የሀገሬ ፖለቲካ መጨረሻው በማይታወቅ የጭለማ ዋሻ ውስጥ እንዲራመድ እንደተፈረደበት መንገደኛ ለምን “ከዘመን ዘመን” እየተደነቃቀፈ የእውር ድንብር ጉዞ ሲጓዝ እንደሚኖር አልገባኝም፤ ገብቶኝም አያውቅም። መነጋገር ብርቃችን፣ መደማመጥ ቃራችን፣ መከባበር እርግማናችን፣ መቀባበል እርማችን ለምን እንደሆነም መረር ብለን ስንጠይቅ ብንባጅም ዛሬም ምላሽ አላገኘንም።
ይህን መሰሉን ጥያቄ ጠይቀው መልሱን ሳያገኙ ላለፉት ብዙኃን ወገኖቻችንም ማዘኑ ትርጉም የለውም። ለምን ቢሉ የፖለቲካ ቡድኖችን ጉዳይ በተመለከተ እኛ “ቋሚ” ተብዬዎች ከእነርሱ የምንሻለው “ስለምንተነፍስ” ካልሆነ በስተቀር ተስፋችንማ ከሟቾቹ ጋር አሸልቦ ከመቃብር ከዋለ ሰነባብቷል።
ስመ ፖለቲካ በተጠራ ቁጥር ፈጥኖ ወደ አእምሯችን ከተፍ የሚለው መጠላለፍ፣ መጠላላት፣ መገፋፋት፣ ሲጠናም መጠፋፋት ሆኖ እንደ ባህል ተጎናጽፈነዋል። ሕጻናት ልጆቻችን “ምን እንቁላል ድፍን ያየኸን/ያየሽን እንደሆን …ዐይንህን/ሽን ድፍን” እያሉ እንደሚጫወቱት የልጅነት ዕድሜያቸው መዝናኛ፤ የፖለቲካ ቡድኖች የታቀፉትን “የራእይ እንቁላል” ትእግስትና ማስተዋል ተጎናጽፈው “በመፈልፈል” ለፍሬ እንደማብቃት ለምንና እንዴት መክነውና “ጭር በለው” ምክንያቱ በአግባቡ ሳይገለጥልን ለጉልምስና፣ ለሽበትም ይሁን ለመቃብር የምንበቃው ግራ እንደተጋባን ነው።
ገና ከጽንስ ሳይወጡ “በሽኩቻ ሾተላይ” የመከኑ፣ ከተፈጠሩም በኋላ ለዳዴ ወግ ሳይበቁ “በጥላ ወጊ” የሥልጣን ደዌ እየተጠቁ በአጭሩ ሲቀጩ የኖሩትና ዛሬም እየተቀጩ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖችን ማሰቡ በራሱ በሀገራዊ ተስፋችን ላይ በረዶ የመቸለስ ያህል ክፉ ስራይ ሆኖብናል። ይበልጥ ሀዘናችንን የሚያከብደው ደግሞ የሌሎች ሀገራትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድሜ ማስላትና “እንዴት እንደተከበሩ ኖሩ!?” በማለት ማሰላሰል ስንጀምር ነው።
ለምሳሌ፡- እ.ኤ.አ በ1828 የተፈጠረው የአሜሪካኖቹ የብሔራዊ ሪፐብሊካን ፓርቲ እና በዚያው ዓመት ባለመግባባት ተስማምተው በመለያየት “የታጋሽነት ምሳሌ የሆነችውን አህያ” የፓርቲው መለያ አድርጎ የተቋቋመው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ሁለቱም ወደ ሁለት ክፍለ ዘመን የዕድሜ ጣሪያ በመሸጋገር ከዓለማችን “ሸበቶ” ፓርቲዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሊሆኑ በቅተዋል። እነርሱን የሚቀድሙ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢኖሩም የስልጣን አቀበቱን ተቋቁመው ማሸነፍ ስላልቻሉ በግብራቸው ሳይሆን ስማቸውን እንዳስከበሩ በታሪካቸው ርዝመት ብቻ “አንቱ” እንደተባሉ ዘልቀዋል።
የእንግሊዞቹ የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ እ.ኤ.አ በ1834 መመስረቱን ስናነብና ስንሰማ “ወይ ነዶ! በዕድሜያቸው የከበሩ፤ በፍሬያቸው የጎመሩ ሀገራዊ ፓርቲዎች እንዳይኖሩን በእኛ የፖለቲካ ባህል ላይ እጀ-ሰብ የመተተብን ማን ይሆን?” በማለት በመንፈሳዊ ቅንዓት ብንንተከተክ አይፈረድብንም።
እ.ኤ.አ በ1912 የተመሠረተው የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት የመቶ ዓመት የእድሜ ሻማውን ሲለኮስ በበዓለ ልደቱ ላይ የታደሙት የእኛዎቹ “የፖለቲካ መሪዎች” ምን እንደ ተሰማቸው እንዲመሰክሩ በሞጎደኞቹ የዚያች ሀገር ጋዜጠኞች ያለመሞገታቸው ዕድለኛ አድርጓቸዋል። “የሺህ ዘመናት ስልጡን ነኝ ባዩዋ የእናንተይቱን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እድሜያቸው እንዳይረዝም የሚያመክነው ጨንጋፊ ስሪት ምንድን ይሆን?” ተብለው ሳይፋጠጡ በመቅረታቸው እነርሱን ሳይሆን እኛን ይቆጨናል። መች ያኔ ብቻ ዛሬም “እንደተወለዱ የሚሞቱ” የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመብዛታቸው የተነሳ “ቀብራቸው በወጉ ባለመፈጸሙ” በርካታ አባል ተብዬዎቻቸው ከእነእርማቸው እንዳሉ አሉ።
የሀገራዊ ፓርቲዎቻችን እና የትራፊክ ምልክቶች ተመሳስሎ በርካቶቹ የመንገድ ዳር የትራፊክ ምልክቶች በባህርያቸው ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ናቸው። የመልእክቶቹ ይዘት በአብዛኛው “አድርጉ ወይንም አታድርጉ” በሚል ሕግ ዙሪያ የታጠረ ነው። አንዳንድ ምልክቶች የአስገዳጅነት ባህርይ ሲኖራቸው፤ አንዳንዶችም ቀድመው የሚያስጠነቅቁ ናቸው። የመከልከልና የመወሰን ስልጣን ያላቸው ምልክቶችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
በምሳሌ እናብራራው፡- አንዳንድ ምልክቶች አሽከርካሪው የተሳሳተ መንገድ ውስጥ እንዳይገባ ወይንም ምልክቶቹ የሚያስተላለፉትን መልእክት በቸልታ እንዳይመለከት ያስጠነቅቃሉ። አንዳንዶችም ከፊት ለፊት አደገኛ መንገድ ወይንም ችግር የሚያስከትሉ መሰናክሎች እንደሚኖሩ ይጠቁማሉ። ትክክለኛውን መንገድ መልቀቅ እንደማይገባው ቀድመው የሚያስጠነቅቁ ምልክቶችም የተለመዱ ናቸው።
ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ወይንም አደባባዮችን በአግባቡ ለመዞር ፍቃድ የሚሰጡ ዓይነት ምልክቶችም የተለመዱ ናቸው። ለእነዚህ መሰል አስገዳጅ፣ መካሪና አስጠንቃቂ ምልክቶች ባዕድ ሆኖ በግዴለሽነት ከቤቱ የሚወጣ አሽከርካሪ ምን ገጥሞት እንደሚውል ለመገመት አይከብድም። “አሽከርክር ረጋ ብለህ” የሚለው ሀገራዊ ዝማሬ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊታወስ የሚገባው የጋራ አዋጅ ነው።
አደባባዮችን ከግራ ወደ ቀኝ (Clockwise) መዞር በሚፈቅዱ ሀገራት ሲያሽከረክር የኖረ ሾፌር ሕጉ ከቀኝ ወደ ግራ (Unticlockwise) በሚፈቅድባቸው አካባቢዎች ሲገኝ መተግበር የሚገባው የታዘዘውን ሕግ እንጂ “እኔ እኮ በኖርኩበት ሀገር…” እያለ በመፎከር ከሥርዓቱ ጋር ቢላተም ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚገባው ምናልባትም ነፍሱ ከህልፈት ተርፋ ካገገመ በኋላ ሊሆን ይችላል።
የትራፊክ መብራቶችም ቢሆኑ ለሃያ አራት ሰዓት እየተፈራረቁ የሚያጋፍሩት አሸከርካሪዎቹ እንደ ርችት ቀለማቱን እያዩ እንዲዝናኑ ሳይሆን ሕጉ እንዲከበር ማዘዛቸው ነው። “ጉዳዬ አጣዳፊ ስለሆነ የመብራቶቹን ትዕዛዝ ለመፈጸም ትእግስት የለኝም” ብሎ የሚወስን አሽከርካሪ ያለምንም ጥርጥር የመቀበሪያ ጉድጓዱን እየቆፈረ መሆኑ ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም።
ይህንን መሰል ዝርዝር የመንገድ ዳር የትራፊክ መርህ ለመተንተን የተፈለገው ለአሽከርካሪዎች ትምህርት ለመስጠት ታስቦ ሳይሆን የሀገራችንን ፖለቲካ የሚዘውሩ የፓርቲዎች ጉዞ ከዚህ የእለት ተእለት ክስተት ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ ስለመሰለን ነው።
አብዛኞቹ “ደርሶ ሂያጅ” የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በጽንስ ደረጃ የሚቀጩት ወይንም ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ጠውልገው ሲሞቱ የምናስተውላቸው ከአፈጣጠራቸው ጀምሮ የስሪታቸው ውቅር “በጥቁር ደም” የበቀል ርዕዮተ ዓለም ተነክረው ስለሚወለዱ ይመስላል። ለክፋቱ ደግሞ “የደሙን ሸማ” የሚጠቀልሉት በኢትዮጵያ ስምና በዲሞክራሲ ቅጽል መሆኑ ነው።
“ደም የጠራው” እንዲሉም፤ ገና ከጅምሩ አዲስ የተወለደው ፓርቲ ከእርሱ ቀድሞ ድክ ድክ የሚለውን ጨቅላ ፓርቲ ጡጦውን ካላስጣልኩ ብሎ ከመተቸት አልፎ ተርፎ “ሻምላ መዝዤ ካልተፋለምኩት” በማለት የፖለቲካ ምህዳሩን ወደ ግዳይ ወረዳነት ስለሚለውጠው “የሟችም ሆነ የገዳይ ፓርቲዎቹ ፍጻሜ” የሚጠናቀቀው ከዚያው ከሞት ሸለቆ ውስጥ ሳይወጡ ይሆናል።
የሕዝቡን ሥነ ልቦናና ስሜት ከማጥናትና ከማክበር ይልቅ ያለፍላጎቱና ያለውዴታው “የብሔሩን ስም እንደ ማጌጫና ጋሻ ለመጠቀም” የሞከሩ ፍጻሜቸው እንዴት እንደተደመደመ አይጠፋንም። በቀኝና በግራ መንገደኛነት “የትራፊኩን ሕግ በመጣስ” በርእዮተ ዓለማቸው ጋቢና ውስጥ ሆነው ህመምተኛውን ፖለቲካቸውን ሲዘውሩ የነበሩ የትናንት ከትናንት ወዲያ ስብስቦች ፍጻሜምም በምን እንደ ተደመደመደ ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው።
