አሸባሪው ሸኔ የአሸባሪው ሕወሓት ጽንስ ነው። ለፖለቲካው እንዲመቸው፣ ለስልጣኑ እንዲቀናው በተንኮሉ ልክ አምጦ የወለደው የእኩይ ሀሳቡ በኩር ነው። በለውጡ ማግስት የታየው ሀገራዊ መነቃቃት የክፋት ሕልውናቸውን ፈትኖት መቋቋም ስላልቻሉ ሕወሓት ወደለመደው ጫካ፣ሸኔም በሕወሓት ጭንብል ሀገርና ሕዝብ ማስጨነቁን ቀጥሎበታል። ትርፋቸው በንጹሓን ደም እና ሰቆቃ መቆመር ነው፤ ይኸው ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የአሸባሪው ሕወሓትን የግፍ አገዛዝ አሸንፋ ቀና ባለችበት የለውጡ ማግስት እነኚህ የእፉኝት ልጆች መርዛቸውን እዚህም እዚያም እየረጩ ሀገር በማወክ ላይ ናቸው። መርጠው እየገደሉ፣ መርጠው እያሰቃዩ በወንድማማቾች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር ጎንበስ ቀና በማለት ላይ ናቸው። የነዚህን ኃይሎች ዓላማ ስልጣንና ስልጣን ብቻ ነው።
እስኪ እንጠያየቅ … ሕወሓት ለኢትዮጵያ ምን ነበር? ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ለእኔና ለእናንተ ምን ማለት ነበር? ልክ እንደ ሕወሓት አስተሳሰብ ሁሉ የሸኔ አስተሳሰብም ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው። ሀገር ለምንናፍቅ ለእኔና ለእናንተ፣ ኢትዮጵያዊነት ለሚርበን ለእኔና ለእናንተ እንጂ፣ ማሰብና ማገናዘብ ለማይችሉት ለሕወሓትና ለሸኔ የኢትዮጵያ መፍረስ ምናቸውም አይደለም። በወደመችና ታሪክ በሌላት ሀገር ላይ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ያውቃሉ። ታሪክ አበላሽተው፤ ትውልድ አውድመው በክፋት ልብ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ጥርሳቸውን የነቀሉበት ተግባራቸው ነው።
ለእኔና ለእናንተ እንጂ ለነሱ የኢትዮጵያ መኖርም ሆነ አለመኖር ትርጉም የለውም። ለዚያ እኮ ነው በመግደል ማሸነፍን የሚለማመዱት። ለዚያም ነው ንጹሓንን አሰቃይተው ጀግንነታቸውን ለማሳየት የሚሞክሩት። ተከባብሮ የሚኖርን ሕዝብ በተንኮል ሀሳባቸው ለማባላት የሚፍጨረጨሩት ለዚሁ ነው። ጭር ሲል አይወዱም። የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የማይፈልጉ ኃይሎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች አሁንም በሕዝብና በመንግሥት እንዲሁም በሕዝቦች መካከል መለያየትን ፈጥረው የራሳቸውን ስውር ዓላማ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው።
እነዚህን ኃይሎች ለማሳፈር አንዱ ሕዝብ ስለሌላው መጮህና ‹ያገባኛል› ሊል ይገባል። በየትም ቦታ የሚፈስ የአንዱ ደም የሌላው ወንድሙ ደም ነው። በዚህ የሀሳብ ኅብራዊነት ውስጥ በቅለን ስንጸድቅ ብቻ ነው የጽንፈኞቹን ህልም የምናወድመው። በዚህ የሀሳብ ልዕልና ውስጥ ስንቆም ብቻ ነው ሕወሓትንም ሆነ ልጁን ሸኔን ታግለን የምናሸንፈው።
ለሀገር የሚያስብ ሀገርን አይጎዳም፤ትውልድን አያመክንም። ለወገን የሚቆረቆር በወንድማማቾች መካከል ጸብን አይዘራም፤ ንጹሓንን አይገድልም። አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ ለሀገርና ለሕዝብ ታግለው አያወቁም። በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ ሀገር እያጠፉ ለሀገር መታገል፤ ሕዝብ እየጨፈጨፉ ለሕዝብ መታገል የሚባል ነገር የለም። እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው ሀገር ማውደም እንዲሁም ተከባብሮና ተፋቅሮ የሚኖረውን ሕዝብ መለያየት ነው። መሠረት በሌለው የፖለቲካ እሳቤያቸው ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር አጋጭተው እፎይ ማለትን የሚከጅሉ ናቸው።
ሕዝብ የእነዚህን እኩይ ኃይሎች ዓላማ ተገንዝቦ አንድነቱን መጠበቅ እንጂ ኮሽ ባለ ቁጥር የወንድማማች ጽናቱን መነቅነቅ የለበትም። ሕወሓትና ሸኔ የዚህ ዘመን ቃየሎች ናቸው። የወንድሞቻቸውን ደም የሚጠጡ፣ በወገኖቻቸው ሞት ጮቤ የሚረግጡ ሌንግኖሳዊያን። ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም። ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቢረዱ ኖሮ በዚህ ልክ ወልዳ ባሳደገቻቸው ሀገራቸውና በወገናቸው ላይ ባልጨከኑ ነበር። በመግደል የሚረኩ፣ ዓላማቸውን በመግደል የሚያስፈጽሙ የሰይጣን ጭፍሮች ናቸው።
ሰው በመግደል የፖለቲካ ትርፍ አይገኝም። የአንድ ብሔርን ዘር ለይቶ በማጥቃት በወንድማማቾች መካከል ጠብን ከመፍጠር ባለፈ የፖለቲካ ጥያቄን አይመልስም። አሁን ላይ እነዚህ ሁለት ኃይሎች የያዙት ዓላማ አንዱን ብሔር በማጥቃት ሌላውን ተጠያቂ ማድረግ፣ አንድ ብሔርን ለይቶ በማግለል ሕዝብን በመንግሥት ላይ ማስነሳት ነው። የሕወሓት ማንነት ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው። ያለፉትን ሃያ ሰባት ዓመታት እንተውና ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ በምን አይነት ሀገራዊና ማኅበራዊ ስቃይ ውስጥ እንደነበርን ሁላችንም የምናውቀው ነው።
እነዚህን ኃይሎች ለመታገል የአንድነት ፍቅራችን ግድ ይለናል። እኩይ ዓላማቸውን ተገንዝበን የክፋት ሴራቸውን በወንድማማችነት ስሜት ማውደም እንጂ ኮሽ ባለ ቁጥር ለመለያየት መፍጠን የለብንም። ሕወሓት በባከነ አስተሳሰብ የባከነችን ሀገር ፈጥሯል። የዚህ ብኩን አስተሳሰብ ውጤት ከሆኑት ውስጥ ደግሞ አንዱ ሸኔ ነው። ገዳይነትን ከአባቱ ከሕወሓት ተቀብሎ ይኸው ሕዝብ እያስጨነቀ ነው። የእባብ ልጅ እባብ እንጂ የእባብ ልጅ እርግብ ሆኖ አያውቅም። የእባብ ልጅ ከመንደፍና መርዙን ከመርጨት በቀር ተፈጥሮ የለውም። ሕወሓትና ሸኔም እንደዚህ ናቸው። በአንድ ደረት ላይ የበቀሉ መንታ ጡቶች፣ ወተት ሳይሆን መርዝ የሚያመነጩ፣ ሕይወት ሳይሆን ሞት የሚነግዱ።
አሁን ላይ የሕወሓት ቡድን ያበላሻትን ኢትዮጵያ በአንድነት ስሜት መገንባት እንጂ አምጦ በወለደውና፣ የመርዝ እርጎ እያጠጣ ባሳደገው የሸኔ ቡድን ፍቅራችንን ማጣት የለብንም። ተባብረን በአንድነት የነዚህን ግብዓተ መሬት ማፋጠን እንጂ ለክፋታቸው እጅ መስጠት የለብንም። መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ የሕዝቦችን ደህንነት መጠበቅና ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በዚህ ረገድ መንግሥት የቤት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚወጣ በማመን እስከዚያው ግን እነዚህን እኩይ ቡድኖች በሚያሳፍር መልኩ በአንድነት መቆም ይኖርብናል።
