አሸባሪውን ሕወሓት ሆነ መርዛማ ሰንኮፉን ተለምዷዊ/ኮንቬንሽናል/በሆነ አግባብ መተንተን ፣ መበየንና መረዳትም ሆነ መንቀል አይቻልም። እንዲሁም ሰላምን ፣ ድርድርንና ጦርነትን ከሕወሓት የክህደት ባህሪና ታሪክ ውጭ ለማሰብ መሞከር ራስን በራስ እንደ ማጥፋት ነው ። ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ከአንድም ሁለት ጊዜ ዋጋ የከፈልነው ተልምዷዊ በሆነ አግባብ ስለተመላለስን መሆኑ ሊጤን ይገባል ።
የቡድኑ ፖለቲካዊ ታሪክ ይህን ነው ያስተማረን። የእስከዛሬው ጥረት ሁሉ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ያልሆነው ለዚህ ነው ። ከተለመደው አካሄድና ምላሽ ወጣ ብሎ በጥበብ ማሰብን፣ ማቀድንና ምላሽ መስጠትን ይጠይቃል ። ባለብዙ ማንነት ስለሆነ ከዚህ አንጻር አበክሮ መዘጋጀትም ይፈልጋል።
እንደ ሁኔታው የሚቀያየር እስስት ፤ መርህ የሚባል ነገር ያልፈጠረበት ነውረኛም ነው ። በክህደትና በማጭበርበር ጥርሱን የነቀለ መልቲ መሆኑም ለደቂቃ ሊዘነጋ አይገባም። በዚህ ለሰላም ዝግጁ ነኝ እያለ በዚያ የጦርነት ነጋሪት የሚጎስም ጉድ ነው ። ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ እንዳሉት ጦርነትን እንደ ጣኦት የሚያመልክ መሆኑም ከግምት መግባት አለበት። በዚህ አምልኮ የተለከፈ ለሰላምና ለእርቅ ይታመናል ማለት ዘበት ነው የሚሆነው። ለዚህ ነው ለትግራዋይ፣ ለዲያስፓራው ፣ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ፣ ለአማራ ፣ ለአለማቀፍ ማህበረሰቡ የተለያየ አጀንዳ እየቀረጸ የሚያጭበረብረው ።
የሰብዓዊ እርዳታ ተከለከልሁ ሕዝቤ ተራበ፤ በመድሀኒት እጥረት ትግራዋይ አለቁ እያለ የአዞ እንባውን እያነባ ፤ ወዲህ እርዳታ የጫነ አውሮፕላን መቀሌ ድርሽ እንዳይል ከማለት አንስቶ ብቸኛ የእርዳታ ማጓጓዣ መስመርን ይዘጋል ። እርዳታ ለማድረስ የተላኩ የጭነት ተሽከርካሪዎችን አግቶ ለጦርነት ያውላል። ፈሪኣ ፈጣሪ የሌለው ጉግማንጉግ ፤ ጓዶቹን ገሎ ሀዘን የሚቀመጥ፤ ሀውልት የሚያቆም ፣ ክፍለ ጦር ፣ ማሰልጠኛ የሚሰይም አይነ ደረቅ ነው ። የንጹሐንን ደም ምሱ ያደረገ ጣኦት ፤ እንደ ዘንዶ እርስ በርሱ የሚዋዋጥ አረመኔ ፤ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲል ምንም ከማድረግ የማይመለስ ፤ ጥቅም እስካስገኘለት ሀገሩንና ሕዝቡን ለመሸጥ የሚያስማማ ስግብግብ ነው ።
አይደለም በቁሙ ላለ ሰው ለሬሳ እንኳ ክብር የሌለው አረመኔ ፤ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያስጨፈጭፍና የሚጨፈጭፍ አውሬ ፤ ሰሞነኛ ጭፍጨፋዎች ጨምሮ የበደኖን ፣ የአርባጉጉን ፣ ወዘተረፈ ጭፍጨፋ ልብ ይሏል። በጦርነቱ የሞቱ አመራሮች ማንነት እንዳይለይ አንገት የሚቆርጥ አሪዎስ ነው ። አዲስ አበባ ላይ ፈንጂ አፈንድቶ ንጹሐንን ገሎና አቁስሎ ኦነግ ነው ያፈነዳው ብሎ የሚያስር፣ የሚያሰቃይና የሚገድል አሸባሪ ነው ። ወደ ወንበዴነት ከተቀየረ በኋላ ደግሞ ሲገድል ግዳይ የሚጥል ጀግና፤ ሲሞት ንጹሕና ሰላማዊ ሰው የሚሆን እንደ ሮማውያኑ ጣኦት ጄነስ/Janus/ባለ ሁለት ተቃራኒ ፊት ጣኦት ነው ።
ሲቭል ለብሶና በሰላማዊ ሰዎች መሀከል ሆኖ ጥቃት ይከፍትና ገድሎ ሲፈረጥጥ ጀግና ፤ ሲገደል ግን ሰላማዊ ሰው የሚሆን የምድር ጉድ ነው። በቀድሞው የአክሱም ከንቲባ አይዟችሁ ባይነት የለብለብ ስልጣን የወሰዱ ወጣቶች በመከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው በውጊያ ሲገደሉ ንጹሀንና ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ ብሎ ሀገር ይያዝልኝ የሚል ማፊያ ነው። እንደ አፄ ልብነ ድንግል “ ጦር አውርድ “ እያለ መሬትን 40 እየገረፈና በልመና ባመጣው ጡርነት በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ ደግሞ የድረሱልኝ ጩኽቱን ከሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ጋር አዛንቆ ያቀልጠዋል ። ሕወሓትን ስናስብ ይህን ማንነቱን ለአፍታ መዘንጋት አይገባም ።
ሆኖም በጦርነት ሒደት የንጹሐን ሞት ፣ መቁሰልና መፈናቀል/collateral damage/የለም እያልሁ አይደለም ። ይህ እንዳይሆን ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ እናቶች ፣ ታዋቂ ሰዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች መቐሌ ድረስ እየተመላለሱ እግር ላይ ወድቀው እርቅን የለመኑት። ልቡ የማይገኘውና ሸረኛው ሕወሓት ግን ለጦርነትና ለሌላ ዙር ክህደት እየተዘጋጀ ስለነበር ሽምግልናን መግፋት መረጠ።
ደባው ሲከሽፍ ደግሞ የምዕራባውያን ፣ የአለማቀፍ ድርጅቶችንና ሚዲያዎችን ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ሀሰተኛና የተጋነኑ የሰላማዊ ሰዎች ሞትን ፣ አስገድዶ መደፈርንና እርሀብን በመለፈፍ ዳግም ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጎን ቆመ። ይህ ጊዜያዊ የዲፕሎማሲ ድሉ ግን እውነቱ እያደር ሲገለጥ መሟሸሹ ባይቀርም በሀገራችን ገጽታ ላይ ያደረሰው ጉዳት ግን የሚታበል አይደለም ። ይሄ ክህደቱና ውሸቱ ግን ትናንት የተፈጠረ ሳይሆን አብሮት ያደገ ባህሪው ነው ።
ማሕበረ ገሰገስቲ ብሔረ ትግራይ/ማገብት/ ፣ ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ/ተሓህት/ ፣ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ/ ማሌሊት/እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ ሕወሓት /፤ እነዚህ በሙሉ የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር/ትህነግ/ በተለምዶ የወያኔ እስስታዊ ባህሪና ማንነት መጠሪያ ስሞች ናቸው ። በእነዚህ ሁሉ ምዕራፎች ራሱን የቻለ አስመሳይነትና ነጭ ውሸት አለ ። ነጻነትን ሳያውቁ ነጻ አውጭነት ፤ የላብ አደር መደብ በሌለበት ሌኒኒስትና ማርክሲስትነት ፤ አብዮትም ዴሞክራሲ በሌለበት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊነት ፤ ሀቀኛ ፌደራላዊ ስርዓት በሌለበትና የወያኔ ጉጅሌ የበላይነትና የሞግዚት አስተዳደር በሰፈነበት የፌደራል ስርዓት ፤ ሪፐብሊክም ዴሞክራሲም በሌለበት ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፤ ሕገ መንግስታዊነት ባልዋለበት ሕገ መንግስት ፤ ወዘተረፈ ከወያኔ አስመሳይነት፣ ውሸታምነትና መልቲነት መገለጫዎች ጥቂቶቹ ናቸው ።
የማይታረቅ ግጭት ላይ የርዕዮተ አለም ፣ የታሪክ ፣ የጥሬ መረጃ ውሸት ። የማርክስ ፣ የኤንግልስ ፣ የሌኒን ፣ የስታሊን፣ የማኦ ፣ የፊደል ፣ የቼጎቬራ ፣ የሆቺሜኒ ፣ የገሰሰው አየለ/ስሁል/ ፣ የአረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ፣ የአብርሃም ያየህ ፣ የገብረ መድህን አርአያ ፣ ወዘተረፈ እውነቶች ለጉጅሌ/ለቡድናዊ ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ተበርዘዋል ። ተከልሰዋል ።
ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው የጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋማርያም”ከሕወሓት ጎዳ” ወደ ኋላ 30 አመታት ሄደን የእነ አብርሃም ያየህንና ገብረመድን አርዓያ ፣ “የወያኔው ታላቁ ሴራ” ፣ ወዲህ የአረጋዊ በርሔን(ዶ/ር)፣”A Political History of Tigray People’s Libration Front” ወይም የገብሩ አስራትን ፣”ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ”ን ብታገላብጥ ፤ በአናቱ የተስፋዬ ገብረዓብን፣”የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን ፣”የደራሲው ማስታወሻን” ወይም የኤርሚያስ ለገሰን፣”የመለስ ትሩፋቶች”ን እና”የመለስ ልቃቂት”ን፤ “የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ(2005_2010)” የብርሀነ ፅጋብን ወግ ብትሰልቅ ፤ የጌታቸው ሽፈራውን”የሰቆቃ ድምጾች”፤ሰሞነኛውን የገብረመድህን አርዓያን”መራር ትዝታዎች”፤ በነካ እጅህ የአንዳርገቸው ጽጌን ፣ የአንዷለም አራጌንና የሀብታሙ አያሌውን ተከታታይ መጽሐፍት ብታነብ ወይም ስለ ሕወሓት የተጻፈ ስንክሳር በድረ ገጽ ብትጎለጉል ውሸት ፣ ሴራ ፣ ጭካኔ ፣ ማጭበርበር ፣ አሪዎስነትና ዘረፋ የጋራ አካፋዩ ሆነው ታገኛቸዋለህ ።
ከማገብት እስከ ዛሬው የአሻባሪው ሕወሓት ተክለ ሰዕብናን ብታስስ ተነቅሷቸው ታገኛለህ ። የዛሬው መሰናዘሪያ የሕወሓት ውሸትና ማጭበርበር ነውና እሱ ላይ የእጅ ፍሬን ልያዝ ።
አሸባሪ ሕወሓት የዛኔው ፋኖ ሲሰማራ ማለትም ፤ ወደ “ትግል” ሜዳ ለመውጣት ሲወስንም ሆነ እንደወጣ ታሪክን፣ እውነትን ፣ ሰንደቃላማን ፣ አብሮነትን ፣ ሰብዓዊነትን ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ፣ ፍቅርን ፣ ሰውነትን፣ ፈጣሪን ፣ ወዘተረፈ ሽምጥጥ አርጎ ክዶ የራሱን የፈጠራ ትርክት ነው ያነበረው ። የሀገሪቱን ታሪክ ወደ 100 አመታት አራክሶ፤ እውነትን ኅልቁ መሳፍርት በሌለው ውሸት ተክቶ ፤ ሰንደቃላማን ጨርቅና የአንድ ሀይማኖት አርማ ነው ብሎ፤ አብሮነትን በመለያየት ቀይሮ ፤ ሰብዓዊነትን በአረመኔነት ለውጦ ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጎሳ ለንጥቆ ፤ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የአማራው ገዥ መደብና ኦርቶዶክስ ነው፤ ፈጣሪን ክዶ ራሱን ወደጣኦትነት ቀይሮ እስከማምለክ የደረሰ ወዘተረፈ የራሱን ተረክና እውነት በይኖ በራሱ አለም ሲዳክር የኖረ ባተሌ ስብስብ ነው ።
የእውነትን ፣ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ፣ የዜጋውን የልቦና ውቅርና የታሪክን ፈለግ ተከትሎ ርዕዮት አለም መንደፍ የማታገያ ስልት መተለም ሲገባው ፤ በተቃራኒው እውነትን፣ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን ፣ የዜጋውን የሞራል ልዕልና ፣ የልቦና ውቅርና ታሪክ በድቡሽት ላይ ለተቀለሰ ማንፌስቶው እንዲመጥኑ እጃቸውን ጠምዝዞና አጣሞ እንደገና መበየኑ እና ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚል በስሁት መንገዱ ልምምዱን መቀጠሉ ጎልማሳው ከሀዲና መልቲ አድርጎታል ። ከጥፋቱና ከዕድሜው የማይማር ልበ ቢስ ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ያለፈውን ታሪክን የመርሳት አባዜ ስላለብን ዋና ዋና ክህደቶቹን ብቻ እናስታውስ ።
