በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሚካሄደው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በመጪው ጥቅምት ወር ለአራተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ በውድድሩ ላይ ከ20 በላይ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ኦሊምፒያኖችና የዓለም ቻምፒዮኖች እንዲሁም የአገር ባለውለታዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡
አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዘጋጅነት የሚካሄደውና ባለፉት አራት ዓመታት ፈጣን እድገት እያሳየ በመጣው ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ሲካሄድ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካዊያን ይሳተፋሉ፡፡ ‹‹አብሮነት መሻል ነው›› በሚል መሪ ሃሳብም ውድድሩ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ ሩጫው ከስፖርታዊ ውድድርነቱ ባለፈ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ፣ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብ እንዲሁም ለተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጓል። በ5 ኪሎ ሜትሩ ሩጫ ላይ ከአትሌቶች ባለፈ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተካፋይ ሲሆን፤ ምዝገባውም ከዛሬ ጀምሮ በድረገጽ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በዚህ ዝግጅት ከ20 በላይ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ኦሊምፒያኖችና የዓለም ቻምፒዮኖች እንዲሁም የአገር ባለውለታዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም የገለፁት የውድድሩ አዘጋጆች፣ ባለፉት ሶስት መርሃ ግብሮች ላይ የኢትዮጵያ ብርቅዬ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ የዲባባ ቤተሰብ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ስለሺ ስህን፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና ሌሎችም በክብር እንግድነት መገኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በሺዎች ከሚቆጠሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ባሻገር ታዋቂ ሰዎችም ውድድሩን ለማበረታታት እንደሚካፈሉ ታውቋል። ባለፉት ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኘሬዚደንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በክብር እንግዳነት መገኘቷ ይታወሳል፡፡
ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ከመጀመሪያው ውድድር ጀምሮ በአካል በመግኘት አዘጋጆቹን ስትደግፍ የቆየች መሆኗን ያስታወሱት አዘጋጆቹ፣ ለታየው እድገት አድናቆቷን እንደገለፀችም ጠቁመዋል፡፡ ኮማንደር ደራርቱ ውድድሩ ባለፉት ስልሳ ዓመታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሀገራቸውን መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ ያደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናና እውቅና የሚያገኝበት መድረክ መሆኑን እንደገለፀችም ጠቁመዋል፡፡
የግራንድ አፍሪካን ረን ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ በበኩላቸው፤ ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫነት የበለጠ ፋይዳ ያለው መርሀግብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማቀራረብ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለውም አክለዋል። አያይዘውም ከሩጫው ጎን ለጎን የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለሚኖሩበት የአሜሪካ ማህበረሰብና ለትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የጎላ አስተዋጾኦ ላደረጉ ሰዎች ሽልማት የሚበረከትበት መድረክ እንደሆም አብራርተዋል።
በሩጫው ላይ በአጋርነት ከሚሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የዳሽን ባንክ ሲኒየር የዳያስፖራ ባንኪንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ያስቻለው አልማው፤ ባንካቸው የማህበረሰብ ግዴታውን ለመወጣት እንደ ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስቡ ዝግጅቶችን በቀጣይነት በመደገፍ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ ምስጋናውን የሚገልጽበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ እሴት የሆነውን ሩጫ እንደ እንድ መድረክ በመጠቀም በውጭ የሚኖሩ ወገኖችን ግንኙነት ማጠናከርና የባህል ልውውጥ ማድረግን አበክረው የሚደግፉት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በዝግጅቱ የሚመዘገቡ እና በዕለቱ ውድድሩን የሚያጠናቅቁ ተመዝጋቢዎች በሙሉ ሽልማት በሚያስገኘው እጣ ላይ የሚካተቱ ሲሆን፣ በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ የመኪናው እድለኛ የሆነው ተሳተፊ በይፋ መድረኩ ላይ ይገለጻል። የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ የሴልስ ማኔጀር አቶ ያሬድ ማንአለብህ፤ አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያውያን የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ የረጅም ዓመታት ደንበኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ደጋግመው ያሳዩ ሲሆን፤ ለእምነታቸው እና የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ ቤተሰብ በመሆናቸው በታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በኩል ለማመስገን መርጠዋል። በተለይ ዝግጅቱ ማህበረሰብን በማሰባሰብ እና በማወደስ ረገድ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸው ስራዎች ‹‹ቅድሚያ ለማህበረሰብ›› ከሚለው መርህ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ በቀጣይነትም እንደሚደግፉት ጠቁመዋል። አይይዘውም ዝግጅቱ በማህበረሰቡ የተለየ ቦታ የሚሰጠውን የአትሌቲክስ ስፖርት በመጠቀም አብሮነትን ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2022