እንደ መውጫ
ዛሬ በመውጫው መግባት ስለአሰኘኝ በመውጫው ገብቻለሁ። አንዳንዴ መውጫችን መግቢያም ሲሆን አቋራጭ ስለሚሆን ድካም ይቀንሳል። ጊዜም ይቆጥባል። በነገራችን ላይ ወደ ገደለው ለሚሉ የአራዳ ልጆችም ስል ጭምር ነው ማጠቃለያዬን ወይም መውጫዬን መግቢያዬ ያደረኩት።
መንግስት ዜጎችን ለልዩነት፣ ለመጠራጠር፣ ለግጭት የሚዳርጉ የፈጠራ ትርክቶችን በገለልተኛ የታሪክ ልሒቃንና በሚመለከታቸው ምሁራን አማካኝነት አስጠንቶ የማያዳግም መቋጫ ሊያበጅ የጥል ግድግዳውን ሊያፈርስ ይገባል። እነ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ደጋግመው ባቀረቡት ምክረ ሀሳብ መሰረት ታሪካችንን መፈተሽ እንደ ገና መበየን ይጠይቃል።ይህን ስል እንደ በጀት ታሪክ በቀመር ይደልደል ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ይሏል።
አማራ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ ገዥ መደብ ኦሮሞን ጨቁኗል? አማራ የሚባል ገዥ መደብስ በእርግጥ ነበረ? አማርኛ የተናገረው ገዥ ሁሉስ አማራ ነው? ገዥ መደቡ ኦሮሞውን ከአማራው በተለየ ሁኔታ ጨቁኖት ነበር? በእርግጥ ኦሮሞው ተጨቁኖ ቢሆን ኖሮ እንዲህ እንደ ዋርካ እንደሰፋ ባህሉን፣ ወጉን፣ ታሪኩንና ቋንቋውን አስጠብቆ ይቀጥል ነበር? ተረካችንንና ንጽጽራችንንስ ዘመነ ጓዴነትን/cont mporaries/የተከተለ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በገለልተኛ አካል ተጠንተው ምላሽ ቢያገኙ የሀሰተኛ ትርክት ልፋፌ ነቢቡን ምስ ሊያስጥሉት ይችላሉ።
አሸባሪው ሕወሓት ወደ አገዛዝ ከመጣ በኋላም በአገዛዝ ላይ ለመቆየት ሲል ኦሮሞንና አማራን መለያየት ስለነበረበት ላለፉት 50 አመታት ጥላቻንና ልዩነት መዋቅራዊ አድርጎ ሰርቶበታል። ሕገ መንግስት ቀርጿል። ሀውልት አቁሟል። ይህ አልበቃ ብሎት እንደ ሸኔ ያሉ አሸባሪ ተላላኪዎችን ስፖንሰር በማድረግ ንጹሐንን እያስጨፈጨፈ ይገኛል።
ሌላው በማንነትና በጎሳ ላይ የተዋቀረውን ሕገ መንግስትንም ሆነ ሀገረ መንግስት ስለማለዘብም የተጀመሩ ጥረቶች ሊጠናከሩ፤ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ አደረጃጀትም በሒደት መውጫ ሊበጅለትና ፊት ሊነሳ ይገባል። በማንነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ መዋቅሩን ይዞ ብልጽግናን ማረጋገጥ አይቻልም። ከፍ ሲልም ከ50 አመታት በኋላ ሒሳብ ስንተሳሰብ ከአተረፍነው ይልቅ የከሰርነው የትየለሌ ነውና። ከልዩነት ይልቅ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ላይ ተጠናክሮ ሊሰራ፤ ፖለቲካችንም በማንነት ሳይሆን በሀሳብ ሊጎለብት ሊታነፅ ግድ ይላል።
ይሄን የምለው የግለሰብ ነጻነት ከተከበረ የቡድን መብትም ይከበራል በሚል ማዕቀፍ ነው። አንድነት ስል አንድ አይነትነት ማለቴም አይደለም። በከፊል አቅጣጫውን የሳተውና የጥራት እጥረት ያኮሰመነው ስርዓተ ትምህርትም መለስ ብሎ የመፈተሹ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎን ብሔራዊ እርቅና እውነትን የማፈላለግ እና በሕወሓት የሴራ ደማሚት የፈረሱ የሕዝብ ለሕዝብ መገናኛ ድልድዮች መልሰው መጠገን አለባቸው።
