ኢትዮጵያ ነዳጅ በአነስተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል ተጠቃሽ እንደሆነች ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መረጃዎች ያሳያሉ። በ‹‹ስታቲስታ›› የገበያ መረጃ ተቋም (Statista) መረጃ መሠረት ነዳጅ አምራች ከሆኑት አንጎላ፣ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ በመቀጠል በአፍሪካ ውስጥ የነዳጅ ምርቶችን በአነስተኛ ዋጋ ለሕዝቧ የምታቀርብ አገር ኢትዮጵያ ናት።
መንግሥት የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በማኅበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አቋቁሞ ሲሠራ ቆይቷል። የዚህ ፈንድ ዓላማ በዓለም የነዳጅ ገበያ ዋጋ ላይ በሚከሰተው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጅ ገበያ ዋጋን ማረጋጋት ነው።
ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት ብቻ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ወጪ እንዳደረገችና ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት አምስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ልታወጣ እንደምትችል ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአገሪቱን ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚና የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የአገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋና የዓለም አቀፉን ዋጋ በማጥበብ በኩል ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ከዓለም ገበያ ዋጋ ጋር የተናበበ የዋጋ ማስተካከያ ሳይደረግ ቆይቷል።
በሥራ ላይ የቆየው ድጎማ ለሁሉም ተጠቃሚዎች፣ ማለትም መደጎም ያለባቸውንና የሌለባቸውን አካላት ሳይለይ፣ ሲሠራበት መቆየቱ በግብይቱ ላይ ኢፍትሐዊነትና ብክነት እንዲሰፍን ማድረጉ ይነገራል። የዓለም ነዳጅ ዋጋን ያገናዘበ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ለተጠቃሚው በየወቅቱ ባለመተላለፉም በዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ላይ ከፍተኛ ዕዳ እንዲከማች ምክንያት ሆኗል። መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ድጎማ አገሪቱን ለ132 ቢሊዮን ብር የዕዳ ክምችት እንድትጋለጥ አድርጓታል።
ነዳጁ አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ለግብይት የሚቀርበው ከተገዛበት ዋጋ በግማሽ ባነሰ ገንዘብ ነው። ግብይቱም መንግሥት በሚከተለው የድጎማ አሠራር መሠረት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ያሉ ጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃጸር በግማሽ ያነሰና ሰፊ የዋጋ ልዩነት እንዲኖረው አድርጎታል።
ይህም አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባው ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገራት ኮንትሮባንድ እንዲወጣና በአገር ውስጥ የነዳጅ ሥርጭት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ምክንያት ሆኗል። ነዳጅ አቅራቢ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ነዳጁን የዋጋ ጭማሪ ወዳለበት አካባቢ በመውሰድ የኮንትሮባንድ ንግዱ እንዲስፋፋ አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ነው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የነዳጅ ፍላጎት ዝቅ በማለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቶ የቆየ ቢሆንም፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ዋጋው እየጨመረ መጥቷል። በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ‹‹መንግሥትም የዋጋ ማስተካከያ ሊያደርግ ይችላል›› በሚል ሰበብ ነዳጅን ደብቆ በማስቀመጥ እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉ አካላትም አሉ።
ይህን መነሻ በማድረግም ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ያለባቸው አካባቢዎች ተለይተው በእነዚህ አካባቢዎች (የደቡብና ምሥራቃዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች) የሚገኙ ከተሞች የስርጭት ማስተካከያ ኮታ በማውጣት እንዲጠቀሙ ማድረግ የሚያስችል እርምጃ ተወስዷል። ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባይቻልም በተደረገው ድልድል 70 በመቶ የሚሆነውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ማስቆም ተችሏል።
