የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እምብርት የሆነችው በቆጂ በታሪክ መዛግብትና ከአትሌቲክስ ቤተሰቡ ልብ በማይለቅ የወርቅ ቀለም ስሟ ቢሰፍርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአትሌቲክስ እንቅስቃሴዋ መቀዛቀዝ እየታየ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። በቆጂ በርካታ አትሌቶችን በስፖርቱ አንጻር ለዓለም መድረክ ታብቃ እንጂ ከማህጸኗ የወጡት የዓለም ከዋክብት ግን ውለታዋን እንዳልከፈሏት ቅሬታ የሚያሰሙ ጥቂት አይደሉም። በአንጻሩ ለስፖርቱ ፍቅር ያላቸው እና አትሌቲክስ በደማቸው የሚዘዋወር የስፖርቱ ወዳጆች በቁጭት ተነሳስተው የቻሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከል አንዱ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማራው ወጣት አንዷለም ጌታቸው ነው። በቆጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ አትሌቶችን ያወጣች፤ ነገር ግን የስሟን ያህል መግዘፍ ያልቻለች ትንሽ ከተማ መሆኗን ይጠቁማል። መንግስትን ጨምሮ ከበቆጂ ተነስተው ዝነኛ የሆኑ አትሌቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚገባትን ያህል ድጋፍ ሊያደርጉላት አልቻሉም። ከዚህ ቁጭት በመነሳትም በቆጂን ለማስተዋወቅ ዘርፈ ብዙ ጥረት ከማድረግ ባለፈ ለአምስት ጊዜያት የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎችን አዘጋጅቷል። የመሮጫ ቲሸርቶችን በነጻ በማቅረብ ህዝቡን የሚያሳትፍ ሲሆን፤ ይህንንም የሚያደርገው ስፖርቱን ለማነቃቃት እንደሆነ ይናገራል።
አንዱዓለም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ለመቀነሱ አንድ ምክንያት በቆጂ እንደቀድሞው አትሌቶችን ማፍራት ባለመቻሏ እንደሆነም እምነቱ ነው። ለማሳያም ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ካስመዘገበቻቸው 23 የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል 11 የሚሆኑት ከበቆጂ በፈለቁ አትሌቶች የተመዘገቡ መሆናቸውን ያስቀምጣል። በአንጻሩ ከቅርብ ጊዜያት በኋላ ይህ ቁጥር እየቀነሰ ነው። በቆጂ ላይም በማሰልጠኛ ማዕከላትና በግላቸው ጥረት ከሚያደርጉት ውጪ እንደመንግስት የተደረገ ጥረት ነገር የለም።
የበቆጂ አትሌቶች ሙዚየም ለመገንባት ከ18 ዓመታት በፊት መሰረተ ድንጋይ ይጣል እንጂ እስካሁን እውን መሆን አልቻለም። በ1996 ዓ.ም የተገነባው የበቆጂ ስታዲየምም እስካሁን መም ሊነጠፍለት ቀርቶ የአሸዋ መሮጫ ለማድረግም አልተቻለም። እስካሁንም ድረስ አትሌቶች ስልጠና የሚያደርጉት ከእንስሳት ጋር እየተጋፉ መሆኑን ወጣቱ ይጠቁማል። ከ200 በላይ ኢንተርናሽናል አትሌቶችን ያፈራቸውን በቆጂ ሌላው ዓለም ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ቀጥሎ የሚያውቀው ብቸኛው ስፍራም ናት። በመሆኑም በየመድረኩ በቆጂ የአትሌቶች ምንጭ መሆኗን ከመናገር ባለፈ ሊሰራበት ይገባል ባይ ነው። እንደ ኬንያዎቹ የአትሌት መፍለቂያ ከተሞች የተደራጀና ዘመናዊ የሆነ የማሰልጠኛ እንዲሁም ውድድር የሚካሄድባቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲኖራት ሁሉም እንደየድርሻው መስራት እንዳለበትም ያስቀምጣል።
ሌላኛዋ በቆጂን ወደ አትሌቲክስ ምንጭነቷ ለመመለስ በቁጭት ተነሳስታ ጥረት የምታደርገው ወጣት ፈቲያ አብዲ ናት። ወጣቷ እንደነ ጥሩነሽ ዲባባ እና ቲኪ ገላና ካሉ አትሌቶች ጋር አትሌቲክስን የጀመረች ቢሆንም በህመም ምክንያት የአትሌትነት ህይወቷ ሊቀጥል ባለመቻሉ ወደ አሰልጣኝነቱ ገብታለች። ላለፉት ሰባት ዓመታትም በዚሁ ስራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።
ስልጠናው ‹‹ሲንቄ›› በተባለ ሃገር በቀል የእርዳታ ድርጅት የሚደገፍ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት 80 ታዳጊ አትሌቶች እየሰለጠኑ ይገኛሉ። በዚህ የስልጠና ፕሮጀክት ውስጥ ለሶስት ዓመት በስልጠና ላይ የሚቆዩ ታዳጊዎችም እድሜያቸው ከ15-18 የሚሆኑ ናቸው። በዚህ ፕሮጀክት ላይ በማሰልጠኛ ላይ ከሚገኙት ታዳጊዎች መካከል የተሻለ ተስፋ በማሳየት በርካቶቹ በበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲሁም በጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ተመልምለው በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ።
በቆጂ ከዚህ ቀደም በነበረችበት ሁኔታ አትሌቶችን እያፈራች አይደለም ለሚለው ሃሳብ ድጋፍ እንጂ አትሌቶች እንዳልጠፉ ወጣቷ አሰልጣኝ ትገልጻለች። በርካቶች ከገጠራማ አካባቢዎች ጭምር በመምጣትና ቤት በመከራየት የሚሰሩ ቢሆንም የስልጠና ቁሳቁስ ድጋፍና እገዛ የሚያደርግላቸው የለም። በዚህ ምክንያት እንደከዚህ ቀደሙ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ከቁሳቁስ ድጋፍ ባለፈ ከአካባቢው የፈለቁ ታዋቂ አትሌቶች የሞራል ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ትጠይቃለች። እርሷን ጨምሮ ሌሎች በስፖርቱ ፍቅር ተነሳስተው እየተጉ ያሉ አሰልጣኞችም ከስልጠናው ጎን ለጎን ምክሮችን በመለገስ እንዲሁም ተምሳሌት የሚሆኗቸውን አትሌቶች ታሪክ በመንገር ውጤታማ እንዲሆኑ በማበረታታት ለወደፊት ህይወታቸው ተስፋ እንዲሰንቁ እያደረጉ መሆኑንም ታስረዳለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014