ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አሰልጣኞችን መቀያየር መገለጫቸው ሆኗል። ክለቦቹ አሰልጣኝ ሲያባርሩ ቋሚ የሆነ መስፈርት እንደሌላቸው የሚነገር ሲሆን፣ ሽንፈትን በፀጋ በመቀበል ወደ ስኬታማነት ለመመለስና ስህተትን በሙያዊ መንገድ አርሞ ለማሻሻል የሚያስችል የግምገማና የመመዘኛ መስፈርት በሌለበት አሰልጣኞች ለመባረር በጣም ቅርብ ሆነዋል።
ለአሰልጣኞች በቂ ጊዜ መስጠት የሚባለውም በሊጉ ክለቦች ዘንድ ከተረሳ ሰንበትበት ብሏል። ትልቁ መመዘኛም ውጤት ማምጣት ብቻ ሆኗል። ከውጤት በዘለለ የውጤታማነቱን መንገድ የመመልከት፣ በቡድኑ ላይ የሚታየውን እድገት የመገንዘብና የአሰልጣኞችን ክፍተት ለመሙላት የሚጥሩ ክለቦችም በጣም ጥቂት መሆናቸው ይነገራል።
አሰልጣኞች ላስመዘገቧቸው ውጤቶች ከፍተኛ አድናቆት እና አክብሮት የሚሰጥ ክለብ ጠፍቷል ለማለት ያስደፍራል። አሰልጣኞች ቡድናቸውን በራሳቸው መንገድ እንዲገነቡና እንዲያዋቅሩ ዕድሉን ያልሰጡ ክለቦች ሳይቀር በማባረር ስለመጠመዳቸው በስፋት ይነገራል።
ክለቦች አሰልጣኞችን ለማባረር ሲወስኑ ምክንያታቸው ‹‹በስምምነት ነው›› ይባል እንጂ የደጋፊ ተቃውሞና የተጫዋቾች አድማ እንደሆነም በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል። ክለብና አሰልጣኙ ሲለያዩ የሚከፈለው የካሳ አከፋፈልም ቅጥ አምባሩ የጠፋበት ነው።
የክለቦችና አሰልጣኞች የተረጋጋ የሥራ ግንኙነት መጥፋት በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬም እንደ ትናንቱ ሁሉ በሞቀ ሁኔታ እንደቀጠለ ከሰሞኑ የተሰሙ የስንብት ዜናዎችን መጥቀስ በቂ ማስረጃ ይሆናል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዓመትም ገና በመጀመሪያው ዙር በአሰልጣኝ ስንብት ተንጧል። በመጀመሪያ ዙር የሊጉ መርሃ ግብር ብቻ ስድስት ያህል ክለቦች ከአሰልጣኛቸው ጋር ተፋተዋል።
አሰልጣኞቻቸውን ካሰናበቱ ክለቦች መካከልም፤ ወላይታ ድቻ አንዱ ነው። ድቻዎች የቀድሞውን የኢትዮጵያ ባንክ፣ መከላከያ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ እንዲሁም ኤሌክትሪክና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የመሩትን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በዋና አሰልጣኝነት ሾመዋል።
ባለፈው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ወልዋሎን ከወራጅነት ስጋት የታደጉት ዘንድሮ አዲስ የአንድ ዓመት ኮንትራትን ተፈራርመው የነበሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ሌላኛው በመጀመሪያው የሊጉ ውድድር ክለባቸው የተሰናበቱ አሰልጣኝ ናቸው።
ከቀድሞው የትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሐረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክና አርባምንጭ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጋር በስምምነት የተለያዩት ቢጫ ለባሾቹ ወልዋሎዎች፤ በሁለተኛው ዙር ውጤታማ ለመሆን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ መቀሌ 70 እንደርታን፤ ደደቢትንና ድሬዳዋን ያሰለጠኑትን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ምርጫቸው አድርገዋል።
አሰልጣኙን ያሰናበተው ሌላው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ነው። ቡናማዎቹ፤ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጅማሮ መልካም የሚባል ብቃት ማሳየት ቢችሉም ቀስ በቀስ ውጤት እየራቃቸው በተለይም ክለቡ በሜዳ ላይ የሚያሳየው አሳማኝ ያልሆነ
እንቅስቃሴን ተከትሎ ከፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ጋር የነበራቸውን ውል አቋርጠዋል። ገዛኸኝ ከተማን አሰልጣኝ አድርገውም ሾመዋል።
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሌላኛው ከአሰልጣኙ ጋር የተለያየ ክለብ ስሁል ሽረ ነው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ደካማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ በደረጃ ሰንጠረዡም በወራጅ ቀጣና የሚገኘው ስሑል ሽረ ሳምሶን አየለን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሯል፡፡
ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኛቸውን ካባረሩ ክለቦች መካከል ስሙ ይካተታል። ደቡብ ፖሊስ ከዲላ ከተማ ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት የውጤት ቀውስ ገጥሞት በወራጅ ቀጣና የሚገኘውን ደደቢት ዳንኤል ፀሐዬን ወደ ቀድሞ ቤቱ መልሷል።
የሊጉ ክለቦች በመሰል ሁኔታ በአሰልጣኝ ሹም ሸር መጠመዳቸው ታዲያ አሁን ላይ በርካታ የስፖርት ቤተሰቡን በማነጋገር ላይ ይገኛል። ለመሆኑ የክለቦቹ ወቅታዊ ተግባር መንስኤና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ አበይት ነጥቦች ላይ አዲስ ዘመን ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
አዲስ ዘመን ካነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች
መካከልም አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አንዱ ናቸው። አሰልጣኝ አስራት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት አምስት አስርት ዓመታትን አሳልፈዋል። በርካታ ክለቦችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል። በሙያቸውም ኮከብ ተብለው ተሸልመዋል።
ጉዳዩን በሚመለከት «በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የክለቦች የአሰልጣኝ ሹም ሽር ላይ ግልፅ ያልሆኑ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ» የሚሉት አሰልጣኝ አስራት፤ አንዳንድ አሰልጣኞች ውል ሲፈፅሙም ለምን ያህል ጊዜ ክለቡን ለማሰልጠን እንደተስማሙ ሳይቀር ግልፅ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኞች ወደ አንድ ክለብ ተዘዋወሩ አሊያም ተሰናበቱ ሲባል ብቻ እንደሚሰማም ገልጸዋል።
እንደ አሰልጣኝ አስራት ገለፃ፤ የአገሪቱ ክለብ አሰልጣኝ የሚሾሙና የሚሽሩ ቀጣሪዎች ሙያተኞች አይደሉም። አሰልጣኝ መርጠው ወደ ክለቦች የሚያስገቡትም ሆነ የሚያስወጡት ደላሎች ናቸው። ሁሉም ቡድኖች ከተጫዋቾች እስከ አሰልጣኙ ደካማና ጠንካራ ጎኖችን የሚለዩ የቴክኒክ
ቡድን የላቸውም። የመባረራቸው ዋነኛ ምክንያቱ በዝርዝር ይፋ አይሆንም። አሰልጣኞች ሲቀጠሩም ሆነ ሲባረሩ ምክንያቱ ግልጽ አይደለም።
«ክለቦች ዘንድ ሄደህ አሰልጣኝ ስትቀጥሩም ሆነ ስታባርሩ መስፈርታችሁ ምንድነው? እስቲ አሳዩኝ ብትላቸው ምንም የሚያሳዩት የላቸውም፤ ውጤት ካመጣህ ሊያስቀጥሉህ፤ ውጤት እያስመዘገብክም እንደ ፍላጎታቸው ካልሆንክና ካልተስማማህ ሊያባርሩህም ይችላሉ» ይላሉ።
