ዛሬ ስለ ለውጥ ህግ እናወራለን:: የለውጥ ህግ የህይወት ህግ ነው:: የህይወት ህግ ደግሞ የአጠቃላዩ እንቅስቃሴአችን ህግ ነው:: ህይወት ሶስት ቀን ናት.. ትላንት ዛሬና ነገ :: ትላንት ዛሬን የምናደምቅበት ብዕራችን ነው :: ነገ ደግሞ ምን እንደሆነ የማናውቀው ለእያንዳንዳችን ባዳ ቀን ነው :: እኚህ ሶስት የጊዜ ፈረቃ በህይወታችን ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ እየገለጥን እንይ:: ከዚም በመነሳትም አለም ሁለት አይነት ሰዎች አሏት ለማለት እንደፍራለን ፤ከትላንት የሚማሩና ትላንትን የሚያማርሩ:: ከትላንት የሚማሩ ሁሌም አሸናፊዎች ናቸው::
የዚህን አለም ብርቱና ስኬታማ ሰዎች ብታስተውሉ በትላንት ተምረው ዛሬን መልካም ያደረጉ ናቸው:: በእኛ ሀገር እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው..ትላንትን ለመማረሪያ እንጂ ለመማሪያ ስናደርገው አንታይም:: የዛሬ ችግሮቻችንን ከትላንት አብራክ ውስጥ ጎርጉረን ያወጣናቸው ናቸው:: በትላንት የዛልን፣ በትላንት የምንኖር ህዝቦች ነን:: ሰው ትላንትን መርሳት ካልቻለ ዛሬ አይኖረውም:: ሰው መኖር የሚጀምረው ትላንትን መርሳት ሲችል ብቻ ነው::
ትላንት ከትዝታ ባለፈ በእኛ ህይወት ላይ ህላዊ የለውም:: አብዛኞቻችን በትላንት ዛሬን የምንኖር ነን:: ለዛም ነው እንደ ሀገር ከስረን የቆምነው:: ትላንት ለዛሬ የሚሆን ጉልበት የለውም:: እንድንማርበትና ዛሬን መልካም እንድናደርግበት መጥቶ የሄደ እንጂ በቁጭትና በሮሮ እንድናስታውሰው ሆኖ የተፈጠረ አይደለም:: እኛ ኢትዮጵያውያን ከትላንት ብንማር የሚያስተምሩን በርካታ ታሪኮች ነበሩን:: ግን አንማርም..ዛሬን በትላንት መንፈስ የምንኖር ነን::
በትላንት ጉያ ውስጥ የተደበቁ ብዙ የአንድነት ታሪኮች፣ ብዙ የመለያየት ታሪኮች አሉን:: የሚጠቅመንን እየወሰድን የማይጠቅመንን መተው አናውቅበትም:: ዛሬዎቻችን በትላንት ቁርሾ፣ በትላንት የፖለቲካ ርዮተ አለም የተጨማለቁ ናቸው:: አዲስ ዛሬ መፍጠር አልቻልንም:: ሰው ከትላንት ተምሮ አዲስ ዛሬን መፍጠር ካልቻለ ህልውናውን አደጋ ላይ እየጣለ ነው የሚሄደው:: ስህተት የሰውን ልጅ ካለወጠው በምንም አይለወጥም:: ትላንት መጠቶ የሄደው እንድንማርበት ነው:: በትላንት ችግሮቻችን መማር ካልቻለን የምድርን ትልቁን የለውጥ ህግ ዘንግተናል ማለት ነው::
