በስፖርቱ ዓለም በርካቶች ወደ ስኬት ጎዳና ለመረማመድ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል። ጥቂት የማይባሉ ደግሞ በብልሃት፣ በጥረትና በታታሪነት በአጭር ጊዜ የስኬት ማማ ላይ ይቀመጣሉ። ጽናትና ከፍተኛ ጥረትን በሚጠይቀው የአትሌቲክስ ስፖርት በወጣትነት ዕድሜያቸው የዓለም ከዋክብት የሆኑ አትሌቶችን ማፍራት ከቻሉ አሰልጣኞች መካከል ተሰማ አብሽሮ አንዱ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።ይህ ወጣት አሰልጣኝ ወደ ስፖርቱ የገባው በአትሌትነት አልፎ ሲሆን፤ የንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ ሯጭ በመሆን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ነበር።
የለንደን ማራቶንን ሲሮጥ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት የተነሳም በህክምና ባለሙያዎች መሮጥ እንደማይችል ስለተነገረው በግሎባል ስፖርት ኮሚኒኬሽን ዓለም አቀፍ የአሰልጣኝነት ስልጠና በመውሰድ ሙያውን ተቀላቅሏል።በአትሌትነት እና በስልጠና ካገኘው ልምድ ባለፈም በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ በመማር የግሎባል ስፖርት ኮሚኒኬሽን የኢትዮጵያ ተወካይ በመሆን ማሰልጠኑን ቀጥሏል።
በስምንት ዓመት ውስጥም ገናና ስም ካላቸው ወጣት አሰልጣኞች አንዱ እስከመሆን መድረሱን ኤንኤን ረኒንግ ቲም በቅርቡ በድረገጹ ባስነበበው ሰፊ ጽሑፍ መስክሮለታል።ተሰማ በዚህ ወቅት በዓለም ላይ ካሉ አሰልጣኞች ልዩ የሚያደርገው አንድ ነገር አለ። የእርሱን ያህል በማራቶን ታሪክ ፈጣን የሚባሉ 12 ሴት አትሌቶችን ማፍራት የቻለ አሰልጣኝ አለመኖሩ ልዩ ያደርገዋል።
ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ከሚንቀሳቀሱ የአትሌት ማናጀሮችና አሰልጣኞች ቀዳሚ የሚያደርገው ሲሆን መቀመጫውን በአዲስ አበባ ባደረገው ቡድን ከ70 በላይ አትሌቶችን ያሰለጥናል።ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ባሻገር የእስራኤል እና የጅቡቲ አትሌቶችንም በማሰልጠን ላይ ይገኛል።በስልጠና ቡድኑ ውስጥ 45 ሴት አትሌቶች ሲኖሩ፤ እነዚህ አትሌቶች ተደጋጋሚ ትልልቅ ድሎችን አስመዝግበዋል።
ተሰማ በጎዳና ላይ ሩጫዎች እጅግ ምርጥ የሚባሉ አትሌቶችን ሲያሰለጥን፤ በማራቶን ከ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ በታች የሆነ ሰዓት ያስመዘገቡ እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ከ66 ደቂቃ በታች የገቡ በመሆናቸው የ ‹‹ፕላቲኒየም›› ደረጃ ውስጥ ይካተታሉ። 2:17:58 የሆነ ሰዓት ያላት ደጊቱ አዝመራው፣ 2:19:28 በሆነ ሰዓት የገባችው ዘይነባ ይመር፣ የዘንድሮው ሮተርዳም ማራቶን አሸናፊዋ ሃቨን ኃይሉ እንዲሁም በግማሽ ማራቶን የምንጊዜም ምርጥ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው ፀሐይ ገመቹ ተሰማ በአሰልጣኝነት ሕይወቱ ለትልቅ ስኬት ካበቃቸው ሴት አትሌቶች የሚጠቀሱ ናቸው።
በግማሽ ማራቶን የዓለም ሁለተኛዋ ፈጣን አትሌት እንዲሁም በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠችበት የሃምቡርግ ማራቶን 2:17:23 በመግባት የኢትዮጵያ ሁለተኛውን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበችው ያለምዘርፍ የኋላውም ከአሰልጣኝ ተሰማ የስኬት ማሳያዎች መካከል አንዷ ናት።ተሰማ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ከሴቶቹ ባለፈ ምርጥ የወንድ አትሌቶችንም ለትልልቅ ስኬት አብቅቶ አሳይቷል። ከታናሽ ወንድሙ አየለ አብሽሮ ጀምሮ እንደ አበራ ኩማን የመሳሰሉ በማራቶን ትልቅ ስም ያተረፉ አትሌቶች አሰልጥኖ ለስኬት አብቅቷል። በሃምቡርግ ማራቶን 2:05:07 በሆነ ሰዓት በመሮጥ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ወርቅነህ ታደሰ እንዲሁም በአምስተርዳም ማራቶን 2:05:22 የሮጠው አፈወርቂ ብርሃኔም የተሰማ ፍሬዎች ሆነው ይጠቀሳሉ።
ወጣቱ አሰልጣኝ ተሰማ ሴት አትሌቶቹ በተለየ መልኩ ውጤታማ ሊሆኑ የቻሉት ከባህሪያቸው ጋር በተያያዘ መሆኑን ይናገራል።‹‹ሴት አትሌቶች በስልጠና ወቅት የምላቸውን ሰምተው ይተገብራሉ፤ ማረፍ ሲኖርባቸውም እንዲሁ።የስልጠናውን አስፈላጊነት ስለሚረዱም ውጤታማ ሊሆኑ ችለዋል›› ሲል አስተያየቱን ገልጿል። አትሌቶቹ በትጋታቸው ውጤት ከማስመዝገባቸው ባለፈ የተባሉትን በመተግበራቸው ለጉዳት እምብዛም እንዳይጋለጡ እንዳደረጋቸውም ይጠቁማል።
እርስ በእርሳቸው ያላቸው መግባባትም ተያይዘው እንዲያድጉ ያገዛቸው መሆኑንም ‹‹ሴቶቹ በስልጠና ወቅት እርስ በእርሳቸው ይረዳዳሉ፣ ሃሳባቸውን ይካፈላሉ።በስልጠና ወቅት ሲሳሳቁና ሲቀላለዱ ማየት የተለመደ ነው።ይህ ሁኔታም በጋራ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል›› በማለት ያብራራል።ከአሰልጣኛቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትና ሃሳባቸውን ለመግለጽ ያላቸው ነፃነትም በውድድር እንዲሁም በልምምድ ስፍራዎች በግልጽ የሚስተዋል መሆኑንም ለድረ ገጹ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል።
ከዚህ በመነሳትም ‹‹ተሰማ የሚያሰለጥናቸው ሴት አትሌቶች የስኬታማነቱ ምክንያት ሆነዋል?›› የሚል ጥያቄ ይነሳል።ለዚህም የሚሰጠው ምላሽ ‹‹ሁለቱንም ጾታዎች በማሰልጠን መልካም የሚባል ውጤት አስመዝግቤያለሁ።ቢሆንም የሴት አትሌቶች ከስልጠና ፍልስፍናዬ በልዩነት ከመቀበላቸው አንጻር ስኬታማ ሊሆኑልኝ ችለዋል።በእርግጥ ወንዶቹም ይተገብራሉ፤ ነገር ግን ውጤታማነቱ የሚታየው በሂደት ነው።ቢሆንም እንደሴቶቹ ሊሆን አይችልም›› የሚል እምነት እንዳለው አብራርቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2014