ግማሽ ክፍለ ዘመን የተሻገረው ከብጥብጥና እርስ በእርስ በጥርጣሬና በጥላቻ ከመተያየት በቀር ብዙ ያላተረፈልን የብሔር፣ የፈጠራና የሀሰት ትርክት ልፋፌ ነቢብ እስከ ገቢር ያለው ምዕራፍ፣ ቀይ መፅሐፍ እልባት ሊያገኝ ይገባል። የፈጠራ ትርክት ልፋፌ ነቢብ ከተቀዳበት ታሪካችን ብንነሳ ሁላችንም ባለዕዳ ነን። ሁላችንም ባለዕዳ ከሆን ደግሞ የየራሳችንን የፈጠራ ትርክት መቅረጽ እንችላለን። ችሎታችን ግን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው። ማናችንም አናተርፍም። የዜሮ ድምር ፖለቲካ እንዲሉ። ባለቅኔውና ወግ ሰላቂው በውቀቱ ስዩም ይሄን ወርክብ ከሌላ ማዕዘን ይመለከተዋል።
“ከአሜን ባሻገር” በተሰኘ ከተለመደ ስራው ወጣ ባለ መፅሐፉ፤ “…ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ ለታሪካዊ በደሎች እውቅና መስጠት ‘ የሚለው አጀንዳ የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል የዴሞክራሲና የፍትሕ ጥያቄ እንዳያነሳ ማፈኛ ዘዴ ነው። … ባለፉት ሁለት/ሶስት አስርት አመታት በኦሮሚያ፣ በደቡብና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብዙ ሰላማዊ የአንድ ብሔር ተወላጆች በግፍ የተገደሉትና የተፈናቀሉት የታሪክ እዳ ተሸካሚ ናችሁ በሚል ጦስ ነው” ይላል።
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓም በምዕራብ ወለጋና በጋምቤላ በንጹሐን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ፤ በሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያና እሱን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች በተለይ በሻሸመኔና በባሌ አንድን እምነትና ማንነት ለይቶ የተፈጸመው ግፍ ግን ያለፉት 27 አመታት ቅርሻ ብቻ ሳይሆን መረር፣ ጨከን ያለና ቀድሞ በደንብ የተመከረበትና የተዘከረበት የሚመስል ነው።
በእውቀቱ እንዳለው በታሪክ ተሸካሚነቱ ሲከፍለው ከነበረው አበሳ በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት።ምንም እንኳ የታሪክ እዳ እንተሳሰብ ከተባለ ከራስ ስሁል ሚካኤል ተነስቶ በአሉላ አባ ነጋ በኩል አርጎ በአፄ ዩሐንስ አልፎ ከቱሉማና ከጃዌ ጎሳ ወገን ከነበረው የዘመኑ አባዱላ ጉጂ ላይ ይደርሳል ይላል ባለቅኔው። ያው ሁሉም ባለዳ ነው ለማለት ነው። እዚህ ላይ ከአባ ዱላ ጋር በአጋጣሚ ሞክሼ መሆኑን ያዙልኝ።
ሬነ የተባለ ሊቅ፣ “ ሀገር ምንድናት “ በተባለ ስመ ጥር ስብከቱ፤ “ ሰዎች ሀገር ለመገንባት ከፈለጉ በታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ አንዳንድ ግፎችን ለመርሳት ዝግጁ መሆን አለባቸው። “ ይላል። እስከ ዛሬ ድረስ በሰለባነት ተለይቶ ግፍ እየተፈፀመበት ያለው ማህበረሰብ ከዚህ የሬነ ምክረ ሀሳብ መጸነስና መቀንቀን በፊት ሀገር ለመገንባት ሲል የተፈጸሙበትን ሁሉ ግፎች ቢተውም ዛሬም የግፈኞች ሰለባ እንደሆነ ቀጥሏል።
ሌሎች ማህበረሰቦች ስለ ሀገር፣ ስለ አብሮ መኖር፣ ስለ ይቅርባይነት ሲሉ፣ ወዘተረፈ ሸክሙን፣ ጥቃቱን፣ በደሉንና ግፉን ካላገዙትና ካልተጋሩት ለብቻው እስከ ምን ድረስ ሊቀጥል ይችላል? እገዛና መጋራት ያልሁት እንደሱ ተበደሉ፣ ተጠቁ ለማለት ሳይሆን ከጥላቻ ፖለቲካ እና ከፈጠራ ትርክት ምርኮኝነት መላቀቅ በራሱ ሸክሙን ማገዝ ነው። ይህን ማድረግ ካልተቻለ መጪው ጊዜ ከባድ መሆኑን ለማሟረት ሞራ ገላጭ መሆን አይጠይቅም። በዚህ ማህበረሰብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘግናኝ ግፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም ማቅማማት፣ መሸፋፈንና ማመንታት በአንድ ድምፅ በማውገዝ ሸክሙን የመጋራት ሒደቱን ሀ ብሎ ሊቀላቀል ይችላል። ዛሬም ቢዘገይም አልረፈደም።
እየተፈፀመበት ያለውን ጥቃት በግልጽ ፍርጥርጥ አድርጎ መነጋገርና እውቅና መስጠት፤ ህመሙንና ቁስሉን የመሸከም ሌላ ጅምር ነውና በተለይ ሸኔ ሰኔ 11 ቀን በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ በብዙ መቶዎች በሚቆጠሩ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና ንጹሐን ላይ የተፈጸመው ለመስማት የሚሰቀጥጥ፤ ለማየት የሚዘገንን ጭፍጨፋ ያለ ልዩነት ማውገዝ ያስፈልጋል።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና በጋምቤላ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋም ሆነ ባለፉት አራት አመታት ማንነትን ኢላማ አድርገው በንጹሐን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በዘግናኝነታቸው፣ በአረመኔያዊነታቸው በጭካኔያቸው የከፉ ናቸው። ድርጊቱን መስማት ይረብሻል። ያማል። ስለ ነገዋ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ እንድንቆዝም አድርጎናል።
በተለይ ከሁለት አመታት በፊት የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ ሰኔ 22 ለ23 አጥቢያ ተጀምሮ ለቀናት የቀጠለው ግፍ፤ የተዶለተ በቂ ዝግጅትና ጥናት የተደረገበት ስለመሆኑ ጭፍጨፋውን ይፈፅሙና ይመሩ የነበሩ እኩያን የሰለባዎቻቸውን ማንነትና የመኖሪያ አድራሻ በጹሑፍ በዝርዝር ይዘው እየተመላለሱና እየደጋገሙ እልቂቱን መፈጸማቸው ነው።
ይህን ላዳመጠና ለተመለከተ የተፈጸመው ግፍ ስርዓትን ከማቆም፣ ሰላምንና መረጋጋትን ከማስፈን፣ ፍትሕና ርዕትን፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በላይ በጥልቀትና ሀቀኝነት ማጣራትን የሚጠይቅ ነው። ሀጫሉ በተገደለ በሰዓታት ልዩነት የተቀነባበረና የተጠና በተቀጣጣይ ፈንጅ የሚታገዝ ሽብር መፈጸምም ሆነ ለመፈጸም ከግብታዊነት የተሻገረ ቅድመ ዝግጅትንና ማቀድን ይጠይቃል።
በአንድ ወረዳ በአንድ ጀምበር 38 የሕዝብ ንብረት የሆኑ ተቋማትን በእሳት ማጋየትና ማውደም በደም ፍላት የተፈጸመ ሊሆን አይችልም። የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው “የአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ሰበብ ነው፤ “ ያሉትን እዚህ ላይ ልብ ይሏል።
