ጠቆር ብሎ ለአይን የሚስበው ጎምላላው ተካ በየነ፣ ኑሮ የተወደደበት አይመስልም።ጉንጩ ቂቤ እንደተለቀለቀ ቅል ያብለጨልጫል፡፡ እርሱ ቤት ኑሮ ርካሽ ነው፡፡ እንዲያውም እንደበፊቱ ቤቱ አይጎድልም፤ ሰሞኑን ማስቀመጫ ቦታ እስከሚጠፋ ቤቱ ሞልቶ ተትረፍርፏል፡፡ ሚስቱ አትቸገርም፤ አትክልቱ፣ ፍራፍሬው እና ጥራጥሬው ሁሉም ነገር ተጭኖ ይመጣላታል፡፡ ከከተማ ብቻ አይደለም፤ ከገጠርም ይጫንላታል፡፡
ሚስቱ ለልጆቿ የምታበላው ምሳ አታጣም። በዚህ ጊዜ ከከተሜዎቹም ሆነ ከገጠሬዎቹ እናቶች በላይ ለኢትዮጵያውያን በሚደንቅ መልኩ ልጆቿን በቂ ምግብ መመገብ ችላለች፡፡ እንኳን ተሳካላት፡፡ በዚህች እናት መቅናት ነውር ነው፡፡
ሌላው ቢቀር አንዲት እናት ለልጆቿ የምትመግበው አለማጣቷ ሊያስደስተን እንጂ መቼም ቢሆን ሊያስከፋን አይገባም፡፡ በዚህ የሚከፋ ካለ ምቀኛ ብቻ ነው፡፡ ‹‹እኔ ስላጣሁ ሁሉም ይጣ›› ብሎ የሚመቀኝ ካልሆነ በቀር ያለምንም ክፉ ሥራ ልጆቿን የምትመግብ እናት ለምን አገኘች? ብሎ መበሳጨት ተገቢም ትክክልም አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ሚስት አይደለችም፤ ባልየው ገንዘቡን የሚያመጣበት መንገድ ነው፡፡ እርሱ እንደሚናገረው ከሆነ ቤተሰቡን የሚያጠግበው ለፍቶ ሠርቶ ላቡን አንጠፍጥፎ ነው።
ባሏ ተካ፣ እንዲህ ቤቱን በበረከት ያጥለቀለቀው ገቢውን ከየት አግኝቶት ይሆን? ሰርቶ በደመወዙ ብቻ ነው? ወይስ በሌላ? የሚለው አጠያያቂ ነው። ምክንያቱም ጊዜው ለፍቶ ሠርቶ ቤተሰብን በበረከት የሚያጥለቀልቅ ገቢ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ እንዲህ ጠግበው እያደሩ ገቢው የሚቋረጥበት ሁኔታ ቢፈጠርስ? ይህንን ለማሰብ ይዘገንናል፡፡
እርግጠኛ ሆኖ መልስ ማግኘት አይቻልም። ተካ ኪሱ የማይነጥፈው ለቤቱ ብቻ አይደለም፡፡ ውጪም ኪሱን ሞልቶ ስለሚንቀሳቀስ በሔደበት ጋባዥ ነው፡፡ ከጓደኛው ከንጉሱ አልፎ አንዳንዴ ላገኘው ሁሉ ‹‹ካላበላሁ ካላጠጣሁ ሞቼ ልገኝ›› ይላል፡፡ ክፋቱ ምላሱ ነው፡፡ አብልቶ አጠጥቶ ወዲያው ደግሞ አቦሬ አፉን ይከፍታል፡፡ ያለእርሱ ሰው በልቶ እንደማያድር ይናገራል፡፡ ሰው ያስቀይማል፡፡
ተካ አንዳንዴ ጥጋቡ ልቡን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ አዕምሮውን የደፈነው ይመስላል፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ‹‹አዋቂ እኔ ብቻ ነኝ›› ለማለት ይደፍራል፡፡ ደፋር¡ ለነገሩ ጊዜው የደፋር ነው፡፡ ውሪዎቹ ‹‹የደፈረ ጮማ በላ›› እንደሚሉት፤ ተካም ሲበዛ ደፋር ነው። የተካ በየነ መጥፎ ገፅ ንግግሩ እና የእብሪት ሃሳቡ፤ ከኔ በላይ አዋቂ የለም ማለቱ ብቻ አይደለም፡፡ ሚስቱ የምትጠይቀውን ገንዘብ ከመስጠት ውጪ ለልጆቹም ሆነ ለሚስቱ ተገቢውን ክብር እና ጊዜ አለመስጠቱ ነው። ከሥራ ኃላፊነት ከፓርቲ ስብሰባ የተረፈችውን ጊዜ የሚያሳልፈው መሸታ ቤት ከንጉሱ እና ከአንዳንድ ሌሎች ጠጪዎች ጋር ነው፡፡
