አዲስ አበባ፡- በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ወደ ውጭ ከተላኩ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርቶች 13 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ስርጃቦ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በወሩ 21 የቆዳ ፋብሪካዎች፣ 11 የጫማ ፋብሪካዎች፣ ሶስት የጓንት ፋብሪካዎችና ዘጠኝ የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ 13ሚሊዮን 123 ሺ 880 ዶላር አስገኝተዋል፤ አፈፃፀማቸውም ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር ማሳካት የተቻለው 59በመቶ ብቻ ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በወሩ ለተገኘው ገቢ የውጭ አገር ኩባንያዎች 86ነጥብ 4በመቶ፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች 13ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ የኩባንያዎች የተናጠል ዕቅድ አፈፃፀም ሲታይ፤ ከቆዳ ፋብሪካዎች ፍሬንድሺፕ ቆዳ ፋብሪካ 2ነጥብ 2ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች እንጦጦ ቤተ አርትሲያን 69ነጥብ41 ሺ ዶላር ማስገኘት ችለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ከቆዳ ፋብሪካዎች አምስቱ፣ ከጫማ ፋብሪካዎች ሁለቱ እንዲሁም ከቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች አንዱ ከ80በመቶ በላይ ዕቅዳቸውን ያሳኩ ሲሆን፤ ሁዋጂያን ኢንተርናሽናል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ግንባር ቀደም መሆን እንደቻለ ገልፀዋል፡፡
«የጥቅምት ወር አፈፃፀም የኤክስፖርት ገቢ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ተገኝቶ ከነበረው 13በመቶ ብልጫ አሳይቷል» ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ጭማሪው በምርት ስብጥር ሲታይ ያለቀለት ቆዳ 597 ሺ38፣ በጫማ 368 ሺ38 ፣ በጓንት 123 ሺ23ና በአልባሳትና ዕቃዎች 410ሺ9 ምርቶች ወደ ውጭ መላካቸውን አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በአጠቃላይ ያለፉት አራት ወራት አፈፃፀም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ ቢኖረውም ለማሳካት ከታቀደው አንፃር ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የውጭ ንግድ ተሳትፎ ማደግ ባለመቻሉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
«በውጭ ንግዱ ላይ የሚሳተፉት የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር ያሉትም ቢሆኑ የአለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸው ዝቅተኛ ነው» ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቱት ምርት ጥራትና ስብጥርን ከማሳደግ አኳያ የሚሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
የምርቶቻቸውን መዳረሻ አገሮች ከማስፋትና ለዚያም በሙሉ አቅም ከመስራት ይልቅ የለመዱትን ገበያና ምርት ብቻ ይዘው የሚቀርቡ በመሆናቸው ተወዳዳሪነታቸውን እንደቀነሰ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥና አሜሪካና ቻይና በፈጠሩት የንግድ ውዝግብ ምክንያት የአለም ገበያ መቀዛቀዝ ለአፈፃፀሙ ማነስ የበኩላቸውን አሉታዊ ሚና መጫወታቸውን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን አቅም የማጎልበት ስራ አጠናክሮ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤በተለይም የዘርፉን የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት ከማጎልበት አኳያ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋርም በመተባበር በኢንዱስትሪዎቹ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ማህሌት አብዱል