸማቹና አምራቹ ናቸው። ሸማቹ አዛዥ ሊሆን ሲገባ ለማኝ ነው የሆነው።
በሌሎች አገራት ግን አምራቹ ምን ማምረት እንደሚገባው የሚያዘው ሸማቹ ነው። ምክንያቱም ገንዘቡን ወስዶ የሚጠቀመው ሸማቹ በመሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ‹‹ደምበኛ ንጉስ ነው›› የሚባለው ያለምክንያት አይደለም። በኢኮኖሚስት ህግ የምርቱ አዛዥ ሸማቹ በመሆኑ ነው። የመንግስት ሚና ደግሞ ማገዝ ነው። እኛ አገር ግን ሸማቹም ሆነ አምራቹ መንግስት ላይ ጥገኛ ሆነዋል።
ሸማቹ መንግስት ተቆጣጥሮ ዘይቱንም ሆነ ዱቄቱን እንዲያቀርብለት ይፈልጋል፤ አምራቹም መንግስት መሬት እንዲሰጠው፤ ግብር እንዲቀንስለትና ብድር አመቻችቶለት ነው መስራት የሚፈልገው። አሁን ላይ አምራቹም ሆነ ሸማቹ ከመንግስት ጥገኝነት ገና አልወጣም።
የነፃ ኢኮኖሚ የሚገነባው በዋናነት በእነኚህ ሃይሎች ነው። የመንግስት ሚና ትንሽ ነው። ይሁንና ከማገዝ ያለፈ ትልቅ ስልጣን ሰጥተነዋል፤ ሁሉንም ነገር እሱ እንዲሰራው ነው የምንጠብቀው። ሊሆን የሚገባው ግን ሸማቹ በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አምራቹ ማምረት ነበር። ምክንያቱም ገንዘብ የሚያገኘው ከሸማቹ በመሆኑ ነው። አሁን ላይ እንዳውም የሁሉ ነገር አድራጊ ፈጣሪ አምራቹና ነጋዴው ሆኖ ሳለ ሸማቹ ለማኝ ሆኗል።
በመሰረቱ መለመን አልነበረበትም፤ ታዲያ ምኑን ንጉስ ሆነ? ንጉስ ይለምናል እንዴ!? ከእሱ ኪስ ወስዶ እኮ ነው አምራችና ነጋዴ የሚከብረው። ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት እንቁላል ሁለት ብር ነበር፤ ዛሬ 12 ብር የገባው ዶሮ ጠፍቶ ሳይሆን አምራች ህብረተሰብ መፍጠር ባለመቻላችን ነው።
ከዚያ ይልቅ ነጋዴው ዋጋ እያስወደደ አየር በአየር እንዲከብር ነው ያመቻቸንለት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ምንአልባት የመንግስት ፖሊሲ ችግር ሊኖርበት ይችላል። ለምሳሌ ምርት ለማገበያየት የሚስችል በቂ ጥሬ ገንዘብ ገበያ ውስጥ ማስገባት ሲገባን ከምርቱ በላይ የሆነ ጥሬ ገንዘብ እንዲገባ ሲደረግ የእቃዎች ዋጋ እንዲወደድ ያደርጋል። ምክንያቱም ምርቱ ትንሽ በመሆኑ ነው።
አሁን ካለንበት የኢኮኖሚ ችግር መንግስት ያስወጣናል ብለን መጠበቅ የለብንም። በእርግጥ መንግስት ሊሰራ የሚችልባቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ አስቀድሜ እንዳልኩሽ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን ገበያው ከሚፈልገው በላይ እንዳይሆን መቆጣጠር አለበት። ነገር ግን ሸማቹና አምራቹ መግባባት መቻል አለባቸው። ሸማቹ አምራቹን በትክክል ማዘዝ አለበት፤ አምራቹም ሲያመርት የሸማቹን ፍላጎት አጥንቶ መሆን አለበት። ፍላጎቱንና አቅርቦትን መወሰን የሚችለው በዚህ መልኩ መሆን አለበት። በተለይ ሸማቹ የገበያውን ሁኔታ አጥንቶ ነው መግዛት ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ኃላፊነቱን ሁሉ ወደ ሸማቹ ህብረተሰብ የምናወርድ ከሆነ በተጨባጭ የምንፈልገው ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ጌታቸው፡– ልክ ነሽ፤ ሸማቹና አምራቹ መግባባት መቻል አለባቸው። ለምሳሌ አንቺ ራስሽ ሽንኩርት ማምረት ከመንግስት ስራ በላይ ገቢ የሚያስገኝልሽ ከሆነ ነጋዴውንም ሆነ አምራቹን ከምትለምኚ ለምን ወደ ማምረቱ አትገቢም?። ምክንያቱም እንደሸማች ብቻ ሳይሆን ራስሽን ማየት ያለብሽ እንደአምራችም ነው። አማራጮችን መውሰድ አለብሽ እንጂ ቁጭ ብለሽ ብቻ ሌላ ሰው የሚያቀርብልሽን መጠበቅ የለብሽም። በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ተወደደብኝ እያለ ሁልጊዜ ከሚያማርር ለምን ራሱ አምርቶ አይሸጥም?።
