ባለፈው ዓመት ከከፍተኛ ሊግ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር መመለሱን ያረጋገጠው መከላከያ እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ ሁለት ጨዋታዎች ይቀሩታል፡፡ ያም ሆኖ የመከላከያ ስፖርት ክለብ በመጪው ዓመት ላይ በቀድሞ የመቻል ስሙ ሊጠራ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ውስጥ በስመ ገናናነቱ የሚታወቀው እና የበርካታ ዋንጫዎችና የሜዳሊያዎች ባለቤት በመሆን አኩሪ ስም ያለው መከላከያ በቀድሞ ጊዜ ስሙ በሚጠራበት መቻል ስያሜውን ከመጪው ዓመት ጀምሮ የሚያገኝ እና የሚጠራበት ይሆናል፡፡ ይኸው ክለብ በ81 ዓመት የምስረታ ታሪኩም የመቻል ስፖርት ክለብ በሚል የደጋፊዎች ማህበር አቋቁሞ የእውቅና ፈቃድንም ከማኅበራት ማደራጃ ሚኒስትር ሊወስድም እንደቻለ ተነግሯል።
የመከላከያ ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ማለትም ከአስር በላይ በሚደርሱ ስፖርቶች በመሳተፍ እና ውጤታማም በመሆን ብዙ ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ በርካታ ስፖርተኞችንም ለሀገሪቱ ማፍራት ችሏል። ይሄ ክለብ ከሚወዳደርባቸው የስፖርት ዘርፎች መካከል በተለይም በእግር ኳሱ በጣም የሚታወቅ ሲሆን በቀድሞው ጊዜም እንደ እነ አረፋይኔ፣ ቡታ አስምሮምን፣ መርሻ ሚደቅሳን፣ በሀብቱ ገብረማሪያምን፣ ሙሉዓለም እጅጉን፣ ሙሉጌታ ብርሃኔን፣ ደረጄ በላይን፣ ክፍሌ ቦልተናን፣በሀይሉን፣ ማቲያስ ሀብተማሪያምን፣ ታሪኩ መንጀታን፣ አለምሰገድ አንቼን፣ በለጠ ወዳጆን ማፍራት ችሏል፡፡ ከ1996 ዓም በኋላ ደግሞ እስከዚህ ዘመን ድረስ እየተጫወቱ ያሉ እና ኳስን መጫወት ያቆሙ በርካታ ተጨዋቾችንም ለእውቅና ሊያበቃ ችሏል።
መከላከያ በቀድሞ ጊዜ አሁን የስም ለውጥ በማድረግ የመቻል ስፖርት ክለብ ተብሎ ሊጠራ እንደተዘጋጀ ሁሉ ምድር ጦርም ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን፣ ክለቡ በእግር ኳሱ በተለይም ደግሞ ከ1970ዎቹ አጋማሽ አንስቶ በነበረው ዝናና ውጤታማነት ከደጋፊዎቹ ይሰጠው የነበረው ድጋፍ እና ማበረታታትም ታሪክ የማይረሳው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
መከላከያ ወደ ሜዳ ያኔ ሲገባ መጠሪያ ስሙ ምድር ጦርም ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን “ይናዳል ገደሉ፤ ጦሩ መጣ ሲሉ” የሚለውና “አማሬሳ ሆ! አማሬሳ ሆ! ጦሩ ነመኛታ” የሚሉት ዜማዎችም የሚታወሱለት ናቸው።
የመከላከያ ስፖርት ክለብ በአዲሱ የውድድር ዘመን መቻል በሚል ስያሜው መጠሪያውን በሚያደርግበት ወቅትም አስቀድሞ የቀድሞ የቡድኑ ደጋፊዎች ማኅበራቸውን ከአቋቋሙ በኋላ የሥራ ክፍፍል ያደረጉ ሲሆን፣ አቶ ኤልያስ አብርሃምን በሊቀመንበርነት፣ ወይዘሮ መንበረ ቀፀላን በምክትል ሊቀመንበርነት፣ አቶ ዳንኤል ኃይለ ሚካኤልን በዋና ጸሐፊነት፣ እንደዚሁም ደግሞ አቶ ተስፋዬ ታደሰን በሕዝብ ግንኙነት በመምረጥ እና በአጠቃላይም 15 የሚደርሱ አባላቶችንም በማካተት የሥራ እንቅስቃሴ ሊጀምሩ መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
