በአሜሪካዋ ዩጂን ግዛት ኦሪጎን ከተማ የሚካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል። የውድድሩ አዘጋጅ ከተማ ኦሪጎንም አትሌቶችን ለመቀበል እየተሰናዳች ትገኛለች። የአትሌቲክሱ ዓለም ምርጥ አትሌቶች ብቃታቸውን ለማስመስከር እንዲሁም የሃገራቸውን ስም ለማስጠራትም ዝግጅታቸውን በማጠቃለል ላይ ናቸው። በስፖርቱ ስመጥር ከሆኑት ሃገራት መካከል የምትመደበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በዝግጅት ላይ ይገኛል።
ከአጠቃላይ ቡድኑ ውስጥም በርካታ አትሌቶች የሚካፈሉበት የ5ሺ ሜትር ወንዶች ምድብ ነው። ለተፎካካሪዎች አስፈሪ በሆነው በዚህ ቡድን የዓለም ቻምፒዮናውን ሙክታር እድሪስን ጨምሮ ከእነተጠባባቂው አምስት አትሌቶች ተይዘዋል። ሙክታር በለንደኑ የዓለም ቻምፒዮና ባልተጠበቀ ሁኔታ የርቀቱን የበላይነትን ከኢትዮጵያውያን እጅ በመንጠቅ የግሉ ያደረገውን እንግሊዛዊ አትሌት በመርታት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የስኬት ጉዞው እንዲደመደም በማድረጉ ይታወሳል። በትውልድ ሶማሊያዊ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ የሆነው ሞሃመድ ፋራህ ለሶስት ዓመታት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ድሎችን ለብቻው በመጠቅለል የዓለም ቁንጮ ሆኖ ነበር። ለንደን ላይ ግን ከፍተኛ ግምት ያልተሰጠው ሙክታር በአስደናቂ አጨራረስ የወርቅ ሜዳልያውን ርቆ ከሄደበት አስመልሶ የሀገሩን ስም ዳግም አስጠርቷል።
የእንግሊዛውያን መመኪያ የሆነው ሞ ፋራህ በወቅቱ መቀደሙን ለማመን የተቸገረ ከመሆኑም ባለፈ የውድድር ሕይወቱም ላይ ለውጥ ያስከተለ ሽንፈት ነበር በሙክታር የደረሰበት። ቻምፒዮናው ሙክታርም የርቀቱን ንግስና እአአ በ2019ኙ የኳታር ዓለም ቻምፒዮናም በድጋሚ በመቀዳጀት የበላይነቱን አስጠብቋል። በዓለም አትሌቲክስ ጋባዥነት በኦሪጎን ቻምፒዮና በቀጥታ ተካፋይ የሆነውና ቡድኑን የሚመራው አትሌቱ ጥቂት ሳምንታት ለቀሩት ውድድር እየተደረገ ስላለው ዝግጅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ዝግጅቱን አስመልክቶ ‹‹እንደሌላው ጊዜ የሀገራችንን ባንዲራ ዝቅ ላለማድረግ በትጋት እየሰራን ነው›› ብሏል።
በቡድኑ ጥሩ ብቃት ላይ ያሉ አትሌቶች መኖራቸውን የሚያነሳው አትሌቱ እርሱ ግን ከነበረበት ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ባያገግምም አብሯቸው በመሆን ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ያደርጋል። መቀመጫቸውን በኔክሰስ ሆቴል ያደረጉት የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ በቃሊቲ፣ እንጦጦ እንዲሁም ሱሉልታ አካባቢ እየቀያየሩ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ እንደ ሌላው ሀገር በሳይንሳዊ ዘዴ ሳይሆን በከፍተኛ ስፍራዎች ላይ ልምምዱን የሚያደርግ ሲሆን፤ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ወቅት ክረምት በመሆኑ በተወሰነ መልክ ዝግጅቱን ከባድ አድርጎባቸዋል። ነገር ግን አብዛኛው የዝግጅት ጊዜ እየተጠናቀቀና ወደ ውድድር እየተንደረደሩ በመሆኑ ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር በማጣጣም እየሰሩ መሆኑንም ያስረዳል።
የለንደን እና የኳታር ቻምፒዮን ዘንድሮ ደግሞ በኦሪጎን ሶስተኛውን ተከታታይ ስኬት በማስመዝገብ ታሪካዊ አትሌት ለመሆን እየተሰናዳ ይገኛል። ሶስቱ ተከታታይ ውድድሮች በአትሌቱ ላይ ያላቸው መልክ ምን ይመስላል በሚለው ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል። ሞ ፋራህን ባሸነፈበት የለንደኑ ዓለም ቻምፒዮና በመልካም ጤንነት ላይ ሆኖ ነበር የተሳተፈው። በኳታሩ ቻምፒዮና ላይ ተጋባዥ ቢሆንም ጉዳት ላይ ሆኖ በመሮጥ ያልተጠበቀ አሸናፊነት በማስመዝገብ ነበር በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያውን ያጠለቀው። ዘንድሮም በተመሳሳይ ህመም ቢገጥመውም ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሮጥ ገልጿል።
በዚህ ርቀት ከእርሱ ጋር የሚሮጡትና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀውን ሚኒማ በማሟላት የተመረጡት አትሌቶች በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አትሌቱ ያስረግጣል። አትሌቶቹ በዓመቱ በነበሩ ውድድሮች ላይ ሲያሳዩ የቆዩት ብቃት መልካም የሚባል ሲሆን፤ እርሱ ያለውን የተሻለ ልምድ በማካፈል ዝግጅቱ እየተከናወነ ይገኛል። በውድድሩ ላይም የኢትዮጵያ ቡድን አራት አትሌቶችን ይዞ መቅረቡ በራሱ ለሌሎች ተፎካካሪዎችን ከማድከም አንጻር የራሱን ሚና ከመጫወቱም በላይ የቡድን ስራ ለመስራትም ይመቻል። በመሆኑም በርቀቱ የተለመደው ወርቅ ይታጣል የሚል ግምት እንደሌለው አመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014