ቢያንስ ወደ ስምንት ሺህ አመት የሚጠጋ ቀደምት ሀገረ መንግስትና ታሪክ ያላትን ጥንታዊት ሀገር በልኩ ካሰፋው የታሪክና የርዕዮት አለም ቁምጣ ጋር ለማስኬድ ሲል እንደ ኮለምበስ ወይም ቫስኮ ደጋማ በአሳሽ “የተገኘች” ሀገር ይመስል ታሪኳን የ100 አመት ነው ሲል በአደባባይ የካደ የነውረኞች ስብስብ ነው ።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅርጽ ስሪት በአጼ ምኒልክ የተፈጠረ ነው ሲል ሀፍረት አልፈጠረበትም ። በጎሳ ላይ የተመሰረተው አስመሳይ ፌደራሊዝም የተዋቀረው በዚህ ክህደት ላይ ነው ። የአንድ ሀገር ጥንታዊነት ተካደ ማለት የቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም። የዜጎችን አብሮነት ፣ የሀገሪቱን የሀገረ መንግስት ልምምድና አጠቃላይ ማንነቷን የሚያኮሰምን ክህደት ነው።
ዜጋው በሀገሩና በታሪኩ ያለውን እምነት ለመሸርሸርና አንድ አርገው አጋምደው ያቆዩትን ወረቶች ለማስጣል የተከናወነ መሰሪ ክህደት ነው ። ይህ ብቻ አይደለም ለሀገሪቱ ያለው ጥላቻ ግዘፍ ነስቶ የተገለጠበት ደባ ጭምር ነው ። በአለማችን ላይ የሀገሩን ታሪክ አሳንሶ ሽንጡን ይዞ የተከራከረ እና አምርሮ የሚጠላትን ሀገር በአፈሙዝ የገዛ እንደ ከሀዲው ትህነግ ያለ ቡድን የለም ።
ይህን ጥላቻውን አገዛዝ ላይ እያለ በሚያራምዳቸው ስሁት ፖለቲካዊ አቋሙና አይን ያወጣ ዘረፋው አረጋግጧል ። ገዢነቱ በሕዝባዊ ማዕበልና በለውጥ ኃይሉ ከተሽቀነጠረ በኋላ እኔ ረግጬ የማልገዛትና የማልዘርፋት ሀገር ትውደም በሚል የሔደበትን እርቀት ታሪክም ትውልድም በቁዘማ ሲያስታውሰው ይኖራል ።
አፌን ሞልቼ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ጥቃት ፣ የጥቅምት 30ን የማይካድራን ፣ የጋሊኮማ ፣ የአጋምሳ ፣ የጭና ፣ የአንጾክያ፣ ወዘተረፈ ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ክህደትና ጭፍጨፋ ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ ነው የምለው ለዚህ ነው ። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ ። የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት ። የመከላከያ ሰራዊት ትጥቅ፣ ስንቅና ከባድ መሳሪያ በትግራይ ክልል እንዲደራጅና እንዲከማች የተደረገው የጥቅምት 24ቱን ክህደት ታሳቢ በማድረግ ነው ።
“ …በነገራችን ላይ የመከላከያ ትጥቁም ስንቁም ለአመታት እዚያ ብቻ እንዲከማችበት የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም፤ የሀገሪቱ የመከላከያ እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው ። ምንም ጥርጣሬ ሚስጥርም የለውም ። …” ይህ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትንተና ከፍ ብሎ ክህደቱ ቀድሞ የታሰበበትና የተመከረበት ስለመሆኑ ያነሳሁትን ሙግት ያጠናክርልኛል ። የክህደት ልምምዱ አሀዱ ብሎ ከጀመረበት እስከ ፍጻሜው የሚመዘዙ ቅጥልጥል ክህደቶችን እንዳሉ ልብ ይሏል ።