በዚህ ሳቢያ ልጆቹን እና ሚስቱን የሚያገኝበት ጊዜ የለውም፡፡ ከቤተሰቦች ‹‹ልናገኝህ እንፈልጋለን›› የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ጊዜ የለኝም፤ እያለ ሰበብ ይደረድራል፡፡ ልጆቹም ሆኑ ሚስቱ ክፉኛ ታመው ሳይቀር ሳይሰማ የሚያልፍበት ጊዜ አለ፡፡ ወይ ጭካኔ! የአብራክ ክፋይ የሆነ ልጅን ህመም አጋጥሞት አለማወቅ፤ ከነአካቴው መርሳት፤ ምን ማለት ነው? ልጅን መርሳት የሥልጣን ጥማት፣ የዓላማ ፅናት ወይስ ምንድን ነው? እንግዲህ ተካ በየነ ይህ ነው፡፡ በቤቱ ውስጥ ስላለው ስቃይ አይረዳም፡፡ ቀለብ ከማሟላት ውጪ ስላለው ጉዳይ አያስብም።
አለ ደግሞ የተካ በየነ ጓደኛ ንጉሱ፤ ሁልጊዜ በባዶ ሜዳ ጌታ እኔ ነኝ ባይ ነው፡፡ ነገር ግን ንጉሱ እንደተካ ጋብዞ አያውቅም፡፡ ከየት አምጥቶ ይጋብዛል? ለራሱ ድሃ፤ ትንሽ ፊደል ቆጥሬያለሁ ብሎ እየደሰኮረ፤ የእርሱ ዲስኩር አዳማጮች እየጋበዙት ይሰክራል፡፡ ከዛ እንደተካ ቤቱ ሞልቶ ልጆቹ እና ሚስቱ ጠግበው ሳይሆን ጎድሎባቸው ተርበው እርሱ ግን በጋባዦች ገንዘብ ጠግቦ ጠጥቶ ይለፈልፋል፡፡ የዘር ሃረግ እየቆጠረ ስልጣን ከኛ ወዲያ ለአሣር ይላል፡፡ ድንቄም ለአሣር!
ተካ እና ንጉሱ ብዙ ጊዜ አብረው ሲጠጡ የሚያወሩት ፖለቲካ ነው፡፡ በዘር ሐረግ ስለነበረው ስልጣን ብቻ ሳይሆን በጉልበት ተይዞ ስለቆየው ስልጣን ሲያወሩ ብዙውን ጊዜ ወደ ግጭት ያመራሉ። ደግነቱ አያመሩም፤ ወዲያው ይታረቃሉ፡፡ ንጉሱ መንግስትነት በዘር ሐረግ ወይም በጉልበት ተይዞ ኢኮኖሚን ማሳደግ ይበጃል ባይ ነው፡፡ ተካ በበኩሉ ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲ አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ ሰው በሆድ ብቻ እንደማይኖር፤ ዴሞክራሲ እንደሚያስፈልግ ይናገራል።
ንጉሱ በበኩሉ፤ ‹‹ዴሞክራሲን ማስፈን ቀላል አይደለም፡፡ ስልጣኔ እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ይፈልጋል።›› ሲል፤ በሌላ በኩል ተካ ዴሞክራሲ ካለ ስልጣኔ መምጣቱ እና ኢኮኖሚው ማደጉ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ ዴሞክራሲን ማስፈን መሆኑን ይናገራል፡፡ ንጉሱ ‹‹እንግዲህ በዴሞክራሲ መንገድ መጣን ከሚሉት ይልቅ ሕዝቡ የተሻለ ህይወትን መምራት የቻለው፤ በጉልበት ሥልጣን በያዙት እና በዘር ሐረግ ንጉስ ሆነው በመንግስትነት አገርን ሲያስተዳድሩ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ በዴሞክራሲ መንገድ ተመርጠን ስልጣን ይዘናል ያሉትማ ጭራሽ ቁልቁል እየነዱን ኖረዋል›› ይላል፡፡ ይሄኔ የተካ አይን ይፈጣል፤ ደምሥሩ ይገታተራል፡፡
‹‹ስልጣን በዴሞክራሲ መንገድ ይዘናል ያሉት አገርን አልጠቀሙም›› በማለት የተናገረው ሆን ብሎ እርሱን ለማበሳጨት ሲል ያመጣው ሃሳብ መስሎታል፡፡ ከጦፈው ክርክር አልፈው ነገ የማይገናኙ እስከሚመስል ድረስ መሰዳደብ ይጀምራሉ፡፡ ተካ በየነ መንግስት ለመሆን ቅቡልነትን ማግኘት በቂ ነው፡፡ አንተ ብትጠላንም የሚፈልገን እና የሚወደን ብዙ ሕዝብ አለ። ቅቡልነትን ለማግኘት ደግሞ ዴሞክራሲ እና ኢኮኖሚ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ እየሠራን ነው ይላል፡፡