በሕዝቦች መካከል እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው አንድነት በእነዚህ ቡድኖች የክፋት ሀሳብ መላላት የለበትም። ዓላማቸው ምን እንደሆነ ተገንዝበን በፍቅራችን ልንጥላቸው መተቃቀፍ ይኖርብናል። የፍቅር ክራችን፣ የአንድነት ድራችን በእኩይ ኃይሎች እንዲላላ መፍቀድ የለብንም። ወንድማማችነታችን በክፋት ልቦች መጠልሸት የለበትም። የእኛ መለያየት ለጠላቶቻችን በር ይከፍታል። የእኛ መገፋፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለተነሱት ሕወሓትና ሸኔ ኃይል ይሆናል። የምናሸንፋቸው በአንድነታችን ስንበረታ ነው። የምናንበረክካቸው አንዱ ለሌላው አለኝታ ሲሆን ነው።
የእፉኝት ልጆች ሥራቸው መግደል ብቻ ነው። ካልገደሉ ያልበረቱ የማይመስላቸው፣ ሕዝብ ካላስጨነቁ ያላሸነፉ የሚመስላቸው ናቸው። ዓላማውን ሀገር ያደረገ ግለሰብ ሰው አይገድልም። ዓላማውን ሕዝብ ያደረገ ቡድን ንጹሓንን ያለርህራሄ አይጨፈጭፍም። በነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች ውስጥ ግን ሀገር የለችም፤ሕዝብና ትውልድ ቦታ የለውም። ብቸኛ ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፍረስና ወደ ሕወሓት አስተሳሰብ መመለስ ነው። በብሔር ከፋፍለው ኢትዮጵያ አሳዛኝ የእርስ በእርስ እልቂትን ያስተናገዱ ሀገራት እጣ ፋንታ እንዲገጥማት ማድረግ ነው።
ከዚህ እውነት በመነሳት የእነዚህ ኃይሎች ዓላማ ምን እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ከትላንት እስከዛሬ አንዱ ብሔር ለሌላው ብሔር ጠላት ሆኖ አያውቅም። በሕወሓት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ግን ባለታሪክ ወንድማማቾች እንደጠላት ሲተያዩ ነበር። የእነዚህ ወንድማማቾች የክፋት ጠንሳሽ ሕወሓት ነበር። ምክንያቱም ሕዝቦችን ካላጋጨና ካላባላ ስልጣን ላይ የመቆየት እድል አይኖረውምና ነው።
ዛሬም እንደ ሰማይ ለራቀው ስልጣኑ በፍቅር የተሳሰሩትን ኢትዮጵያውያንን ለመለያየት በሸኔ በኩል አዲስ ክፋት እየጎነጎነ ነው። ይሄን ቡድን በተመለከተ ራሳችንን የምንጠይቀው ጥያቄ ይኖራል … ሕወሓት የኢትዮጵያ የምንግዜም ጠላት ከሆነ፣ ሸኔ በሕወሓት ሰልጥኖ፣ በሕወሓት በልጽጎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እፉኝት ከሆነ ከእኛ ምን ይጠበቃል? ከእኛ የሚጠበቀው በአንድነት የክፋት ጉንጉናቸውን መበጣጠስ ነው።
አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን ሳይቀስር በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ጠላቶቻችን ላይ የበላይ መሆን አለብን። ሕወሓትና ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አንድ ሆነዋል፤ እኛ ኢትዮጵያን ለማቆም አንድ ብንሆን ምን ይገርማል?! ሕወሓትና ሸኔ የብሔር ጦርነትና የዘር ፍጅት ለመፍጠር ቀን ከሌት እየሠሩ ነው። እኛ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በአንድነት ብንሰለፍ ችግሩ ምንድነው? ሕወሓትና ሸኔ በአንድ አይነት አስተሳሰብ አንድ አይነት ሆነው የቆሙ ናቸው፣ እኛ ለኢትዮጵያ ህልውና በአንድ አይነት አስተሳሰብ፣ አንድ አይነት ሆነን ብንቆም ምን እንጎዳለን? መልሱ ምንም ነው።
