ለገለልተኝነት የማንታማ በርካታ ዜጎች የፖለቲካውንና የፖለቲከኞችን ጉዳይ አብጠርጥረን፣ ፈትነንና ፈትገን ገለባው በርክቶ የሚያጠግብ ፍሬ ስላጣንበት ባለጉዳዮቹ በእጃቸውና በአፋቸው የሚያሽሞነሙኗቸውን “የሥልጣን መናጠቂያ ሰነዶቻቸውን (ፕሮግራሞቻቸውን)” በሰንዱቅ ውስጥ አሽገን ካስቀመጥን ሰነባብቷል። አንዳንድ እርባና ቢስ “ማኒፌስቶዎችንም” በገለጥናቸው ጊዜ ሁሉ ከሚያበግኑንና ከሚያሾፉብን ብለን እንደሚሆን እንደሚሆን አድርገናቸዋል። ምክንያቱም በሰነዶቹም ሆነ በሰናጆቹ ሕይወት ውስጥ ምሳሌነትና ተስፋ ስላጣንባቸው ምን ይሉት ሞራል ኖሮን “ይደልዎ” እያልን እናሞካሻቸዋለን?
“ትልቁ የሕገ መንግሥት መጽሐፍ ተብዬውም” ቢሆን “ቄሱም ዝም፣ መጽሐፉም ዝም” እንዲሉ፤ መከራና አሳር ገጥሞን አዬዬ እያልን ለትድግና ስንጮኽበት የማይመልስ ዲዳ፣ የማይራመድ ሽባ፣ የማይወስን ፈሪ፣ ጨከን ብለው ሲቆጡት ደግሞ “እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ” እያለ “ዱታ ነኝ ባይ” መሆኑ፣ አቅምህን አሳየን እያሉት እድል ሲሰጡት ደግሞ “ልፍስፍስ” እያለ “ካብ አይገባ ድንጋይ ስለሚሆንብን” በዚያም ብንል በዚህ ተስፋ አጥተን ግራ መጋባት ውስጥ ስለተዘፈቅን “ለጊዜ ጊዜ በመስጠት” ከገጾቹ ጋር ተኳርፈን ዓይናችንን ከገጾቹ ላይ ካነሳን ሰነባብቷል።
ከላይ የተጠቀምንባቸው ቃላት በእጅ የተቀረጸ ጣኦትን የሚሄስ አንድ ግጥም ያስታውሰናል። ከስንኙ ውስጥ አንድ ቃል ብቻ ለውጠን እንጥቀሰው፡-
[ሰነዳቸው] ዐይን አለው አያይም፣
አፍ አለው አያውራም፣ ጆሮ አለው አይሰማም።
እርሱንም ሁሌ ይሸከሙታል፣
ወደዚያ ወደዚህ ያረጉታል…
(ግጥሙ አልተጠናቀቀም)
ለምን እንዲህ መረር ለማለት እንደተፈለገ ከራሱ ከሰነዱ እየጠቀስን በምሳሌ እናስረዳ። “ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው – አንቀጽ 18፡1” እና አንቀጽ 24 ላይ ደግሞ “1. ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፣ 2. ማንኛውም ሰው የራሱን ስብዕና ከሌሎች ዜጎች መብቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በነፃ የማሳደግ መብት አለው፣ 3. ማንኛውም ሰው በማንኛውም ስፍራ በሰብዓዊነቱ እውቅና የማግኘት መብት አለው” የሚሉትና በአንቀጽ 28 ላይ የተዘረዘሩትን “በስብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች” የሚለውን “በቃላት ተቆንጃጅቶ ለተግባር የኮሰመነውን” ክፍል እንዳለ ብንዘከዝከው ብዙ ሰዎችን ስለሚያበሳጭ ያለመነካካቱን መርጠናል። “የወረቀት ነብር” የሚለው አባባል ይታወስ።
ወዲያም ብንቃብዝ ወዲህ፤ “በሰዎች አእምሮ የተደረሱ ሰንዶች” ህመም ላይ የጣለንን ወቅታዊ ሀገራዊ ደዌ በቃላት ቅባት ማበስ ካልሆነ በስተቀር ሰንኮፉን ነቅለው ሊፈውሱልን ስላልቻሉ ፊታችንን ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ለመመለስ ግድ ይለናል። ለምን ቢሉ፡- ዘጠና ዘጠኝ ከምንትስ ፐርሰንት ዜጎቿ “ተግባሩ እንኳን ቢቀር፣ ለወጉ ያህል የእምነት ቤተሰቦች ናቸው” በማለት ሀገራዊው እስታትስቲክስ “ሊያቄለንም ይሁን ሊያደፋፍረን” እቅጩን ስለሚነግረን “በዓለማዊው መንግሥታዊ ሚዲያዎች ላይ የቅዱሳት መጻሕፍት ምክሮች” እንዲስተናገዱ የብረት በሩ መከፈት አለበት።