ለምን ስልጣኔ ራቀን ? ፊት ተፈጥረን ለምን ኋላ ቀረን? ለዛሬ የሚሆን አዲስ ልብ ስለሌለን ነው:: ችግሮቻችንን ችግር ፈጣሪ በሆነ ሀሳቦቻችን ለመፍታት ስለምንሞክር ነው:: በመሰረቱ ችግር.. ችግር ፈጣሪ በሆነ ጭንቅላት አይፈታም:: የመፍትሄ ስፍራው ምክንያታዊ አእምሮ ነው:: ጭንቅላታችን በትላንትና በአምና የፖለቲካ አስተሳሰብ ተመርዞ፣ በትላንት የታሪክ ቁርሾ ተይዞ ከፍ ማለትም ሆነ ለችግሮቻችን መፍትሄ መውሰድ አንችልም:: ለአስተዋይ ሰው በስህተት ውስጥ መፈጠር ልክ በሆነ ነገር ላይ ከመፈጠር የበለጠ አዋጭ ነው::
ብዙዎቻችን ስህተት የሚያበላሸን እንጂ የሚሞርደን አይመስለንም:: ለዚህም ነው በእውቀት ድርቀት የምንሰቃየው:: ስህተት ዋጋ ቢስ የሚሆነው የማንማርበትና የማንለወጥበት ከሆነ ብቻ ነው:: እውቀት የትም አለ፣ የሰው ልጅ የትም፣ በማንም ሊማር ይችላል:: በስህተት ውስጥ የመማርን ያክል እውቀት ግን የትም አይገኝም:: እንከን አልባ እውቀት አንድ ጊዜ ነው የሚቀርጸን የስህተት እውቀት ግን እድሜአችንን ሙሉ የሚከተለን ፍጹምናችን ነው::
እኛ ግን ከስህተቶቻችን አንማርም:: ትላንትን ዋና የችግሮቻችን ምንጭ አድርገን የምንገልጥ ነን:: ስህተት ካልተማርንበት ሌሎች ችግሮችን እየፈጠረ የመከራ ሎሌ ነው የሚያደርገን:: የሰው ልጅ ደግሞ ትላንትን እያስታወሰ እንዲቆዝም ሳይሆን በዛሬ በረከት ተደስቶ ተመስገን እያለ እንዲኖር ነው ሰው የሆነው::
በህይወታችን የትኛውም ቦታ ላይ በስህተት ውስጥ ካላለፍን ምሉ አንሆንም:: ሳንገዳገድ መቆም አንችልም:: በአንድ ነገር ላይ የበላይ ስንሆንና ሀይልን ስንላበስ የትም ቦታ ላይ ያለአንዳች ተግዳሮት እንፈሳለን:: ይሄ ደግሞ በስህተት ውስጥ የመፈጠር ልዕልና ነው:: አንዳንዶች በችግራቸው ሌላ ችግር ይፈጥራሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ በችግራቸው ነጋቸውን ብሩህ ያደርገሉ:: በችግራቸው ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች የእውቀት ባይተዋር ናቸው::
በችግራቸው የሰላምን ግንብ ገንብተው የሚኖሩ እነሱ ደግሞ መለኛ ናቸው:: እኛም ለድሀዋ ሀገራችን መለኛ መሆን ይጠበቅብናል:: በችግራችን ላይ ሌላ ችግር ሳይሆን ችግሮቻችንን የምንሽርበት የመነጋገርና፣ የመወያየት ብልሀትን የእኛ ማድረግ ይጠበቅብናል:: መንግስት እንደ መንግስት፣ ህዝብም እንደ ህዝብ ከችግሩ ተምሮ ለሰላም የሚሆን አቅም፣ ለአንድነት የሚሆን ሀይል ማጎልበት አለበት::
ጥበቦቻችን በትላንት አስተሳሰብ ታውረው የዛሬን በረከት ማየት ካልቻሉ እንደ ለመድንው ከጦርነትና ከመጠላላት አንወጣም:: ጦርነትና እኔነት ባህላዊ ጨዋታችን እስኪመስሉ ድረስ ለዘመናት ኖረንባቸዋል:: ኢትዮጵያዊነት መገዳደል እስኪመስል ድረስ ለዛውም ከወንድሞቻችን ጋር፣ ለዛውም እኛ ከምንላቸው ጋር ደም ተቃብተናል:: ሰው በሰላም ዋርካ ስር መጠለል ሲገባው በመከራ ሮሮ ውስጥ መውደቁ ተገደናል :: ችግሮቻችን ብልህ እንዲያደርጉን እንጂ ሞኝ እንዲያደርጉን መፍቀድ የለብንም::
አለም የስህተት መልክ ናት:: ስህተት ነው እንዲህ ጠፍጥፎ ያበጃት:: የአሁኑ ውብ መልኳ በስህተት ውስጥ የተፈጠረ ነው:: አለም የብዙ ትውልዶች አስተሳሰብ፣ የብዙ ሀሳቦች የስህተት ነጸብራቅ ናት:: በተለያየ ዘመን የመጡ አስተሳሰቦች፣ በተለያየ ዘመን የመጡ አመክንዮ ሀሳቦች አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ በመሆን የፈጠሯት ናት:: እያጠፉ የሳሏት፣ እያደመቁ ያደበዘዟት የልክነትና የስህተት ቅይጥ:: አለም እኮ ዛሬም ድረስ ተሰርታ አላለቀችም..ዛሬም ድረስ ተስላ አልተጠናቀቀችም:: እኛም በብዙ ስህተት ውስጥ አልፈን ነው ዛሬን ያየነው::
ስህተት ውስጥ ጥበብ አለ:: ውድቀት ውስጥ መስፈንጠር አለ:: እኛም ከትላንት እየተማርን፣ ካለፈው እየተረዳን ዛሬን በዋጋ መኖር ግድ ይለናል:: ጠቢብ ሰው ማለት መከራ የማይደርስበት ማለት ሳይሆን ከመከራው ተምሮ አዲስ ዛሬን የሚፈጥር ማለት ነው:: እኛስ ምን አይነቶች ነን? እንደሚታወቀው የሀገራችን አብዛኞቹ ችግሮች ከትላንት ማህጸን ውስጥ የሚመዘዙ ናቸው:: ይህ ማለት ዛሬም ድረስ ከትላንት አስተሳሰብ አሎጣንም ማለት ነው:: ይህ ማለት ዛሬም ድረስ እንደትላንቱ ነን ማለት ነው:: እንደ ሀገር ከትላንት እኩይ አስተሳሰብ መለየት ይኖርብናል:: እንደ ህዝብ፣ እንደመንግስት ትላንትን በይቅርታ የሚሻገር አእምሮና ልብ ልናዳብር ይገባል ::
ሰው በእውቀት ሲዘመን፣ በስልጣኔ ሲቀድም ነገ ላይ በኩራት የሚያወራውን ታሪክ ዛሬ ይሰራል እንጂ በትላንት ጦስ ዛሬን አይኖርም:: ዛሬ ለሁላችንም አዲስ ቀን ነው:: ስለምንድነው በትላንት ነውር ዛሬአችንን የምናጨልመው? ስለምንድነው በአንድ አይነት አስተሳሰብ አንድ አይነት ሆነን የምንኖረው? ይሄ ሁላችንም ጠይቀን የምንመልሰው የጋራ ጥያቄአችን ነው:: ከትላንት አስተሳሰብ ለመውጣት የዛሬን ዋጋ መረዳት ይኖርብናል:: ከትላንት አስተሳሰብ ለመመለስ መንግስትና ህዝብ አዲስ ነገር መናፈቅ ይኖርባቸዋል::
ከትላንት የጦርነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ የትላንትን ቁስል የሚያሽር የፖለቲካ ስርዐት መገንባት ይኖርብናል:: ትላንትን መማሪያ እንጂ መማረሪያ ያላደረገ ትውልድ ሀገራችን ያስፈልጋታል:: እኛ ኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ያመረቀዘው የብሄር ቁስል አለብን:: እኔነትና ተረኝነት የወለደው የመገፋፋት ህመም አለብን:: ራስ ወዳድነትና ጎጠኝነት የጸነሰው የመጠላላት ነቀርሳ አለብን:: ከነዚህ ደዌአችን ለመፈወስ ደግሞ ትላንትን ገሎ መቅበር አለብን:: ከነዚህ ደዌአችን ለመዳን እንደ ትላንት ያልሆነ አእምሮና መንፈስ ያስፈልገናል::
ሰው ወደ ትላንት ሲሳብ የዛሬን በረከት አይደርስበትም:: ስልጣኔ ሊርበን ይገባል:: እድገትና ዘመናዊነት ሊጠማን ይገባል:: ይሄን ሁሉ ዘመን ኋላ ቀርተን እንኳን በሌሎች መቀደማችን አይቆጨንው:: በማይጠቅመን ነገር ያባከንው ጊዜ ሊቆጨን ይገባል::
አንድነት አጥተን የተገፋፋንባቸው ጊዜአቶች ሊያስቆጩን ይገባል:: ትውልድ ካልተቆጨ፣ መንግስት ካልተቆጨ፣ ህዝብ ካልተቆጨ ከትላንት አስተሳሰብ መላቀቅ አይችሉም:: የሀገራችን ሰላም ማጣት፣ የህዝባችን ኋላ መቅረት፣ የፖለቲከኞቻችን አለመግባባት ሊቆጨን ይገባል::
የትውልዱ ብሄር ተኮር አስተሳሰብ፣ በትላንት አስተሳሰብ ዛሬን መኖራችን ሊቆጨን ይገባል:: የስኬት ህግ አስተሳሰብን መሰረት ያደረገ ነው:: የለውጥ ህግ አምናን ሳይሆን ዘንድሮን፣ ትላንትን ሳይሆን ዛሬን የተንተራሰ ነው:: እኛንም ሆነ ሌሎችን የምንቀይረው በአስተሳሰባችን ስንቀየር ነው:: ህይወታችንንም ሆነ ሀገራችንን የምንቀይረው ከማይጠቅሙን አፍራሽ አመለካከቶች ስንርቅ ነው:: ዛሬ ላይ የሀገራችን መልክ ወያባ ነው:: የእርቅና የይቅርታ ሀሳብ አጥታ ሀገራችን ጠውልጋለች:: የውይይትና የተግባቦት መድረክ አጥቶ ህዝባችን ተጎሳቁሏል:: ዳገቱን እናልፍ ዘንድ አዲስ አስተሳሰብ ያስፈልገናል:: ከነበርንበት ዝቅታ ከፍ እንል ዘንድ እውቀት መር የህይወት ልምድ ግድ ይለናል::
ህይወታችንን ከትላንት በመማር እናለምልም:: ሀገራችንን ከትላንት በመማር እናሻግር:: የዚህ አለም ከባዱ ጥፋት ትላንትን ዛሬ ላይ መድገም ነው:: ሰው የትላንቱን ጉስቁልና ዛሬ ላይ ከደገመው፣ የትላንቱን ስህተት ዛሬ ላይ ከመለሰው እንደ ትላንቱ ሆኖ ከመኖር ባለፈ አዲስነት አይጎበኘውም:: ነውር እየመሰላቸው መሳሳትን አጥብቀው የሚፈሩ ብዙ ሰዎች አሉ:: ስህተትን በመፍራት ተጠንቅቀው የሚረግጡ፣ ተጠንቅቀው የሚኖሩ፣ አድብተው የሚንቀሳቀሱ ብዙ ናቸው:: እኚህ ሰዎች ሳያውቁ ራሳቸውን ከጥበብ ያራቁ ናቸው ::