የመከላከያ ስፖርት ክለብ መቻል በሚል የቀድሞ ስሙ በመጪው ዓመት ላይ ሊጠራ ዝግጁ በሆነበት በአሁኑ ሰዓት እንደ ቡድኑ የቀድሞ ቀንደኛ ደጋፊዋ መንበረ ቀፀላ ሁሉ በበፊቱ ጊዜ ቡድኑን አብራት ባማረ ሁኔታ ትደግፍ የነበረችው ፍሬሕይወትም ከምትኖርበት አሜሪካ በመምጣት የቡድኑ የደጋፊዎች የክብር አባል እንድትሆን የተደረገች ሲሆን፣ በምትኖርበት የሰሜን አሜሪካ ላስቬጋስ ከተማም የቡድኑ ተጠሪ ልትሆን ችላለች። ሌላዋ ደጋፊ ገነት አየለም በፈረንሳይ ሀገር የመቻል ስፖርት ክለብ ተጠሪ እና በእዚህ የተመሠረተው የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር የክብር አባልም ለመሆን በቅታለች።
የመከላከያ በአዲሱ ስያሜው የመቻል ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማኅበር የአባልነት ምዝገባውን በቅርቡ እንደሚጀምር የተነገረ ሲሆን የማኅበሩ ጽሕፈት ቤትም ለጊዜው ጃንሜዳ በሚገኘው የክለቡ ካምፕ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የመከላከያ ስፖርት ክለብ ምስረታ ጣሊያን ከአገር በወጣ ማግስት በ1938 ዓ.ም ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የክለቦች ምስረታ ታሪክ ከቀዳሚዎቹ የሚመደብም ነው። ዓመታትን ባስቆጠረ ጉዞውም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገርን ያኮሩ ስፖርተኞችን በማፍራት ቀዳሚ ነው። ክለቡ በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቮሊቦል እና እጅ ኳስ ስፖርቶች በክለብ ደረጃ ንቁ ተሳትፎ ከማድረግም በላይ ለብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ተጫዋቾችና በማፍራትም ጭምር ምስጉን ክለብ ነው።
በአጠቃላይ ስፖርተኛው 500 የሚደርሱ ሲሆን፤ ተቋሙ በጃንሜዳ አካባቢ ባለው ካምፕም መቀመጫቸውን አድርጓዋል። ክለቡ ስፖርተኞችን ከታዳጊ ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን የሚያሳድግ በመሆኑ ለምልመላ ይረዳው ዘንድም በየዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች የራሱን ውድድር ያካሂዳል። በአትሌቲክስ ስፖርትም ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ለሆኑት እንዲሁም ከሠራዊቱ መካከል ለስፖርቱ ብቁ የሆኑትን ክለቡ አቅፎ ይይዛል።
የአትሌቲክስ ስፖርት የክለቡ መነሻ ነው፤ በኦሊምፒክ መድረክ ባዶ እግሩን በመሮጥ ‹‹ብቻውን ሮምን ወረራት›› የተባለለት አበበ ቢቂላ ደግሞ የክለቡ ፍሬ ነው። ባሻዬ ፈለቀ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ እሸቱ ቱራ፣ መሃመድ ከድር እና ሃዲስ አበበም የውትድርናው ዓለም ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው ቀደምት እንቁዎች ናቸው። አሁንም ኢብርሂም ጄይላን፣ ኢማና መርጋ፣ ሱሌ ኡቱራ፣ የማነ ጸጋዬ፣ አልማዝ አያና፣ ሙክታር እድሪስ፣ እቴነሽ ዲሮ፣ አስካለ ቲክሳ፣…. ከበርካቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014