ክለቦች በአሰልጣኝ ሹም ሽር ለመጠመዳቸው ውጤትን ምክንያት ማድረጋቸው የማይስማሙበት አሰልጣኝ አስራት፤ «ከአንድ ውጤታማ ያልሆነ ክለብ የተባረረ አሰልጣኝ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሌላ ክለብ ሲዘዋወር እየተመለከትን ይህን ማሰብ አግባብ አይደለም» ይላሉ። ይልቅስ አንድ የተለየ የእርስ በእርስ ጥቅም ትስስር እንዳለና ሙስና ውስጥ ስለመሆናቸው ፍንጭ የሚሰጥ መሆኑንም ያሰምሩበታል።
አሰልጣኝ አስራት፤ ክለቦች አንድ አሰልጣኝ ለማበረር ሲወስኑ ውጤት በምክንያትነት ማንሳታቸው አሳማኝ ላለመሆኑ ሌላም ማስረጃ አላቸው። ይህም ውጤት የአንድ ሰው ብቻ ድምር ግኝት አለመሆኑንና በአንድ ሰው ተጠያቂነት ላይ ሊወድቅ እንደማይገባውም ነው የሚያስረዱት።
ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህገ ደንብ በራሱ ትክክል አለመሆኑንና የሚያምታቱና ግራ የሚያጋቡ መሆናቸውን አሰልጣኙ ያመለክታሉ፡፡ እንዲሁም አሰልጣኞችንም ሆነ ክለቦችን የሚጎዱ ውሎችን መያዙን ጠቅሰው፤ የአገሪቱ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃንም የሚደግፏቸውና የሚቃወሟቸው፤ ውጤት አጥተው ሳለ ደግሞ ውጤታማ ናቸው
ብለው የሚያንቆለጳጵሷቸው አሰልጣኞች መኖራቸውንና ይህም ሙያና ስፖርቱን እጅጉን መፈተኑን ነው ያብራሩት።
መሰል ችግሮች ለመሻገር ከሁሉ በላይ አሰልጣኝ ለመሾምና ለመሻር መጣደፉ አግባብ አለመሆኑን አሰልጣኙ ጠቅሰው፤ ለአሰልጣኞች ጊዜ መስጠት እንዲሁም እግር ኳሱን በአግባቡ መምራት የሚችልና ለስፖርቱ ፍቅር ላላቸው ሙያተኞች ቦታ መስጠት ተገቢነቱን አብራርተዋል፡፡ አሻሚ የሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሕገ ደንቦች ሊስተካከሉ እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የቀድሞውን የኢትዮጵያ ባንክ፣ መከላከያ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ እንዲሁም ኤሌክትሪክና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የመሩትና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን አስተያየት ከጠይቅናቸው ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። እርሳቸውም እንደተናገሩት፤ መሰል የሊጉ ክለቦች የአሰልጣኞች ሹም ሽር ተግባር በአገሪቱ ዛሬ ላይ የጀመረ ሳይሆን ትናንትም የነበረ ስለመሆኑና የዚህም ዋና ችግር ለአሰልጣኞች በቂ ጊዜ አለመስጠት ነው።
እንደ አሰልጣኝ አሸናፊ ገለፃ፤ የፕሪሚየር ሊጉ ደጋፊዎችም ሆኑ የክለብ አመራሮች ለአሰልጣኞች በቂ ጊዜ ሲሰጡ አይስተዋሉም። ይህ ደግሞ ለውጤት ከመጓጓት አንፃር የሚፈጠር ነው። በእርግጥም አሰልጣኞች የሚመዘኑት በውጤት ነው። ውጤታማ ያልሆነ አሰልጣኝ መነሳቱም የግድ ነው። ይሁንና አሰልጣኞች ወደ ሥራ ሲገቡ የሚሰጣቸው የጊዜ ገደብ ወሳኝነት አለው።
ለአሰልጣኞች ብዙ ጊዜን መስጠት እጅጉን ወሳኝ ነው የሚሉት አሰልጣኝ አሸናፊ፣ ጊዜ ሳይሰጠው በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ውጤት እንዲያመጣ መጠበቅ ደግሞ አግባብ አለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ማንኛውም አሰልጣኙ በተረጋጋ ሁኔታ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣና ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ቢያንስ የአራት ዓመት ጊዜን መስጠት እንደሚገባ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
«ለአሰልጣኞች በቂ የሆነ ጊዜን መስጠት በአገር አቀፍ ደረጃ ሊታሰብበት መፍትሄ የሚፈልግ አጀንዳ ነው የሚሉት» አሰልጣኝ አሽናፊ፤ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ለአሰልጣኞች ጊዜ ከመስጠት ባሻገር የክለብ አመራሮችን ከሙያው ጋር የቀረበ እውቅትና ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባውም ነው አፅዕኖት የሰጡት።
አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በአሰልጣኝነት ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዋና አሰልጣኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አሰልጣኝ ብርሃኑ፣ ‹‹የአገሪቱ የክለቦች በአሰልጣኝ ሹም ሽር መጠመድ ምክንያት ሌላ ሳይሆን ከላይ እስከ ታች ራሱን የቻለ ወጥ ሥርዓት አለመኖርና በሥርዓቱም ያለመመራቱ ችግር የወለደው ነው» ይላሉ።
እንደ አሰልጣኝ ብርሃኑ ገለፃ፤ የአንድ ቡድን ቴክኒካል ዳይሬክተር ባለሙያ መሆን አለበት። ይሁንና ይህ በአግባቡ ተግባራዊ የሚደረገው በጥቂት ክለቦች ዘንድ ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ እግር ኳስ አሳሳቢ ችግር ውስጥ የገባው ለሙያው የማይመጥኑና ሙያ የሌላቸው ሰዎች በአመራር ቦታው ላይ በመቀመጣቸው ነው።
ከሁሉ በላይ የክለብ አመራሮች ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኃላፊነታቸው ምን እንደሆነ ተለክቶ አይሰጣቸውም። ይህ በመሆኑም አንድ ውሳኔ ለማስተላለፍ ግድ አይሰጣቸውም። የአሰልጣኞች ቅጥር ልምድ፣ ብቃትና ውጤት ሳይሆን ቡድንተኝነትን መሠረት ያደረገ ነው። አንድ አሰልጣኝ ሲመጣ ለአንድ ዓመት ይፈርማል፤ ይህ በራሱ ትክክል አይደለም።
ይባስ ብሎ አሁን አሁን ለአንድ ዓመት የተሰጠውን ጊዜ ሳይጨርስ በስድስት ወራት ውስጥ የሚባረርበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። ክለብና አሰልጣኙ ሲለያዩ መጀመሪያውኑ ውል ሲፈፅሙ ግልፅ ባለመሆኑ ሲለያዩም ግልፅ የሚሆን ነገር አይኖርም።
በእርግጥ ለአሰልጣኞች ውጤት ዋነኛ መመዘኛ ነው። ከታች ጀምሮ ሥራዎች በአግባቡ ቢከናወኑ ውጤታማ መሆን ይቻላል። ይሁንና ከላይ እስከ ታች በሥርዓት መመራት አይስተዋልም። የክለብ ፕሬዚዳንትም ፀሐፊም ሆነ አሰልጣኞች የሚሾሙት በሰበሰቧቸው ደጋፊዎች ተፅዕኖ ታግዘው ነው። ይህም ተደጋጋሚ ሹም ሽሮች ለመታየታቸው አብይ ምክንያት ነው።
«ክለቦች አሰልጣኞችን የሚመዝኑበት መመዘኛ የላቸውም። ይህም ከዓመት ዓመት መሻሻል የተሳነው ነው» የሚሉት አሰልጣኙ ብርሃኑ፤ አሰልጣኞች በክለብ ቆይታቸው በሚሰሯቸው ሥራዎች ለመፈተሽ የሚዘጋጁ መስፈርቶች ቢኖሩም እንኳን አሻሚ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ።
መመዘኛው እንደ አገር የተቀመጠ አሊያም ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሊጉ ከፍታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን የሚያስገነዝቡት አሰልጣኙ፤ አመራሮቹ ከአሰልጣኝነት እውቀት ጋር የሚዛመድ በቂ እውቀት ባለመያዛቸውም ግምገማዎች በዘፈቀደ እንደሚከናወኑ ነው ያስረዱት።
መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ሊደረጉ ስለሚገባቸው አበይት ተግባራት ሲናሩም፤ በቀዳሚነት ሁሉም የሚመራበት ስርዓት መቀመጥ እንዳለበት ነው ያመለከቱት፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ቡድንተኝነትና ዘመድ ያነቀውን አሰራር የሚያስተካክልበት ህግ ደንብ ያስፈልገዋል» የሚሉት አሰልጣኝ ዘላለም፤ በክለቦች አሰልጣኞቹ ሹም ሽር በርካታ ረብጣ የአገር ሃብት እየፈሰሰ እንደመሆኑ መንግስት ችግሩ ምንድነው ብሎ ሊጠይቅ እንደሚገባ ነው አፅንዖት የሰጡት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2011
በታምራት ተስፋዬ