በፈጠራ ሥራ የሚሰማሩ ወጣቶችን መደገፍ አገር የምትሻውን ጠንካራ አቅምና እድገት ለማምጣት ወሳኝ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች የኑሮ ዘይቤን ከማሻሻል ባሻገር ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር ይረዳል። ለዚህ ነው መንግሥታት ፖሊሲዎቻቸውን ሲቀርጹና ረዘም ያሉ የእድገትና ምጣኔ ሀብት አስተዳደር እቅድ ሲነድፉ ብሩህ አእምሮ ያላቸው የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚደግፉበትን መንገድ በቀዳሚነት የሚያመቻቹት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ አጋዥ ሚና ያላቸው የቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል እንዲሁም የተለያዩ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶችን የሚያግዙ የፈጠራ ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ግለሰቦችን በልዩ ሁኔታ የማበረታታትና የመደገፍ ፖሊሲዎች እየተከተለ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። በዋናነትም ታዳጊዎች ክህሎታቸውን አዳብረው እምቅ አቅማቸውን ለአገር ልማት እንዲያውሉ በትምህርትና ማሰልጠኛ ተቋማት ለማገዝ እየተሰራ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ እርምጃ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን በመሰብሰብ፣ በማብቃት፣ ወደ ውጤት በመቀየርና የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢትዮጵያ ያላትን ብዙ የወጣት ኃይል ሀብት መጠቀም የምትችልበትን ሥርዓት ይፈጥራል።
ከዚህ ባሻገር የግል ተቋማት፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ያሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አካላት ልዩ ልዩ ዘርፎች በቴክኖሎጂና አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦች ታግዘው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በፕሮግራማቸው ድጋፍ ሲያደርጉ ይስተዋላል። በተለይ ወጣቶች የፈጠራ አቅማቸውን እንዲጠቀሙና ሃሳቦቻቸውን እውን እንዲያደርጉ ለማገዝ በግል ተቋማት አማካኝነት የሚቀረጹ ፕሮጀክቶች አሉ።
የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድ ላይ መንግሥት ዘርፉ እንዲያድግና የፈጠራ ባለሙያዎች አቅማቸውን ተጠቅመው ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የሌሎች አካላት ድርሻ ምን ይመስላል? የሚለውን ሃሳብ ለመዳሰስ እንሞክራለን። በተለይ በቅርቡ የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚረዳ የፈጠራ ውድድር ስላዘጋጀው ሄይፈር ኢትዮጵያ “አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ” እና ውድድሩን ተካፍለው በስኬት ስላጠናቀቁ ወጣቶች የሚከተሉትን ጉዳዮች እናነሳለን።
ማህደር አካሉ በሄይፈር ኤንድ ሰስቴነብል ኢትዮጵያ የአዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ መሪ አዘጋጅ ነች። ሄይፌር ኢትዮጵያ ስላዘጋጀው የግብርና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውድድር፣ እውቅና መስጠትና ሽልማትን በተመለከተ ላነሳንላት ጥያቄዎች በሚከተለው መልኩ ምላሽ ሰጥታናለች።
ስለ ሄይፈር ኢንተርናሽናል ተልእኮ ስትናገር “ምድርን እየተንከባከቡ ረሃብን እና ድህነትን ማጥፋት ነው” በማለት ላለፉት 75 ዓመታት ኑሮ ለከበደባቸው ማሕበረሰቦች የከብት እርባታ እና የዘላቂ ግብርና ሥልጠና እና ድጋፍ ሲሰጥ የቆየ ተቋም እንደሆነ ትናገራለች። በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በ21 አገሮች የሚገኙ የአገር ውስጥ ምግብ አምራቾች ንግዶቻቸውን እንዲያስፋፉ እና ለመኖር የሚያስችል በቂ ገቢ እንዲያገኙ ለማገዝ እየሰራ መሆኑንም ትገልፃለች።
እንደ መሪ አዘጋጇ ማህደር ገለፃ በ2021 ሄይፈር ከመላው አፍሪካ ለተውጣጡ እጅግ ተስፋ የሚጣልባቸው የግብርና ቴክኖሎጂ ኢኖቬተር ወጣቶች የገንዘብ ስጦታ የሚሰጠውን አዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ በይፋ አስጀምሯል። የአዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ በአህጉሪቱ ካሉት ታላላቅ የግብርና ውድድሮች አንዱ ለመሆን ያለመ ሲሆን፤ ይህም የአፍሪካ ወጣቶችን ኃይል ከተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማጣመር በመላ አፍሪካ የሚገኙ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች ምርታቸውን እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የማድረግ ርእይ ያለው ነው። ይህንን ለማሳካትም፣ ሄይፈር በያዝነው ዓመትም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የፈጠራ ውድድሮችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማዘጋጀት አቅዶ፣ የመጀመሪያውን ሀገራዊ የግብርና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውድድሩን ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች “አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ” በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ አካሂዷል።