ንጉሱ፤ መንግስት ለመሆን አገር መውደድ የግድ ነው፡፡ አገሩን የሚወድ ባለስልጣን መኖር አለበት። መንግስት አገሩን በሚወድ እንጂ ቤተሰቡን፣ ጎጡን እና ዘሩን በሚያስቀድም ባለስልጣን የታጨቀ ሊሆን አይገባም እያለ ይጮሃል፡፡ ንጉሱ ይህን ሲል ተካ ይበልጥ ይበሳጫል፡፡
ንጉሱ ይቀጥላል፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጥተናል ሲሉ የነበሩት መጨረሻቸው ምን ሆነ? አሁንስ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠናል የምትሉት እናንተ ምን አደረጋችሁ? ሲል፤ ተካ በበኩሉ፤ ‹‹ደርግ አገር ወዳድ ነኝ ይል ነበር፤ ነገር ግን ጉልበተኛ እና እብሪተኛ ስለሆነ አገር አወደመ፡፡ የተማረውን አስፈጀ፤ በደርግ ዘመን ዴሞክራሲ እና ምርጫ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ የተማረው ሃይል ዕድል አላገኘም።
ነፃነት ብሎ ነገር አይታሰብም ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱን በትጥቅ ትግል ለመጣል ብዙ ሰዎች አለቁ፡፡ እንዲያውም አሁን ኢትዮጵያ ለደረሰችበት ችግር ተጠያቂው እርሱ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ካለመኖሩም በተጨማሪ፤ ኢኮኖሚው የተንኮታኮተ፤ ሕዝብ በርሃብ እንዲሁም ቀይሽብር፣ ነጭ ሽብር እየተባለ የሚፋጅበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሔ በምንም መልኩ መልካም መንግስትነት አያስብልም፤ ደርግ አገር ወዳድ ነው ለማለትም አያስደፍርም›› አለ፡፡
ንጉሱ በበኩሉ፤ ቀዝቀዝ ብሎ ‹‹ደርግ እኮ ቢያንስ መሬት ላራሹ ብሎ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እኩልነትን አምጥቷል፡፡ አስገባሪ ባላባቶች ከገበሬው ጋር እንዲመጣጠኑ አድርጓል፡፡ ይህ በአገር ወዳድ የመንግስትነት ዘመን የተፈፀመ ትልቅ ድል ነው፡፡ ይህንን መካድ አትችልም፡፡ እናንተ ደግሞ በዴሞክራሲ ስም እየነገዳችሁ የውሸት ምርጫ እያካሔዳችሁ ሕዝብን ያታለላችሁ መስሏችሁ ራሳችሁን ስታታልሉ ኖራችኋል። በእናንተ ዘመን ኢትዮጵያ አልሞላችም፤ ከላይ ከላይ ዴሞክራሲ በሚል ሽፋን አጉድላችኋታል፡፡›› አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ተካ ተረጋጋ፤ ‹‹ነገሩ አልፈርድብህም፤ አንተ የጠላኸውን ሁሉ ሕዝብ እንዲጠላው፤ አንተ የወደድከውን ሁሉ ሕዝብ እንዲወደው ትፈልጋለህ፡፡ ነገር ግን ከነችግሩም ቢሆን ምርጫ መኖሩ የዴሞክራሲ ልምምድ መጀመሩ ከመልካም መንግስትነት የመነጨ እንጂ የመጥፎ መንግስትነት ባህሪ እንዳልሆነ ታውቀዋለህ ፡፡ እኛ የህዝብ መብትን አክባሪዎች ነን›› አለው፡፡
