በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንድ የአጥቂ መስመር ተጫዋች በክለቡና በብሔራዊ ቡድን በሚያስቆጥራቸው ወሳኝ ግቦች ከሌሎች ተለይቶ ይታያል።ስሙ ግን በጉልህ ሲነሳ አይስተዋልም።ይህ የግብ አነፍናፊ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለክለቡ አዳማ ከተማ ተሰልፎ የሚያስቆጥራቸው ግቦችና የሚያሳየው አስደናቂ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቋሚነት የፊት መስመሩን ከሚመሩ አጥቂዎች አንዱ አድርጎታል። ‹‹ግብ ለማስቆጠር የትኛውንም መስዋእትነት ይከፍላል›› ይሉታል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን በቅርብ የሚከታተሉ።
መቆጠር ለሚችል ኳስ ብቻ ሳይሆን የመቆጠር እድሉ ጠባብ የሆነን ኳስ ወደ ውጤት ለመቀየር ከግብ ቋሚ ብረት ጋር መጋጨት ካለበት ወደ ኋላ አይልም። ግብ ለማስቆጠር ከተከላካዮች ጋር አይደለም ከሜዳ ጋር መታገል ካለበት ጉዳት ይገጥመኛል ብሎ የሚሰስተው ጉልበት የለውም። ደፋርና ሌሎች አጥቂዎች ለማድረግ የማይደፍሩትን መሞከሩ የተለየ ተጫዋች እንደሚያደርገው ይነገርለታል። ይህ የዋልያዎቹ ፊት አውራሪ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ የማይበገሩት አንበሶችን (የካሜሩን ብሔራዊ ቡድንን) መረብ ደፍሯል።
በቅርቡም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን(ፈርኦኖቹ) ላይ ያስቆጠራት ግብ ታጋይነቱን በግልጽ ያሳየች ነበረች። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለዋልያዎቹ ተሰልፎ በአፍሪካ ሁለት ታላላቅ ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ግቦችን ያስቆጠረው ዳዋ ሆጤሳ። ከምንም ተነስቶ ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ግቦችን ለማስቆጠር የበቃበት የህይወት መንገድ ለብዙዎቹ ታዳጊ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች አስተማሪ ነው።በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ ስለዚህ ተጫዋች ለመዳሰስ ሞክረናል።
ዳዋ በልጅነቱ የከብቶች እረኛ ነበር። የወላጆቹን ከብቶች ያግዳል፣ ተማሪም ነበር። ይሁን እንጂ ፍቅሩ ከኳስ ጋር ነበር አብሮ የነጎደው። በልጅነቱ በአካባቢው በሚገኝ ሜዳ አልያም በወላጆቹ ሰፊ ግቢ ውስጥ ከኳስ ጋር ሲሯሯጥ ማደጉን ዛሬ ላይ ያስታውሰዋል። ወላጆቹ እግር ኳስን አብዝቶ መጫወቱንና መውደዱን አልወደዱትም ነበር።
እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ወላጆች የቤተሰቦቹ ፍላጎት ልጃቸው ትኩረቱ ትምህርት ላይ እንዲሆን ነበር። የኳስ ፍቅሩ ከልክ ያለፈባቸው ወላጆችም ልጃቸውን ወደ ሚፈልጉት መስመር ለማስገባት በብዙ መንገድ ለመቅጣት ሞክረዋል። ቅጣቶቹ ግን ታዳጊው ዳዋን ኳስ ይዞ ከመሯሯጥ አላገዱትም። በመጨረሻም ‹‹ከትምህርትና ከኳስ አንዱን ምረጥ!›› ተባለ፣ ዳዋም ሳያቅማማ ምርጫውን አስታወቀ፣ ኳስን መረጠ።
‹‹ተወልጄ ካደግኩባት ከተማ እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ የወጣ ያለ አይመስለኝም ወይም አላውቅም›› የሚለው ዳዋ በአካባቢው ወደ እግር ኳስ ለመሳብ ምሳሌ የሚሆነው ሰው ባይኖርም በልጅነቱ እግር ኳስ ለመከታተል ከሳተላይት ቴሌቪዥን አይርቅም ነበር። ይህም ግን በለጋነት እድሜው በቀላሉ የሚገኝ እድል አልነበረም። ኳስ ለማሳየት ገንዘብ ያስፈልጋል። በልጅነት ጊዜ ደግሞ ገንዘብ ማግኘት ቀላል አልነበረም።