በርካታ ደፋር የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የመጀመሪያውን የመቋቋሚያቸውን “አዋጅ” ይፋ ሲያድርጉ የኖሩትም የብሔረሰቦችን ያደረ ወይንም የመሸበትን የቁርሾ ትርክት በመዘርዘር ሙሾ እያሞሹና ሙሾ አውራጆችን እያሰባሰቡ ሰላማዊውን ሕዝብ “ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት” በሚሉ መፈክሮች ሞራሉን እያጋጋሉ እንደነበር ደጋግመን አስተውለናል። ዛሬም ወደ ቀልብያቸው ተመለሰው እንደሆን እርግጠኞች አይደለንም።
አንዳንዶችም ገና ከማለዳው ሕጋዊ የሚሰኘውን “ማህተማቸውንና ሰነዳቸውን” በእጅ ቦርሳቸው ውስጥ አጭቀው ርእዮተ ዓለማቸውን የሚያስተዋውቁት “መደበኛውን ፖለቲካዊ የትራፊክ ሕጎች እየጣሱና አባላቶቻቸውም እንዲጥሱ እያበረታቱ ጭምር ነበር።” ይህን መሰሉ “የጠብ ያለሽ ፖለቲካ” ጅማሮ ዛሬ ዛሬ ቀርቷል የሚለን ተሟጋች ብናገኝ ደስታው እያስፈነደቀን “ስለ ብዕራችን የአፍ ወለምታ” ንሰሃ ለመግባቱ አይከብደንም ነበር።
አንዳንዶችም አሉ፡- ከቀደምት የፖለቲካ ጠባሳቸው ገና ሳያገግሙ ለድጋሚ “ዓላማ ቢስ ፍልሚያ” መሪዎቻቸው ግፋ በለው እያሰኙ በማስፎከር “ቀይ መብራት እንዲጥሱ” የሚያበረታቱ። እንዲህ ዓይነቱ በሽታ የተጠናወታቸው “የፓርቲ መሪዎች ተብዬ” የማይገባውን ድንበር ካላለፍን፣ የማይፈቀደውን ካልጣስን፣ የተከለከለውን ካልሞከርን ወዘተ. እያሉ ተጓዦችን አግተልትለው ሲጓዙ መና ቀርተው መና ያስቀሩም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ “የደም ውርስ ሾተላይ” ያለበት ይመስል ለመጨንገፍ እጅግ ቅርብ ነው። ተጀምሮ ያልከሸፈ፣ ለመዋሃድ ተማምለው ያልተበተነ የፓርቲዎች ስብስብ አለ የሚል ምስክር ከተገኘ ደግመን የምናረጋግጠው እርሱን ለመስማት፣ እኛም ለሰነዘርነው ሃሳብ “አፉ በሉን – ስሜት አሳስቶን ነው!” ለማለቱ አናፍርም፤ አንሸማቀቅምም።
የፖለቲካችን ምህዳር እብቅ እንጂ ፍሬ አልባ የመሆኑ ጉዳይ በአግባቡ ተመርምሮ መፍትሔ እስካልተገኘለት ድረስ ጭንገፋው ባህል ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። እንዲያው ለማሳያነት እንዲረዳ በነበር የሚዘከሩትንም ሆነ ዛሬም ድረስ እስትንፋሳቸው ሊጨልም ጭል ጭል የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖችን የሚመሩ ፊት ቀደሞቻቸውን በየሚዲያው አየር ላይ ብቅ ሲሉ ልብ ብለን እስቲ እናድምጣቸው፤ እናስተውላቸውም።
ገና መድረኩን እንደተቆጣጠሩ አንዳች የሚያንዘረዝር በሽታ ያለባቸው ይመስል ሌላውን ማጠልሸት፣ መወራጨት፣ መተቸት፣ መዘርጠጥ ልማድ አድርገውታል። ረጋ ብሎ፣ ሰክኖና ሃሳብን በአግባቡ አደራጅቶ የማስረዳት አቅም ሲጎላቸው ፈጥነው የሚሸጋገሩት ወደ “መቧቀስ ነው!” የገዢውን ፓርቲ ጥንብ እርኩስ ማውጣት፣ የተቀሩትን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳልባሌ መቁጠር ወዘተ. ጨዋታው እንዲህ ነው።
የገዢው ፓርቲ ሰዎችም ቢሆኑ ከዚህን መሰሉ ወረርሽኝ የተላቀቁ አይመስልም። የራስን ስኬት በራስ ዐውድ መጥኖ “እወቁልኝ፣ አመስግኑኝ” ከማለት ይልቅ ከቀደምት ሙታን የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ራሳቸውን ማወዳደራቸውን “የእነርሱን ቤተኞች” ባናውቅም አብዛኛው ሕዝብ ግን ይህንን ባህርያቸውን የወደደላቸው አይመስልም። “የፖለቲካውን የትራፊክ ሕግ” በመጣስ ረገድ ሥልጣን የተቆናጠጠው ፓርቲም ቢሆን “ከደሙ ንፁህ ነኝ!” ብሎ የማይሟገትባቸውን በርካታ ጥሰቶች ሲፈጽም እያስተዋልን ስለሆነ ቢታረም አይከፋም።
በተለይም ይህን ያህል ሚሊዮን አባላት አለኝ “የሚሉት ፉከራ” በመሪነት በትሩ ሥር የተጠለሉትን ተራ የእለት እንጀራ ፈላጊ ዜጎች እንዴት እንደሚያበግናቸው ቢረዳው መልካም ይሆናል። ካሻቸው እዚያው በቤታቸው ቁጥሩን እየጠቀሱ “ዋንጫ ኖር!” ይበሉ እንጂ በሕዝብ ሚዲያና መድረክ ብቅ ባሉ ቁጥር “ይህንን ያህል አባላት አለን” የሚለውን ትምክህት ባይለማመዱት ይበጃቸዋል።
ይህንን የምንለው “ከሚሊዮኖቹ የገዢው ፓርቲ አባላት” መካከል ብዙዎቹ በሥራና በሕይወታቸው ውስጥ ቅጠላቸው ተንዠርግጎ ካልሆነ በስተቀር ከየግል የኃላፊነት አተገባበራቸውና የውሎ መስካቸው ፍሬያቸውን በገሃድ ለማየት ስላልቻልን ነው። በየመስኩ ሲባዝኑ፣ ሲወጡና ሲወርዱ፣ ሲሰደቡ ወይንም ሲመሰገኑ የምናያቸው ጥቂቶቹን “አንቱዎች” ብቻ ነው። እነዚያ ሚሊዮን አባላት በየመንግሥታዊ ተቋማት የተገልጋዩን እምባ ሲያብሱ፣ በተግባራቸው ምሳሌ ሆነው ሲጠቀሱስ፣ ከጉቦና ከዘረፋ ነፃ ሆነው ሲመሰገኑ አድምጠናል? መልሱን እያወቅን የምናልፈው በሆድ ይፍጀው የተለመደ ብሂላችን ይሆናል።
ለማንኛውም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጨንገፍና ከሾተላይ ሕመም እንዲፈወሱ ካስፈለገ ይደማመጡ፣ ሲፎካከሩም ይከባበሩ፣ ሲተቻቹም እርስ በእርስ በመተናነጽ ይሁን እንጂ በነገር ጎራዴ እየተሞሻለቁ አይተላለቁ። እነርሱ ብቻ ለሀገር የሚያስቡ፤ እነርሱ ብቻ ለሕዝብ ጽድቅ “ቅባ ቅዱስ የተቀቡ” ነፃ አውጪ አድርገው ራሳቸውን በራሳቸው ከማጽደቅም ይፈውሱ። መልእክቱ ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014