ንጉሱ መልስ ሰጠ ‹‹ መልካምነት ለማንም ቢሆን የሚበጅ ነው፡፡ በጎ ሥራ ከመቃብር በላይ መሆኑን ማንም ያምናል፡፡ በጎ ተሠራ የሚባለው ሁሉንም እኩል ማየት ሲቻል ነው፡፡ እኩልነት ሳይኖር አገርን በትክክል መጥቀም ላይ ማተኮር አይቻልም፡፡ ብሔርን ሳይሆን አገርን ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡ በምንም መልኩ አገር ላይ ሳያተኩሩ እና ለአገር ሳይሰሩ መልካም ሊያሰኝ አይችልም፡፡ እኔ በበኩሌ በምንም መልኩ መልካምነታችሁ አልታየኝም፡፡›› አለ።
ተካ በበኩሉ፤ ‹‹ ችግሩ እኮ ‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር› እንደሚባለው ዳር ቆሞ ከማሽሟጠጥ ጠጋ ብላችሁ ከወሬ ባለፈ በሁሉም መስክ ብትተባበሩ የት በደረስን ነበር፡፡ ነገሩ ከሠሪው ይልቅ እንደአንተ አይነት አሽሟጣጩ በዝቶ በየት በኩል ውጤት ይምጣ? መንግስት እኮ አንድ ሰው አይደለም፡፡ የብዙዎች ቅንጅት ነው፡፡ አንተ በተሰጠህ ኃላፊነት ካልሰራህ የሚወቀሰው መንግስት ነው፡፡ እነንጉሱ ለምታጠፉት አሁንም እየተወቀሰ ያለው መንግስት ነው፡፡›› አለ፡፡
ንጉሱ ደግሞ ‹‹ አየህ ለወቀሳው እንኳን ማን አስጠግቶን?›› ሲል ወቀሳውን ቀጠለ፡፡ ‹‹ስልጣን የሚያዘው በአገር ወዳድነት ሳይሆን በሌላ መንገድ ነው።›› ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡ ተካ በዚህ ጊዜ ‹‹እንግዲህ በብቃት ከሠራህ አይደለም ለትናንሽ ስልጣን ለትልቁም ትታጫለህ፡፡ ዋናው ጉዳይ ወሬ ሳይሆን ሥራ ነው፡፡ በትንሹ ያልታመነ ለትልቁ አይታጭም እንደሚባለው በወረዳ ተራ ባለሙያ ሆነህ ኃላፊነትህን በብቃት ሳትወጣ አገር እመራለሁ ብሎ መመፃደቅ ከተራ ቅዠት ያለፈ አይደለም›› አለው፡፡
ንጉሱ ተበሳጨ፤ ደሙ ተንተከተከ፤ አፉ ደረቀ፤ ስካሩ ጠፋ፤ የሚናገረውን አጣ፡፡ ‹‹አንተ ለትልቁ የታጨኸው ለትንሹ ታምነህ ነው? በምን መልኩ ታመንክ? ንገረኝ እስኪ የከተማ አስተዳደር እና ፌዴራል ላይ የተሾምከው ወረዳ ላይ ሕዝብን አስደስተህ ነው? ለየትኛው ሕዝብ ቆምክ? የትኛውን ሠርተህ? እስኪ ይሔንን በለኝ? ለአገርህ፣ ለብሔርህ ወይስ ለቤተሰብህ? ብትሠራ እንኳን የምትሠራው ለይተህ ነው፡፡
አገርን አስበህ ሁሉንም ለመጥቀም ከሠራህ ቤተሰብህን ትጎዳለህ፡፡ ሹመት ብሎ ነገር ይናፍቅሃል፡፡ ስልጣን ከፈለግክ ተቃውመህ ሳይሆን ደግፈህ የሚሆን የማይሆነውን ለፍልፈህ፤ ከወንዝ ወዲህ ከወንዝ ወዲያ እያልክ ካገለገልክ አንድ የወንዝህ ልጅ ይስብኻል፡፡ ያለበለዚያ መብለጫም ሆነ ማምለጫ የለህም፡፡ ቤተሰብህንም ሁሉንም ድሃ አድርገህ ትኖራለህ፡፡ አሁን እኔ ድሃ ሆኜ እየኖርኩ እንዳለሁት ማለት ነው፡፡›› አለ።
‹‹አሁን እኔ ቤተሰቤን እንደጠቀምኩ አመንክ፤ ነገር ግን እኔ ለስልጣን የበቃሁት በወንዜ ልጅ ተስቤ ሳይሆን ሰርቼ ነው›› አለ ተካ፡፡ ‹‹እኔ በመስራቴ ቤተሰቦቼ ጠግበው ያድራሉ፡፡ አንተ ደግሞ በመስነፍህ እኔ የምጥልልህን ፍርፋሬ ትለቅማለህ፡፡ ለድህነትህ የተለያዩ ሰበቦችን ትደረድራለህ፡፡ ነገር ግን ምክንያቱ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ አ-ለ-መ-ስ-ራ-ት-ህ›› ሲል ከረር አድርጎ ተናገረው፡፡
