የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) ከሳምንት በፊት በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ አራት ሁለት ጨዋታዎችን አከናውነዋል። ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም የሌላት መሆኑን ተከትሎ ዋልያዎቹ ከሁለቱ አንዱን የማጣሪያ ጨዋታ በሜዳቸው ማድረግ ሲገባቸው በገለልተኛ አገር ለማከናወን መገደዳቸው ይታወቃል።
ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከማላዊ አቻቸው ጋር ሊሎንዌ ቤንጉ ስቴድየም አድርገው 2ለ1 ቢሸነፉም በጨዋታው ያሳዩት አስደናቂ እንቅስቃሴ አድናቆትን አትርፎላቸዋል። በዚህ ጨዋታ ካገኙት አድናቆት ባለፈም በተመሳሳይ አገርና ስቴድየም የአህጉሪቱን ትልቅ ብሔራዊ ቡድን ግብጽን በቀናት ልዩነት 2ለ 0 በማሸነፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማስደሰት ችለዋል። ዋልያዎቹ ይህን ታላቅ ጨዋታ በፍጹም የበላይነት ማሸነፍ ቢችሉም ድሉን በሜዳቸው ከደጋፊያቸው ጋር ሆነው ማጣጣም አለመቻላቸው የስፖርት ቤተሰቡን ቁጭት ውስጥ ከቷል።
ከእግር ኳስ በዘለለ ብዙ ትርጉም ያለው የዋልያዎቹ ድል በጅምር የቀሩ በርካታ የኢትዮጵያ ስቴድየሞችን ጉዳይ ከተዳፈነበት ቀስቅሷል። “ከመቶ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት አንድ ታላቅ አገር እንዴት አንድ የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም አይኖራትም?” የሚለው ጥያቄ ከዋልያዎቹ ድል ጎን ለጎን በስፋት መወያያነቱ አሁንም ቀጥሏል። ይህ ጥያቄ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የየእለት አጀንዳም ሆኗል።
እግር ኳስ አፍቃሪው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለስፖርት ግድ የሌለው ጭምር ይህን ጥያቄ በመቆጨት ስሜት እየጠየቀና እየተወያየም ይገኛል። ኢትዮጵያውያንን በአንድ ያስማማው የዋልያዎቹ ድል በቀጣይ የማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑ ፍልሚያዎችን በሜዳው እንዲያደርግ የሚመለከተው አካል ጥረት እንዲያደርግም ጥያቄው ዛሬም ቀጥሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነባ የሚገኘውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስቴድየም በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ የሚገልጸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በተጨማሪም እየታደሰ የሚገኘው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስቴድየም ዋልያዎቹ በቀጣይ መስከረም ለሚጠብቃቸው ፍልሚያ እንዲደርስ ጥረቱን እንደሚቀጥል ሲገልጽ ቆይቷል።
ለዚህ ጥረቱ ማሳያም ባለፈው አርብ የአዲስ አበባ ስቴድየምን የመጫወቻ ሜዳ የሳር ማንጠፍ ስራ እንደጀመረ በማህበራዊ ትስስር ገጹ በፎቶ ግራፍ አስደግፎ ያወጣው መረጃ ጠቁሟል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህ ረገድ ስለቀጣዩ የዋልያዎቹ ፍልሚያ ተጨንቆ ስቴድየሙን ብቁ ለማድረግ ያሳየው ተነሳሽነትና ጥረት ሳይደነቅ አይታለፍም። ሆኖም ጥረቱ ያለውን ችግር በአጭር ጊዜ ለመፍታት የሚበቃ እንዳልሆነ እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች መገንዘብ ይቻላል።
የአዲስ አበባ ስቴድየም መጫወቻ ሜዳ የሳር ማንጠፍ ስራ እየተከናወነ የሚገኘው በጣት በሚቆጠሩ ሰዎች ኋላ ቀር በሆነ መንገድ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥረቴን እዩልኝ ብሎ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያጋራው ፎቶ ግራፍ ምስክር ነው። ካፍ የኢትዮጵያ ስቴድየሞች ቢያንስ ዝቅተኛ መስፈርት ማሟላት አለባቸው ብሎ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው ባለ ዘጠኝ ገጽ ምክረ ሃሳብ በዋናነት የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳውን የሚመለከት ነው።
ይህም የመጫወቻ ሜዳው የሳር ማንጠፍ ስራ ሲከናወን በሙያው ከካፍና ከፊፋ እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት አማካሪ መሆን እንዳለባቸው ያስቀምጣል። በሳር ማንጠፉ ስራ ብቻ ሳይሆን ሳሩ ከተነጠፈ በኋላም በሙያው የተካኑ አማካሪ ተቋማት ሜዳውን በመንከባከብ ረገድ አስፈላጊ መሆናቸውን ካፍ በምክረሃሳቡ በዝርዝር አስቀምጧል።
አሁን የአዲስ አበባ ስቴድየም የሳር ማንጠፍ ስራ እየተከናወነ የሚገኘው ግን ከዚህ ከካፍ ምክረ ሃሳብ በተቃራኒ ስለመሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። በቀደሙት በርካታ አመታት ሲደረግ እንደነበረው በተወሰኑም ይሁን በበርካታ ሰዎች እንደማንኛውም የመጫወቻ ሜዳ የሳር ነጠፋ ስራው ተከናውኖ ካፍን እንዴት ማሳመን እንደሚቻል መልስ ያላቸው ስራውን የሚያከናውኑት ብቻ ናቸው። እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ግን አሁን እየተሰራ ባለው መንገድ ካፍን አሳምኖ በመጪው መስከረም የአዲስ አበባ ስቴድየም ለዋልያዎቹ ጨዋታ ብቁ ማድረግ እንደማይቻል ነው።
የአዲስ አበባ ስቴድየም ይህን የመጫወቻ ሜዳ በተመለከተ የካፍን ይሁንታ ያገኛል ብለን ብናምን እንኳን የመታጠቢያና መጸዳጃ ቤቶች፣ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሚሰጥበትን አዳራሽ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዴት መስፈርቱን አሟልተው የካፍ ይሁንታ እንደሚገኝ ለብዙዎች ግራ ነው። በአጭሩ ዋልያዎቹ ቀጣዮቹን ጨዋታዎች በሜዳቸው የማድረጋቸው ጉዳይ ያከተመለት ነው ብሎ በድፍረት ሳይሆን ካለው ነባራዊ ነገር ተነስቶ መደምደም ይቻላል።
ዋልያዎቹ ቀጣዮቹን ጨዋታዎች በአገራቸው ለማድረግ ትንሽም ቢሆን ተስፋ የነበረው የአዲስ አበባ ስቴድየም ነበር። ሆኖም “የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው የስቴድየሙ እድሳት በተለይም ዋናው የመጫወቻ ሜዳ የሳር ማንጠፍ ስራ ከዘመኑ ጋር እየተራመደ አለመሆኑ ያለውን ተስፋ የሚያጨልም ሆኗል።
የአደይ አበባን ብሔራዊ ስቴድየምን በተመለከተ ለዋልያዎቹ የመስከረም ጨዋታ ይደርሳል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ አይኖርምና የእሱ ጉዳይ ይቆይ። ሌላው የተሻለ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የባህርዳር ስቴድየምም ቢሆን ከላይ ሲመለከቱት በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኝ ይምሰል እንጂ በአጭር ጊዜና ገንዘብ ለካፍ መስፈርት ብቁ የማያደርጉት በርካታ መሟላት ያለባቸው ችግሮች እንዳሉበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ባለፈው መግለጫ ላይ ጠቁመው ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2014