ሄይፈር ኤንድ ሰስተነብል ኢትዮጵያ ከበርካታ የመንግሥት አካላት እና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ውድድሩን መርቶታል ያለችው ማህደር አካሉ፤ አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ የአህጉር አቀፉ የአዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ ሀገር አቀፍ መልክ መሆኑን ትገልፃለች። የአዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና ምርትና ምርታማነትን፣ ገቢን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን የመቋቋም አቅምን መፍጠር የሚችሉ የግብርና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሃሳቦችን መርጦ መሸለም ነው። አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ወጣት አመልካቾች ልቀው ለሚወጡ ወጣት የአግሪ-ቴክ ፈጠራ ባለሙያዎች በሙሉ ክፍት እንደነበርም ታስረዳለች።
የመጨረሻው ቀንና የውደድሩ አሸናፊዎች
የሄይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል አዩቴ ቻሌንጅ የመጨረሻ የአመልካቾች ውድድር በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ነበር የተካሄደው። በቴክኖሎጂ ውጤት አዲስ የፈጠራ ሃሳብ ውድድሩ ተመዝግበው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ለመጨረሻው አምስት እጩ ተወዳዳሪነት የተመረጡት ወጣቶችም በስፍራው ተገኝተው ሃሳባቸውንና የሰሩትን ሥራ ለዳኞች፣ ለተጋባዥ እንግዶች ማቅረብ ችለዋል።
ፕሮጀክቶቻቸውን ባቀረቡበትና የመጨረሻ አሸናፊ ይፋ በሆነበት እለት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ የዲግሪ ተመራቂ የሆነችው መስከረም የማነ አንደኛ በመውጣት 10 ሺህ ዶላር አሸናፊ ሆናለች። ወጣቷ የፈጠራ ባለሙያ መስከረም ለገበሬው በተለይ ደግሞ የዶሮ እርባታ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩ አርሶ አደሮች ሽታን የሚቀንስና ምቹ የሆነ “የዶሮ ማርቢያ ቤት” በመስራትና በማስተዋወቅ ነው ተሸላሚ መሆን የቻለችው።
መሪ የፕሮግራሙ አዘጋጅ የሆነችው ማህደር አካሉ ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሰችን መረጃ መሰረት የዶሮ ማርቢያው ለአሶአደሩ ኑሮ መሻሻል፣ ዘመናዊ የማርቢያ ዘዴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ስለታሰበበት በዳኞች ተመርጦ ለአሸናፊነት መብቃቱን ነግራናለች። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ዶሮ የማርባትና ለገበያ የማቅረብ አቅም ቢኖርም በዘመናዊ መንገድ በብዛትና ጥራት የሚሰራው ሥራ ግን አነስተኛ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህ እንደ አንድ ችግር ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ ቴክኖሎጂን መሰረት አድርጎ የመስራት ተግዳሮት በመኖሩ ነው። ይህንን መሰል ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ሄይፌርን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘርፉን ለማበረታታት እየሰሩ ይገኛሉ።
ሌላኛው “የአዩቴ ቻሌንጅ” የግብርና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ተወዳዳሪ በመሆን ከአምስቱ የመጨረሻ እጩዎች ወስጥ ውድድሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ይስሃቅ አምደስላሴ ነው። ወጣቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከወሎ ዩኒቨርሲቲና በማኔጅመንት ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሲሆን፣ በአዩቴ የግብርና ቴክኖሎጂ ውድድር ላይ የሰራው ፈጠራ የግብርና መረጃዎችን በቀላሉ ለተጠቃሚዎች የሚያደርስ መተግበሪያ “ኢንተራክቲቭ አፕሊኬሽን” (AgrInfoBot) ነው። አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ከመረጃ መዛባትና ትክክለኛነት አንፃር ምርትና ምርታማነትን ጨምሮ በርካታ ኪሳራዎች እንደሚደርሱ ይታወቃል። የዚህ ወጣትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያም ይህንን ለማስቀረት ያግዛል ያለውን መተግበሪያ በመስራቱ ምክንያት የአዘጋጆቹንና የዳኞቹን ቀልብ በመሳብ የሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የ6 ሺ 500 የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ መሆን ችሏል።
በአዩቴ የግብርና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ ላይ በመጨረሻ አምስት እጩነት ከቀረቡት ውስጥ የሦስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ደግሞ ሳሙኤል ጌታቸውና ዮሴፍ ላቀው ናቸው። በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (አስቱ) የኤሌክትሪካል ኮምፒዩተር ኢንጅነሪንግ እንዲሁም የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆኑት ሁለቱ የፈጠራ ባለሙያዎች “ከመህር በፊትና በኋላ” የግብርና የባለሙያ ምክር አርሶ አደሩ የሚያገኝበትን ዲጂታል መተግበሪያ መስራት ችለዋል። ይህ ቴክኖሎጂ ተግባር ላይ ሲውል በቂ የባለሙያ ምክር የሚገኝበትን አማራጭ የሚፈጥር መሆኑ በዳኞች ታምኖበት በሦስተኛ የአሸናፊነት ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ችሏል። በዚህም 3ሺ 500 የአሜሪካ ዶላር አሸናፊ በመሆን ከአዘጋጆቹ የእውቅና ሽልማት ተቀብለዋል።