ንጉሱ በበኩሉ እንደደከመው በሚያሳብቅ መልኩ በሥራህ የተሾምክ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ያንተ ቤተሰቦች ጠግበው የኔ ቤተሰቦች መራባቸውን በሚመለከት እኔ የተናገርኩትም ሆነ አንተ የተናገርከው ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ከኔ ድህነት የእናንተ ድህነት ይብሳል፡፡ ሠርቼ የማመጣው ምንም ግፍ የለም። ልጆቼ ቢራቡም ወደ እነርሱ የሚተላለፍ መርገምት የለባቸውም፡፡ እናንተ ግን በሠራችሁት ግፍ ልጆቻችሁ የሚተላለፍባቸው መርገምት ከባድ ነው፡፡ ሰው ላይ ወገን ላይ ግፍ የሚሠራ ለተወሰነ ጊዜ የተመቸው ቢመስልም የግፉ መዘዝ ከእርሱ አልፎ ልጆቹ ላይ መድረሱ አይቀርም፡፡ አውቃችሁም ሆነ ሳታውቁ ላጠፋችሁት ጥፋት ዋጋ ትከፍሉበታላችሁ አለ፡፡
ተካ በበኩሉ፤ ‹‹የሠራ ያጠፋል፡፡ የተቀመጠ ግን ባያጠፋም አያለማም፡፡ ጭራሹኑ ካለማልማት እየሠሩ ማጥፋት ይሻላል፡፡ እንደአንተ አይነት ሰግቶ እና ፈርቶ አደር ሆኖ በድህነት ከመቆራመድ እየሠሩ እየደከሙ እየወደቁ እና እየተነሱ ቤተሰብን፣ ቀስ በቀስ ዘመድ አዝማድን ከዛ አልፎ ተርፎ አገርን መጥቀም እና ምድሪቱን የጥጋብ ሰፈር ማድረግ ይሻላል፡፡›› አለው፡፡
ንጉሱ በዚህ ጊዜ ‹‹አገር የምትለውን እንኳን ተወው፤ አምስቱን ቤተሰብህን ማጥገብህ በእርግጥም ከኔ የተሻልክ ያደርግሃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ለአገር እናገለግላለን የምትሉትን የውሸት ሃሳብ ቢያንስ እኔ ፊት ባትናገረው ደስ ይለኛል›› አለው፡፡
ተካ በበኩሉ፤ አሁን አምነሃል፡፡ እኔ እና አንተ እንለያያለን፡፡ እኔ ቀን ስሠራ እውላለሁ፡፡ አንተ ደግሞ የመንግስት ሠራተኛ ሆነህ መንግስትን ስታማ ትውላለህ። የኔ ቤተሰብ ይጠግባል፡፡ ያንተ ቤተሰብ ይራባል፡፡ ነገር ግን አንተም ሌላውም አግዞን ቢሆን ኖሮ አገር ትጠግብ ነበር፡፡ ሲለው ንጉሱ በበኩሉ፤ ‹‹ ቅድም ነገርኩህ እኮ በምን ላግዛችሁ? ውላችሁ አይገባኝም፡፡ ሰውን እኩል አታዩም፤ በዛ ላይ ‹ደሃ ማታ አስር ያጠምዳል፤ ጠዋት አንድ ያጣል› አይነት ናችሁ፡፡
ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ እኩልነት፣ ነፃነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ሌላም ብዙ ብዙ ትላላችሁ፡፡ ነገር ግን አንዱም አልሆነላችሁም፡፡ እናንተ የደሃው ቢጤ ሆናችኋል፡፡ የምታቅዱት እና የምትሠሩት ግልፅ አይደለም፡፡ ከምታስገኙት ይልቅ የምታጎድሉት፤ ከምታጠግቡት ይልቅ የምታስርቡት ተበራክቷል። ስለዚህ በአገር ደረጃ ስትታዩ ከኔ ከድሃው በምንም አትለዩም፡፡›› ሲለው ተካ ከዚህ በላይ መልስ መስጠት አልፈለገም፡፡ የዕለቱ የተጠጣበትን ሒሳብ ጠይቆ ከመሸታ ቤቱ ወጣ፡፡ ንጉሱም ለብቻው ትንሽ ከተከዘ በኋላ ወደ ቤቱ ለማምራት ጠረጴዛውን ተሞርኩዞ ቆመና መራመድ ጀመረ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2014