በሀገሪቱም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰቱ ሁነቶች ምክንያት የሸቀጥና የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡ በተለይ መሰረታዊ በተባሉ የምግብ ፍጆታዎች ላይ በየቀኑ በሚባል ደረጃ ዋጋቸው እየናረ ነው፡፡ የዋጋዎች መጨመር ደግሞ ተጠቃሚውን ወይም ሸማቹን ህብረተሰብ በከፍተኛ ሁኔታ እያስጨነቀው ይገኛል፡፡
በሀገሪቱ እየሆነ ያለውን የዋጋ ግሽበት ደረጃ ለመረዳት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በ2014 ዓ.ም ያወጣቸውን ወርሃዊ ሪፖርቶች አለፍ አለፍ ብሎ በወፍ በረር መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በኤጄንሲው ሪፖርት መሰረት በ2014 ዓ.ም የመስከረም ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 ነጥብ 8 በመቶ፤ የታኅሣሥ ወር አገራዊ የዋጋ ግሽበት 35 ነጥብ አንድ በመቶ ጭማሪ የምግብ ዋጋ ግሽበት ደግሞ 41 ነጥብ 6 በመቶ፤ የመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ34 ነጥብ 7፤ የግንቦት ወር 36 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል። ይህ የምግብ እና የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ መናር የሸማቹን ማህበረሰብ የመግዛት አቅም በማዳከም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚያዳክመው ቅንጣት ያህል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
በጊዜ ሂደት የሸማቹ የመግዛት አቅም እየተዳከመ ሲሄድ ሸማቹ ማህበረሰብ ወደ ዝርፍያና ሁከት መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከነዋሪው ጋር የሚመጣጠን የኑሮ ቀመር ባለመዘርጋቱ ምክንያት ነጋዴውም ሆነ ሌላው አገልግሎት ሰጪ እንዳሻው በሚጨምረው ዋጋ በቀን ሶስቴ ከመብላት ወደ አንድ ጊዜ መብላት የሚሸጋግረው ሰው እየበዛ እንደሚመጣ መገመት አያዳግትም፡፡
አንድ የዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመላከተው በአንጎላ፣ ቱርክ ፣ ብራዚል እና በሲሪላንካ ያለው የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ጥናት በኢትዮጵያ ያለቀውን የኑሮ ውድነት አላካተተም፡፡ ይሁን እንጂ በጥናቱ የዋጋ ግሽበት ያሰጋቸዋል የተባሉት ሀገራት የዋጋ ንረት እና የኢትዮጵያን በንጽጽር ስንመለት በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረት ስጋት አለባቸው ከተባሉት ሀገራት የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም ፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ በችግር፣ በደስታና በሌሎች ጉዳዮች ተረዳድቶ መኖር እንዲሁም የሚኖርበትን ሀገር ከጠላት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ በተጨማሪም በመረዳዳት መንፈስ ለሀገር ብልፅግናና እድገት መስራት ይኖርበታል፡፡
በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው እውነታ ግን ከዚህ የተገላቢጦሽ እየሆነ ነው። ‹‹እኔ ብቻ ልጠቀም›› በሚል መንፈስ የተበከሉ ሰዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የብዙኃኑን ኑሮ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያመሰቃቅለው እየተስተዋለ ነው፡፡ የዚህ ሀገራዊ ችግር በጊዜ መቅረፍ ካልተቻለ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ውድቀት የሚያፋጥን እና ሀገርን አለመረጋጋት ውስጥ የሚከት ይሆናል፡፡
የኑሮ ውድነቱ ሲነሳ ከምግብ ጀምሮ ያልጨመረ ነገር አለመኖሩ ሲታሰብ ይህ ሁኔታ ወዴት እያመራ ይሆን? የሚለው ጉዳይ ሁሉንም ሰው በውስጡ እንዲያስብ አድርጎታል፡፡ በተለይ ደግሞ የገንዘብ የመግዛት አቅም እየተዳከመ መምጣት ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጠው ያደር ገዋል፡፡
ከሸቀጦች መወደድ በላይ የሚፈለጉት ምርቶች አለመገኘት የስጋቱን ሁኔታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ገንዘብ ያለው ሰው በራሱ የኑሮ ሁኔታ ቢጠየቅ ምንም ከሌለው ሰው እኩል ኑሮ እየፈተነው ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት ያወራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የገንዘብ የመግዛት አቅምና የሸቀጦች በገበያው አለመገኘት በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሀገሪቱ አብዛኛውን ምርት ከውጭ የምታስገባ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ምርት ደግሞ የምትሸፍናቸው ብዙ የሸቀጥ ምርቶች አሉ፡፡ የበለጠ አሳሳቢው ጉዳይ ግን ከውጭ የሚገባውም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረተውም የምግብ እና ሌሎች የፍጆታ እቃዎች በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸው ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መወደድ ተከትሎ በሀገር ውስጥም የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ ይታወቃል፡፡ ይህም የሸቀጥ ገበያ ዋልታ ረገጥ እንዲሆን አድርጎታል። ትንሽ ሰበብ የሚፈልገው የንግዱ ማህበረሰብ ገና በቀጣይ ነዳጅ ሊጨምር ይችላል በሚል ግምት ሁሉም ምርቶች ላይ አግባብ ያልሆነ ጭማሪ ማድረጋቸው የተለመደ ሆኗል።
ለዚህ ሕገወጥ አካሄድ ተገቢው እርምጃ አለመወሰዱ ለችግሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። ለኑሮ ወድነቱ ተጨማሪ ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በቀጣይም ችግሩን ለመቅረፍ ለሚደረጉ ጥረቶች ዋነኛ ተግዳሮት እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኑሮ ውድነት ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ እንደገለጹትም፤ ባለፉት ስድስት ወራት መንግሥት 30 ቢሊዮን ብር በመመደብ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ሠርቷል::
የምርት እጥረትና የፍላጎት መጨመር፣ የንግድ ሥርዓቱ መዛባት፣ ምርት እያለ ማቅረብ አለመቻል፣ ግጭትና የገንዘብ አጠቃቀም ጉድለት ለኑሮ ውድነቱ እንደ ዋነኛ ምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
በዓለም ደረጃ ያለውን የዋጋ ንረት መገንዘብ ተገቢ መሆኑን ፤ በበርካታ ሀገራት ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየታየ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት 33 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።ቁጥሩ ትንሽ ቢመስልም እያስከተለ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው።
የኑሮ ውድነቱ በሀገሪቱ በተለይም በዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለመቋቋም በመንግስት በኩል የተለያዩ ስራዎችን እንደሚሰሩ አመልክተው፤ መላው ህዝብም ችግሩን በመፍታት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚጠበቅበት ማሳሰባቸው ይታወሳል።
በርግጥ ቀደም ሲል እንደ ሀገር ከገባንበት ፈተናና ይዘናቸው ከመጣናቸው የቤት ስራዎች አንጻር አሁን ያለንበት ሀገራዊ ቁመና ለኑሮ ውድነቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደሚሆን መገመት የሚከብድ አይሆንም።
በዚህ ተጨባጭ እውነታ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ሲደመሩበት የፈተናው አቅም እንደ ሀገር ተገዳዳሪ ሆኗል። ከዚህ አንጻር ዜጎች ሁሉ በተለይም የንግዱ ህብረተሰብ ያልተገባ ጥቅም ከማጋበስ ወጥቶ ስለ ሀገርና ህዝብ ሊያስብ ይገባል ።ይህንንም የማድረግ የዜግነት ከዛም በላይ የሞራል ግዴታ አለበት ! መልዕክቴ ነው፡፡ ሰላም
አምኃየስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2014