“ምን ሲደረግ!” የሚሉ ተቆጭዎች “ዘራፍ የሚሉ” ከሆነም “እንደየእምነታችን በሕዝባዊ ሚዲያዎች ላይ መጽናናትን አትከልክሉን” በማለት “በሕግ አምላክ! በጉልበት አምላክ! ወይንም በእውነት አምላክ!” እያልን በመማጸን አደብ እንዲገዙ ብንጠይቅ ተዳፈራችሁ ልንባል አይገባም። ሌላ ተስፋ የሚያሳዩን ከሆነም እሰየው እንዲያመላክቱን ልባችንንም፣ ዓይናችንንም ሆነ ጆሯችንን እንከፍትላቸዋለን።
ይህንን መሰሉን ተማጽኗችንን የሚያከብሩ ከሆነ ይህ ጸሐፊ ብቻም ሳይሆን ሌሎቹ የዚህ ጋዜጣ ቤተኞችም አልፎ አልፎም ቢሆን ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በየእምነታችን እየተከባበርን የሚያንጹንን፣ ከክፋትና ከጭካኔ የሚከለክሉንን፣ ልጓሙን ለቆ የሚጋልበው ቀልብያችንም አደብ ገዝቶ እንዲሰክን የሚመክሩ አናቅጽን ቢያስታውሱን አይከፋም። ወደ መልካምነት የሚመሩን፣ በትንሽ በትልቁ ምክንያትም ሽንቁር የበዛበትን የሀገራችንን ወቅታዊ መጠፋፋትና አሳፋሪ ገመናዎች እንድንደፍን ቢያስተምሩን ጽድቅም በጎነትም እንደሆነ ሊታመን ይገባል። በዚሁ መሠረትም በዛሬው ጽሑፍ ህሊናችንን የሚሞግት አንድ አንቀጽ ከቅዱስ መጽሐፍ ጠቅሰን እንንደረደራለን፡-
“እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው። ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች። ትዕቢተኛ ዓይንን፣ ሐሰተኛ ምላስን፣ ንጹሕ ደምን የሚያፈሱ እጆችን፣ ክፉ ሃሳብን የሚያውጠነጥን ልብን፣ ወደ ክፋት የሚቻኮሉ እግሮችን፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሃሰተኛ ምስክርን፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚዘራ ሰውን።” (ምሳሌ 6፡16 – 19)።
ፈጣሪ የተጠየፋቸው እነዚህ ሰባት የደደሩ በደሎችና ኃጢያቶች ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን፣ ለመከራ እንደዳረጉንና የእምባ ምክንያት እንደሆኑን ብዙዎቻችን ምስክሮች ነን። ምስክርነቱን ሰፋ እናድርገው ከተባለም የውጤቶቹን ገፈት በነጋ በጠባ የሚጎነጨውን ሕዝብ በጅምላ ዋቢ መጥራት ይቻላል።
በትዕቢተኛ ዓይን የተጠቁ፣ በሐሰተኛ ምላስ ተነድፈው ፍትሕ የተዘባባቸው፣ ንጹሕ ደም ባፈሰሱ እጆች መከራ የወደቀባቸው፣ ክፉ ሃሳብ ሲያውጠነጥኑ አድረው የብዙዎችን ቤት ያዘጉና ተስፋቸውን ያመከኑ፣ በክፋት በተበከሉ እግሮች እየተሽቀዳደሙና በማደነቃቀፍ የበርካቶችን ሩጫ መና ያስቀሩ፣ በዋሾዎች ምስክርነት ኑሮና ሕይወት የተመሰቃቀለባቸው፣ በወንድማማቾች መካከል የጠብ አሜክላ እየዘሩ ደም ያቃቡና ያጫረሱ ብዙዎች ናቸው። ከፍ ሲልም በእነዚህ እኩይ የማሕበረሰብ አራሙቻዎች ጥቁር ከል የለበሰችው ሀገር ራሷ ናት።