ጠላቶቻችን ባጠመዱልን የሞትና የመለያየት ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ ምክራቸውን የሚያፈርስ የፍቅር ኃይል ያስፈልገናል። ጠላቶቻችን በቆፈሩልን የብሔር ጉድጓድ ውስጥ እንዳንወድቅ ሀሳባቸውን የሚሽር የአንድነት ጉልበት ግድ ይለናል። ጠላቶቻችን በደገሱልን የሞት ድግስ እንዳንታደም ህልማቸውን የሚያመክን የወንድማማችነት ስሜት ያስፈልገናል። ሕወሓትና የእንግዴ ልጁ ሸኔ በሀሳብም በተግባርም የሚሞቱት እኛ ስንበረታ ነው። ምክራቸውን ለማጥፋት፣ ሀሳባቸውን ለማምከን እኛ በአንድነት መቆም አለብን።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ለመጣል ተግተው እየሠሩ ነው። አንዱን ወገን በመግደል ለብሔር ጥላቻ ያለው ትውልድ ለመፍጠር እየታተሩ ነው። ንጹሓንን በመግደል፣ ሕጻናትን በመድፈር፣ ሴቶችን በማሰቃየት መልስ ለሌለው ጥያቄ መልስ እየፈለጉ ነው። ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ የተከሰተው አማራ ተኮር የንጹሓን እልቂትም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ከዚህ በፊትም በነዚህ ኃይሎች የተከሰተው የጅምላ እልቂትም ቡድኑ አንዱን ብሔር ከአንዱ ብሔር ለማጋጨትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሄደበት ያለው መንገድ የት ድረስ እንደሆነ አመላካች ነው።
በነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች የቡድኑን ተልዕኮና ዓላማ መረዳት ይቻላል። እነሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይኖራሉ፤ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ እንኖራለን። ኢትዮጵያን የምንወድ እኛ ከነሱ ብዙ ነን። መካከላችን ፍቅር ሲኖር ደግሞ ጠላቶቻችንን ከእግራችን በታች ለማንበርከክ ኃይል እናገኛለን። እናም በፍቅር ጠላቶቻችንን እናንበርክክ። አሁን የሚያስፈልገን የጠላቶቻችንን ዓላማ ማወቅ ብቻ ነው። የጠላቶቻችንን ዓላማ ካወቅን ምን ሊያደርጉን እንደሚገድሉን፣ ምን አስበው እንደሚያሳድዱን መረዳት አይከብደንም።
የጠላቶቻችንን ዓላማ ካወቅን በነሱ ላይ የበላይ መሆን አይቸግረንም። እነርሱ በሁሉ ነገሯ የተሻለችውን ታላቋን ኢትዮጵያ ማየት አይፈልጉም። እነርሱ ከሕወሓት አስተሳሰብ የጸዳችውንና እውነተኛይቱንና ፍትሐዊቷን ኢትዮጵያን ማየት አይሹም። እነርሱ ኢትዮጵያ በልጽጋ፣ ሕዝቦቿም የተሻለ ሕይወት ሲመሩ ማየት ያማቸዋል። በዚህ ሁሉ ማስረጃ፣ በዚህ ሁሉ ምክንያት አሁናዊውንም ሆነ ቀጣዩን የሕወሓትንም ሆነ የሸኔን ዓላማ መረዳት እንችላለን።
ኢትዮጵያን መጠበቅ የሁላችንም ግዴታ ነው። ሕወሓት አምጦ በወለደው ሸኔ ምክንያት የድሮ ፍቅራችንን እንዳናጣ የዚህን ክፉ ቡድን ዓላማና ተልዕኮ መረዳት ይኖርብናል። ዓላማውም ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። የትናንቶቹ የጋምቤላና የወለጋ ጥቃቶች የታሪካዊ ጠላቶቻችን የሰኔዎች ሥራ አካል መሆኑንም መረዳት ተገቢ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014