ስለዚህ ሸማቹ ራሱ የተወደደበትን ምርት በማምረት ገበያውን ማረጋጋት ይገባዋል። ራሳችንም ገበያ ውስጥ ገብተን ገበያውን ማረጋጋት እንችላለን። ምክንያቱም ምርት በስፋት ሲገባ ውድድሩም በዚያው ልክ ይሰፋል። እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማምረት መሬትና ካፒታል በቀላሉ አታገኚም፤ ምቹ ሁኔታም ማግኘት ከባድ ነው። እነዚህ ነገሮች ከተመቻቹ ግን ከመግዛት ይልቅ ማምረት የበለጠ ጠቃሚ ነው። ይህንን ስልሽ የመንግስትን ኃላፊነት ልቀንስ አይደለም። በማክሮ ኢኮኖሚክስ ፖሊሲው ገበያው የማረጋጋት ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን ዝም ብሎ መጠበቅ የባሰ አረንቋ ውስጥ እየከተተን ነው የሚሄደው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ በሂደት የሚያነሳ ከሆነ የዋጋ ንረቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ሚና ምንድነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ጌታቸው፡– እኔ መከራከር ያለብን የድጎማው መነሳት ተገቢነት ላይ ሳይሆን በአንድ ጊዜ መነሳቱ ላይ ነው። መንግስትማ ደሃ ገበሬ እያለ ሃብታም ባለመኪና ሊደጉም የሚችልበት ምክንያት እንደሌለ ነግሮናል። ከዚያ ይልቅም በማዳበሪያ እጦት የሚንገላታውን ገበሬ እንደሚደጉም ከተናገረ፤ ሃብቱ የራሱ የመንግስት ሆኖ ሳለ ደጉመኝ ብለሽ ልትሞግችው አትቺይም። በእርግጥ የህዝብ ትራስፖርት አገልግሎት የሚሰጡትን ቀስ በቀስ ድጎማ እየሰጠ እንደሚቀጥል ነው የተናገረው። ይህም ሲባል መንግስት እየከሰረ ለባለመኪናዎች ሊያቀርብ እንደማይችል ግልፅ አድርጓል። ማንም ቢሆን መንግስትን እየከሰርክ አቅርብ ለማለት ምንም መብት የለውም። አሁንም ቢሆን ጭንቅላታችን ከድጎማና ከጠባቂነት አልወጣም ማለት ነው።
እንዳልሽው ግን የነዳጅ ዋጋ መጨመር በትራንስፖርት ዘርፉ ላይም ሆነ በምርት አቅርቦቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ችግር የሚያጠያይቅ አይደለም። ግን ያንን የሚያካክስ ነገር መስራት እንጂ መንግስትን ማስገደዱ ለውጥ አያመጣም። ድሮም ቢሆን በድጎማው ተጠቃሚ የነበረው በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል እንጂ ገበሬው አይደለም። አሁንም ቢሆን በአንድ ጊዜ ድጎማውን አነሳለሁ ያለው የራሱን መኪና ለሚጠቀም እንጂ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ እንዳልሆነ መረሳት የለበትም።
ድጎማውን በአንዴ ሁሉም ላይ አነሳለሁ ካለ ግን ትልቅ ቀውስ ነው የሚከሰተው። የዋጋ ንረቱ 50 በመቶ ከደረሰ ግሽበት ይከሰትና ለኢኮኖሚው አስጊ ይሆናል። ስለዚህ መንግስት እንዲህ አይነቱ ነገር እንዲፈጠር ይፈልጋል ብዬ አላምንም። አሜሪካም ብትሆን ነፃ ኢኮኖሚ ስርዓት የምትከተል ብትሆን ለስንዴ ምርት ትደጉማለች። እኛም አገር ፍልስፍናዬ ነጻ ገበያ ስርዓት ነው ተብሎ በአንዴ ድጎማ ይነሳል ብዬ አላምንም፤ ወደዚያ ቢገባ ደግሞ ቀውስ ነው የሚያመጣው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ጌታቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014