መልካቸው የተዥጎረጎረው እኒህን መሰል የአመጽና የበደል ተግባራት ከትናንት ይልቅ ዛሬ፣ ከአምና ይልቅ ዘንድሮ በግላጭ እያስተዋልን ብቻ ሳይሆን ጥቃቱ አይሎብን ሕይወት መሮብናል። ግፉን ለመሸከምም ወገባችን ጎብጧል። በእውነት እነዚህን የከፉ በደሎችና ግፎች የፈጣሪ ዓይኖች እያስተዋሉ ጆሮውም የግፉዓንን እሪታ እየሰማ ታግሶ ዝም ይላልን? በፍጹም። የፈጣሪ ፍርዱ ይዘገይ ካልሆነ በስተቀር ይቀራል ማለት የአምላካዊ ባህርይው መገለጫ አይደለም። የምድራዊ በደል ፍጻሜ በዘለዓለማዊ ኩነኔ እንደሚጠናቀቅ የየትኞቹም እምነቶች ቅዱሳን መጻሕፍት አስረግጠው የሚያስተምሩት አይቀሬ እውነታ ስለሆነ ጥርጥር አይገባንም።
የኢስላም ሃይማኖት መምህራን “ተውበት – “ወደ አላህ መመለስ” የሚለውን የሃይማኖት መርህ የሚያብራሩት እንዲህ በማለት ነው። “የኢማንን (ልባዊ የሆነ እምነት ማለት ነው) ጥንካሬ ከሚፈጥሩት ውስጥ በጣም አስፈላጊውና ተቀዳሚው ተውበት ወይንም ወደ ፈጣሪ ለመመለስ መወሰን ዋነኛው ጉዳይ ነው። ኃጢአትን የማያከብድ፣ ነውርን የማይገልጥ፣ ለዚህም ዋጋ የማይጠየቅበት መሠረታዊ እውነታው ወደ ፈጣሪ ተመልሶ ከኃጢያትና ከበደል መራቅ ነው።
“ተውበት” የፈጣሪን ተውፊቅ (እገዛና ብርታት) የሚፈልግ ቢሆንም የሚከብድ ግን አይደለም። ከአማኙ የሚጠበቀው ከስህተት መመለስ፣ ከጥፋት መጸጸት፣ ዳግም በደል ላለመፈጸም መወሰን ብቻ ነው። ከክፋት መራቅ፣ ለወንድማማች ጠብ ምክንያት ያለ መሆን፣ ፍትሕንና ርትእን በማጓደል በደልን በራስ ላይ ያለማንገስ በላጲስ የሚመሰሉ ናቸው፤ በኃጢአት የቆሸሸና ያደፈ ነፍስን ለማጽዳት ኃይል አላቸውና።” በማለት አስተምህሮው ይመክረናል። የቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ እንደተከበረ ሆኖ የህሊናችንም ድርሻ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ህሊናችን “የፈጣሪን እውነት ለመግለጽ ውክልና ወስዷል” እየተባለ በተለምዶ መነገሩም ስለዚሁ ነው።
በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውሎ አምሽቷችን ውስጥ የምናስተውላቸውና የምናደምጣቸው በርካታ ጉዳዮች ጆሯችንን ጭው ከማድረግ አልፈው ለድንዛዜም ምክንያት ሆነውናል። በቅርቡ በነበረው የፓርላማ ውሎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶ/ር) የሕዝብን ጸጥታ እንዲያስከብሩ በትከሻቸው ላይ ከፍተኛ ሀገራዊ አደራ የወደቀባቸው አንዳንድ የጸጥታ ክፍል ባልደረቦችና ለፍትሕ አካላት ቤተኛ የሆኑ ግለሰቦች እጃቸውና ህሊናቸው ንጹሕ እንዳልሆነ በግልጽ ቋንቋ አረጋግጠውልናል። ምንም እንኳን የልቅሷችን ዋና ሰበቦች ከሆኑ ቢሰነባብቱም።
የፍትሕና የርትእ ምንጩ የደፈረሰ ከሆነ ሌላው ሀገራዊ ጉዳያችን እንዴት ኩልል ብሎ ሊጠራ ይችላል? ችግሮቻችን ሊከፉብን የቻሉት ነገራችን ሁሉ “ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ፤ ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ” ብጤ ስለሆነብን ሳይሆን አይቀረም።
