ስፖርት አእምሯዊና አካላዊ ጤናን በመጠበቅ፣ ምርታማ ዜጎችን በማፍራት፣ ለብዙዎች የስራ ዕድልን በመፍጠር፣ የሃገራትን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ ተፈጥሮን በመንከባከብ፣ ሰላምና መተሳሰብን በማስፈን ወዘተ ከፍተኛ ሚናን የሚጫወት ዘርፍ መሆኑ ተደጋግሞ ይነገራል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ ዘርፍ የሃገራት ኢኮኖሚ ምንጭ እና እጅግ ተመራጭ ከሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል አንዱ እየሆነ ይገኛል።ቢሊየን ዶላሮች የሚዘዋወሩበት በመሆኑም የዓለም ታላላቅ ባለሃብቶችና የተለያዩ አገራት የንጉሳዊያን ቤተሰቦችን ሳይቀር ለመሳብ እየቻለ ነው።
ስፖርት ከውድድርነት ባለፈ በዓመት በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር እንደሚያሳፍስ ብዙ ማሳያዎች አሉ።በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ዓለም ነገሮች በከፉበትና የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ዓመት (እአአ 2020) ከዚህ ዘርፍ 388 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የተገኘ ቢሆንም፤ ካለፈው ዓመት (እአአ 2019) በ15 ከመቶ ቅናሽ የታየበት ሆኖ ተመዝግቧል።ከሶስት ዓመታት በኋላም በዓመት ከስፖርት የሚገኘው ገቢ ወደ 600 ቢሊየን ዶላር ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።በመሆኑም ባለሃብቶችና ሃገራት ከኢኮኖሚ ትኩረት አቅጣጫዎቻቸው መካከል ስፖርትን አንዱ አድርገዋል።
ይህን ሁኔታ ከሃገራችን አንጻር ብንመለከተው ምንም ያልተሰራበት ዘርፍ ሆኖ እናገኘዋለን።በእርግጥ የአትሌቶች ሃገር በመሆኗ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ከእነሰንደቋ ከማሳወቅም አልፎ በስመጥር አትሌቶቿ ክብርን ለመደረብ ችላለች።ይሁንና መልካም ገጽታዋን በገነባችበት በዚህ ስፖርት የሚገባትን ማግኘት ሳትችል ዘመናትን አስቆጥራለች።በእርግጥ አትሌቶቻችን ባደረጉት የግል ጥረታቸው ሃገራቸውን ለመጥቀም በቅተዋል።ነገር ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ካለበት ሁኔታ አኳያ የመፍትሄ ስልቶች መካከል ዘርፉን ማካተት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ከተቸሯት ጸጋዎች መካከል አንዱ የተለያየ የአየር ሁኔታ ያለው የቦታ አቀማመጥ አንዱ ነው።ይህንን ተክትሎም እንደየአካባቢው ሁኔታና አኗኗር የተለያየ ተክለ ሰውነት ያላቸው ዜጎች መገኛ አገር ናት።ታዲያ ይህ የአኗኗር እና የተክለ ቁመና ስብጥር ለተለያዩ ስፖርቶች ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች ሊኖሯት እንደሚገባ የስፖርት ባለሙያዎች ይናገራሉ።ከዚህ ጎን ለጎን የሚነሳው ሌላው ሃሳብ ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከግማሽ በላዩ ወጣት እንደመሆኑ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ መሆኑ አይቀሬ ነው።በመሆኑም ስፖርት ለሃገሪቷ እምቅ ሊባል የሚችል የሃብት ምንጭ ለመሆን ይችላል ማለት ነው።
ሃገሪቷ በታወቀችበት የአትሌቲክስ ስፖርት የተገኘውን ውጤት ለዚህ በማሳያነት ማንሳት ይቻላል።ለአብነት ያህል የበረቱ አትሌቶች ከሃገራቸው አልፈው በሚካፈሉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሃገርን ስምና ክብር በበጎ ከማስጠራት አልፈው የውጪ ምንዛሬን ወደሃገራቸው በብዛት በማምጣትም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።በተለያዩ የዓለም ከተሞች ላይ በየሳምንቱ መጨረሻ በርካታ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እንደሚካሄዱ ይታወቃል።በእነዚህ የሩጫ ውድድሮች ላይ በግምት ሃምሳ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተካፋይ ይሆናሉ።ከእዚህ በመነሳትም በየሳምንቱ ከሽልማት የሚገኝ ምን ያህል የውጪ ምንዛሬ ገቢ ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።
በአትሌቲክስ ምክንያት መላው ዓለም ያወቃት ኢትዮጵያ በስልጠና እንዲሁም በውድድሮች በርካቶችን የመሳብ አቅም ያላት ሃገር ናት።በርካታ አትሌቶችን ባፈሩ ስፍራዎች ላይ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን እና ሆቴሎችን በመገንባት የስፖርት ቱሪዝሙን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩም አያጠራጥርም።ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ሃገር ውስጥ በማምጣትም ከዘርፉ አገር መጠቀም እንደምትችል ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በላይ ማሳያ አይኖርም።
አትሌቶቹ በሚሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች በርካታ ዜጎችን ቀጥረው በማሰራት ለሃገር የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግረው በተግባር አሳይተዋል።ለዚህ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር ያሉ ምርጥ አትሌቶች ለሃገራቸው እያበረከቱ ያሉትን ውለታ ያላስተዋለና የማይመሰክር የለም።ይህ ሁኔታ በሌላውም ስፖርት የሰፋ ቢሆንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃገርን መወከል የሚችሉ በርካታ ስፖርተኞችን ማፍራት ቢቻል ከእነርሱ የሚገኘው ጠቀሜታ ሃገርን ከመገንባት አኳያ ምን ያህል ፋይዳ እንደሚኖረው መገመት ይቻላል።
እግር ኳስን ጨምሮ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የውጪ ሃገር ክለቦች ላይ ተሳታፊ መሆን አንዱ የውጪ ምንዛሬ ምክንያት መሆኑ እርግጥ ነው።በአውሮፓ ሊጎች ብቻ ከ500 በላይ የሚሆኑ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ያሉ ሲሆን፤ ሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ኮትዲቯርና ጋና የመሳሰሉት ሃገራት ደግሞ በዚህ ረገድ ቀዳሚዎቹ ናቸው።ከ10-150ሺ ዶላር ድረስ በወር እንደሚከፈላቸው መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፤ ከዚህ ተጠቃሚ የምትሆነውም ሃገር ናት።በኢትዮጵያ ደግሞ እድልና ትኩረት ያላገኙ ነገር ግን እግር ኳስን መጫወት የሚችሉ በርካታ ታዳጊና ወጣቶች አሉ።ቦታ እና ትኩረት ቢሰጣቸውም እንደሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በውጪ ክለቦች ተጫውተው ለሃገራቸው ኢኮኖሚ የድርሻቸውን የማበርከት ዕድል ይኖራቸዋል።
ስፖርት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የገቢና የስራ ምንጭ ከመሆኑም ባለፈ በስፖርት ተሳታፊ የሚሆኑ ወጣቶች አላስፈላጊ ነገሮች ላይ የሚያጠፉት ጊዜ ስለሌለ በሃገር ሰላም ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።ስፖርት ሰላምንና መከባበርን ይሰብካል፤ በስፖርት የታነጹ ወጣቶችም ሃገርን ሊጎዱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ እድላቸው ጠባብ ሲሆን ለአልባሌ ነገሮችም ቦታ አይኖራቸውም።ስፖርት አለመግባባትና ሁከትን የመፍታትና እርቅን የማውረድ ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑን ከኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን በላይ አስረጂ አይኖርም።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ለዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ግጭትና በዚህም ምክንያት የፈሰሰውን የብዙዎች እንባ ያደረቁት እአአ በ2006ቱ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኗ አባላት ናቸው።ተጫዋቾቹ በጉልበታቸው ተንበርክከው በሃገራቸው ሰላም እንዲወርድ ያደረጉት ተማጽኖ ፍሬ አፍርቶ ተመልክተናል።በመሆኑም በሰላማዊው የፉክክር ሜዳ የሚሳተፉ ወጣቶችን ማብዛት በጦር ሜዳ የሚያልፈውን ዜጋ ቁጥር ሊቀንሰው እንደሚችል ግልጽ ነው።
ወጣቱን በዚህ ዘርፍ አሰማርቶ ከራሱ ባለፈ ሃገሩንም እንዲጠቅም ለማድረግ ደግሞ ስፖርቱን የሚከውንበትን ሁኔታ ማስፋት የግድ ይሆናል።በተለይ ታዳጊዎች በሚኖሩባቸውና በሚማሩባቸው ስፍራዎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋት፣ ተምሳሌት ይሆኗቸው ዘንድ በስፖርት ውጤታማ ሆነው የሃገራቸውን ስም ያስነሱ ስፖርተኞችን ታሪክ ማውሳት እንዲሁም ስኬትን ላስመዘገቡ ስፖርተኞች ተገቢውን አክብሮት በመስጠት ታዳጊና ወጣቶች ይበልጥ ወደ ስፖርቱ እንዲሳቡ ማድረግ ይቻላል።በአጠቃላይ የሀገሪቱን ስፖርት ከዓመታዊ ውድድር በዘለለ ያሉትን ጠቀሜታዎች እየፈተሹ መሬት ማውረድ በመስኩ ካሉት ኃላፊዎች የሚጠበቅ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2014