ስህተትን በመፍራት መናገር ያቆሙ፣ መጠየቅ እርም ያሉ፣ መሞከርና መጀመር የፈሩ ብዙ አሉ:: ስህተት አያስፈራም የሚያስፈራው ከስህተት አለመማርና አንድ አይነት ሆኖ መኖር ነው:: የሚያስፈራው በአንድ ጥፋት ሁልጊዜ እየተጸጸቱ መኖር፣ ሁልጊዜ እያለቀሱ መኖር ነው:: የሚያስፈራው በአዲስ አስተሳሰብ ከዘመኑ ጋር አብሮ አለመራመድ ነው:: የሚያስፈራው የዛሬን አዲስ ማለዳ በትላንት ጨለማ መሰወር ነው:: የሚያስፈራው ሀገርና በአዲስ ልብ፣ ህዝብን በአዲስ ተስፋ አለማሻገር ነው::
ህይወት ትምህርት ቤት ናት:: ጊዜ ደግሞ መምህራችን:: እኛ ደግሞ ተማሪዎች:: በዚህ የተፈጥሮ ሂደት ውስጥ ነን:: በህይወት ትምህርት ቤት ውስጥ ጊዜ ሲያስተምረን ጥሩ ተማሪ መሆን ግዴታችን ነው:: ጊዜ ሲያስተምረን ጥሩ ተማሪ አለመሆን ማለት ለመውደቅና ለመሸነፍ መዘጋጀት ማለት ነው:: አለም ደግሞ ለተሸናፊዎች ቦታ የላትም:: አለም የባለራዕዮች ናት::
አለም ራሳቸውን ለመቀየር ከሌሎች ጋር ለሚተባበሩ የተገለጠች ናት:: አለም ተነጋግረው ለሚግባቡ ነፍሶች የተሰጠች ናት:: አለም በትጋትና በጥረት ከፍ ለማለት ለተሰናዱ የተዘጋጀች ናት:: የእኛ ጥሩ ተማሪ መሆን ጥሩ ሀገርና ጥሩ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ላይ የአንበሳ ድርሻ አለው:: ጥሩ የህይወት ተማሪ መሆን ማለት ከትላንት ተላቆ ዛሬን ብቻ መኖር ነው:: ጥሩ ተማሪ መሆን ማለት ከዘልማድ ወጥቶ እውቀት መር በሆነ እሳቤ ሀገርን ማራመድ ነው:: ጥሩ ተማሪ መሆን ማለት ጥላቻን በይቅርታ መሻር ማለት ነው::
በየትኛውም የህይወት ስፍራ ውስጥ ትልቅ ነገር ለማግኘት ስንነሳ የምናጣው ትንሽ ነገር ይኖራል:: አላማችን ትልቁን ነገር ማግኘት እስከሆነ ድረስ የምናጣው ትንሽ ነገር ሊያስቆጨን አይገባም:: አላማችን ሊሆን የሚገባው በትልቅ ሀሳብ ትልቅ ነገር ማግኘት ነው:: በይቅርታ ማሸነፍ ነው:: ዘመኑ በከሸፈ ሀሳብ የምንራመድበት ሳይሆን በታደሰ ሰውነት አንድነትን የምናጠናክርበት ነው::
አሁን ላይ እየባከንን ነው:: በትላንት ዛሬን መኖር አልቻልንም:: እጃችን ላይ ያለውን ውድ ነገር በርካሽ እየቀየርን ነው:: ወርቃችንን በጠጠር እየመነዘርን ነው:: ቁራ ማግኘት ርዕግባችንን እየሸጥን ነው:: ምን እንደሚያስፈልገን ማወቅ አልቻልንም:: የትላንት ስህተቶቻችንን ዛሬም በመድገም ላይ ነን:: ለሰላም ስንደክም፣ ለአንድነት ስንበረታ አንታይም:: ችግሮቻችን ሌላ ችግር ሲፈጥሩብን እንጂ ሰላም ሲያወርዱልን አናይም:: ከስህተቶቻችን መማር ለምን አቃተን?!።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2022