የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለ43ኛው ጊዜ የፊታችን ቅዳሜ በዴንማርክ አርሁስ ከተማ ይጀመራል። ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ይፋ እንዳደረገውም በዚህ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከስልሳ ሰባት አገራት የተውጣጡ አምስት መቶ ሰማንያ ሁለት አትሌቶች ይሳተፉበታል።
በአራት ውድድሮች የሚካሄደው የዘንድሮው መርሃ ግብርም በአዋቂና በታዳጊዎች ከሃያ ዓመት በታችም አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም የድብልቅ ሪሌ ውድድሮች እንደሚካሄድም ታውቋል። ኢትዮጵያም በእነዚህ ውድድሮች የሚወክሏትን አትሌቶች መርጣለች።
ሰለሞን ባረጋ፣ አንድአምላክ በልሁ፣ ቦንሳ ዲዳ፣ ሰለሞን በሪሁ፣ አብዲ ፉፋ፣ ሞገስ ጥኡማይና እንየው መኮንንም በአዋቂ ወንዶች ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ሆነዋል። በወጣት ወንዶች፤ ድንቃለም አየለ፣ ፀጋዬ መኮንን፣ ቢተው አደም፣ ጌትነት የትዋለ፣ ሚልኬሳ መንገሻ፣ ገብረጊዮርጊስ ተክላይና ታደሰ ወርቁ ተካተዋል።
በአዋቂ ሴቶች ለተሰንበት ግደይ፣ ደራ ዲዳ፣ ጌጤ አለማየሁ፣ ሃዊ ፈይሳ፣ ዘነቡ ፍቃዱ፣ ፀሐይ ገመቹ እንዲሁም ፎቴን ተስፋዬ ተመርጠዋል። በወጣት ሴቶች፤ አሚናት አህመድ፣ ሚዛን ዓለም፣ መሰሉ በርሄ፣ ፅጌ ገብረሰላማ፣ ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር፣ ውዴ ከፍአለ እንዲሁም
አለሚቱ ታሪኩ የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል። በድብልቅ ሪሌይ፤ ቦኔ ጮሎቄ፣ ከበደ እንዳለ፣ ታደሰ ለሚና ፋንቱ ወርቁ ተመርጠዋል።
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን አባላት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪና በአዲስ አበባ በጃንሜዳና በስቴድዮም ጠንከር ያለ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉና ሌሎችም አመራሮች በቦታው በመገኘት ሲያበረታቱና ክትትል ሲያደርጉላቸው መቆየታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በዚህ መድረክ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በቂ ዝግጅት ማድረጉንና አትሌቶቹም ውጤታማ ሆነው እንደሚመለሱ እምነት ይዟል። በመካከለኛው ርቀት በግሉ፣ እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ ብቃቱን እያስመሰከረ የሚገኘው ሰለሞን ባረጋ በዚህ ውድድር ይጠበቃል፡፡
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከወራት በፊት ጃንሜዳ በተከናወነው ውድድር ላይ በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች 31፡18፡36 በመግባት ነበር ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ የቻለው፡፡ በዘንድሮው ፍልሚያ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የወጠነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድንም ትናንት ምሽት በአራራት ሆቴል ሽኝት ተደርጎለታል።
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ይፋ ባደረገው መሠረት፤ በመድረኩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች፤ በአጠቃላይ ሦስት መቶ አስር ሺ ዶላር ተዘጋጅቷል። በሁለቱም ፆታዎች በአዋቂዎች ምድብ አሸናፊዎች ለሚሆኑ አትሌቶች አንድ መቶ አርባ ሺ ዶላር የሚቋደሱ ይሆናል።
በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታ አንደኛ ለሚወጡት እያንዳንዳቸው ሰላሳ ሺ ዶላር፤ ሁለተኛ አስራ አምስት ሺ፤ ሦስተኛ አስር ሺ፤ አራተኛ ሰባት ሺ፤ አምስተኛ አምስት ሺ እንዲሁም ስድስተኛ ሦስት ሺ ዶላር ሽልማት የሚሰጣቸው መሆኑም ታውቋል። ለድብልቅ ሪሌም ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በወጣቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችም የእውቅና ሽልማት የሚሰጣቸው ይሆናል።
በአገር አቋራጭ ውድድር ላይ እንደ ቡድን የሚመዘገበው ውጤት ፋይዳው የላቀ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ በዘንድሮው ፍልሚያም በቡድን አንደኛ መሆን የቻለ አገርም ከአስራ ሁለት ሺ ዶላር አንስቶ በየደረጃው ሽልማቱን እንደሚረከብ ለማወቅ ተችሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በተከናወነው 42ኛው አገር አቋራጭ ውድድር ኬንያ በ4 ወርቅ፣ በ5 ብር እና በ3 ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳልያ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያ በአንፃሩ በ4 ወርቅ፣ በ4 ብር እና በ1 ነሐስ ዘጠኝ ሜዳልያዎችን በማምጣት ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።
አዲሰ ዘመን መጋቢት 17/2011
ታምራት ተስፋዬ