እውቁ የሥነፅሁፍ ሰው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን «ፍቅርን ፈራን» በሚለው ግጥማቸው ዛሬ ላይ ያለንበትን ሁኔታ አስቀድመው የተነበዩ ይመስላል፡፡
ፍቅርን ፈራን መቀራረብ ፈራን፤
እንዳልተዛመድን እንዳልተዋለድን፤
ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን፤
እኛነትን ትተን እኔነት ለመድን፤
አዎ የኢትዮጵያዊነታችን ወግና ልማድ የነበሩትና የጋራ መገለጫ የሆኑት ጨዋነት፣ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ወደ ጎን እየተገፉ ግንፍልተኝነትና ግትርነት እየገነኑ ይገኛሉ፡፡ ክብርና ሞገስ እየተረሳና እየተናቀ ግለኝነት ሰፍኖብን ፣ አመለካከታችን ሁሉ «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል» እንዳለችው አይነት እንስሳ ለመሆን እየተንደረደርን ይመስላል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን ዕውቀት ገብይተው ሥልጡን ዜጋ ይሆናሉ፤ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ይይዛሉ፤ ሲባል ለአንድ ብሔር ጠበቃ ሆነው፣አንዲት ጠባብ መንደር ይገባኛል ፣ የእኔ ማንነት እከሌ ነው በሚል ግለኛ ፖለቲካ ወርደው የፀብ መነሻ ሆኖአቸው ሲራኮቱ ማየት ምንኛ ያሳዝናል፡፡
አላስፈላጊ የቃላት ልውውጥ ግጭትን የሚያባብሱና ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ መሆናቸውን እያወቁ በማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ) ላይ ሥራዬ ብለው ለተሰማሩ ኃይሎች ዱላ ሲያቀብሉና ግጭትን ሲያቀጣጥሉ ይታያል፡፡
በዓለም ላይ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመስፋፋታቸው የሰው ልጅ የሚዲያ እና ፖለቲካ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም ህብረተሰቡ ልቅ በሆነ መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎችን በአግባቡ መጠቀምና የስህተትን ምንነት ጠንቅቆ ማወቅ ተስኖታል፡፡
በሰለጠኑ ሀገራት ማህበራዊ ሚዲያዎች ችግር እምብዛም አይታይም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ግን የመረጃ አጠቃቀም ዕውቀት ማነስ ነው ባይባልም የሀሰት መረጃን ማሰራጨት ግን ትልቅ ችግር እያስከተለ ነው፡፡
ስህተት በመረጃ ውስጥ የሚቀርብ ሸፍጥ፣ የሀሳብ ጉድለት ወይም ያለመሟላት ሲሆን፤ ለሕዝብ በሚሰራጩ መረጃዎች ውስጥ የሚቀርቡ የመከራከርያና የንግግር ሃሳቦች ያለመሟላታቸው፣ ተስተካክለው ያለመገኘታቸው፣እውነታው አሳማኝ ወይም አጥጋቢ ያለመሆን ወይም የመደበላለቅና የመምታታት ሁኔታ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሃላፊነት የጎደላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞች ግጭት በመቀስቀስ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት እንዲያልፍ ፣ ማህበራዊ ኑሮ እንዲቃወስና የሀገር ሰላም እንዲናጋ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ የጥፋት መልእክቶች በመገናኛ ብዙሃን ተሰራጭተው ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አገሮች መካከል ሩዋንዳና ማይናማር በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
በሩዋንዳ በሁቱና በቱትሲ ጎሳዎች መካከል ደም አፋሳሽ ብጥብጥ ተነስቶ ለስምንት መቶ ሺ ሕዝብ እልቂት ምክንያት የሆነው በአገሪቱ ራዲዮ ጣቢያ የተላለፈ የጥፋት ቅስቀሳ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በማይናማር ከ10 ሺህ በላይ በሆኑ በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋና ከ700 ሺ በላይ ለስደት መዳረግ መንስዔ የሆነው በፌስቡክ በተደረገ የጥላቻ ቅስቀሳ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚሁ ዓመት በአገራችን በተለያዩ ክልሎች ለብዙ ዜጎቻችን የሕይወት መጥፋት፣ለአካል ጉዳትና መፈናቀል የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደረገው ማህበራዊ ሚዲያው ለመሆኑ እማኝ መቁጠር አያስፈልግም፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን በትምህርት ገበታቸው ላይ ተረጋግተው እንዳይማሩ ከጥፋት መልዕክተኞች የተሰጣቸውን አደራ እየፈፀሙ በሚገኙ የፌስ ቡክ አርበኞች በሚደረግ ቅስቀሳ የእርስ በርስ ፀብ እየተከሰተ ቢሆንም የነገው አገር ተረካቢ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የጥፋት መልዕክተኞቹን ሃሳብ ተረድቶ ትንኮሳዎችን በትዕግሥት በማለፍ በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ እንዳይደናቀፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
“የአህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት መሬት” እንዲሉ ሆኖብን አንዳንዶቻችን ባልረባ ምክንያት ይህን ለውጥ እንቃወም እንደሆነ እንጂ የተጀመረው ለውጥ ያልተጠበቀና ሀገራችንን ከውድመት፣ ዜጎቻችንን ከዕልቂትና ከውርደት የታደገ፣ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በተሰሩ ስራዎች ኢትዮጵውያንን ብቻ ሣይሆን መላው ዓለምን ያስደመመ ነው፡፡
ይህንን መልካም አጋጣሚ ሊያጨናግፉ የሚፈልጉትን አካላት ሴራ መመከት የሚቻለው በፌስ ቡክ የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩትን ለምን ያሰራጫሉ ብሎ በመኮነን ሳይሆን ፤ መልዕክታቸውን ሼር ባለማድረግ፣ አስተያየት ወይም ኮሜንት ባለመስጠት፣ ግንኙነታቸውን በማቋረጥ ሊሆን ይገባል፡፡ ጠቃሚ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መለየትና ፍቅራችንን ሊያሻክሩ፣ወደ ግጭት ሊያስገቡንና አገራችንን ወደባሰ የድህነት አዘቅት ሊወረውሩ የሚታገሉንን ፍላጎታቸውን ባለማሳካት አገራችንን ከጥፋት መታደግ ይኖርብናል፡፡