ይህ የእፉኝት ስብስብ በሀገርና በሰሜን ዕዝ በፈጸመው ክህደትና ጭፍጨፋው መንግስት ተገዶ ወደ የህልውናና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ ገብቶ ድባቅ ሲመታ ወዲያው የሀገርንና የመንግስት ስም በሀሰተኛና በተዛባ መረጃ ለማጠልሸት የተቀናጀና የተናበበ ዘመቻ ሲከፍት ጊዜ አልወሰደበትም ። የሀገሪቱን ሚዲያ ሲያዘምርና ሲያስጨበጭብ ኖሮ የራሱን መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያ ግን በአራት ትላልቅ ዘርፎች አደራጅቷል ። እርሱም ፦ 1ኛ . መደበኛ ሚዲያ 2ኛ. ማህበራዊ ሚዲያ 3ኛ .አለማቀፍ ሚዲያና ተቋማት 4ኛ.ስፒን ዶክተር ሰና ሎቢስትስ ናቸው።
የመጀመሪያው ማለትም እነ ትግራይ ቴሌቪዥንን ፣ ድምጺ ወያኔን ፣ ወይንን ፣ ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH)፣ ትግራይ ፈርስትን ፣ አይጋ ፎረምን ፣ ትግራይ ፕሬስን፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ ፣ ትግራይ ኦን ላይንና አውራምባ ታይምስ የሚያካትት ሲሆን ፤ሁለተኛው ዲጂታል ወያኔ አካልና ምን አልባት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የዲጂታል ጭፍራ ያለው ሲሆን በአንድ ለአምስትና በአንድ ለሀያ ተደራጅቶ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ በፌስ ቡክ ፣ በቲዊተር ፣ በዩቲውብ ፣ በቴሌግራም ፣ ወዘተረፈ የተዛባ መረጃን ፣ ውሸትን ፣ ጥላቻን ፣ ልዩነትን ፣ መጠራጠርን፣ ሴራን ፣ ወዘተረፈ የሚነዛ ተከፋይና ምንደኛ ስብስብ ሲሆን ፤ ሶስተኛው አለማቀፍ ሚዲያውን የተዛባ መረጃ የሚመግብ ምድብተኛ ነው ። አራተኛውና ሶስተኛው ምድብተኛ ተመጋጋቢ ናቸው ።
በዚህ ምድብ ነጮች ስፒን ዶክተርስና ሎቢስትስ ( spin doctors & lobbyist ) የሚሏቸው ሲሆን አላማቸው እንደቅደም ተከተላቸው አንድን ርዕሰ ጉዳይ እነሱ ከሚፈልጉት አቅጣጫ አንጻር እንዲተረጎምና እንዲበየን ጥረት ማድረግ ሲሆን ሎቢስቶች ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈላቸው የመንግስት ባለስልጣናትን ፣ የምክር ቤትና የሰኔት አባላትን በማግባባትና በማባበል ከቀጠራቸው ወይም ከከፈላቸው መንግስት ወይም ቡድን ጎን ለማሰለፍ ግፊት የሚያደርጉና የሚያግባቡ ናቸው ። እነዚህ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አለማቀፍ ሚዲያውንና እንደ መንግስታቱ ደርጅት ያሉ አለማቀፍ ተቋማትን የሚመግቡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው ።
እውነትን ይዘን ፣ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ሰቆቃ ተፈጽሞብን ፤ ጦርነት ተከፍቶብን ፣ በአደባባይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እንወርዳለን ተብለን፤ በሕዝብ ግንኙነቱ ፣ በፕሮፓጋንዳውና በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲው ብልጫ የተወሰደብን ሳያንስ ዛሬም አጀንዳ ተቀባይና ተከላካይ መሆናችን ሊያስቆጨን ይገባል ። እጀ ሰባራ ያደረገንን የሕዝብ ግንኙነት ስራችንን በደንብ ፈትሸን ማሻሻያ ልናደርግ ወቅቱና ዘመኑ የሚጠይቀውን ቁመና ልንይዝ ይገባል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2014