ከላይ የተጠቀሱት ቁጥሮችና እውነታዎች የሚያሳዩት ሃቅ ቢኖር፤ የአገሪቱ የነዳጅ ዘርፍ ግብይት ፈጣን፣ የተቀናጀና ጠበቅ ያለ የቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት ሊበጅለት እንደሚገባ ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግም የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ እንደሚተገበር ተገልጿል።
መንግሥት የነዳጅ ማስተካከያ ድጎማው አነስተኛ ገቢ ባላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና ለማቃለል ታሳቢ ያደረገ እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናን በማይፈጥር መልኩ እንደሚካሄድ ገልጿል። ማስተካከያውም ልዩነቱን በአንድ ጊዜ ሕዝቡ ላይ በመጫን ሳይሆን ጫናውን ታሳቢ በማድረግ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነና ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅትና ግለሰቦችም የሚደረገው ድጎማ እንደሚቀጥል ተነግሯል።
ታዲያ በነዳጅ ግብይት ዘርፍ ለተፈጠሩ ችግሮች አንድ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ የታመነበት ይህ የድጎማ ማስተካከያ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ከመንግሥትም ሆነ ከኅብረተሰቡ ልዩ ክትትል ያስፈልገዋል። ሕዝቡ ‹‹የነዳጅ ዋጋ ጨመረ›› በሚል ሰበብ አሁን ባለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ትልቅ ስጋት አድሮበታል።
በተግባር እንደሚታየው የዋጋ ንረት በየጊዜው ማሻቀብ እንጂ ዝቅ ማለት አልሆነለትም። ይህም የኅብረተሰቡን፣ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል፣ ኑሮ እጅግ የከበደ እንዲሆን አድርጎታል። የዋጋ ንረቱ እንኳን ቅናሽ ማሳየት ይቅርና ባለበት መቀጠልም አልቻለም።
አሁን ያለው የዋጋ ንረት ከእስካሁኑ ሁሉ የከፋ ነው፤ ነገ ደግሞ ከዛሬውም የባሰ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። በአንዳንዶቹ ምርቶች ላይ ደግሞ የሚታየው የዋጋ ንረት ደግሞ ጠዋት እና ከሰዓት በኋላ ሰፊ የዋጋ ልዩነት እስከማሳየት የደረሰ ነው። የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች የሚሳዩትም የዋጋ ንረቱ እየተባባሰ መሄዱን ነው።
ይህ የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያ ደግሞ ተጨማሪ የኑሮ ውድነት እንዳይፈጥር በንቃት መከታተል ያስፈልጋል። ለሸማቹና ለነጋዴው ኅብረተሰብ ስለድጎማ ማስተካከያው ግንዛቤ መፍጠር፣ በሕገ ወጦች ላይ እርምጃ መውሰድ እና የትራንስፖርት ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር መቆጣጠር ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
የነዳጅ ማስተካከያ ድጎማው ከተተገበረ በኋላ የድጎማ ተጠቃሚ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም እስከ ስድስት ወራት ድረስ የዋጋ ጭማሪ እንደማያደርጉ በመንግሥት የተቀመጠው አቅጣጫ በትክክል እየተተገበረ ስለመሆኑ ክትትል ሊደረግበት ይገባል።
በሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችና ግለሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል። ከሕዝብ የሚሰወር ወንጀልና ወንጀለኛ አይኖርምና ኅብረተሰቡም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ሲያስተውል ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥቆማ መስጠት ይኖርበታል።
ነዳጅ የማታመርተው ኢትዮጵያ፤ ነዳጅ አምራች ከሆኑ አገራት በላይ ባነሰ ዋጋ ነዳጅ ለዜጎቿ የምታቀርበው መንግሥት ለዘርፉ በሚያደርገው ድጎማ ምክንያት ነው። ድጎማው የነዳጅ ገበያ ዋጋን በማረጋጋት አዎንታዊ ሚና ማበርከቱ ባይካድም በአተገባበሩ ምክንያት አገሪቱን ለእዳ የዳረጉ ችግሮች ተፈጥረዋል።
ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች እንኳንስ የተደራጀ የመረጃና የሰው ኃይል መዋቅር ካለው ከመንግሥት ይቅርና፣ ከግለሰቦችም የተሰወሩ ተዓምራዊ ነገሮች አይደሉም። ነገም በድጎማው ትግበራ ላይ የሚከሰቱት ችግሮችም ሆነ መፍትሄያቸው መንግሥት የማያውቃቸው ሊሆኑ አይችሉም።
በሕገ ወጦች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ፣ መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ፣ ከፖለቲካ ሴራ ለመላቀቅ የሚያስችል ቁርጠኛነት እንዲሁም ከራስ ጥቅም ይልቅ ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችል ፍላጎትና ድፍረት ሊኖር ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014