‹‹እኔ እግር ኳስ ብወድም ቤተሰቦቼ ግን ኳስ እንድጫወት አይፈቅዱልኝም ነበር፣ በኳስ ምክንያት ብዙ ቅጣት ደርሶብኛል፣ ከብቶቼን ትቼ ወደ ኳስ ሜዳ ሄጄ ኳስ እጫወት ነበር፣ በዚህም ምክንያት ብዙ ቅጣቶችን ተቀብያለሁ›› ይላል ዳዋ በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ።
ወላጆቹ ኳስ አትጫወትም ብለው ሲከለክሉት ምግብ አልበላም እያለ ያስቸግር እንደነበረ ዳዋ ያስታውሳል። ዘጠነኛ ክፍል እስኪደርስም በዚህ ሁኔታ ቆየ። ‹‹ቀስ በቀስ ለትምህርት ቤት መጫወት ጀመርኩ›› የሚለው ዳዋ ልምድ ለማግኘት ወደ ነገሌ ቦረና ከሰዎች ጋር መሄዱ ለዛሬው የእግር ኳስ ህይወቱ መንገድ እየከፈተለት ሄደ። በወቅቱ ነገሌ ክለቡ በኦሮሚያ ሊግ ውስጥ ይጫወት ነበር። ለነገሌ ሲጫወትም የመጀመሪያ ክፍያው 300 ብር ነበር።
በልጅነቱ ብዙ መስዋእትነት የከፈለለት እግር ኳስ ኋላ ላይ የወደፊት የኑሮ እጣፋንታውን ብቻም ሳይሆን የፍቅር አጋሩን አገናኘው። የልጆች አባት ሆነ። ‹‹የሕይወት አጋሬ ኳስና አትሌቲክስ ትወዳለች ግን እሷ በትምህርት ገፍታበታለች፣ በልጅነት ነው የተጋባነው፣ ብዙ ዓመት በፍቅር ቆይተናል። ከስድስት ዓመት በፊት ነው የተጋባነው አሁን ሁለት ልጆች አሉን›› በማለትም ከኳስ ውጪ ያለውን ህይወት ይናገራል። ዳዋ አሁን እየተጫወተለት በሚገኘው በአዳማ ከተማ ቤት ገዝቶ ኑሮውን እዚያው አድርጓል።
ዳዋ ማለት በአፋን ኦሮሞ ሰው መንካት የማይችለው ትልቅ ደን ማለት ነው። ሆጤሳ ማለት ደግሞ እኩለ ሌሊት ላይ የተወለደ ሰው ማለት ነው። ዳዋ ዛሬም ኳስ እያንከባለለ ያደገባትን ከተማ አልዘነጋም። ወደ ትውልድ ከተማው ሲሄድ በተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል ውድድር በማካሄድ ታዳጊዎች እንዲበረታቱ ጥረት ያደርጋል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደረጃ መጫወት ከጀመረ ሰባት አመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ ዓመታትም ለናሽናል ሲሚንት (ድሬዳዋ)፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለሁለት ዓመት፣በአዳማ ለአራት ዓመት፣በሃዲያ ሆሳዕና አንድ ዓመት ተጫውቷል። አሁንም ዳግም ለአዳማ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል።
ከዚህ በላይ ግን በአፍሪካ ዋንጫ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ ግብ ማስቆጠሩ ልዩ ስሜት ይሰጠዋል። “የአፍሪካ ዋንጫ ማለት ትልቅ ውድድር ነው፣ በትልቅ ውድድር ላይ ተሰልፌ ግብ ማስቆጠሬ በጣም ነው ያስደሰተኝ” ይላል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚጎለው ነገር እንደሌለ የሚናገረው ዳዋ “እንደ ተጫዋች ብዙ መስራት ያለብን ነገር አለ፣ ለምሳሌ በቴክኒክ እንጂ በአካል ብቃት ከሌሎች ጋር አንወዳደርም” በማለት ስለ ዋልያዎቹ ይናገራል።
ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ እንደ አትሌቲክሱ ብዙ የስኬት ደረጃ ላይ መድረስ አለመቻሉ የሚያበሳጨው ዳዋ “እንደ አንድ ግለሰብ ያሳዝነኛል፣ ለዚህች አገር ብዙ ማድረግ እፈልጋለሁ” በማለትም በእግር ኳሱ ላይ ያለውን ቁጭት ያጋራል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2014