የእለቱ መልእክት
በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው የመጨረሻ ዙር ውድድር ላይ በርካታ እንግዶች ተገኝተው ነበር። ከእነዚህ መካከል የሥራና ክህሎት ሚኒስትቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ይገኙበታል። በመልእክታቸውም “ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሄይፌርን የመሳሰሉ የግብርና ቴክኖሎጂን ለማላቅ ለሚሰሩ ወጣቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ ያበረታታል” ከማለታቸውም ባሻገር በውድድሩ ላይ ተካፋይ ሆነው ላሸነፉት የፈጠራ ባለሙያዎች እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሱ አፅንኦት ሰጥተው ከተናገሩት መካከል በቅርቡ የገጠር ሥራ አጥነት ዋነኛው ነበር። በአስደንጋጭ ፍጥነት እያደገ መሆኑን አንስተው ግብርናው በበቂ መልኩ ሥራ መፍጠር አለመቻሉን ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ፣ በረሃማነት እና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች ውስጥ ያለው ጨዋማነት፣ ከፍተኛ ዝናብ በሚዘንብባቸው አካባቢዎች አሲድነት፣ ተባዮች እና በዝናብ ጥገኝነት ምክንያት በርካታ ችግሮች እንደሚከሰቱም አንስተዋል። ይህንን ችግር ለመቋቋም መሰል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎችን ማበረታታት እንደሚያስፈልግም አንስተው መንግሥት በቂ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አዴሱዋ ኢፍዲ በሄይፈር ፕሮጀክት ኢንተርናሽናል፣ የአፍሪካ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው። በውድድሩ መክፈቻ ላይ በተመሳሳይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ሰፊ ምርት ሊሰጥ የሚችል መሬት፣ የሰው ሃይል እንዳለ ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆኑና አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ላይ መስራት የሚችሉ ወጣቶች በብዛት እንዳሉ በመግለጽም ይህን ማቀናጀትና መስራት ከተቻለ እራስን ከመመገብ አልፎ ለቀሪው ዓለም የሚተርፍ የግብርና አቅም መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል። ሄይፌር ኢንተርናሽናልም ይህን ለመደገፍ መሰል ፕተሮጀክቶችን በመቅረጽ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
ስለ አዩቴ ኢትዮጵያ
ሄይፈር በጣም ተስፋ ለተጣለባቸው ወጣቶች የግብርና ቴክኖሎጂ (አግሪቴክ) ፈጣሪዎች የገንዘብ ድጎማዎችን ይሸልማል። ይህን እሚያደርገው በአፍሪካ በሚያካሂደው ዓመታዊው አዩቴ “AYuTe Africa Challenge” በኩል ነው። ይህ የውድድርና ሽልማት ፕሮጀክት በየዓመቱ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ነው። በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል እና ኡጋንዳ በ2022 በእያንዳንዱ ሀገር እስከ 20 ሺህ ዶላር ይሸለማሉ። አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ፣ የግብርና ቴክኖሎጂ (አግሪ-ቴክ) ፈጠራ ውድድር ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተዘጋጀ ሲሆን በሄይፈር ፕሮጄክት ኢንተርናሽናል ተነሳሽነት በግንቦት 23 ቀን 2022 በይፋ የተጀመረው ነው። ብቃት ያላቸው ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችንና ጀማሪዎችን የመለየት እና የመሸለም ዓላማ ከመያዙም በላይ አነስተኛ ገበሬዎችን ለመርዳት አዲስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለውጥ የሚያመጣ አስተዋፅዖ በማድረግ እና በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ማሻሻልን ታሳቢ ያደረገ ነው። ውድድሩ ከ 18 እስከ 29 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ እና ለሁሉም ወጣት ኢትዮጵያውያን ክፍት ነበር።
በስምንት ቀናት ውስጥ በጠቅላላው 535 ማመልከቻዎች ቀርበው ነበር። ከአጠቃላይ አመልካቾች 56 ሴት እና 479 ወንድ ነበሩ። በተጨማሪም 108 አመልካቾች የዩኒቨርሲቲ ወይም የኮሌጅ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ 228 አመልካቾች ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። 59 አመልካቾች የማስተርስ ዲግሪ የያዙ ሲሆን 56 ደግሞ 12ኛ እና ከዚያ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው ነበሩ። ይህም በኢትዮጵያ ወጣቶች ለፈጠራ ሃሳብ እና ክህሎት የሚሰጡት ትኩረት እጅግ አበረታች መሆኑን የሚያመላክት ነው። ፕሮጀክቱ ለእነዚህ የፈጠራ ባለሙያዎች ተስፋ ሰጪና በቀጣይ በተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂ ላይ አዳዲስ ሃሳብ እንዲያመጡ በር ከፋች መሆኑ ተመስክሮለታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም