የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ በ1990 እንደ አዲስ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ እንደ ዘንድሮው የውድድር ዓመት መጨረሻው እጅግ አጓጊና ጣፍጭ የሆነበት አጋጣሚ በቅርብ ዓመታት ታይቶ አያውቅም። ከመጀመሪያው አንስቶ የቻምፒዮንነት ጉዞው የአንድ ክለብ ግልቢያ የመሰለው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ የማታ ማታ ከሃያ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች በኋላ ቀድሞ ከነበሩ ግምቶች ተቃራኒ የሆኑ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ሄደዋል። ይህም ትልቁን ዋንጫ የመሳም እድሉ ወደ አንድ ክለብ ብቻ እንዳያዘነብል አድርጎ የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታዎች በጉጉት የተሞላ አድርጎታል።
የሊጉ ያለፉ አምስትና ከዚያ በላይ ሳምንታት ጨዋታዎች ከመጀመሪያ አንስቶ በሰፊ የነጥብ ልዩነት እየመራ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስና በተከታዩ ፋሲል ከነማ መካከል ፉክክሩ እየጦዘ መጨረሻው ሳምንት መርሃግብር ድረስ ዘልቋል። የመጨረሻውና ሰላሳኛው ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ በባህርዳር ስቴድየም ሲካሄዱም ፈረሰኞቹና አጼዎቹ ዋንጫውን የማንሳት ተስፋቸውን ይዘው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የዓምና የሊጉ ቻምፒዮን አጼዎቹ በታሪካቸው ሁለተኛውን ዋንጫ ለመሳም አጀማመራቸው ደካማ ቢመስልም ከሊጉ አጋማሽ በኋላ አስደናቂና ስኬታማ ጉዞ አድርገው ከፈረሰኞቹ ጋር የነበራቸውን ሰፊ የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ በማጥበብ የቻምፒዮንነት ፉክክሩ አጓጊ እንዲሆን ነብስ ዘርተውበታል። ፈረሰኞቹ በአንጻሩ ለረጅም ሳምንታት መሪነታቸውን አስጠብቀው ቢጓዙም በአጼዎቹ የደረሰባቸው የመጀመሪያ ሽንፈትና በተደጋጋሚ ነጥብ መጣላቸው ለአስራ አምስተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት የነገውን የመጨረሻ መርሃግብር እንዲጠብቁ አስገድዷቸዋል።
ያምሆኖ የቻምፒዮንነት እድላቸው በአንድ ነጥብ ልዩነት ከሚከተሏቸው አጼዎቹ የተሻለ ሆኖ ለነገው ወሳኝ ፍልሚያ አድርሷቸዋል። ፈረሰኞቹ ዋንጫውን ለመሳም በነገው የመጨረሻ ፍልሚያ አዲስ አበባ ከተማን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው ይገጥማሉ። ከማሸነፍ ውጪ የአቻ ውጤት እንኳን ፈረሰኞቹ ዋንጫውን ለማንሳት አያዋጣቸውም። በአንጻሩ አጼዎቹ የፈረሰኞቹን ነጥብ መጣል እየተጠባበቁ ከሊጉ ላለመውረድ የሚጥረው ድሬዳዋ ከተማን በነገው ፍልሚያ ማሸነፍ ብቻ የዋንጫ ተስፋቸው ይሆናል።
የሊጉ ዋንጫ ከሁለቱ ብርቱ ተፎካካሪዎች በአንዱ እጅ መግባቱ እርግጥ ነው። ይህም በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክለው በአፍሪካ ታላላቅ ውድድሮች የሚካፈሉበትን እድል ቀድመው እጃቸው እንዲያስገቡ አድርጓቸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ካፍ የአፍሪካን ታላላቅ የክለቦች ውድድሮችን በተመለከተ የክለቦችና የተጫዋቾች ምዝገባ እንዲሁም የውድድሮቹን ቀናት መረጃዎች ይፋ አድርጓል።
የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ካፕ በየአመቱ የአገራት የሊግ አሸናፊዎችና ሁለተኛ የወጡ እንዲሁም የጥሎ ማለፍ ባለድሎችን እንደየአገራቱ የውስጥ ሊግ ህጎች እያሳተፈ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከኢትዮጵያም በየትኛው ውድድድ የትኛው ክለብ እንደሚሳተፍ ነገ የሚለይ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ ነገ የሚጠብቃቸው ፍልሚያ ለሊጉ ቻምፒዮንነት ብቻ ሳይሆን በትልቁ የአፍሪካ ቻምፒዮንስሊግ ለመሳተፍ ጭምር የሚዋደቁበት ሆኗል። የሊጉን ዋንጫ የሚያነሳው ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ያመራል። ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀውም የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል።
ካፍ የ2022/23 አህጉራዊውን ፍልሚያ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን ከቀናት በፊት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በሁለቱም ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሚያስታውቁበት ቀን ወደ ሐምሌ 24 (ጁላይ 31) መገፋቱ ተረጋግጧል። በመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ዙር የሚካፈሉ ክለቦች የሚጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች የሚያስገቡበት ቀን ደግሞ ከሐምሌ 25-ነሐሴ 9 ድረስ መሆኑ ተጠቁሟል።
በካፍ የክለቦች ውድድር ደረጃ የመጀመሪያ 12 ቦታዎችን የያዙት አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ዲ አር ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ጊኒ፣ ሊቢያ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ቱኒዚያ በሁለቱም ውድድሮች ሁለት ሁለት ተሳታፊ ክለቦችን እንደሚወክሉ ይታወቃል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎቹ ሀገራት ግን እንደየደረጃቸው ከመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጀምሮ ጨዋታዎችን እያደረጉ ለዋናው ውድድር የሚበቁ ይሆናል።
የመጀመሪያው ቅድመ ማጣሪያ የሜዳ/ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ከጿጉሜ 4-መስከረም 1/ መስከረም 6-8 ሲደረጉ ሁለተኛው የቅድመ ማጣሪያ የሜዳ/ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ደግሞ መስከረም 27-29/ ጥቅምት 4-6 ድረስ እንደሚከናወን የወጣው መርሐ-ግብር ያስታውቃል። ከቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛው ቅድመ ማጣርያ የወደቁ ክለቦች ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ከጥቅምት 23-30 ተጨማሪ የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ይሆናል። የተጠቀሱትን ዙሮች ያለፉ ክለቦች ከታህሣስ 23-ጥር 23 ድረስ ተጨማሪ የተጫዋቾች ምዝገባ አከናውነው የካቲት 3-5 የመጀመሪያ ጨዋታ ማድረግ ወደሚጀምረው ዋናው ውድድሩ እንደሚያመሩ ተመላክቷል።
ክለቦች በውድድሩ የሚጠቀሙባቸውን 40 ተጫዋቾች ማስመዝገብ ሲችሉ በተጠባባቂ ወንበር ላይ 9 ተጫዋቾችን አድርገው በጨዋታ 5 ተጫዋቾችን የመቀየር መብት እንዳላቸው ተጠቁሟል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2014