የ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሃያ ስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ ደርሰዋል። በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ውድድሩ ከአዳማ ወደ ባህርዳር አምርቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ እስከ ተገናኙበት የጨዋታ ውጤት ድረስ ቻምፒዮኑ ክለብ ማን እንደሚሆን ቀድመው ግምታቸውን ማስቀመጥ ችለው ነበር። ይሁን እንጂ የዚያ ጨዋታ ውጤት እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ነገሮች ባልተጠበቁ ውጤቶች ተቀያይረዋል። ይህም የፕሪሚየር ሊጉን መገባደጃ ከተገማችነት ወደ አጓጊነት የቀየረው ሲሆን እያንዳንዱ ጨዋታ ለቻምፒዮንነትም ይሁን ላለመውረድ የሚደረገውን ትግል የሚወስን ሆኗል።
ከሊጉ ጅማሬ አንስቶ አሁንም ድረስ በመሪነቱ የቀጠለው ቅዱስ ጊዮርጊስ(ፈረሰኞቹ) ውድድሩ ከአዳማ ወደ ባህርዳር እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ ለቻምፒዮንነት ሰፊ እድል ነበራቸው። ፈረሰኞቹ አሁንም ይህ ወርቃማ እድል በእጃቸው ቢገኝም ውድድሩ ባህርዳር መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ለበርካታ ሳምንታት የነጥብ ልዩነታቸውን አስፍተው በተጓዙበት መንገድ መቀጠል አልቻሉም።
ፈረሰኞቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፈው በአንዱ አቻ ሲለያዩ በውድድር አመቱ የመጀመሪያውን ሽንፈት በቅርብ ርቀት በሚፎካከራቸው ፋሲል ከነማ አስተናግደዋል። በዚህም ሁለት ግቦች ማስቆጠር ሲችሉ ሁለት ደግሞ ተቆጥሮባቸዋል። ይህም ለበርካታ ሳምንታት በሰፊ የነጥብ ልዩነት ሊጉን ሲመሩ የቆዩት ፈረሰኞቹ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ በመጣላቸው በመጨረሻ ሰአት ላይ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይከታቸው የሚያሰጋ ሆኗል።
በአንጻሩ የአምና ቻምፒዮን አጼዎቹ ከነበሩበት የውጤት ቀውስ ወጥተው ከባለ ድሉ አሰልጣኛቸው ስዩም ከበደ ጋር ከተለያዩም በኋላ ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የቻምፒዮንነት ፉክክሩ ላይ ያላቸውን ተስፋ ነብስ ዘርተውበታል። ከመሪዎቹ ፈረሰኞች ጋር ያላቸውን ሰፊ የነጥብ ልዩነት አጥበውም አንድ ጨዋታ ወይም ሶስት ነጥብ አድርሰውታል።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ቻምፒዮኑንና ወራጁን ለመለየት ቀሪ አራት ጨዋታዎች ብቻ ይጠበቃሉ። ከነዚህ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ ሶስቱን በድል መወጣት ከቻሉ የማንንም ውጤት ሳይጠብቁ ለአስራ አምስተኛ ጊዜ በውድድሩ መንገስ ይችላሉ። በተቃራኒው አጼዎቹ የፈረሰኞቹን መሸነፍና የአቻ ውጤት ላይ ተሞርኩዘው የሊጉን ዋንጫ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ለማንሳት እድሉ አላቸው።
አጼዎቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ወጥ አቋም ማሳየታቸውና ፈረሰኞቹ በተመሳሳይ መንገድ መጓዝ አለመቻላቸው ከግምት ውስጥ ሲገባ የቀሪዎቹን ጨዋታዎች አጓጊነት ከፍ አድርጎታል። አጼዎቹ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች መቶ በመቶ የአሸናፊነት ጉዞ የነበራቸው ሲሆን በነዚህ ጨዋታዎች አስር ግብ ሲያስቆጥሩ መረባቸውን ያስደፈሩት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። አጼዎቹ ሀይሉ ነጋሽ እየተመሩ ባለፉት አስር ጨዋታዎች ከሚጠበቅባቸው ሰላሳ ነጥቦች ሃያ ስምንቱን ማሳካታቸውም ለቻምፒዮንነት ፉክክሩ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ማሳያ ነው።
ፈረሰኞቹና አፄዎቹ በአፍሪካ መድረክ በቻምፒዮንስ ሊግና በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመወዳደር የሚያበቃቸውን ውጤት በሃያ ሰባተኛው ሳምንት መርሃ ግብር ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ከወዲሁ አረጋግጠዋል። ሁለቱ ክለቦች እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ 27 ጨዋታዎችን ብቻ ማድረግ በቂያቸው ሆኗል።
16 ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻሉት ፈረሰኞቹ 10 ጊዜ የአቻ ውጤት ገጥሞት በአንድ ጨዋታ ብቻ ተሸንፏል። በዚህም 44 ግቦችን አስቆጥረው 10 ግብ ብቻ ተቆጥሮባቸዋል። ይህም በ34 የግብ ልዩነትና በ58 ነጥብ ከሊጎ አናት ላይ መቀመጥ ችለዋል። አጼዎቹ በአንጻሩ በ7 ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ቢያስመዘግቡም 4 ሽንፈት አስተናግደዋል። በዚህም 43 ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን 20 ጊዜ መረባቸውን አስደፍረዋል። ይህም በ23 የግብ ልዩነት በ55 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል።
ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱም ክለቦች የቻምፒዮንነት እድላቸው በእጃቸው ላይ እንዳለ የሚያከናውኑት ይሆናል። የተሻለ የቻምፒዮንነት እድሉ ያላቸው ፈረሰኞቹ ከሶስቱ ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ብቻ ማሳካት በቂያቸው ነው። ይህም ማለት ፈረሰኞቹ ሁለት ጨዋታ ማሸነፍ ወይም ሶስቱንም አቻ መለያየት ይጠበቅባቸዋል።
ይህን ካሳኩም አጼዎቹ ሶስቱንም ጨዋታ ቢያሸንፉ እንኳን ዋንጫው በፈረሰኞቹ እጅ ይቀራል። የግብ ልዩነትን በተመለከተ ለምሳሌ ፈረሰኞቹ በሁለት ጨዋታ አንዳንድ ግብ እያስቆጠሩ ቢያሸንፉና አንዱን ጨዋታ 1ለባዶ ቢሸነፉ ነጥባቸው 64 ይሆናል። አስራ አንድ ግብ ብቻ ተቆጥሮባቸውም 35 የግብ ልዩነት የሚይዙ ይሆናል።
አጼዎቹ በአንፃሩ በሶስቱ ጨዋታዎች 12 ግቦችን አስቆጥረው ቢያሸንፉ በ64 ነጥብና በ35 የግብ ልዩነት እኩል የመሆን እድል አላቸው። ነገር ግን የተቆጠረባቸው የግብ ብዛት 20 ስለሚሆን ይሆናል። ሁለቱ ክለቦች በነጥብም ይሁን በግብ ክፍያና በተቆጠረባቸው የግብ መጠን እኩል ከሆኑ ቻምፒዮኑን ለመለየት የደርሶ መልስ ጨዋታ ውጤታቸው የሚወስን ይሆናል።
በአስገራሚ ሁኔታ ከቻምፒዮንነት ፉክክሩ በተጨማሪ ላለመውረድ የሚደረገው ፍልሚያ ከአምስተኛ እስከ አስራ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው የሚገኙ ክለቦች በሶስቱ ቀሪ ጨዋታዎች እድላቸውን የሚወስኑበት መሆኑ የዘንድሮውን የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ከመቼውም በላይ የማይገመትና አጓጊ አድርጎታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2014