አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ በየዓመቱ አዲስ በኤች. አይ.ቪ. ቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመቀነስ እ.ኤ.አ በ2020 ለማሳካት የተያዙትን የሦስቱን ዘጠና ግቦች ከማሳካት አኳያ አስፈፃሚ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ ሊጠየቁ እንደሚገባ የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ.ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ፅሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የየፅሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድህን ነገ ቅዳሜ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን በዓል አስመልከተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የቫይረሱ ስርጭትና በበሽታው የሚሞቱን ሰዎች ቁጥር ካለፉት ዓመታት አንፃር ባይጨምርም አመራሩም ሆነ ባለድርሻ አካላት ከዚህ በፊት በተመዘገበው ውጤት በመኩራራትና በመዘናጋት የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መጥቷል፡፡
በዓለምአቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የቫይረሱን ስርጭት ለመካለከል ይሰጥ የነበረው ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ቀንሶ ለህክምና አገልግሎት ብቻ እንዲውል በመደረጉ ለበሽታው የሚሰጠው አገራዊ ምላሽ በከፍተኛ ደረጃ መዳከሙን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ቫይረሱ አምራቹን ኃይል በመንጠቅ ኢኮኖሚን፥ ፖለቲካንና ማህበራዊ አኗኗርን የሚያናጋ ከመሆኑጋር ተያይዞ የበሽታው ስርጭት አሳሳቢ በሚባል ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ በትምህርት ቤቶች፣ አዳዲስ እየተገነቡ ባሉ የልማት ፕሮጀክቶችና በዋና ዋና ከተሞች ላይ በበሽታው ዙሪያ የሚሰጠው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ የበሽታውን ስርጭት ከመግታት ይልቅ የሚሰፋባቸው ዕድሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ባለ ብዙ ዘርፍ ቫይረሱን የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢሰጣቸውም በተጨባጭ መሬት የወረደ ሥራ እያከናወኑ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች ከእያንዳንዱ ሠራተኛ ደመወዝ የሚቀረጠው ሁለት በመቶ የሚሆነው ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ እያዋለ ነው ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል፡፡
« የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ቀን በየዓመቱ የሚከበረው በሽታው መከበር የሚገባው ሆኖ አይደለም፤ ይልቁኑ በበሽታው አዳዲስ የሚያዙትን ዜጎች ለመታደግ ንቅናቄ የምንፈጥርበት እንጂ» ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይሁንና አብዛኞቹ ተቋማት በዓሉን ለአንድ ቀን ከማክበር በዘለለ ከመደበኛ ሥራቸው እኩል ግንዛቤ የማስጨበጥና የመከላከል ሚናቸውን በመወጣት ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
«የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በአዋጅ የተነገረ እስኪመስል ድርስ በበሽታው ዙሪያ የሚሠሯቸውን ሥራዎች እርግፍ አድርገው ነው የተውት» ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ህግ አውጪው አካል በአገር ደረጃ ለተያዘው ግብ መሳካት በሽታውን የመከላከል ሥራ ያልሠሩትን አካላት ሊጠይቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በፅህፈት ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባባሪያ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ምትኩ በበኩላቸው ፤ ዘንድሮ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበረው የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ቀን ዋና ትኩረት በእ.ኤ.አ 2020 የሦስቱን90 ግቦች ማለትም90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ራሱን እንዲያውቅ ማድረግ፣ ካወቁት ውስጥም90 በመቶ የሚሆኑት የፀረ ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መድሃኒት እንዲጀምሩ ማድረግ፣ መድሃኒቱን በጥብቅ ስነምግባር ሳያቋርጡ በደማቸው ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን ትርጉም በሌለው ደረጃ ስለሚቀንስ 90በመቶ የአጋላጭነታቸውን መጠን መለካት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኃላፊው በዓሉ ለኤች. አይ.ቪ. ቫይረስ መከላከል ሥራዎች መቀዛቀዝ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በአመራር ደረጃ የጋራ በማድረግ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲቀመጥ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ በተጨማሪም ይበልጥ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በፈቃደኝነት ምርመራ የሚያደርጉትን ለማነሳሳት እንደሚያግዝ ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራም ተከታተይነት ባለው መልኩ በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በልማት ፕሮጀክቶችና በመስፋፋት ላይ ባሉ ከተሞች አካባቢ በስፋት እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡
የዘንድሮው የዓለም ኤድስ ቀን «ለኤች.አይ.ቪ. ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ ነን፤ እንመርመር፣ ራሳችንን እንወቅ» በሚል መሪ ቃል ለ31ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡
ማህሌት አብዱል