አንድ ሀገራዊ ተስፋ ብልጭ ብሎ እኛ ዜጎችም በደስታ እየተፍነከነክን “ጥርሳችንን ብልጭ” ማድረግ ገና ስንጀምር ለእምባና ለኀዘን የሚዳርጉ ችግሮች ተግተልትለው ከፊታችን ይገሸራሉ። “በቅንነትና በታማኝነት” ሕዝብን ለማገልገል በአደባባይ መሃላ ገብተው በሥልጣን ወንበር ላይ ፊጥ ያሉ “ባለጊዜዎች” ሳይውሉ ሳያድሩ የአስመሳይነት ካባቸውን አውልቀው “ለሆድና ለነፍሳቸው” ማሸርገድን ስራዬ ብለው ይያያዙታል። ቃል የእምነት ዕዳ መሆኑን ዘንግተው ቃል ለራስ የሚቆርሱት እንጀራ እንደሆነ በመቁጠር ለነፍሳቸው ብቻ ሲዳክሩ ይስተዋላል።
አንዳንዱ ተመርጦ የሕዝብ ወኪል እስኪባል ድረስ በጠባይም ሆነ በግብር ፊት ፊት እየቀደመ “ከሰል ካላነጣሁ፤ ወተት ካላጠቆርኩ” እያለ ማማለሉን ይችልበታል። ተመርጦ የሕዝብ አደራ በተሸከመ ማግስት ግን “የተውኔት ካባውን አውልቆ” የውስጥ ምኞቱን ገመና ይፋ በመግለጥ ኑሮውን ሊያደላድል ይርመጠመጣል። ከሰኔ እስከ ሰኔ አጃኢብ ካሰኙንና “ዘንድሮ፣ ዘንድሮ” እያልን እንድናንጎራጉር ምክንያት ከሆኑን ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህ ትዝብት ነው።
“ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣
የስንቱ ተወርቶ፣ የስንቱ ተነግሮ – ዘንድሮ።
በዚያኛው ተገርመን ጥቂት ሳንቆይ፣
የዚህኛው መባስ አያስቆጭም ወይ።”
ብለን እምባ በተቀላቀለበት መነፋረቅ አንድንቆዝም የተገደድንበት አንዱ ብሶት የሚገለጸው በዚህ መልኩ ነው።
በአንድ የግል ገጠመኝ ጉዳዩን ለማሳየት ልሞክር። ይህ ጸሐፊ “እኛን ለመወከል ስለሚመጥኑ ድምጻችንን አንንፈጋቸው” በማለት ለብዙ ወዳጆቹ ቅስቀሳ ካደረገላቸው አንዱ “የተከበሩ” የሚለውን ክብር ከተጎናጸፈ በኋላ፤ “ሀገርና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥለውን ይህንን ጉዳይ ለሚመለከተው ክፍል በፍጥነት አድርሰህ መፍትሔ ይፈለግለት” ብሎ ሲያማክረው (ያውም ከብዙ የስልክ ሙከራ በኋላ) በድምጹ ውስጥ ሥልጣኑን እየገለጸ የሰጠው መልስ፤ “ምን ያስደንቃል ሀገሪቷ ውስጥ እኮ ከዚህም የከፉ በርካታ ችግሮች ሞልተዋል። ሊገርመን አይገባም” የሚል ነበር።
እርግጥ ነው ሀገሬ ወደፊት እንዳትገሰግስ በየጎዳናዎቿ ላይ “የአረንቋ ሐይቆች” እያሰነካከሉ ጉዞዋን ለመግታት እንደሚሞክሩ አያየንና እየሰማን ነው። የውጭ ጠላቶቻችን የሚወረውሩብን የጥፋት ቋጥኞች ለሕዝብ የሚገለጡት ከመከኑ በኋላ እንጂ በነጋ በጠባ “ይህንና ይህንን የመሳሰሉ ሴራዎች እየተሞከሩብን ነው” እየተባለ ቢገለጽ ኖሮ ድብርት ውስጥ ይከተን ነበር።
ይህም ያነሰ ይመስል በዘርና በብሔር ተኮር እየተፈጸመ ያለው የልጆቿ እልቂት ሀገሬን እንደ ቅዱስ መጽሐፏ ራሄል “እንባዋን ወደ ጸባኦት እንድትረጭ” ግድ ብሏታል። በዚህም ምክንያት እስከ ዛሬም ድረስ የኀዘን ጨርቋን እንኳን ለመቀየር ፋታ አላገኘችም። እርግጥ ነው እንደ ሕዝብ ከውስጥና ከውጭ ፋታ የሚነሱን በርካታ ወጀቦች ቢያስገመግሙም ችግሮቻችን ጊዜያዊ እንጂ በቋሚነት ስለማይዘልቁ ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቧ እንዳነቡ አይኖሩም። ለዚህ ነው ወደ ቀልባችን ተመልሰን ከበደል እጃችንን እናንጻ፤ ከመጻኢ ኩነኔም እንጠበቅና የየድርሻችንን ኃላፊነት እንወጣ የሚል ምክር ለመወርወር የተገደድነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2014