በኦሮሚያ በተለይ በምዕራብ ወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብና በሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች የተፈጸሙ ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ጭፍጨፋዎችን በዘላቂነት ለማስቆም ከጀርባ ያሉ መግፌኤዎችን በገለልተኛ አካል አጥንቶ መለየት ይጠይቃል። ከጭፍጨፋዎች በፊት ሴራዎች የተሸረቡበትን፤ ደባዎች የተዶለቱበትን አግባቦች መመርመር፤ ነጥቦችን አገናኝቶ ትርጉም ያለው ምስል ላይ መድረስ እና በዘላቂነት ከምንጩ ማድረቅ የግድ ይላል። በዘመነ ቴክኖሎጂ እንደ ሸኔ ያሉ አሸባሪዎችን ዕንቅስቃሴ ተከታትሎና የመገናኛ ዘዴዎቻቸውን ጠልፎ እየፈጸሟቸው ያሉትን ጭፍጨፋዎች አበክሮ ለምን መከላከልና ማስቆም አልተቻለም የሚለውም መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው።
ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎ ፈሪሃ እግዚአብሔር / አላህ ባደረባቸው ኦሮሞ ጎረቤቶቻቸው ከለላ ከሞት ተርፈው በየቤተ ክርስቲያናቱ ተጠልለው ይገኙ በነበሩ ወገኖች የጭፍጨፋው መሀንዲሶች፤ “ለቃችሁ ካልወጣችሁ ማንም አያስጥላችሁም! አያድናችሁም! አይደርስላችሁም! ቀዬአችንን ከተማችንን ለቃችሁ ውጡ፤ “ የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርሱባቸው እንደነበረ የሚያስታውስ ዜጋ ከጭፍጨፋው ለተረፉ የዛሬዎች ወገኖቹ ምን ዋስትና አላቸው ብሎ ቢጠይቅና ቢሰጋ ሊያስገርም አይገባም።
የሚያሳዝነው ያን ሁሉ ዘግናኝ ግፍና ሰቆቃ በመፈጸሙ ምንም ጸጸት ያልተሰማው አሸባሪ ቡድን የትላንቱን ጭፍጨፋ ከመድገም እንደማይመለስ እንደሰጋሁት ሰሞነኛውን ጨምሮ በርካታ ቅስምና ልብ ሰባሪ ጭፍጨፋዎች በተለይ አንድን ብሔር ኢላማ አድርገው ተፈጽመዋል። እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ከጀርባ ሆኖ አይዟችሁ የሚላቸው የጦር መሳሪያና ገንዘብ የሚያቀርብላቸው ማነው? በእርግጥ ከሕወሓት በተጨማሪ ሌላ ኃይልስ ከጀርባ የለም ወይ? ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም የአካባቢው የአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር ሆነ የክልሉ ልዩ ኃይልስ ለምን የንጹሀንን ህይወት መታደግ አቃተው ? ለእነዚህ ጥያቄዎች የግፉ ሰለባዎች፣ ቤተሰቦችና መላ ሕዝቡ ግልጽ መልስ ይፈልጋሉ።
የክልሉ የአስተዳደርም ሆነ የጸጥታ መዋቅር ከላይ እስከታች ድረስ ለውጡን ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት አምኖ ተቀብሎታል ወይ የሚለው ጥያቄ እዚህ ላይ እንደገና ማንሳት ተገቢ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ጥያቄ የሚነሳው ለሁሉም የብልፅግና ፓርቲ ነው። በቀዳማይ ትህነግ/ኢህአዴግ ትዝታ ዛሬም የሚተክዙና የሚቆዝሙ አባላት፣ አሰራሮችና አደረጃጀቶች ቁጥር ቀላል አይደለምና። ደጅ ከቆሙ ተፎካካሪዎችና አክቲቪስቶች እንደ ኦነግ፣ ኢዜማ፣ ኦፌኮ፣ አብን፣ ከኦጋዴን ነጻ አውጭ፣ ከሲአን፣ ወዘተረፈ ካሉት ጋር ልቡ የሸፈተ፤ አንድ እግሩ ብልፅግና ሌላው እግሩ ውጭ የሆነ፣ ቀን ቀን ብልፅግና ብልፅግና እየተጫወተ መሸት ሲል ሸኔ ሸኔ፣ ኢዜማ ኢዜማ፣ አብን አብን፣ ወዘተረፈ የሚጫወተው ቁጥርም ቀላል አይደለም።
የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ የግፉ ማዕከል epicenter በነበረችው ሻሸመኔም ሆነ ባሌ ( አጋርፋ )፣ ባቱ ከተሞች በተፈጸሙ ቀውሶች ቁጥሩ ቀላል የማይባል የብልፅግና አመራርና የጸጥታ መዋቅር አባላት የዜጎችን፣ ሀብት ንብረታቸውንና የህዝብ የልማት ተቋማት መታደግ፣ መከላከልና መጠበቅ ሲገባቸው የጥፋቱ ተባባሪና ተሳታፊ ከመሆናቸው ባሻገር ቀውሱ ሲከሰት የተጣለባቸውን ድርጅታዊም ሆነ ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን፣ ቃል የገቡለትን አደራ መወጣት ሲገባቸው ስልካቸውን አጥፍተው መጥፋታቸው፤ በእርግጥ የብልፅግና መዋቅር መሬት ላይ አለ እስከማለት ደርሰው ነበር። ያም ሆነ ይህ የኦሮሚያ ብልፅግናም ሆነ ሌሎች መዋቅራቸውን በደንብ መፈተሽ ማጥራት ይጠበቅባቸዋል።
ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ ቀውስ፣ ሰቆቃና ግፍ አስኳል በሆነው አሸባሪው ሕወሓት ነው። ከዚህ ቡድን ጋር ከአንድም ሁለት ጊዜ ወደ ጦርነት ገብተናል። ሶስተኛ ዙር ጦርነት ላለመቀስቀሱም ዋስትና የለንም። በቅድመ ጦርነቱም ሆነ በድህረ ጦርነቱ እንደ ሀገር የከፈልነው ዋጋም ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ የምንዘነጋው አይደለም።
በየትኛውም አለም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሀገር አንጡራ ሀብት፣ በግብር ከፋዩ ገንዘብ እና በሀገር መሰረተ ልማት ሀገረ መንግስቱን ለማፍረስ፣ ሕገ መንግስቱን ለመናድ፣ የእርስበርስ ግጭት ለመቀስቀስ፣ በሀገሪቱ መሪ ላይ የግድያ ሙከራ አርጎ፣ የሀገሪቱን ሀብት በጠራራ በአደባባይ ዘርፎ፣ ለ30 አመታት በዜጎች ላይ የከፋ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ፈፅሞ፣ ሀሳባቸውን የገለጹ ዜጎችን በጅምላ አስሮ ያሰቃየ፣ የገረፈ፣ አካል ያጎደለ፣ የገደለ፣ ወዘተረፈ፤ እንደ አፄ ልብነድንግል “ጦር አውርድ! “ እያለ ምድርን 40 ጅራፍ እያስገረፈ፣ የጎበዝ አለቃ ሆኖ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምን ለመሸጥ ላይ ታች እያለ፣ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር እየዶለተ፣ የሕግ የበላይነትን እየጣሰ፣ ሕዝብን አግቶ እና በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት ሆኖ እያለ፤የለውጥ ኃይሉ ይሄን እፉኝት ቡድን በተለያዩ ተቀባይነት ሊኖራቸውና ላይኖራቸው በማይችሉ ምክንያቶች በጊዜ እርምጃ ባለመውሰዱ አፈር ልሶ ሊነሳ ችሏል።
ከግብፅ፣ ከሸኔና ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር ግንባር በመፍጠር ለውጡን ለማኮላሸት፣ የርስ በርስ ግጭት ለመለኮስ፣ ሀገር ለማፈራረስና በሕዝባዊ ትግል የተነጠቀውን ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ ሌት ተቀን እየማሰነ ይገኛል። የአርቲስት ሀጫሉ ግድያና እሱን ተከትሎ የተከተለው ሁከትም ሰሞኑን በጊምቢ ወረዳና በጋምቤላ ከተማ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እንደ ሰሞኑ ካለ ጭፍጨፋና ሰቆቃ ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቃት!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014